ኢዩኤል 2:12-17

ኢዩኤል 2:12-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አሁ​ንስ ይላል አም​ላ​ካ​ችሁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፥ “በፍ​ጹም ልባ​ችሁ በጾም፥ በል​ቅ​ሶና በዋ​ይታ ወደ እኔ ተመ​ለሱ። ልባ​ች​ሁን እንጂ ልብ​ሳ​ች​ሁን አት​ቅ​ደዱ፤ አም​ላ​ካ​ች​ሁም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መሓ​ሪና ይቅር ባይ፥ ቍጣው የዘ​ገየ ምሕ​ረ​ቱም የበዛ፥ ለክ​ፋ​ትም የተ​ጸ​ጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመ​ለሱ።” የሚ​መ​ለ​ስና የሚ​ጸ​ጸት እንደ ሆነ፥ ለአ​ም​ላ​ካ​ች​ሁም ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የእ​ህ​ልና የመ​ጠጥ ቍር​ባን የሚ​ሆን በረ​ከ​ትን በኋላ የሚ​ያ​ተ​ርፍ እንደ ሆነ ማን ያው​ቃል? በጽ​ዮን መለ​ከ​ትን ንፉ፤ ጾም​ንም ቀድሱ፤ ምህ​ላ​ንም ዐውጁ፤ ሕዝ​ቡ​ንም ሰብ​ስቡ፤ ማኅ​በ​ሩ​ንም ቀድሱ፤ ሽማ​ግ​ሌ​ዎ​ቹ​ንም ጥሩ፤ ጡት የሚ​ጠ​ቡ​ት​ንና ሕፃ​ና​ትን ሰብ​ስቡ፤ ሙሽ​ራው ከእ​ል​ፍኙ፥ ሙሽ​ራ​ዪ​ቱም ከጫ​ጕ​ላዋ ይውጡ። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም አገ​ል​ጋ​ዮች ካህ​ናት በወ​ለ​ሉና በም​ሥ​ዋዑ መካ​ከል እያ​ለ​ቀሱ፥ “አቤቱ! ለሕ​ዝ​ብህ ራራ፤ አሕ​ዛ​ብም ይገ​ዙ​አ​ቸው ዘንድ ርስ​ት​ህን ለማ​ላ​ገጫ አሳ​ል​ፈህ አት​ስጥ፤ ከአ​ሕ​ዛ​ብም መካ​ከል፦ አም​ላ​ካ​ቸው ወዴት ነው? ስለ ምን ይላሉ?” ይበሉ።

ኢዩኤል 2:12-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“አሁንም ቢሆን፣ በጾም፣ በልቅሶና በሐዘን፣ በፍጹም ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ” ይላል እግዚአብሔር። ልባችሁን እንጂ፣ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ እርሱ መሓሪና ርኅሩኅ፣ ቍጣው የዘገየና ፍቅሩ የበዛ፣ ክፉ ነገር ከማምጣትም የሚታገሥ ነውና። በምሕረቱ ተመልሶ፣ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የሚሆነውን፣ የእህል ቍርባንና የመጠጥ ቍርባን እንዲተርፋችሁ፣ በረከቱን ይሰጣችሁ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ቅዱስ ጾምን ዐውጁ፤ የተቀደሰን ጉባኤ ጥሩ። ሕዝቡን ሰብስቡ፤ ጉባኤውን ቀድሱ፤ ሽማግሌዎችን በአንድነት አቅርቡ፤ ሕፃናትን ሰብስቡ፤ ጡት የሚጠቡትንም አታስቀሩ፤ ሙሽራው እልፍኙን ይተው፣ ሙሽሪትም የጫጕላ ቤቷን ትተው። በእግዚአብሔር ፊት የሚያገለግሉ ካህናት፣ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አደባባይ መካከል ሆነው ያልቅሱ፤ እንዲህም ይበሉ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብህን አድን፤ ርስትህን በአሕዛብ መካከል መተረቻ፣ መሣቂያና መሣለቂያም አታድርግ፤ ለምንስ በሕዝቦች መካከል፣ ‘አምላካቸው ወዴት ነው?’ ይበሉን።”

ኢዩኤል 2:12-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፥ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፥ ቍጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ። የሚመለስና የሚጸጸት እንደ ሆነ፥ ለአምላካችሁም ለእግዚአብሔር የእህልና የመጠጥ ቍርባን የሚሆነውን በረከት የሚያተርፍ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? በጽዮን መለከትን ንፉ፥ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፥ ሕዝቡንም አከማቹ፥ ማኅበሩንም ቀድሱ፥ ሽማግሌዎቹንም ሰብስቡ፥ ሕፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ፥ ሙሽራው ከእልፍኙ፥ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ። የእግዚአብሔርም አገልጋዬች ካህናት ከወለሉና ከመሠዊያው መካከል እያለቀሱ፦ አቤቱ፥ ለሕዝብህ ራራ፥ አሕዛብም እንዳይነቅፉአቸው ርስትህን ለማላገጫ አሳልፈህ አትስጥ፥ ከአሕዛብ መካከል፦ አምላካቸው ወዴት ነው? ስለ ምን ይላሉ? ይበሉ።

ኢዩኤል 2:12-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “አሁንም ቢሆን በጾም፥ በለቅሶና በሐዘን በፍጹም ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ። ሐዘናችሁን ለመግለጽ ልብሳችሁን መቅደድ ብቻ በቂ አይደለም፤ ይልቅስ ልባችሁንም በመስበር ንስሓ ግቡ” እግዚአብሔር አምላካችሁ ቸር፥ መሐሪ፥ ለቊጣ የዘገየ፥ በዘለዓለማዊ ፍቅር የበለጸገና ለቅጣት የዘገየ በመሆኑ ወደ እርሱ ተመለሱ። ምናልባት እግዚአብሔር አምላካችሁ ቊጣውን መልሶ፥ በረከቱን ይሰጣችሁ ይሆናል፤ እናንተም በዚያን ጊዜ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የእህልና የመጠጥ ቊርባን ታቀርባላችሁ። በጽዮን ተራራ ላይ መለከት ንፉ! ሕዝቡን ለመንፈሳዊ ስብሰባ ጥሩ! ጾምንም ዐውጁ! ሕዝቡን ሁሉ በአንድነት ሰብስባችሁ፥ ለተቀደሰ ጉባኤ አዘጋጁ፤ ሽማግሌዎችን ጥሩ፤ ልጆችንና ጡት የሚጠቡ ሕፃናትን ጭምር ሰብስቡ፤ ሙሽራዎችም ሳይቀሩ ከጫጒላቸው ይውጡ። እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ካህናት፥ በመሠዊያውና በመተላለፊያው መካከል ሆነው ያልቅሱ፤ “ጌታ ሆይ! ለሕዝብህ ራራ፤ አሕዛብ አምላካችሁ የት አለ? በማለት እንዲንቁንና እንዲዘባበቱብን አታድርግ” ይበሉ።

ኢዩኤል 2:12-17

ኢዩኤል 2:12-17 NASVኢዩኤል 2:12-17 NASV