ኢዮብ 24:1-25
ኢዮብ 24:1-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“እግዚአብሔር ዘመኖችን ለምን ረሳቸው? ኃጥኣን የድንበሩን ምልክት አለፉ፤ እረኛውንም ከመንጋዎቹ ጋር ይነጥቃሉ። የድሃአደጎቹን አህያ ይነዳሉ የመበለቲቱንም በሬ ስለ መያዣ ይወስዳሉ። ደካሞችን ከእውነት መንገድ ያወጣሉ፤ የምድርም የዋሃን ሁሉ በአንድነት ይሸሸጋሉ። እነሆ፥ በምድረ በዳ እንዳሉ እንደ ሜዳ አህዮች ሆኑ። ስለ እኔም ሥራቸውን ትተው ይወጣሉ፤ መብል፦ ከልጅነታቸው ጀምሮ ይጥማቸዋል። “የራሳቸው ያልሆነውን እርሻ ያለ ሰዓቱ ያጭዳሉ። ኃጥኣን ድሆችን በወይናቸው ቦታ ያለ ዋጋና ያለ ቀለብ ያሠሩአቸዋል። ብዙዎችን የተራቈቱትንም ያለ ልብስ ያሳድሩአቸዋል። መጐናጸፊያቸውንም ይገፍፏቸዋል። በካፊያና ከተራሮች በሚወርድ ጠል ይረጥባሉ፤ መጠጊያም የላቸውምና ቋጥኙን ተተገኑ። ድሃአደጉን ልጅ ከጡቱ ይነጥላሉ፤ ችግረኛውንም ያሠቃያሉ። ችግረኞችን በደሉአቸው፥ ጣሉአቸውም፤ ከተራቡትም የሚጐርሱትን ነጠቋቸው። በጠባብ ቦታ በዐመፅ ይሸምቃሉ፥ የጽድቅንም መንገድ አያውቁም። ድሆችን ከከተማውና ከገዛ ቤቶቻቸው አባረሩአቸው የሕፃናትንም ነፍስ እጅግ አስጮሁ፤ “እግዚአብሔር ግን እነዚህን ለምን አልገሠጻቸውም? በምድር ላይ ሳሉ አላስተዋሉም፥ የቅንነት መንገድንም አላዩም። በአደባባይዋም አልሄዱም። ሥራቸውንም ዐውቆ ለጨለማ ዳረጋቸው። በሌሊትም እንደ ሌባ ናቸው። የአመንዝራም ዐይን ድግዝግዝታን ይጠብቃል፦ የማንም ዐይን አያየኝም ይላል፥ ፊቱንም ይሸፍናል። በጨለማ ቤቶችን ይነድላል፤ በቀን ይሸሸጋሉ፤ ብርሃንንም አያዩም። የጥዋት ብርሃን ለእነርሱ ሁሉ እንደ ሞት ጥላ ነው፤ የሚሆነውን ድንጋጤ ያውቃሉና። ሞትንም ይጠራጠራሉና። እርሱ በውኃ ፊት ላይ በርሮ ያልፋል፤ እድል ፋንታውም በምድር ላይ የተረገመች ናት፤ ተክላቸው በምድር ላይ ሲደርቅ ያያሉ። ያላቸውም ድሀኣደጉን በዘበዙት። ከዚህም በኋላ ኀጢአቱን ያስባል። እንደ ጤዛ ትነት ይጠፋል። እንደ ሥራውም ይከፈለዋል። ዐመፀኛም ሁሉ እንደ በሰበሰ ዛፍ ይሰበራል። ለማትወልደው ለመካኒቱ በጎነትን አላደረገላትም፤ ለምትወልደውም አልራራም። ነገር ግን ረዳት የሌላቸውን በቍጣው አጠፋቸው። እርሱም በተነሣ ጊዜ ሰው በሕይወቱ አይታመንም። በታመመም ጊዜ መዳንን ተስፋ አያደርግም። ነገር ግን እርሱ በሕማሙ ይሞታል። ከፍ ከፍ ባለ ጊዜም ብዙዎችን አስጨነቃቸው። እንደ አመድማዶ በሙቀት ይጠወልጋል። ከቃርሚያው እንደሚወድቅ እሸትም ይቈረጣል። እንዲህስ ባይሆን ሐሰተኛ ነህ የሚለኝ፥ ነገሬንስ እንደ ኢምንት የሚያደርገው ማን ነው?”
ኢዮብ 24:1-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ሁሉን ቻይ አምላክ ለምን የፍርድ ቀን አይወስንም? እርሱን የሚያውቁትስ ለምን ያን ቀን እንዲያው ይጠባበቃሉ? ሰዎች ድንበር ይገፋሉ፤ የሰረቁትን መንጋ ያሰማራሉ። የድኻ አደጉን አህያ ቀምተው ይሄዳሉ፤ የመበለቲቱንም በሬ በመያዣነት ይወስዳሉ። ድኾችን ከመንገድ ያስወግዳሉ፤ የምድሪቱም ችግረኞችን ይሸሸጋሉ። በምድረ በዳ እንዳሉ የሜዳ አህዮች፣ ድኾች ምግብ ፍለጋ ይራወጣሉ፤ ከበረሓው ምድር ለልጆቻቸው ምግብ ይሻሉ። ከሜዳ መኖ ይሰበስባሉ፤ ከክፉዎች የወይን ቦታም ይቃርማሉ። ዕራቍታቸውን ያለ ልብስ ያድራሉ፤ በብርድም ጊዜ የሚለብሱት የላቸውም። ከተራራ በሚወርድ ዝናብ በስብሰዋል፤ መጠለያ ዐጥተው ቋጥኝ ዐቅፈዋል። አባት የሌለው ልጅ ከዕቅፍ ተነጥቋል፤ የድኻውም ልጅ በዕዳ ተይዟል። ዕራቍታቸውን ያለ ልብስ ይሄዳሉ፤ ነዶ ይሸከማሉ፤ ግን ይራባሉ። በየተረተሩ የወይራ ዘይት ያወጣሉ፤ ወይን እየጠመቁ፣ ራሳቸው ግን ይጠማሉ፤ የሟቾች ጣር ጩኸት ከከተማዋ ይሰማል፤ የቈሰሉት ሰዎች ነፍስ ለርዳታ ይጮኻል፤ እግዚአብሔር ግን ተጠያቂዎቹን ዝም ብሏል። “በብርሃን ላይ የሚያምፁ፣ ጐዳናውን የማያውቁ፣ በመንገዱም የማይጸኑ አሉ። ቀኑ ሲመሽ፣ ነፍሰ ገዳይ ይነሣል፤ ችግረኞችንና ድኾችን ይገድላል፤ በሌሊትም እንደ ሌባ ያደባል፤ አመንዝራ በዐይኑ ድንግዝግዝታን ይጠባበቃል፤ ‘ማንም አያየኝም’ ብሎ ያስባል፤ ፊቱንም ይሸፍናል። በጨለማ፣ ቤት ሰርስረው ይገባሉ፤ በቀን ግን ይሸሸጋሉ፤ ብርሃንንም አይፈልጉም። ድቅድቅ ጨለማ ለሁላቸው እንደ ንጋት ነው፤ አሸባሪውን ጨለማ ይወዳጃሉ። “ይሁን እንጂ፣ በውሃ ላይ የሚኵረፈረፍ ዐረፋ ናቸው፤ የወይን ቦታው ሰው የማይደርስበት፣ ርስታቸው ርጉም ነው። ድርቅና ሙቀት የቀለጠውን በረዶ ከቦታው እንደሚያስወግድ፣ ሲኦልም ኀጢአተኞችን ትነጥቃለች። የተሸከመቻቸው ማሕፀን ትረሳቸዋለች፤ ትል ይቦጠቡጣቸዋል፤ ክፉዎች እንደ ዛፍ ይሰበራሉ፤ የሚያስታውሳቸውም የለም። የማትወልደውን መካኒቱን ይቦጠቡጣሉ፤ ለመበለቲቱም አይራሩም። ነገር ግን እግዚአብሔር ኀያላንን በኀይሉ ጐትቶ ይጥላል፤ ቢደላደሉም የሕይወት ዋስትና የላቸውም። ያለ ሥጋት እንዲኖሩ ትቷቸው ይሆናል፤ ዐይኖቹ ግን በመንገዳቸው ላይ ናቸው። ለጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ሆኖም ይጠፋሉ፤ ዝቅ ዝቅ ብለው፤ እንደ ሌሎቹ ይከማቻሉ። እንደ እህል ራስም ይታጨዳሉ። “ይህ እንዲህ ካልሆነማ፣ የሚያስተባብለኝ ማን ነው? ቃሌን ከንቱ የሚያደርገውስ ማን ነው?”
