ኢዮብ 14:1-17
ኢዮብ 14:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ከሴት የተወለደ ሟች ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ነው፥ የቍጣ መከራንም የተሞላ ነው። እንደ አበባ ይወጣል፥ ይረግፋልም፤ እንደ ጥላም ያልፋል፥ እርሱም አይኖርም። እንደዚህስ ያለውን ሰው አንተ የምትመረምረው አይደለምን? በፊትህስ እርሱን ወደ ፍርድ ታገባዋለህን? ከርኵሰት የሚነጻ ማን ነው? አንድ ስንኳ የለም። በምድር ላይ አንድ ቀንም እንኳ ቢኖር፤ ወሮቹም በአንተ ዘንድ የተቈጠሩ ናቸው፤ ዘመኑንም ወስነህ ትሰጠዋለህ፤ እርሱም ከዚያ አያልፍም። “እንደ ምንደኛ ሕይወቱን እንዲጠባበቃት፥ ያርፍ ዘንድ ከእርሱ ዘወር በል። ዛፍ ቢቈረጥ ደግሞ ያቈጠቍጥ ዘንድ፥ ተስፋ አለው፤ ቅርንጫፉም አያልቅም። ሥሩም በምድር ውስጥ ቢያረጅ፥ ግንዱም በጭንጫ ውስጥ ቢሞት፥ ከውኃ ሽታ የተነሣ ያቈጠቍጣል፤ እንደ አዲስ ተክልም ያፈራል። ሰው ግን ከሞተ ፈጽሞ ይተላል፤ ሟች ሰው ከሞተ በኋላ እንግዲህ አይኖርም። ባሕር ይጐድላል፤ ወንዙም ይነጥፋል፤ ይደርቅማል። ሰውም ከተኛ በኋላ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፤ ከእንቅልፉም አይነሣም። “በመቃብር ውስጥ ምነው በጠበቅኸኝ ኖሮ! ቍጣህ እስኪበርድም ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ! እስከምታስበኝም ምነው ቀጠሮ በሰጠኸኝ ኖሮ! ሰው የሕይወቱን ዘመን ፈጽሞ ከሞተ በኋላ በሕይወት የሚኖር ቢሆን ዳግመኛ እስክወለድ ድረስ፥ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር። በጠራኸኝም ጊዜ በመለስሁልህ ነበር፤ የእጅህንም ሥራ አትናቀኝ። አሁን ግን ኀጢአቶችን ቈጥረሃል፤ ከበደሌም እንዲቱንስ እንኳ አልረሳህም። መተላለፌን በከረጢት ውስጥ አትመሃል፥ ኀጢአቴንም ለብጠህባታል።
ኢዮብ 14:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ከሴት የተወለደ ሰው፣ ዘመኑ ዐጭርና በመከራ የተሞላ ነው፤ እንደ አበባ ይፈካል፤ ይረግፋልም፤ እንደ ጥላ ይፈጥናል፤ አይጸናምም። እንደዚህ ባለ ሰው ላይ ዐይንህን ታሳርፋለህን? ለፍርድስ በፊትህ ታቀርበዋለህን? ከርኩስ ነገር ውስጥ ንጹሕን ማን ሊያወጣ ይችላል? አንድ እንኳ የሚችል የለም! የሰው ዕድሜ አስቀድሞ የተወሰነ ነው፤ የወራቱንም ብዛት ወስነህ አስቀምጠሃል፤ ሊያልፈው የማይችለውንም ገደብ አኖርህለት። እንግዲህ ዘመኑን እንደ ምንደኛ እስኪፈጽም ድረስ፣ ፊትህን ከርሱ መልስ፤ ተወው። “ዛፍ እንኳ ቢቈረጥ፣ እንደ ገና ሊያቈጠቍጥ፣ አዳዲስ ቅርንጫፍም ሊያበቅል ተስፋ አለው። ሥሩ በምድር ውስጥ ቢያረጅ፣ ጕቶው በመሬት ውስጥ ቢበሰብስም፣ የውሃ ሽታ ባገኘ ጊዜ ያቈጠቍጣል፤ እንደ ተተከለም ችግኝ ቅርንጫፍ ያወጣል። ሰው ግን ይሞታል፤ ክንዱንም ይንተራሳል፤ ነፍሱም ትወጣለች፤ ከእንግዲህስ የት ይገኛል? ውሃ ከባሕር ውስጥ እንደሚያልቅ፣ የወንዝ ውሃም ጠፍቶ እንደሚደርቅ፣ እንደዚሁም ሰው ይተኛል፤ ቀናም አይልም፤ ሰማይ እስከሚያልፍ ድረስ አይነቃም፤ ከእንቅልፉም አይነሣም። “ምነው መቃብር ውስጥ በሰወርኸኝ! ቍጣህም እስከሚያልፍ በሸሸግኸኝ! ምነው ቀጠሮ ሰጥተህ፣ ከዚያ በኋላ ባስታወስኸኝ! ሰው ከሞተ በኋላ ተመልሶ በሕይወት ይኖራል? እድሳቴ እስከሚመጣ ድረስ፣ ተጋድሎ የሞላበትን ዘመኔን ሁሉ እታገሣለሁ። ትጠራኛለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ የእጅህንም ሥራ ትናፍቃለህ። በዚያ ጊዜ በርግጥ ርምጃዬን ትከታተላለህ፤ ነገር ግን ኀጢአቴን አትቈጣጠርም። መተላለፌ በከረጢት ይቋጠራል፤ ኀጢአቴንም ትሸፍናለህ።
