ኢዮብ 38:1-41
ኢዮብ 38:1-41 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኤልዩስ ንግግሩን ካቆመ በኋላ እግዚአብሔር በደመናና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ኢዮብን ጠየቀው፤ እንዲህም አለው፦ “ከእኔ ምክርን የሚሸሽግ፥ በልቡም ነገርን የሚደብቅ ማን ነው? ከእኔ ይሰውረዋልን? እንግዲህ እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም መልስልኝ። ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ? ታስተውል እንደ ሆነ ንገረኝ። ብታውቅ መስፈሪያዋን የወሰነ፥ በላይዋስ የመለኪያ ገመድን የዘረጋ ማን ነው? መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር? የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው? ከዋክብት በተፈጠሩ ጊዜ መላእክቴ ሁሉ በታላቅ ድምፅ አመሰገኑኝ ከእናቷ ማኅፀን በወጣች ጊዜ፥ ባሕርን በመዝጊያዎች ዘጋኋት፤ ደመናውን ልብስ አደረግሁላት። በጭጋግም ጠቀለልኋት። ድንበርም አደረግሁላት። መወርወሪያዎችንና መዝጊያዎችንም አኖርሁ። እስከዚህ ድረስ ድረሺ፥ ከወሰንሽም አትለፊ፤ ነገር ግን ማዕበልሽ በመካከልሽ ይገደብ አልኋት። “የንጋት ወገግታ በአንተ ተፈጥሮአልን? የአጥቢያ ኮከብስ ትእዛዙን በአንተ ዐውቋልን? የምድርን ዳርቻ ይይዝ ዘንድ፥ ከእርስዋም ኃጥኣንን ያናውጥ ዘንድ። አንተ ጭቃውን ከመሬት ወስደህ ሕያው ፍጥረትን ፈጥረሃልን? በምድርስ ላይ እንዲናገር አድርገሃልን? የኃጥኣንን ብርሃናቸውን ከልክለሃልን? የትዕቢተኞችንስ ክንድ ሰብረሃልን? ወደ ባሕር ምንጭስ ውስጥ ገብተሃልን? በጥልቁስ መሠረት ውስጥ ተመላልሰሃልን ከግርማህስ የተነሣ የሞት በሮች ተከፍተውልሃልን? የሲኦል በረኞችስ አንተን አይተው ይደነግጣሉን? ከሰማይ በታች ያለ የምድርንስ ስፋት አስተውለሃልን? መጠኑም ምን ያህል እንደ ሆነ እስኪ ንገረኝ! “የብርሃን ማደርያው ቦታ የት ነው? የጨለማስ ቦታው ወዴት አለ? ትችል እንደ ሆነ፥ መንገዳቸውንም ታውቅ እንደሆነ፥ ወደ ዳርቻቸው እስኪ ውሰደኝ። በዚያን ጊዜ ተወልደህ ነበርና፥ የዕድሜህም ቍጥር ብዙ ነውና፥ በእውነት አንተ ሳታውቅ አትቀርም። በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን? የበረዶውንስ ቅንጣት ቤተ መዛግብት አይተሃልን? ይህስ በጠላትህ ጊዜ ለሰልፍና ለጦርነት ቀን ይጠበቅልሃልን? አመዳይ ከየት ይወጣል? ከሰማይ በታች ያለ የአዜብ ነፋስስ እንዴት ይበተናል? ለኀይለኛው ዝናብ መውረጃውን፥ ወይስ ለሚያንጐዳጕደው መብረቅ መንገድን ያዘጋጀ ማንነው? ማንም በሌለበት ምድር ላይ፥ ሰውም በማይኖርበት ምድረ በዳ ይዘንም ዘንድ፥ ባድማውንና ውድማውን ያጠግብ ዘንድ፥ ሣሩንም በምድረ በዳ ያበቅል ዘንድ፥ የዝናብ አባቱ ማን ነው? ወይስ የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው? በረዶስ ከማን ማኅፀን ይወጣል? የሰማዩንስ አመዳይ ማን ወለደው? እርሱም እንደ ፈሳሽ ውኃ ይወርዳል። ውኆች እንደ ድንጋይ ጠነከሩ፥ የኃጥኣንንስ ፊት ማን አዋረደ? “በውኑ የሰባቱን ከዋክብት ዘለላ ታስር ዘንድ፥ ወይስ ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ ትፈታ ዘንድ ትችላለህን? ወይስ ማዛሮት የሚባሉትን ከዋክብት በጊዜያቸው ታወጣ ዘንድ፥ ወይስ የምሽቱን ኮከብ ከልጆቹ ጋር ትመራ ዘንድ ትችላለህን? የሰማይን ሥርዐት፥ ከሰማይ በታችስ የሚሆነውን ታውቃለህን? ደመናውን በቃልህ ትጠራዋለህን? ብዙ ውኃስ እየተንቀጠቀጠ ይመልስልሃልን? መብረቁን ትልከዋለህን? እርሱስ ይሄዳልን? ደስታህስ ምንድን ነው ይልሃልን? ለሴቶች የፈትልን ጥበብና የተለያዩ የጥልፍ ሥራዎችን ዕውቀት ማን ሰጠ? የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቈጥር የሚችል ማን ነው? ሰማይንም ወደ ምድር ያዘነበለ ማን ነው? እንደ ትቢያ በምድር ተዘርግቷል፤ እንደ ዓለት ድንጋይም አጣበቅሁት። “ለአንበሳዪቱ አደን ታድናለህን? የእባቦችንስ ነፍስ ታጠግባለህን? በዋሾቻቸው ውስጥ ተጋድመው በጫካም ውስጥ አድብተው ይቀመጣሉና። ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፥ የሚበሉትም ፈልገው ሲቅበዘበዙ፥ ለቍራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው?
ኢዮብ 38:1-41 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰለት፤ እንዲህም አለው፤ “ዕውቀት በጐደለው ቃል፣ ዕቅዴን የሚያጨልም ይህ ማን ነው? እስኪ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤ እኔ ልጠይቅህ፣ አንተም መልስልኝ። “ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ የት ነበርህ? በርግጥ የምታስተውል ከሆንህ ንገረኝ። ካወቅህ፣ መጠኗን ለይቶ ማን ወሰነ? በላይዋስ መለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው? መሠረቶቿ ምን ላይ ተተከሉ? የማእዘን ድንጋይዋንስ ማን አቆመ? ይህም የሆነው የንጋት ከዋክብት በዘመሩበት ጊዜ፣ መላእክትም እልል ባሉበት ጊዜ ነበር። “ባሕር ከማሕፀን በወጣ ጊዜ፣ በር የዘጋበት ማን ነው? ደመናውን ልብሱ፣ ጨለማንም መጠቅለያው አደረግሁለት፣ ድንበር ወሰንሁለት፤ መዝጊያና መወርወሪያውን አበጀሁለት። ‘እስከዚህ ድረስ ትመጣለህ፤ ማለፍ ግን አትችልም፤ የዕቡይ ማዕበልህም ገደብ ይህ ነው’ አልሁት። “ከተወለድህ ጀምሮ ንጋትን አዝዘህ ታውቃለህን? ወይስ ወጋገን ስፍራውን እንዲይዝ አድርገሃል? በዚህም የምድርን ዳርቻ ይዞ፣ ክፉዎችን ከላይዋ እንዲያራግፍ አድርገሃልን? ምድር ከማኅተም በታች እንዳለ የሸክላ ጭቃ ቅርጿ ይወጣል፤ ቅርጿ እንደ ልብስ ቅርጽ ጐልቶ ይታያል። ክፉዎች ብርሃናቸውን ተከልክለዋል፤ ከፍ ያለው ክንዳቸውም ተሰብሯል። “ወደ ባሕር ምንጭ ወርደህ ታውቃለህን? ወይስ ወደ ጥልቀቱ ገብተህ በመሠረቱ ላይ ተመላልሰሃልን? የሞት ደጆች