ኢዮብ 24:1-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ ዘመናት አልተሰወረምና እርሱን የሚያውቁ ለምን ወራቱን አያዩም? የድንበሩን ምልክት የሚያፈርሱ አሉ፥ መንጋዎቹን በዝብዘው ያሰማራሉ። የድሀ አድጎቹን አህያ ይነዳሉ፥ የመበለቲቱን በሬ ስለ መያዣ ይወስዳሉ። ድሆቹን ከመንገድ ያወጣሉ፥ የምድርም ችግረኞች ሁሉ ይሸሸጋሉ። እነሆ፥ በምድር በዳ እንዳሉ እንደ ሜዳ አህዮች፥ መብልን ፈልገው ወደ ሥራቸው ይወጣሉ፥ ምድረ በዳውም ለልጆቻቸው መብልን ይሰጣቸዋል። እነዚያ በእርሻ ውስጥ እህላቸውን ያጭዳሉ፥ የበደለኛውንም ወይን ይቃርማሉ። ራቁታቸውን ያለ ልብስ ያድራሉ፥ በብርድ ጊዜ መጐናጸፊያ የላቸውም። ከተራሮች በሚወርድ ዝናብ ይረጥባሉ፥ መጠጊያም አጥተው ቋጥኙን ያቅፋሉ። ድሀ አደጉን ልጅ ከጡቱ የሚነጥሉ አሉ፥ ከችግረኛውም መያዣ ይወስዳሉ። ያለ ልብስ ራቁታቸውን ይሄዳሉ፥ ተርበው ነዶዎችን ይሸከማሉ፥ በእነዚህ ሰዎች አጥር ውስጥ ዘይት ያደርጋሉ፥ ወይንም ይጠምቃሉ፥ ነገር ግን ይጠማሉ። ከከተማውና ከገዛ ቤቶቻቸው ይባረራሉ፥ የልጆችም ነፍስ ለእርዳታ ትጮኻለች፥ እግዚአብሔር ግን ስንፍናቸውን አይመለከትም። እነዚህ በብርሃን ላይ የሚያምፁ ናቸው፥ መንገዱን አያውቁም፥ በጎዳናውም አይጸኑም። ነፍሰ ገዳዩም ሳይነጋ ማልዶ ይነሣል፥ ችግረኞችንና ድሆችን ይገድላል፥ በሌሊትም እንደ ሌባ ነው። የአመንዝራም ዓይን ድግዝግዝታን ይጠብቃል፦ የማንም ዓይን አያየኝም ይላል፥ ፊቱንም ይሸፍናል። ቤቶቹን በጨለማ ይነድላሉ፥ በቀን ይሸሸጋሉ፥ ብርሃንም አያውቁም። የጥዋት ብርሃን ለእነርሱ ሁሉ እንደ ሞት ጥላ ነው፥ የሞትን ጥላ ድንጋጤ ያውቃሉና። እነርሱ በውኃ ፊት ላይ በርረው ያልፋሉ፥ እድል ፈንታቸውም በምድር ላይ የተረገመች ናት፥ ወደ ወይኑ ቦታ መንገድ አይዞሩም። ድርቅና ሙቀት የአመዳዩን ውኃ ያጠፋሉ፥ እንዲሁ ሲኦል በደለኞችን ታጠፋለች። ማኅፀን ትረሳዋለች፥ ትልም በደስታ ይጠባዋል፥ ዳግመኛም አይታሰብም፥ ክፋትም እንደ ዛፍ ይሰበራል። የማትወልደውን መካኒቱን ይበድላታል፥ ለመበለቲቱም በጎነት አያደርግም። ነገር ግን በኃይሉ ኃያላንን ይስባል፥ እርሱም በተነሣ ጊዜ ሰው በሕይወቱ አይታመንም። እግዚአብሔር በደኅና አኑሮአቸዋል፥ በዚያም ይታመናሉ፥ ዓይኖቹ ግን በመንገዳቸው ላይ ናቸው። ጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፥ ይሄዳሉ፥ ይጠወልጋሉም፥ እንደ ሌሎች ሁሉ ይከማቻሉ፥ እንደ እሸትም ራስ ይቈረጣሉ። እንዲህስ ባይሆን ሐሰተኛ የሚያደርገኝ፥ ነገሬንስ እንደ ምናምን የሚያደርገው ማን ነው?
