ኢዮብ 2:9-10
ኢዮብ 2:9-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሚስቱም፦ “እስከ አሁን ፍጹምነትህን ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት” አለችው። እርሱ ግን፦ “አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፥ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን?” አላት። በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም።
ኢዮብ 2:9-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ብዙ ወራትም ካለፈ በኋላ ሚስቱ እንዲህ አለችው፥ “እስከ መቼ ትታገሣለህ? 9 ‘ሀ’ ዳግመኛም እግዚአብሔርን ጥቂት ወራት ደጅ እጠናዋለሁ፤ ዳግመኛም መከራውን እታገሠዋለሁ፤ የቀድሞው ኑሬዬንም ተስፋ አደርገዋለሁ ትላለህን? 9 ‘ለ’ እንደዚህስ እንዳትል ከዚህ ዓለም እነሆ ስም አጠራርህ ጠፋ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቼም ሞቱ፥ ማኅፀኔም በምጥ ተጨነቀ፥ በከንቱም ደከምሁ። 9 ‘ሐ’ አንተም በመግልና በትል ትኖራለህ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ትዛብራለህ። 9 ‘መ’ እኔ ግን እየዞርሁ እቀላውጣለሁ። ከአንዱ መንደር ወደ አንዱ መንደር፥ ከአንዱ ቤትም ወደ አንዱ ቤት እሄዳለሁ፤ ከድካሜና በእኔ ላይ ካለ ችግሬም ዐርፍ ዘንድ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ እጠብቃለሁ፤ ነገር ግን አሁን እግዚአብሔርን ስደብና ሙት።” እርሱ ግን፦ ወደ እርስዋ ተመለከተና እንዲህ አላት፥ “አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፤ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉውን ነገርስ አንታገሥምን?” በዚህ በደረሰበት ሁሉ ኢዮብ በእግዚአብሔር ፊት በከንፈሩ አልበደለም።
ኢዮብ 2:9-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሚስቱም፣ “አሁንም ታማኝነትህን አልተውህምን? ይልቁን እግዚአብሔርን ርገምና ሙት!” አለችው። እርሱም፣ “አነጋገርሽ እንደ ሞኝ ሴት ነው፤ መልካሙን ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ተቀበልን፤ ክፉውንስ አንቀበልምን? አላት።” በዚህ ሁሉ፣ ኢዮብ በንግግሩ አልበደለም።
ኢዮብ 2:9-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሚስቱም፦ እስከ አሁን ፍጹምነትህን ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት አለችው። (የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።) ዳግመኛ እግዚአብሔርን ጥቂት ወራት ደጅ እጠናዋለሁ፥ ዳግመኛም መከራውን እታገሠዋለሁ የቀድሞ ኑሮዬንም ተስፋ አደርገዋለሁ ትላለህን? አለችው። እንደዚህሳ እንዳትል ከዚህ ዓለም እነሆ ስም አጠራርህ ጠፋ፥ ሴቶች ልጆቼና ወንዶች ልጆቼም ሞቱ እኔስ ዘጠኝ ወር ሳረግዝ ሳምጥ ስወልድ ሳይረቡኝ ሳይጠቅሙኝ በከንቱ ደከምሁ አለች። አንተም በመግል ተውጠህ በትል ተከብበህ ትኖራለህ፥ ሌሊቱን ሁሉ ስትዛብር ታድራለህ። እኔ ግን እየዞርሁ እቀላውጣለሁ። ከአንዱ አገር ወደ አንዱ አገር ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት እሄዳለሁ፥ ከድካሜ በእኔ ላይ ካለ ከችግሬም አርፍ ዘንድ ከጧት ጀምሮ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ እጠብቃለሁ፥ አሁን ግን እግዚአብሔርን የማይገባ ቃል ተናግረኸው ሙት አለች። እርሱ ግን፦ አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፥ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን? አላት። በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም።
ኢዮብ 2:9-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሚስቱም “አሁንም በእግዚአብሔር ላይ ያለህ ቅንነት እንደ ጸና ነውን? ይልቅስ እግዚአብሔርን ካደውና ሙት!” አለችው። ኢዮብም “እንዴት የሞኝ ሴት ንግግር ትናገሪያለሽ? እግዚአብሔር መልካም ነገር ሲሰጠን በደስታ እንቀበላለን፤ ታዲያ፥ መከራ ሲያመጣብን በእርሱ ላይ ማጒረምረም ይገባናልን?” አላት። ኢዮብ ምንም እንኳ ይህ ሁሉ መከራና ሥቃይ ቢደርስበት በእግዚአብሔር ላይ ክፉ ነገር በመናገር ኃጢአት አልሠራም።