ተገልጠውልሃልን? የሞትንስ ጥላ በሮች አይተሃልን? የምድርን ስፋት ታውቃለህን? ይህን ሁሉ ዐውቀህ ከሆነ፣ ንገረኝ። “ወደ ብርሃን መኖሪያ የሚያደርሰው መንገድ የትኛው ነው? የጨለማ መኖሪያስ ወዴት ነው? ወደ ማደሪያቸው ልትወስዳቸው ትችላለህን? የመኖሪያቸውን መንገድ ታውቃለህ? ያን ጊዜ ተወልደሃል! ዕድሜህ ትልቅ ነውና፣ አንተስ በርግጥ ሳታውቅ አትቀርም! “ወደ በረዶው መጋዘን ገብተሃልን? የዐመዳዩንስ ማከማቻ አይተሃልን? ይኸውም ለመከራ ጊዜ፣ ለጦርነትና ለውጊያ ቀን ያስቀመጥሁት ነው። መብረቅ ወደሚሠራጭበት ቦታ የሚያደርሰው መንገድ፣ የምሥራቅም ነፋስ በምድር ላይ ወደሚበተንበት ስፍራ የሚወስደው የትኛው ነው? ለዝናብ መውረጃን፣ ለመብረቅም መንገድን ያበጀ ማን ነው? በዚህም ማንም የማይኖርበትን ምድር፣ ሰውም የሌለበትን ምድረ በዳ የሚያጠጣ፣ ባድማውንና በረሓውን መሬት የሚያጠግብ፣ ሣርም እንዲበቅልበት የሚያደርግ ማን ነው? ዝናብ አባት አለውን? የጤዛን ጠብታ ማን ወለደው? በረዶ ከማን ማሕፀን ይወጣል? የሰማዩንስ ዐመዳይ ማን ይወልዳል? ውሆች እንደ ድንጋይ ይጠነክራሉ፤ የጥልቁ ገጽ እንደ በረዶ ይጋገራል። “ፕልያዲስ የተባሉትን ውብ ከዋክብት ልትለጕም፣ ወይም የኦርዮንን ማሰሪያ ልትፈታ ትችላለህን? ማዛሮት የተባለውን የከዋክብት ክምችት በወቅቱ ልታወጣ፣ ወይም ድብ የተባለውን ኮከብና ልጆቹን ልትመራ ትችላለህ? የሰማያትን ሥርዐት ታውቃለህ? ይህንስ በምድር ላይ እንዲሠለጥን ማድረግ ትችላለህ? “ድምፅህን ወደ ደመናት አንሥተህ፣ ራስህን በጐርፍ ማጥለቅለቅ ትችላለህን? መብረቆችን መስደድ ትችላለህ? እነርሱስ፣ ‘እነሆ፤ እዚህ አለን’ ይሉሃል? ለልብ ጥበብን፣ ለአእምሮም ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው? ትቢያ ሲጠጥር፣ ጓሎችም እርስ በርስ ሲጣበቁ፣ ደመናትን ለመቍጠር ጥበብ ያለው ማን ነው? የሰማያትንስ የውሃ ገንቦ ዘንበል ማድረግ ማን ይችላል? “ለአንበሳዪቱ ዐድነህ ግዳይ ታመጣለህን? የተራቡ የአንበሳ ግልገሎችንስ ታጠግባለህን? እነርሱ በዋሻ ውስጥ ያደባሉ፤ በደን ውስጥም ይጋደማሉ። ልጆቿ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፣ ምግብ ዐጥተው ሲንከራተቱ፣ ለቍራ መብልን የሚሰጥ ማን ነው?
ኢዮብ 38:1-41 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲህም አለ፦ ያለ እውቀት በሚነገር ቃል ምክርን የሚያጨልም ይህ ማነው? እንግዲህ እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ፥ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ። ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ? ታስተውል እንደ ሆንህ ተናገር። ብታውቅስ መሠፈሪያዋን የወሰነ፥ በላይዋስ የመለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው? አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ፥ የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ፥ መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር? የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው? ከማኅፀን እንደሚወጣ በወጣ ጊዜ ባሕርን በመዝጊያዎች የዘጋ ማን ነው? ደመናውን ለልብሱ፥ ጨለማንም ለመጠቅለያው አደረግሁ፥ ድንበሩን በዙሪያው አድርጌ፥ መወርወሪያዎቹንና መዝጊያዎቹን አኑሬ፦ እስከዚህ ድረስ ድረሺ፥ አትለፊ፥ በዚህም ለትዕቢተኛው ማዕበልሽ ገደብ ይሁን አልሁ። የምድርን ዳርቻ ይይዝ ዘንድ፥ ከእርስዋም በደለኞች ይናወጡ ዘንድ፥ በውኑ ከተወለድህ ጀምሮ ማለዳን አዝዘሃልን? ለወገግታም ስፍራውን አስታውቀኸዋልን? ጭቃ ከማኅተም በታች እንደሚለወጥ እንዲሁ እርስዋ ትለወጣለች፥ ነገርም ሁሉ እንደ ልብስ ተቀልሞአል። ከበደለኞች ብርሃናቸው ተከልክሎአል፥ ከፍ ያለውም ክንድ ተሰብሮአል። ወደ ባሕር ምንጭስ ውስጥ ገብተሃልን? በቀላዩስ መሠረት ውስጥ ተመላልሰሃልን? የሞት በሮች ተገልጠውልሃልን? የሞትንስ ጥላ ደጆች አይተሃልን? ምድርንስ በስፋትዋ አስተውለሃታልን? ሁሉን አውቀህ እንደ ሆነ ተናገር። ወደ ዳርቻው ትነዳው ዘንድ፥ ወደ ቤቱም የሚያደርሰውን ጐዳና ታውቅ ዘንድ፥ የብርሃን መኖሪያ መንገድ የት ነው? የጨለማውስ ቦታ ወዴት አለ? በዚያን ጊዜ ተወልደህ ነበርና፥ የዕድሜህም ቍጥር ብዙ ነውና፥ በእውነት አንተ ሳታውቅ አትቀርም። በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን? የበረዶውንስ ቅንጣት ቤተ መዛግብት አይተሃልን? ይኸውም ለመከራ ጊዜ ለሰልፍና ለጦርነት ቀን የጠበቅሁት ነው። ብርሃንስ በምን መንገድ ይከፈላል? የምሥራቅስ ነፋስ በምድር ላይ እንዴት ይበተናል? ባድማውንና ውድማውን እንዲያጠግብ፥ ሣሩንም እንዲያበቅል፥ ማንም በሌለባት ምድር ላይ፥ ሰውም በሌለባት ምድረ በዳ ላይ ዝናብን ያዘንብ ዘንድ፥ ለፈሳሹ ውኃ መንዶልዶያውን፥ ወይስ ለሚያንጐደጕድ መብረቅ መንገድን ያበጀ ማን ነው? በውኑ ለዝናብ አባት አለውን? ወይስ የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው? በረዶስ ከማን ማኅፀን ወጣ? የሰማዩንስ አመዳይ ማን ወለደው? ውኆች እንደ ድንጋይ ጠነከሩ፥ የቀላዩም ፊት ረግቶአል። በውኑ የሰባቱን ከዋክብት ዘለላ ታስር ዘንድ፥ ወይስ ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ ትፈታ ዘንድ ትችላለህን? ወይስ ማዛሮት የሚባሉትን ከዋክብት በጊዜያቸው ታወጣ ዘንድ፥ ወይስ ድብ የሚባለውን ኮከብ ከልጆቹ ጋር ትመራ ዘንድ ትችላለህን? የሰማይን ሥርዓት ታውቃለህን? በምድርስ ለይ እንዲሠለጥን ልታደርግ ትችላለህን? የውኆች ብዛት ይሸፍንህ ዘንድ። ቃልህን ወደ ደመናት ታነሣ ዘንድ ትችላለህን? መብረቆች ሄደው፦ እነሆ፥ እዚህ አለን ይሉህ ዘንድ፥ ልትልካቸው ትችላለህን? በውስጡስ ጥበብን ያኖረ፥ ለሰውስ ልብ ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው? የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቈጥር የሚችል ማን ነው? ትቢያ በተበጠበጠ ጊዜ፥ ጓሎቹም በተጣበቁ ጊዜ፥ የሰማይን ረዋት ሊያዘነብል የሚችል ማን ነው? በዋሾቻቸው ውስጥ ተጋድመው፥ በጫካም ውስጥ አድብተው ሳሉ፥ ለአንበሳይቱ አደን ታድናለህን? የልጆችዋንስ ነፍስ ታጠግብ ዘንድ ትችላለህን? ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ፥ ለቍራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው?
ኢዮብ 38:1-41 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ኢዮብን እንዲህ አለው፦ እግዚአብሔር “ይህ፥ ያለ ዕውቀት በሚነገሩ ቃላት ምክሬን የሚያቃልል እርሱ ማነው? እስቲ በፊቴ እንደ ወንድ ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፤ አንተም መልስልኝ። ለመሆኑ ዓለምን ስፈጥር አንተ በዚያ ነበርክን? የምታውቅና የምታስተውል ከሆነ እስቲ ንገረኝ። የምድርን መጠን የወሰነ ማን ነው? በእርሱዋ ላይስ የመለኪያ መስመሮችን የዘረጋ ማን እንደ ሆነ ታውቃለህን? የምድርን ምሰሶዎች አጽንቶ የያዘ ኀይል ምንድን ነው? የዓለምንስ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጠ ማን ነው? የንጋት ከዋክብት በአንድነት ሲዘምሩ፥ መላእክትም ሁሉ እልል ሲሉ አንተ የት ነበርክ? “ከምድር ውስጥ ፈንድቶ በወጣ ጊዜ የመፍለቂያ በሮቹን የዘጋ ማነው? ባሕርን በደመና የጋረድኩ በድቅድቅ ጨለማም የሸፈንኩ እኔ ነኝ። ለባሕር ወሰንን የሠራሁ፥ በርና ገደብም እንዲኖረው ያደረግኹ እኔ ነኝ። እስከዚህ ድረስ ትመጣለህ! ከዚህም አታልፍም! የአንተም ብርቱ ማዕበል እዚህ ይቁም! ያልኩ እኔ ነኝ። ኢዮብ ሆይ! በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ከቶ ንጋትን አዘህ ታውቃለህን? ለንጋት ወገግታስ ቦታ መድበህለታልን? ንጋት በምድር ላይ ብርሃን እንዲያሳይ፥ ክፉ ሰዎችንም ከተደበቁበት ቦታ እንዲያጋልጥ ትእዛዝ ሰጥተህ ታውቃለህን? የንጋት ብርሃን ኰረብቶችንና ሸለቆዎችን እንደ ተጣጠፈ ልብስ ቈመው እንዲታዩ ያደርጋቸዋል፤ በሸክላ ላይ እንዳለ መኅተምም አጒልቶ ያሳየዋል። ክፉዎች ብርሃን ተከልክለዋል፤ ለዐመፅ ያነሡአቸው ክንዶቻቸውም ተሰብረዋል። “ወደ ባሕሩ ጥልቀት ወርደሃልን? በውቅያኖስ ወለል ላይ ተመላልሰህ ታውቃለህን? የሞትን በሮች እንድታይ ተደርገሃልን? የድቅድቅ ጨለማንስ መዝጊያ አይተሃልን? ዓለም ምን ያኽል ትልቅ እንደ ሆነች ማወቅ ትችላለህን? እስቲ ይህን ሁሉ ታውቅ እንደ ሆነ ንገረኝ። “ወደ ብርሃን የሚወስደውን መንገድ ጨለማስ የት እንደሚኖር ታውቃለህን? ብርሃንንና ጨለማን ወደየቦታቸው ልትወስዳቸው ትችላለህን? ወደ መኖሪያቸው የሚወስደውን መንገድ ታውቃለህን? ዓለም በተፈጠረ ጊዜ ተወልደህ ስለ ነበረ በእርግጥ ታውቃለህ! ዕድሜህም በጣም የገፋ ነው! “ወደ በረዶ ማስቀመጫ ቤት ገብተሃልን? ወይስ የተቀመጠውን የበረዶ ክምችት አይተሃልን ይህም በረዶ እኔ በጦርነትና በውጊያ ላይ እንድጠቀምበት ለችግር ጊዜ ያስቀመጥኩት ነው። ብርሃን የሚከፋፈልበት ቦታ ወዴት ነው? ወይስ ደረቅ ነፋስ በምድር ላይ የሚሠራጭበት ቦታ ወዴት ነው? “ለዝናብ መውረጃን ያዘጋጀለት፥ ነጐድጓድ ለተቀላቀለበት ውሽንፍርም መንገድ ያበጀለት ማነው? እንዲሁም ማንም በሌለበት ምድር፥ ሰው በማይኖርበት ምድረ በዳ፥ ዝናብ እንዲዘንብ የሚያደርግ ማነው? ጠፍና ባድማ የሆነውን መሬት ረስርሶ ምድሩንም ሣር እንዲያበቅል ያደረገው ማነው? ዝናብንና ጤዛን የሚያስገኝ ማነው? በረዶንና አመዳይን የሚያስገኝ ማነው? ውርጩ ውሃን እንደ ድንጋይ ያጠጥራል፤ የባሕሩም ወለል እንደ በረዶ እንዲረጋ ያደርገዋል። “ ‘ፕልያዲስ’ የተባሉትን ከዋክብት በአንድነት ማሰር ትችላለህን? ኦርዮን የተባሉትንስ ከዋክብት የተያያዙበትን ገመድ መበጠስ ትችላለህን? ከዋክብትን ሁሉ በየወቅታቸው ማሰማራት ትችላለህን? የድብ ቅርጽ ያላቸውን ከዋክብትስ ከልጆቻቸው ጋር መምራት ትችላለህን? ሰማያት በምን ዐይነት ሥርዓት እንደሚተዳደሩ ታውቃለህን? ይህንንስ ደንብ በምድር ላይ እንዲሠራ ለማድረግ ትችላለህን? “ብዙ ዝናብ እንዲያዘንብልህ፥ ደመናን ልታዘው ትችላለህን? መብረቅ በአንተ ትእዛዝ ይበርቃልን? ለልብ ጥበብን ለአእምሮስ ማስተዋልን የሰጠ ማነው? በጥበቡ ደመናን ለመቊጠር የሚችል ማነው? የተሰበሰበው ዐፈር ርሶ ጭቃ እንዲሆን ከማከማቻው ከሰማይ ውሃ ወደታች ለማፍሰስ የሚችል ማነው? በጫካው ውስጥ ታጋድመውና አድብተው ሳሉ ለአንበሳይቱ አደን ታድናለህን? የተራቡ ልጆችዋንስ መመገብ ትችላለህን? ልጆችዋ ምግብ አጥተው ሲቅበዘበዙ ወደ እኔም ሲጮኹ ለቁራ ምግብ የሚሰጣት ማነው?”
ኢዮብ 38:1-41 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “እውቀት በጎደለው ንግግር ምክርን የሚያጨልመው ማነው? እንግዲህ እንደ ጎበዝ ወገብህን ታጠቅ፥ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ታሳውቀኛለህ። ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ የት ነበርህ? ታስተውል እንደሆንህ ተናገር። የምታውቅ እንደሆነ መሠፈሪያዋን የወሰነ፥ በላይዋም የመለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው? አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ፥ የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ፥ መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር? የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው? ከማኅፀን እንደሚወጣ በወጣ ጊዜ ባሕርን በመዝጊያዎች የዘጋ ማን ነው? ደመናውን ለልብሱ፥ ጨለማንም ለመጠቅለያው አደረግሁ፥ ድንበሩን በዙሪያው አድርጌ፥ መወርወሪያዎቹንና መዝጊያዎቹን አኑሬ፦ እስከዚህ ድረስ ድረሺ፥ አትለፊ፥ በዚህም ለትዕቢተኛው ማዕበልሽ ገደብ ይሁን