ኢዮብ 14:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፥ መከራም ይሞላዋል። እንደ አበባ ይወጣል፥ ይረግፋልም፥ እንደ ጥላም ይሸሻል፥ እርሱም አይጸናም። እንደዚህስ ባለ ሰው ላይ ዓይኖችህን ትከፍታለህን? ከአንተስ ጋር እኔን ወደ ፍርድ ታገባለህን? ከርኩስ ነገር ንጹሕን ሊያወጣ ማን ይችላል? አንድ እንኳ የሚችል የለም። የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው፥ የወሩም ቍጥር በአንተ ዘንድ ነው፥ እርሱም ሊተላለፈው የማይችለውን ዳርቻ አደረግህለት። እንደ ምንደኛ ዕድሜው እስኪፈጸም ድረስ ያርፍ ዘንድ ከእርሱ ጥቂት ዘወር በል። ዛፍ ቢቈረጥ ደግሞ ያቈጠቍጥ ዘንድ፥ ቅርንጫፉም እንዳያልቅ ተስፋ አለው። ሥሩም በምድር ውስጥ ቢያረጅ፥ ግንዱም በመሬት ውስጥ ቢሞት፥ ከውኃ ሽታ የተነሣ ያቈጠቍጣል፥ እንደ አትክልት ቅርንጫፍ ያወጣል። ሰው ግን ይሞትና ይጋደማል፥ ሰውም ነፍሱን ይሰጣል፥ እርሱስ ወዴት አለ? ውኃ ከባሕር ውስጥ ያልቃል፥ ወንዙም ያንሳል ይደርቅማል። ሰውም ተኝቶ አይነሣም፥ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፥ ከእንቅልፉም አይነሣም። በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! ቍጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ! ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ! በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? መለወጤ እስኪመጣ ድረስ፥ የሰልፌን ዘመን ሁሉ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር። በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፥ የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር። አሁን ግን እርምጃዬን ቈጥረኸዋል፥ ኃጢአቴንም ትጠባበቃለህ። መተላልፌ በከረጢት ውስጥ ታትሞአል፥ ኃጢአቴንም ለብጠህበታል።
ኢዮብ 14:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ሥጋ የለበሰ ሰው ዕድሜው አጭር ነው፤ ያውም ቢሆን በመከራ የተሞላ ነው። እንደ አበባ ታይቶ ወዲያውኑ ይረግፋል፤ እንደ ጥላም ብዙ ሳይቈይ ወዲያው ያልፋል። ታዲያ እንዲህ ዐይነቱን ሰብአዊ ፍጡር ትከታተላለህን? በፊትህስ ለፍርድ ታቀርበዋለህን? ከርኩስ ነገር ንጹሕ ነገርን ማግኘት የሚችል ከቶ ማንም የለም። የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው፤ የሚኖርባቸውም ወራት በአንተ ዘንድ የተቈጠሩ ናቸው፤ አንተም ከወሰንክለት የዕድሜ ገደብ የሚያልፍ የለም። ቅጥረኛ የቀን ሥራውን ሲፈጽም እንደሚደሰት፥ ሰውም በድካም ዘመኑ እንዲደሰት