ዮሐንስ 7:1-53
ዮሐንስ 7:1-53 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህ በኋላም ጌታችን ኢየሱስ በገሊላ ይመላለስ ነበረ፤ ወደ ይሁዳ ምድርም ሊሄድ አልወደደም፤ አይሁድ ሊገድሉት ይሹ ነበርና። የአይሁድም የዳስ በዓላቸው ደርሶ ነበር። ወንድሞቹም ጌታችን ኢየሱስን እንዲህ አሉት- “ደቀ መዛሙርትህ የምትሠራውን ሥራህን እንዲያዩ ከዚህ ወጥተህ ወደ ይሁዳ ሀገር ሂድ። ሊገለጥ ወድዶ ሳለ በስውር አንዳች ነገር የሚያደርግ ማንም የለምና፤ አንተ ግን ይህን የምታደርግ ከሆነ ራስህን ለዓለም ግለጥ። ወንድሞቹ ገና አላመኑበትም ነበርና። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “ጊዜዬ ገና አልደረሰም፤ የእናንተ ጊዜ ግን ዘወትር የተዘጋጀ ነው። ዓለም እናንተን ሊጠላችሁ አይችልም፤ እኔን ግን ይጠላኛል፤ ሥራዉ ክፉ እንደ ሆነ እኔ እመሰክርበታለሁና። እናንተም ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔ አሁን ወደዚህ በዓል አልወጣም፤ ጊዜዬ ገና አልደረሰምና።” እርሱም እንዲህ ብሎአቸው በገሊላ ቀረ። ወንድሞቹ ለበዓል ከወጡ በኋላ፥ እርሱም ያንጊዜ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ። አይሁድም፥ “ያ ወዴት ነው?” እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ጀመር። ሕዝቡም ስለ እርሱ ብዙ አንጐራጐሩ፥ “ደግ ሰው ነው” ያሉ ነበሩ፤ ሌሎች ግን፥ “አይደለም፤ ሕዝቡን ያስታል እንጂ” አሉ። ነገር ግን፥ አይሁድን በመፍራት የእርሱን ነገር ገልጦ የተናገረ አልነበረም። በበዓሉ ቀኖች እኩሌታም ጌታችን ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ጀመረ። አይሁድም፥ “ይህ ሳይማር መጽሐፍን እንዴት ያውቃል?” እያሉ ትምህርቱን አደነቁ። ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ትምህርቴ የላከኝ ናት እንጂ የእኔ አይደለችም። ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድድ ግን ትምህርቴ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ሆነች፥ የምናገረውም ከራሴ እንዳይደለ እርሱ ያውቃል። ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይሻል፤ የላከውን ያከብር ዘንድ የሚፈልግ ግን እውነተኛ ነው፤ ሐሰትም የለበትም። ሙሴ ኦሪትን ሰጥቶአችሁ የለምን? ከእናንተ አንዱ ስንኳ ኦሪትን የሚያደርግ የለም፤ እንግዲህ ልትገድሉኝ ለምን ትሻላችሁ?” ሕዝቡም፥ “ጋኔን አለብህን? ማን ሊገድልህ ይሻል?” ብለው መለሱለት። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አላቸው፥ “አንድ ሥራ ሠራሁ፤ ሁላችሁም አደነቃችሁ። ስለዚህ ሙሴ ግዝረትን ሰጥቶአችሁ ነበር፤ ነገር ግን ከአባቶች ናት እንጂ ከሙሴ አይደለችም፤ በሰንበትም ሰውን ትገዝሩታላችሁ። የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት የሚገዘር ከሆነ እንግዲያ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ባድነው ለምን ትነቅፉኛላችሁ? የእውነት ፍርድ ፍረዱ እንጂ ለሰው ፊት በማድላት አትፍረዱ።” ከኢየሩሳሌም ሰዎችም እንዲህ የሚሉ ነበሩ፥ “ይህ አይሁድ ሊገድሉት የሚሹት አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በገሀድ ይናገራል፤ እነርሱ ግን ምንም የሚሉት የለም፤ ይህ በእውነት ክርስቶስ እንደ ሆነ ምናልባት አለቆች ዐውቀው ይሆን? ነገር ግን ይህን ከየት እንደ ሆነ እናውቃለን፤ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜስ ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም”። ጌታችን ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር ቃሉን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፥ “እኔን ታውቁኛላችሁ፤ ከወዴትም እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔ ራሴ የመጣሁ አይደለሁም፤ ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ አለ። እኔ ግን አውቀዋለሁ፤ እኔ ከእርሱ ነኝና፥ እርሱም ልኮኛልና። ስለዚህም ሊይዙት ወደው ነበር፤ ነገር ግን እጁን በእርሱ ላይ ያነሣ የለም፤ ጊዜዉ ገና አልደረሰም ነበርና። ከሕዝቡም ብዙዎች አመኑበትና፥ “በውኑ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ይህ ሰው ካደረገው ተአምራት የሚበልጥ ያደርጋልን?” አሉ። ፈሪሳውያንም ሕዝቡ በእርሱ ምክንያት እንደ አጕረመረሙ ሰሙ፤ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ይይዙት ዘንድ ሎሌዎቻቸውን ላኩ። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “ጥቂት ቀን አብሬአችሁ እኖራለሁ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ላከኝ እሄዳለሁ። ትሹኛላችሁ፤ አታገኙኝምም፤ እኔ ወደምሄድበትም እናንተ መምጣት አትችሉም።” አይሁድም እርስ በርሳቸው እንዲህ አሉ፥ “እኛ ልናገኘው የማንችል ይህ ወዴት ይሄዳል? ወይስ የግሪክን ሰዎች ለማስተማር በግሪክ ሀገር ወደ ተበተኑት ይሄዳልን? ‘ትሹኛላችሁ፤ አታገኙኝምም፤ እኔ ወደምሄድበት እናንተ መምጣት አትችሉም’ የሚለን ይህ ነገር ምንድን ነው?” በኋለኛዪቱ በታላቅዋ የበዓል ቀንም ጌታችን ኢየሱስ ቆመና ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፥ “የተጠማ ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔም የሚያምን መጽሐፍ እንደ ተናገረ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈስሳል።” ይህንም የሚያምኑበት ሰዎች ይቀበሉት ዘንድ ስለ አላቸው ስለ መንፈስ ቅዱስ ተናገረ፤ ጌታችን ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ቅዱስ ገና አልወረደም ነበርና። ከሕዝቡም ብዙ ሰዎች ይህን ነገር ሰምተው “በእውነት ይህ ነቢይ ነው” አሉ። “ክርስቶስ ነው” ያሉም አሉ፤ እኩሌቶቹም እንዲህ አሉ፥ “በውኑ ክርስቶስ ከገሊላ ይወጣልን? መጽሐፍ ‘ክርስቶስ ከዳዊት ዘርና ከዳዊት ከተማ ከቤተ ልሔም ይመጣል’ ይል የለምን?” ስለ እርሱም ሕዝቡ እርስ በርሳቸው ተለያዩ። ከእነርሱም ሊይዙት የወደዱ ነበሩ፤ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጁን ያነሣ የለም። ሎሌዎቹም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን ተመለሱ፤ እነርሱም፥ “ያላመጣችሁት ለምንድን ነው?” አሉአቸው። ሎሌዎቻቸውም መልሰው፥ “ያ ሰው እንደ ተናገረው ያለ ከቶ ሰው አልተናገረም” አሉአቸው። ፈሪሳውያንም መልሰው እንዲህ አሉአቸው፥ “እናንተም ደግሞ ተሳሳታችሁን? ከአለቆች ወይም ከፈሪሳውያን ያመነበት አለን? ኦሪትን ከማያውቁ ከእነዚህ ስሑታን ሕዝብ በቀር፤ እነርሱም የተረገሙ ናቸው።” ከእነርሱም አንዱ ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ የሄደው ኒቆዲሞስ እንዲህ አላቸው። “ሕጋችን አስቀድሞ ሳይሰማ፤ የሠራውንም ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” እነርሱም መልሰው፥ “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ከገሊላ ነቢይ እንደማይነሣ መርምርና እይ” አሉት። ሁሉም እያንዳንዳቸው ወደ ቤታቸው ሄዱ።
