ኢዮብ 9:1-20

ኢዮብ 9:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኢዮ​ብም እን​ዲህ ሲል መለሰ፦ “በእ​ው​ነት እን​ዲህ እንደ ሆነ ዐወ​ቅሁ፤ ሰውስ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ጻድቅ መሆን እን​ዴት ይች​ላል? ከእ​ርሱ ጋር ይከ​ራ​ከር ዘንድ ቢወ​ድድ፥ ከሺህ ነገር አን​ዱን መመ​ለስ አይ​ች​ልም። በልቡ ጠቢብ ነው፥ ኀይ​ለ​ኛም፥ ታላ​ቅም ነው፤ ክፉስ ሆኖ በፊቱ የቆመ ማን ነው? ተራ​ሮ​ችን ይነ​ቅ​ላል፤ አያ​ው​ቁ​ት​ምም፤ በቍ​ጣ​ውም ይገ​ለ​ብ​ጣ​ቸ​ዋል። ምድ​ርን ከሰ​ማይ በታች ከመ​ሠ​ረቷ ያና​ው​ጣ​ታል፥ ምሰ​ሶ​ዎ​ች​ዋም ይን​ቀ​ጠ​ቀ​ጣሉ። ፀሐ​ይን ያዝ​ዛ​ታል፥ አት​ወ​ጣ​ምም፤ ከዋ​ክ​ብ​ት​ንም ያት​ማል። ሰማ​ያ​ትን ብቻ​ውን ይዘ​ረ​ጋል፥ በም​ድር ላይ እን​ደ​ሚ​ሄድ በማ​ዕ​በል ላይ ይሄ​ዳል። ድብ የሚ​ባ​ለ​ውን ኮከ​ብና ኦሪ​ዮን የሚ​ባ​ለ​ውን ኮከብ፥ የአ​ጥ​ቢያ ከዋ​ክ​ብ​ት​ንም፥ በአ​ዜ​ብም በኩል ያሉ​ትን የከ​ዋ​ክ​ብት ማደ​ሪ​ያ​ዎች ፈጥ​ሮ​አል። ታላ​ቁ​ንና የማ​ይ​መ​ረ​መ​ረ​ውን ነገር፥ እን​ዲ​ሁም የከ​በ​ረ​ው​ንና እጅግ መል​ካም የሆ​ነ​ውን የማ​ይ​ቈ​ጠ​ረ​ው​ንም ተአ​ም​ራት አደ​ረገ። እነሆ፥ ቢመ​ጣ​ብኝ አላ​የ​ውም፤ ቢያ​ል​ፍ​ብ​ኝም አላ​ው​ቀ​ውም። እርሱ ቢያ​ርቅ የሚ​መ​ልስ ማን ነው? እር​ሱ​ንስ፦ ምን ታደ​ር​ጋ​ለህ? የሚ​ለው ማን ነው? እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እኔን ከመ​ቅ​ጣት አል​ተ​መ​ለ​ሰም፥ ከእ​ር​ሱም የተ​ነሣ ከሰ​ማይ በታች ያሉ አና​ብ​ርት ይዋ​ረ​ዳሉ። ቃሌን እን​ዴት ይሰ​ማ​ኛል? እን​ዴ​ትስ ይተ​ረ​ጕ​መ​ዋል? በጽ​ድቅ ብጠ​ራው፥ ባይ​ሰ​ማ​ኝም፥ የእ​ር​ሱን ፍርድ እለ​ም​ና​ለሁ። ብጠ​ራው፥ እር​ሱም ቢመ​ል​ስ​ልኝ ኖሮ፥ እንደ ሰማኝ አላ​ም​ንም ነበር። “በዐ​ውሎ ነፋስ ይቀ​ጠ​ቅ​ጠ​ኛል፤ ያለ ምክ​ን​ያት ብዙ ጊዜ ያቈ​ስ​ለ​ኛል። እተ​ነ​ፍስ ዘንድ አይ​ተ​ወ​ኝም፤ ነገር ግን መራራ ነገ​ርን አጥ​ግ​ቦ​ኛል። እርሱ በኀ​ይል ይይ​ዛ​ልና፤ ፍር​ዱን ማን ይቃ​ወ​ማል? ጻድቅ ብሆን አፌ ይወ​ቅ​ሰ​ኛል፤ ፍጹ​ምም ብሆን ጠማማ ያደ​ር​ገ​ኛል።