ኢዮብ 24:1-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ሁሉን የሚችል አምላክ ፍርድ የሚሰጥበትን ጊዜ ለምን አይወስንም? የእርሱ ታማኞችስ የፍርዱን ቃል እስከ መቼ ይጠባበቃሉ? “ክፉ ሰዎች ድንበር ያፈርሳሉ። በጎችንም እየሰረቁ ያሰማራሉ። የድኻ አደጉን አህያ ይቀማሉ፤ ባልዋ የሞተባትን ሴት ንብረት የሆነውንም በሬ፥ በመያዣ ስም ይወስዳሉ። ድኾችን በመጸየፍ ከየመንገዱ ያባርራሉ፤ ከፊታቸውም ሸሽተው እንዲደበቁ ያደርጋሉ። “ድኾች በበረሓ እንዳሉ የሜዳ አህዮች ለልጆቻቸው ምግብ ለመፈለግ ወጥተው ይንከራተታሉ፤ ተቀጥረውም የሌላ ሰው መከር ሰብሳቢ ይሆናሉ፤ የክፉ ሰው ንብረት በሆነ የወይን አትክልት ቦታ ይቃርማሉ። ሌሊቱን ሙሉ ራቁታቸውን ተኝተው ያድራሉ፤ ብርድ የሚከላከሉበትም ልብስ የላቸውም። በተራራ ላይ በሚዘንበው ዝናብ ሰውነታቸው ይረሰርሳል፤ መጠለያም አጥተው ቋጥኝ ተጠግተው ያድራሉ። “አባቱ የሞተበት ልጅ አገልጋይ እንዲሆናቸው የእናቱን ጡት አስጥለው ይነጥቃሉ፤ የችግረኛውንም ልጅ የዕዳ መያዣ አድርገው ይወስዳሉ። ድኾች ምንም ልብስ ሳይኖራቸው ራቁታቸውን ወደ ሥራ ይሰማራሉ። በመከር ወራት ነዶ ተሸክመው እያጋዙ እነርሱ ይራባሉ። በክፉ ሰዎች የአትክልት ቦታ ከወይራ ፍሬ ዘይት ያወጣሉ፤ ከወይን ዘለላም የወይን ጠጅን ይጠምቃሉ፤ እነርሱ ግን ይጠማሉ። በየከተማው ለመሞት የሚያጣጥሩ ሰዎች ይቃትታሉ፤ የቈሰሉትም ሰዎች ርዳታ በመጠየቅ ይጮኻሉ። እግዚአብሔር ግን በእነርሱ ላይ የተሠራውን ግፍ አልተመለከተም። “ብርሃንን የሚጠሉ ሰዎች አሉ፤ ብርሃንም ምን እንደ ሆነ ስለማያውቁ የብርሃንን መንገድ አይከተሉም። ነፍሰ ገዳይ ገና ሳይነጋ በማለዳ ተነሥቶ፥ ድኾችንና ችግረኞችን ይገድላል፤ በሌሊትም ለስርቆት ይሰማራል። አመንዝራ ሰው የቀኑን መምሸት ይጠባበቃል፤ ማንም ሰው እንዳያየው ፊቱን ይሸፍናል። ሌቦች በሌሊት ቤት ሰርስረው ለስርቆት ይገባሉ፤ ቀን ግን ተሸሽገው ይውላሉ። ብርሃንንም ይጠላሉ። የጨለማ ሽብር ስለሚያስደስታቸው ለሁሉም ድቅድቅ ጨለማ ማለዳቸው ነው።” “ሆኖም እነርሱ በውሃ ላይ እንደሚታይ ዐረፋ ለጥቂት ጊዜ ብቻ ይታያሉ፤ ርስታቸው የተረገመ ይሆናል፤ ወደ ወይን ተክል ቦታቸውም ማንም አይሄድም። በረዶ በሙቀት ቀልጦ ውሃውም በድርቅ እንደሚጠፋ፥ ኃጢአተኞችም ሞተው በሙታን ዓለም ይጠፋሉ። እናቶቻቸው ሁሉ ይረሱአቸዋል፤ ሥጋቸውንም ትል ይበላዋል፤ ክፉ ሰዎች አይታወሱም፤ ነገር ግን እንደ ዛፍ ይሰባበራሉ። ይህ ሁሉ የደረሰባቸው እነርሱ ልጆች የሌላቸው መኻኖች ሴቶችን በመበዝበዛቸውና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች ምንም ርኅራኄ ባለማሳየታቸው ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር በኀይሉ በሥልጣን ላይ ያሉትን ሰዎች ያስወግዳቸዋል። ኑሮአቸው የተሳካ ቢመስልም እንኳ የመኖር ዋስትና የላቸውም። እግዚአብሔር በሰላም እንዲኖሩ ቢፈቅድላቸውም እንኳ የሚሄዱበትን መንገድ ሁሉ አተኲሮ ይመለከታል። ክፉ ሰዎች ለጥቂት ጊዜ ይበለጽጋሉ፤ ነገር ግን ወዲያውኑ እንደ አረም ጠውልገው ይጠፋሉ፤ እንደ እህልም ይታጨዳሉ። እንደዚህ አይደለም ከተባለ እኔ ሀሰተኛ መሆኔንና የተናገርኩትም ቃል ትክክል አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ማነው?”