አልሁ። በውኑ ከተወለድህ ጀምሮ ማለዳን አዝዘህ ታውቃለህን? ለወገግታም ስፍራውን አስታውቀኸዋልን? የምድርን ዳርቻ ይይዝ ዘንድ፥ ከእርሷም በደለኞች ይናወጡ ዘንድ፥ ጭቃ ከማኅተም በታች እንደሚለወጥ እንዲሁም እርሱ ይለወጣል፥ ፍጥረትም ሁሉ እንደ ልብስ ተቀልሞአል። ከበደለኞች ብርሃናቸው ተከልክሎአል፥ ከፍ ያለውም ክንድ ተሰብሮአል። ወደ ባሕር ምንጭስ ውስጥ ገበተሃልን? በቀላዩስ መሠረት ውስጥ ተመላልሰሃልን? የሞት በሮች ተገልጠውልሃልን? የሞትንስ ጥላ ደጆች አይተሃልን? ምድርንስ በስፋትዋ አስተውለሃታልን? ሁሉን አውቀህ እንደሆነ ተናገር። ወደ ዳርቻው ትነዳው ዘንድ፥ ወደ ቤቱም የሚያደርሰውን ጐዳና ታውቅ ዘንድ፥ የብርሃን መኖሪያ መንገድ የት ነው? የጨለማውስ ቦታ ወዴት አለ? በዚያን ጊዜ ተወልደህ ነበርና፥ የዕድሜህም ቍጥር ብዙ ነውና፥ በእውነት አንተ ሳታውቅ አትቀርም። በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን? የበረዶውንስ ቤተ መዛግብት አይተሃልን? ይኸውም ለመከራ ጊዜ ለውጊያና ለጦርነት ቀን የጠበቅሁት ነው። ብርሃንስ በምን መንገድ ይከፋፈላል? የምሥራቅስ ነፋስ በምድር ላይ እንዴት ይበተናል? ባድማውንና ውድማውን እንዲያጠግብ፥ ሣሩንም እንዲያበቅል፥ ማንም በሌለባት ምድር ላይ፥ ሰውም በሌለባት ምድረ በዳ ላይ ዝናብ እንዲዘንብ፥ ለፈሳሹ ውኃ መተላለፊያውን፥ ወይም ለሚያንጐደጉድ መብረቅ መንገድን ያበጀ ማን ነው? በውኑ ለዝናብ አባት አለውን? ወይም የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው? በረዶስ ከማን ማኅፀን ወጣ? የሰማዩንስ አመዳይ ማን ወለደው? ውኆች እንደ ድንጋይ ጠነከሩ፥ የቀላዩም ፊት ረግቶአል። በውኑ የሰባቱን ከዋክብት ዘለላ ታስር ዘንድ፥ ወይስ ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ ትፈታ ዘንድ ትችላለህን? ወይስ ማዛሮት የሚባሉትን ከዋክብት በጊዜያቸው ታወጣ ዘንድ፥ ወይስ ድብ የሚባለውን ኮከብ ከልጆቹ ጋር ትመራ ዘንድ ትችላለህን? የሰማይን ሥርዓት ታውቃለህን? በምድርስ ለይ እንዲፈጸም ማድረግ ትችላለህን? የውኆች ሙላት ይሸፍንህ ዘንድ። ቃልህን ወደ ደመናት ታነሣ ዘንድ ትችላለህን? መብረቆች ሄደው፦ ‘እነሆ፥ እዚህ አለን’ ይሉህ ዘንድ፥ ልትልካቸው ትችላለህን? በውስጡስ ጥበብን ያኖረ፥ ለሰውስ ልብ ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው? የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቈጥር የሚችል ማን ነው? ትቢያ በተበጠበጠ ጊዜ፥ ጓሎቹም በተጣበቁ ጊዜ፥ የሰማይን ደመና ለዝናብ ሊያዘነብል የሚችል ማን ነው? በዋሾቻቸው ውስጥ ተጋድመው፥ በጫካም ውስጥ አድብተው ሳሉ፥ ለአንበሳይቱ አደን ታድናለህን? የልጆችዋንስ ነፍስ ታጠግብ ዘንድ ትችላለህን? ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ፥ ለቁራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው?”