ኢዮብ 9:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “በርግጥ ነገሩ እንዲህ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ሥጋ ለባሽ በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ጻድቅ ሊሆን ይችላል? ሰው ከርሱ ጋራ ለመከራከር ቢፈልግ፣ ከሺሕ ጥያቄ አንዱን እንኳ መመለስ አይችልም። ጥበቡ ጥልቅ፣ ኀይሉም ታላቅ ነውና፤ እርሱን ተቃውሞ ያለ አንዳች ጕዳት የሄደ ማን ነው? ሳያውቁት፣ ተራሮችን ይነቅላቸዋል፤ በቍጣውም ይገለብጣቸዋል። ምድርን ከስፍራዋ ያናውጣታል፤ ምሰሶዎቿንም ያንቀጠቅጣል። ፀሓይን ያዝዛታል፤ አትወጣምም፤ ከዋክብትንም በማኅተም ያሽጋል። እርሱ ብቻውን ሰማያትን ዘርግቷል፤ በባሕርም ማዕበል ላይ ይራመዳል። እርሱ የድብና የኦሪዮን፣ የፕልያዲስና የደቡብ ከዋክብት ፈጣሪ ነው፤ የማይመረመሩ ድንቅ ነገሮችን፣ የማይቈጠሩ ታምራትንም ያደርጋል። እነሆ፤ በአጠገቤ ሲያልፍ አላየውም፤ በጐኔም ሲሄድ፣ ልገነዘበው አልችልም። ቢነጥቅ፣ ማን ይከለክለዋል? ‘ምን መሥራትህ ነው?’ የሚለውስ፣ ማን ነው? እግዚአብሔር ቍጣውን አይመልስም፤ ረዓብን የሚረዱ እንኳ ይሰግዱለታል። “ታዲያ፣ ከርሱ ጋራ እሟገት ዘንድ፣ ልከራከረውም ቃላት እመርጥ ዘንድ፣ እንዴት እችላለሁ? ጻድቅ ብሆንም እንኳ፣ ልመልስለት አልችልም፤ ዳኛዬን ምሕረት ከመለመን ሌላ ላደርግ የምችለው የለም። ጠርቼው ‘አቤት!’ ቢለኝም፣ ያዳምጠኛል ብዬ አላምንም። በዐውሎ ነፋስ ይሰብረኛል፤ ቍስሌንም ያለ ምክንያት ያበዛል፤ ምሬትን አጠገበኝ እንጂ፣ ለመተንፈስ እንኳ ፋታ አልሰጠኝም። የኀይል ነገር ከተነሣ፣ እርሱ ኀያል ነው! የፍትሕም ነገር ከተነሣ፣ መጥሪያ ሊሰጠው የሚችል ማን ነው? ንጹሕ ብሆን እንኳ፣ አንደበቴ ይፈርድብኛል፤ እንከን የለሽ እንኳ ብሆን፣ በደለኛ ያደርገኛል።

ኢዮብ 9:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦ በእውነት እንዲህ እንደ ሆነ አወቅሁ፥ ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ መሆን እንዴት ይችላል? ከእርሱ ጋር ይከራከር ዘንድ ቢወድድ፥ ከሺህ ነገር አንዱን መመለስ አይችልም። ልቡ ጠቢብ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ ደፍሮትስ በደኅና የሄደ ማን ነው? ተራሮችን ይነቅላል፥ አያውቁትም፥ በቍጣውም ይገለብጣቸዋል። ምድርን ከስፍራዋ ያናውጣታል፥ ምሰሶችዋም ይንቀጠቀጣሉ። ፀሐይን ያዝዛታል፥ አትወጣምም፥ ከዋክብትንም ያትማል። ሰማያትን ብቻውን ይዘረጋል፥ በባሕሩም ማዕበል ላይ ይረግጣል። ድብ የሚባለውን ኮከብና ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ፥ ሰባቱንም ከዋክብት፥ በደቡብም በኵል ያሉትን የከዋክብት ማደሪያዎች ሠርቶአል። የማይመረመረውን ታላላቅ ነገር፥ የማይቈጠረውንም ተአምራት ያደርጋል። እነሆ፥ ቢመጣብኝ አላየውም፥ ቢያልፍብኝም አላውቀውም። እነሆ፥ ፈጥኖ ቢነጥቅ የሚከለክለው ማን ነው? እርሱንስ፦ ምን ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው? እግዚአብሔር ቍጣውን አይመልስም፥ ከእርሱ በታች ረዓብን የሚረዱ ይዋረዳሉ። ይልቁንስ እመልስለት ዘንድ፥ ቃሌንስ በፊቱ እመርጥ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ጻድቅ ብሆን ኖሮ አልመልስለትም ነበር፥ ወደ ፈራጄም እለምን ነበር። ብጠራው እርሱም ቢመልስልኝ ኖሮ፥ ቃሌን እንደ ሰማ አላምንም ነበር። በዐውሎ ነፋስ ይሰብረኛል፥ ቍስሌንም ያለ ምክንያት ያበዛል። እተነፍስ ዘንድ አይተወኝም፥ ነገር ግን መራራን ነገር አጥግቦኛል። የኃይል ነገር ቢሆን እርሱ ኃያል ነው፥ የፍርድ ነገር ቢሆን፦ ጊዜን ወሳኙ ማን ነው? ይላል። ጻድቅ ብሆን አፌ ይወቅሰኛል፥ ፍጹምም ብሆን ጠማማ ያደርገኛል።

ኢዮብ 9:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “አዎ! እኔ ይህ እውነት መሆኑን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ሰው በእግዚአብሔር ፊት፥ እንዴት ጻድቅ መሆን ይችላል? ከእርሱስ ጋር ማን ሊከራከር ይችላል? እርሱ አንድ ሺህ ጥያቄዎች ቢጠይቅ ከእነርሱ አንዱን እንኳ መመለስ የሚችል የለም። እግዚአብሔር ጠቢብና ኀያል ነው፤ ማነው እርሱን ተቋቊሞ ያልተሸነፈ? ሳይታሰብ በድንገት ተራራዎችን ያናውጣል፤ በቊጣውም ይገለባብጣቸዋል። እግዚአብሔር ምድርን ከቦታዋ ያንቀጠቅጣል፤ ምሰሶችዋንም ያነቃንቃል። ፀሐይ እንዳትወጣ ሊያደርግ ይችላል፤ ከዋክብትም እንዳያበሩ ያደርጋል። ማንም ሳያግዘው ሰማይን የዘረጋ እርሱ ነው፤ እርሱ በባሕር ሞገድ ላይ ይራመዳል። ድብ፥ ኦሪዮንና፥ ፕልያዲስ የተባሉትን ከዋክብት፥ እንዲሁም በደቡብ በኩል ያሉትን የከዋክብት ክምችቶች በሰማይ ላይ ያኖራቸው እግዚአብሔር ነው። እርሱ የሚያደርጋቸውን ድንቅ ነገሮች መርምረን ልናስተውል አንችልም፤ እርሱም የሚፈጽማቸውን ተአምራት ልንቈጥራቸው አንችልም። “እግዚአብሔር በአጠገቤ ቢያልፍ አላየውም፤ ወደ እኔም ቢቀርብ ለይቼ አላውቀውም፤ የፈለገውን ቢወስድ ማንም አይከለክለውም፤ ‘ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?’ ብሎ ሊጠይቀው የሚደፍርም የለም። እግዚአብሔር ከቊጣው አይመለስም፤ ረዓብ የተባለው የባሕር አውሬ ረዳቶች እንኳ በእግሩ ሥር ይንበረከካሉ። ታዲያ፥ እኔ ለእርሱ መልስ መስጠት እንዴት እችላለሁ? ከእርሱ ጋር ለመከራከርስ ምን ቃላት አገኛለሁ? ንጹሕ ሆኜ ብገኝ እንኳ፥ ፈራጁ አምላክ እንዲምረኝ እለምነዋለሁ እንጂ መልስ ልሰጠው አልደፍርም። የእርሱን ስም ብጠራና መልስ ቢሰጠኝም እንኳ አቤቱታዬን ያዳምጣል ብዬ አላምንም። በዐውሎ ነፋስ ያደቀኛል ያለ ምክንያትም ቊስሌን ያበዛል። ትንፋሽ እስካገኝ እንኳ ፋታ አይሰጠኝም፤ ሕይወቴን በሥቃይ ሞልቶታል። ባለኝ ኀይል ልታገለው እንዳልል፥ በኀይል እርሱን የሚቋቋም የለም፤ ተሟግቼ እረታዋለሁ እንዳልል፥ እርሱን ወደ ፍርድ ሸንጎ ሊያቀርበው የሚችል የለም። እኔ ንጹሕና እውነተኛ ነኝ፤ ነገር ግን አነጋገሬ በደለኛ ያደርገኛል፤ የምናገራቸው ንግግሮች ሁሉ ይፈርዱብኛል።

ኢዮብ 9:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “በእውነት እንዲህ እንደሆነ አወቅሁ፥ ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ መሆን እንዴት ይችላል? ከእርሱ ጋር መከራከር ቢፈልግ፥ ከሺህ ነገር አንዱን መመለስ አይችልም። ልቡ ጠቢብ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ እርሱንስ ተዳፍሮ በደኅና የቆየ ማን ነው? ተራሮችን ይነቅላል፥ ነገር ግን አያውቁትም፥ በቁጣውም ይገለብጣቸዋል። ምድርን ከስፍራዋ ያናውጣታል፥ ምሰሶችዋም ይንቀጠቀጣሉ። ፀሐይን ያዝዛታል፥ አትወጣምም፥ ከዋክብትንም ያትማል። ሰማያትን ብቻውን ይዘረጋል፥ በባሕሩም ማዕበል ላይ ይረግጣል። ድብ የሚባለውን እና ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ፥ ሰባቱንም ከዋክብት፥ በደቡብም በኩል ያሉትን የከዋክብት ማደሪያዎች ሠርቶአል። የማይመረመረውን ታላላቅ ነገር፥ የማይቈጠረውንም ተአምራት ያደርጋል። እነሆ፥ ቢመጣብኝ አላየውም፥ ቢያልፍብኝም አላውቀውም። እነሆ፥ ፈጥኖ ቢነጥቅ የሚከለክለው ማን ነው? እርሱንስ፦ ምን ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው?” “እግዚአብሔር ቁጣውን አይመልስም፥ ከእርሱ በታች ረዓብን የሚረዱ ይዋረዳሉ። ይልቁንስ እመልስለት ዘንድ፥ ቃሌንስ በፊቱ እመርጥ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ጻድቅ ብሆንም እንኳን ልመልስለት አልችልም፥ ፈራጄን እማጸናለሁ እንጂ። ብጠራው እርሱም ቢመልስልኝ ኖሮ፥ ቃሌን ሰማ ብዬ አላምንም ነበር። በዐውሎ ነፋስ ይሰብረኛል፥ ቁስሌንም ያለ ምክንያት ያበዛል። እተነፍስ ዘንድ አይተወኝም፥ ነገር ግን መራራን ነገር አጥግቦኛል። የኃይል ነገር ከሆነ፥ ኃያሉ እርሱ እነሆ፥ የፍርድ ነገር ከሆነም፥ የችሎቱን ጊዜ ወሳኙ ማን ነው? ይላል። ጻድቅ ብሆን እንኳን አፌ ይወቅሰኛል፥ ፍጹምም ብሆን ጠማማ ያደርገኛል።