ታገሠው። “ለተቈረጠ የዛፍ ጒቶ እንኳ ተስፋ አለው፤ እንደ ገና ሊያቈጠቊጥና ቅርንጫፎችም ሊያበቅል ይችላል። ምንም እንኳ ሥሮቹ በመሬት ውስጥ ቢያረጁ ግንዱም በዐፈር ውስጥ ቢበሰብስ፥ የውሃ ጠል ካገኘ እንደ ገና ያቈጠቊጣል፤ እንደ አዲስ ተክልም ቅርንጫፎችን ያወጣል። ሰው ግን ሞቶ እንዳልነበረ ይሆናል፤ ከሞተ በኋላስ የት ይገኛል? “የሐይቅ ውሃ ተኖ እንደሚያልቅ፥ የወንዝም ፈሳሽ እንደሚደርቅ፥ ሰውም እንዲሁ ከሞተ በኋላ አይመለስም፤ ሰማይ እስከሚያልፍ ድረስ አይነቃም፤ ከእንቅልፉም አይነሣም። “ምነው፥ በሙታን ዓለም ብትሰውረኝ! ቊጣህም እስከሚያልፍ ብትሸሽገኝ! የቀጠሮም ቀን ወስነህ ብታስበኝ! ሰው ከሞተ በኋላ በሕይወተ ሥጋ ሊኖር ይችላልን? ዕረፍቴ እስከምትመጣበት ጊዜ ድረስ፥ ይህን የትግል ዘመኔን ፍጻሜ በትዕግሥት እጠባበቃለሁ። በዚያን ጊዜ አንተ ትጠራኛለህ፤ እኔም ‘አቤት’ እልሃለሁ፤ ፍጡርህ የሆንኩትን እኔን ለማየት ትናፍቃለህ። እነሆ አሁን እርምጃዬን ሁሉ ትከታተላለህ፤ ሆኖም ኃጢአቴን አታስብብኝም። በከረጢት ታሽጎ እንደሚወረወር ጒድፍ በደሌን ሁሉ ታስወግድልኛለህ ኃጢአቴንም ትደመስስልኛለህ።
ኢዮብ 14:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፥ በመከራም የተሞላ ነው። እንደ አበባ ይፈካል፥ ይረግፋልም፥ እንደ ጥላም ይሸሻል፥ እርሱም አይጸናም። እንደዚህስ ባለ ሰው ላይ ዐይኖችህን ትተክላለህን? ከአንተስ ጋር እኔን ወደ ፍርድ ታገባለህን? ከርኩስ ነገር ንጹሕን ማን ሊያወጣ ይችላል? አንድ እንኳን የሚችል የለም። የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው፥ የወሩም ቍጥር በአንተ ዘንድ ነው፥ እርሱም ሊተላለፈው የማይችለውን ዳርቻ አደረግህለት። እንደ ምንደኛ ዕድሜው እስኪፈጸም ድረስ ያርፍ ዘንድ ከእርሱ ጥቂት ዘወር በል።” “ዛፍ እንኳን ተሰፋ አለው፥ ቢቈረጥ የማቈጠቁጥ፥ ቅርንጫፉም የማደግ እድል አለው። ሥሩም በምድር ውስጥ ቢያረጅ፥ ግንዱም በመሬት ውስጥ ቢሞት፥ በውኃ ሽታ ያቈጠቁጣል፥ እንደ አትክልት ቅርንጫፍ ያወጣል። ሰው ግን ይሞትና ይጋደማል፥ ሰውም ነፍሱ ትወጣለች፥ እርሱስ ወዴት አለ? ውኃ ከባሕር ውስጥ ያልቃል፥ ወንዙም ያንሳል ይደርቅማል። ሰውም እንዲሁ ተኝቶ አይነሣም፥ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፥ ከእንቅልፉም አይነሣም። በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! ቁጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ! ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ! በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? ዕረፍቴ እስኪመጣ ድረስ፥ የአገልግሎቴን ዘመን ሁሉ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር። በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፥ የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር። አሁን ግን እርምጃዬን ቈጥረኸዋል፥ ይልቁንም ኃጢአቴን ባልተጠባበቅህ። መተላላፌን በከረጢት ውስጥ ታትሞ፥ ኃጢአቴንም በለበጥህበት ነበር።”