ኢዮብ 2:3-9

ኢዮብ 2:3-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሰይ​ጣ​ንን አለው፥ “በባ​ሪ​ያዬ በኢ​ዮብ ላይ እን​ዲህ እን​ዳ​ታ​ስብ ተጠ​ን​ቀቅ፤ በም​ድር ላይ እንደ እርሱ ያለ ገር፥ ጻድ​ቅና ንጹሕ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን የሚ​ፈራ፥ ከክ​ፋ​ትም ሁሉ የራቀ፥ ዳግ​መ​ኛም ቅን የሆነ ሰው የለ​ምና፤ አንተ ግን ሀብ​ቱን በከ​ንቱ አጠፋ ዘንድ ነገ​ር​ኸኝ።” ሰይ​ጣ​ንም መልሶ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፥ “ቍር​በት ስለ ቍር​በት ነው፤ ሰው ያለ​ውን ሁሉ ስለ ሕይ​ወቱ ይሰ​ጣል። ነገር ግን አሁን እጅ​ህን ዘር​ግ​ተህ አጥ​ን​ቱ​ንና ሥጋ​ውን ዳስስ፤ በእ​ው​ነት በፊ​ትህ ይሰ​ድ​ብ​ሃል” ብሎ መለሰ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሰይ​ጣ​ንን አለው፥ “እነሆ፥ ሥጋ​ው​ንና አጥ​ን​ቱን በእ​ጅህ ሰጠ​ሁህ። ነገር ግን ሕይ​ወ​ቱን ተው።” ሰይ​ጣ​ንም ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ወጣ፥ ኢዮ​ብ​ንም ከእ​ግሩ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቍስል መታው። ቍስ​ሉ​ንም ያክ​ክ​በት ዘንድ ገል ወሰደ፥ ከከ​ተ​ማም ወጥቶ በአ​መድ ላይ ተቀ​መጠ። ብዙ ወራ​ትም ካለፈ በኋላ ሚስቱ እን​ዲህ አለ​ችው፥ “እስከ መቼ ትታ​ገ​ሣ​ለህ? 9 ‘ሀ’ ዳግ​መ​ኛም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ጥቂት ወራት ደጅ እጠ​ና​ዋ​ለሁ፤ ዳግ​መ​ኛም መከ​ራ​ውን እታ​ገ​ሠ​ዋ​ለሁ፤ የቀ​ድ​ሞው ኑሬ​ዬ​ንም ተስፋ አደ​ር​ገ​ዋ​ለሁ ትላ​ለ​ህን? 9 ‘ለ’ እን​ደ​ዚ​ህስ እን​ዳ​ትል ከዚህ ዓለም እነሆ ስም አጠ​ራ​ርህ ጠፋ፤ ወን​ዶ​ችና ሴቶች ልጆቼም ሞቱ፥ ማኅ​ፀ​ኔም በምጥ ተጨ​ነቀ፥ በከ​ን​ቱም ደከ​ምሁ። 9 ‘ሐ’ አን​ተም በመ​ግ​ልና በትል ትኖ​ራ​ለህ፤ ሌሊ​ቱ​ንም ሁሉ ትዛ​ብ​ራ​ለህ። 9 ‘መ’ እኔ ግን እየ​ዞ​ርሁ እቀ​ላ​ው​ጣ​ለሁ። ከአ​ንዱ መን​ደር ወደ አንዱ መን​ደር፥ ከአ​ንዱ ቤትም ወደ አንዱ ቤት እሄ​ዳ​ለሁ፤ ከድ​ካ​ሜና በእኔ ላይ ካለ ችግ​ሬም ዐርፍ ዘንድ ፀሐይ እስ​ኪ​ገባ ድረስ እጠ​ብ​ቃ​ለሁ፤ ነገር ግን አሁን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ስደ​ብና ሙት።”

ኢዮብ 2:3-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም፥ በከንቱም አጠፋው ዘንድ አንተ በእርሱ ላይ ምንም ብታንቀሳቅሰኝ፥ እስከ አሁን ፍጹምነቱን ይዞአል። ሰይጣንም መልሶ እግዚአብሔርን፦ ቁርበት ስለ ቁርበት ነው፥ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል። ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳብስ፥ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል አለው። እግዚአብሔም ሰይጣንን፦ ሕይወቱን ተወው እንጂ እነሆ፥ እርሱ በእጅህ ነው አለው። ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፥ ኢዮብንም ከእግሩ ጫማ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቍስል መታው። ሥጋውንም ይፍቅበት ዘንድ ገል ወሰደ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ። ሚስቱም፦ እስከ አሁን ፍጹምነትህን ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት አለችው። (የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።) ዳግመኛ እግዚአብሔርን ጥቂት ወራት ደጅ እጠናዋለሁ፥ ዳግመኛም መከራውን እታገሠዋለሁ የቀድሞ ኑሮዬንም ተስፋ አደርገዋለሁ ትላለህን? አለችው። እንደዚህሳ እንዳትል ከዚህ ዓለም እነሆ ስም አጠራርህ ጠፋ፥ ሴቶች ልጆቼና ወንዶች ልጆቼም ሞቱ እኔስ ዘጠኝ ወር ሳረግዝ ሳምጥ ስወልድ ሳይረቡኝ ሳይጠቅሙኝ በከንቱ ደከምሁ አለች። አንተም በመግል ተውጠህ በትል ተከብበህ ትኖራለህ፥ ሌሊቱን ሁሉ ስትዛብር ታድራለህ። እኔ ግን እየዞርሁ እቀላውጣለሁ። ከአንዱ አገር ወደ አንዱ አገር ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት እሄዳለሁ፥ ከድካሜ በእኔ ላይ ካለ ከችግሬም አርፍ ዘንድ ከጧት ጀምሮ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ እጠብቃለሁ፥ አሁን ግን እግዚአብሔርን የማይገባ ቃል ተናግረኸው ሙት አለች።

ኢዮብ 2:3-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔርም ሰይጣንን “አገልጋዬን ኢዮብን ልብ ብለህ አየኸውን? እርሱን የመሰለ ታማኝና ደግ ሰው በምድር ላይ አይገኝም፤ እርሱ ከክፋት ሁሉ ርቆ እኔን የሚፈራ ቀጥተኛ ሰው ነው፤ እርሱን ማጥፋት እንድትችል እፈቅድልህ ዘንድ ያነሣሣኸኝ በከንቱ ነው፤ እነሆ፥ ኢዮብ አሁንም በቅንነቱ እንደ ጸና ነው” አለው። ሰይጣንም “በቊርበት ፈንታ ቊርበት” እንዲሉ፥ “ሰው እኮ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል። ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ በመላ ሰውነቱ ላይ ጒዳት ብታደርስበት በእርግጥ ፊት ለፊት ይሰድብሃል!” አለው። እግዚአብሔርም ሰይጣንን “መልካም ነው፤ አትግደለው እንጂ በእርሱ ላይ የፈለግኸውን ማድረግ ትችላለህ” አለው። ከዚህ በኋላ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ኢዮብን ከራስ ጠጒሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ በከባድ ቊስል እንዲሠቃይ አደረገው። ከዚህም የተነሣ ኢዮብ በዐመድ ክምር ላይ ተቀምጦ ቊስሉን በገል ያክ ጀመር። ሚስቱም “አሁንም በእግዚአብሔር ላይ ያለህ ቅንነት እንደ ጸና ነውን? ይልቅስ እግዚአብሔርን ካደውና ሙት!” አለችው።