ኢዮብ 24:1-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ሁሉን የሚችል አምላክ የወሰናቸውን ጊዜያት ለምን አያሳውቅም? የሚያውቁትስ ቀኖቹን ለምን አያዩም? የድንበሩን ምልክት የሚያፈርሱ አሉ፥ መንጋዎቹን ቀምተው ያሰማራሉ። የወላጅ አልባውን አህያ ይነዳሉ፥ የመበለቲቱን በሬ ለመያዣነት ይወስዳሉ። ድሆቹን ከመንገድ ያስወጣሉ፥ የምድርም ችግረኞች ሁሉ ይሸሸጋሉ። እነሆ፥ በምድረ በዳ እንዳሉ እንደ ሜዳ አህዮች፥ መብልን ፈልገው ወደ ሥራቸው ይወጣሉ፥ ምድረ በዳውም ለልጆቻቸው መብልን ይሰጣቸዋል። እነዚያ በእርሻ ውስጥ እህላቸውን ያጭዳሉ፥ የበደለኛውንም ወይን ይቃርማሉ። ራቁታቸውን ያለ ልብስ ያድራሉ፥ በብርድ ጊዜ የሚደረብ የላቸውም። ከተራሮች በሚወርድ ዝናብ ይረጥባሉ፥ መጠጊያም አጥተው ቋጥኙን ያቅፋሉ። አባቱ የሞተበትን ልጅ ከጡቱ የሚነጥሉ አሉ፥ ከችግረኛውም መያዣ ይወስዳሉ። ያለ ልብስ ራቁታቸውን ይሄዳሉ፥ ተርበው ነዶዎችን ይሸከማሉ፥ በእነዚህ ሰዎች አጥር ውስጥ ዘይት ያወጣሉ፥ ወይንም ይጠምቃሉ፥ ነገር ግን ይጠማሉ። በከተማው ለመሞት የሚያጣጥሩ ያቃስታሉ፥ ቁስለኞችም ለእርዳታ ይጮኻሉ፥ እግዚአብሔር ግን ልመናቸውን አይመለከትም።” “እነዚህ በብርሃን ላይ የሚያምፁ ናቸው፥ መንገዱን አያውቁም፥ በጎዳናውም አይጸኑም። ነፍሰ ገዳዩም ሳይነጋ ማልዶ ይነሣል፥ ችግረኞችንና ድሆችን ይገድላል፥ በሌሊትም እንደ ሌባ ነው። የአመንዝራ ሰው ዐይን ጨለማን ይጠብቃል፦ የማንም ዐይን አያየኝም ይላል፥ ፊቱንም ይሸፍናል። ቤቶቹን በጨለማ ይሰረስራሉ፥ በቀን ይሸሸጋሉ፥ ብርሃንም አያውቁም። የጥዋት ብርሃን ለእነርሱ ሁሉ እንደ ሞት ጥላ ነው፥ የሞትን ጥላ አስደንጋጭነት ያውቃሉና።” “እነርሱ በውኃ ላይ ተንሳፈው ያልፋሉ፥ ድርሻቸውም በምድር ላይ የተረገመች ናት፥ ወደ ወይኑ ቦታ መንገድ አይመለሱም። ድርቅና ሙቀት የበረዶውን ውኃ ያጠፋሉ፥ እንዲሁ ሲኦል በደለኞችን ታጠፋለች። ማኅፀን ትረሳዋለች፥ ትልም በደስታ ይጠባዋል፥ ዳግመኛም የሚያስታውሰው የለም፥ ክፋትም እንደ ዛፍ ይሰበራል።” “የማትወልደውን መካኒቱን ይበድላታል፥ ለመበለቲቱም መልካም አያደርግም። ነገር ግን በኃይሉ ኃያላንን ያስቀጥላል፥ እርሱም በተነሣ ጊዜ ሰው በሕይወቱ አይታመንም። እግዚአብሔር በደኅና አኑሮአቸዋል፥ በዚያም ይታመናሉ፥ ዐይኖቹ ግን መንገዳቸውን ይመለከታሉ። ጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፥ ይሄዳሉ፥ ይጠወልጋሉም፥ እንደ ሌሎች ሁሉ ይከማቻሉ፥ እንደ እሸትም ራስ ይቈረጣሉ። እንዲህስ ባይሆን ሐሰተኛ የሚያደርገኝ፥ ነገሬንስ እንደ ከንቱ የሚያደርገው ማን ነው?”