ዮሐንስ 9:35-41
ዮሐንስ 9:35-41 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌታችን ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ፤ አገኘውምና፥ “አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?” አለው። ያ ሰውም፥ “አቤቱ፥ አምንበት ዘንድ እርሱ ማነው?” ብሎ መለሰለት። ጌታችን ኢየሱስም፥ “የምታየው፥ ከአንተ ጋርም የሚነጋገረው እርሱ ነው” አለው። እርሱም፥ “አቤቱ፥ አምናለሁ” ብሎ ሰገደለት። ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ የማያዩት እንዲያዩ፥ የሚያዩትም እንዲታወሩ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጥቻለሁ” አለው። ከፈሪሳውያንም ከእርሱ ጋር የነበሩት ይህን ሲናገር ሰምተው፥ “እኛ ደግሞ ዕዉሮች ነን?” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ዕዉሮችስ ብትሆኑ ኀጢኣት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ትላላችሁ፤ አታዩምም፤ ስለዚህም ኀጢኣታችሁ ጸንቶ ይኖራል” አላቸው።
ዮሐንስ 9:35-41 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስም ሰውየውን እንዳባረሩት ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ፣ “በሰው ልጅ ታምናለህን?” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታዬ፤ አምንበት ዘንድ እርሱ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አይተኸዋል፤ አሁንም ከአንተ ጋራ የሚነጋገረው እርሱ ነው” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፤ አምናለሁ” አለ፤ ሰገደለትም። ኢየሱስም፣ “ዕውሮች እንዲያዩ፣ የሚያዩም እንዲታወሩ፣ ለፍርድ ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ” አለ። ከርሱ ጋራ ከነበሩት ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ይህን ሰምተው፣ “ምን ማለትህ ነው? ታዲያ እኛም ዕውሮች መሆናችን ነው?” አሉት። ኢየሱስም፣ “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኀጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ስለምትሉ፣ ኀጢአታችሁ እንዳለ ይኖራል” አላቸው።
ዮሐንስ 9:35-41 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ ያገኘውም፦ “አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?” አለው። እርሱም መልሶ፦ “ጌታ ሆይ፥ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው?” አለ። ኢየሱስም፦ “አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው” አለው። እርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ” አለ፤ ሰገደለትም። ኢየሱስም፦ “የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ” አለ። ከፈሪሳውያንም ከእርሱ ጋር የነበሩት ይህን ሰምተው፦ “እኛ ደግሞ ዕውሮች ነንን?” አሉት። ኢየሱስም አላቸው፦ “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ አሁን ግን፦ ‘እናያለን’ ትላላችሁ፤ ኃጢአታችሁ ይኖራል።
ዮሐንስ 9:35-41 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሰውየውን ከምኲራብ እንዳስወጡት ኢየሱስ ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ “በሰው ልጅ ታምናለህን?” አለው። እርሱም “ጌታ ሆይ! በእርሱ እንዳምን እርሱ ማን ነው?” አለ። ኢየሱስ “ከዚህ በፊት አይተኸዋል፤ አሁንም የሚያነጋግርህ እርሱ ነው” አለው። እርሱም “ጌታ ሆይ! አምናለሁ” ብሎ ሰገደለት። ኢየሱስም “የማያዩ እንዲያዩ፥ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጥቼአለሁ” አለ። በዚያን ጊዜ በኢየሱስ አጠገብ የነበሩ ፈሪሳውያን ይህን ሰምተው “ታዲያ፥ እኛም ዕውሮች መሆናችን ነውን?” አሉት። ኢየሱስም “ዕውሮች ብትሆኑማ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ስለምትሉ፥ ኃጢአተኞች ሆናችሁ ትቀራላችሁ” አላቸው።
ዮሐንስ 9:35-41 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ፤ ሲያገኘውም “አንተ በሰው ልጅ ታምናለህን?” አለው። እርሱም መልሶ “ጌታ ሆይ! በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው?” አለ። ኢየሱስም “አይተኸዋል፤ ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው፤” አለው። እርሱም “ጌታ ሆይ! አምናለሁ፤” አለ፤ ሰገደለትም። ኢየሱስም “የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ፤” አለ። ከእርሱ ጋር ከነበሩት ፈሪሳውያንም መሀል ይህንን ሰምተው “እኛ ደግሞ ዕውሮች ነንን?” አሉት። ኢየሱስም አላቸው “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ አሁን ግን ‘እናያለን’ ትላላችሁ፤ ኀጢአታችሁም በዚያው ይኖራል።