ዮሐንስ 7:1-53 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፣ በዚያ የነበሩት አይሁድ ሊገድሉት ስለ ፈለጉ፣ በይሁዳ አውራጃ መዘዋወር ትቶ በገሊላ ተዘዋወረ። የአይሁድ የዳስ በዓል በተቃረበ ጊዜ ግን፣ የኢየሱስ ወንድሞች እንዲህ አሉት፤ “ደቀ መዛሙርትህም ደግሞ የምታደርገውን ታምራት እንዲያዩ፣ ከዚህ ወደ ይሁዳ ሂድ፤ ራሱን ሊገልጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ ማንም የለምና። አንተም እነዚህን ነገሮች የምታደርግ ከሆነ፣ ራስህን ለዓለም ግለጥ።” የገዛ ወንድሞቹ እንኳ አላመኑበትም ነበር። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ለእኔ ትክክለኛው ጊዜ ገና አልደረሰም፤ ለእናንተ ግን ማንኛውም ጊዜ ምቹ ነው። ዓለም እናንተን ሊጠላ አይችልም፤ እኔ ግን፣ አድራጎቱ ክፉ መሆኑን ስለምመሰክርበት ይጠላኛል። እናንተ ወደ በዓሉ ሂዱ፤ ለእኔ ትክክለኛው ጊዜ ስላልደረሰ ወደ በዓሉ አልሄድም።” ይህን ብሏቸው በገሊላ ቈየ። ይሁን እንጂ፣ ወንድሞቹ ወደ በዓሉ ከሄዱ በኋላ፣ እርሱም በግልጽ ሳይሆን በስውር ወደ በዓሉ ሄደ። በበዓሉም ላይ አይሁድ፣ “ያ ሰው የት አለ?” እያሉ ይፈልጉት ነበር። ስለ እርሱ በሕዝቡ መካከል ብዙ ጕምጕምታ ነበር። አንዳንዶች፣ “ደግ ሰው ነው” አሉ። ሌሎች ግን፣ “የለም፤ ሕዝቡን የሚያስት ነው” አሉ። ይሁን እንጂ አይሁድን ከመፍራት የተነሣ ስለ እርሱ በግልጽ የተናገረ ማንም አልነበረም። በበዓሉም አጋማሽ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ጀመር። አይሁድም በመደነቅ፣ “ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ሊያውቅ ቻለ?” አሉ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “የማስተምረው ትምህርት ከራሴ ሳይሆን፣ ከላከኝ የመጣ ነው። ማንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ቢፈልግ፣ የእኔ ትምህርት ከእግዚአብሔር ወይም ከራሴ የመጣ መሆኑን ለይቶ ያውቃል፤ ከራሱ የሚናገር፣ ያን የሚያደርገው ለራሱ ክብርን ስለሚሻ ነው፤ ስለ ላከው ክብር የሚሠራ ግን እርሱ እውነተኛ ነው፤ ሐሰትም አይገኝበትም። ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ነገር ግን አንዳችሁም ሕጉን አልጠበቃችሁም። ለምን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ?” ሕዝቡም፣ “አንት ጋኔን ያደረብህ! ደግሞ አንተን ማን ሊገድል ይፈልጋል?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አንድ ሥራ ብሠራ፣ ሁላችሁም ተገረማችሁ። ግዝረት የመጣው ከአባቶች እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ ሆኖም ሙሴ ግዝረትን ስለ ሰጣችሁ፣ በሰንበት እንኳ ሕፃን ትገርዛላችሁ። የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሕፃን በሰንበት የሚገረዝ ከሆነ፣ የሰውን ሁለንተና በሰንበት ስለ ፈወስሁ ለምን በእኔ ላይ ትቈጣላችሁ? የሰውን ፊት በማየት መፍረድ ትታችሁ ቅን ፍርድ ፍረዱ።” በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ አሉ፤ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ሰው ይህ አይደለምን? ይኸው እርሱ በአደባባይ ይናገራል፤ አንድም ቃል አይናገሩትም፤ ክርስቶስ ነው ብለው ባለሥልጣኖቹም ተቀብለውት ይሆን? ይህ ሰው ግን ከየት እንደ ሆነ እኛ እናውቃለን፤ ክርስቶስ ሲመጣ እኮ ከየት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም።” ኢየሱስ በቤተ መቅደስ አደባባይ ሲያስተምር ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “አዎን፣ እኔን ታውቁኛላችሁ፤ ከየት እንደ ሆንሁም ታውቃላችሁ። እኔ እዚህ ያለሁት በገዛ ራሴ አይደለም፤ ነገር ግን የላከኝ እርሱ እውነተኛ ነው። እናንተ አታውቁትም፤ እኔ ግን ከርሱ ዘንድ ስለ ሆንሁ፣ እርሱም ስለ ላከኝ ዐውቀዋለሁ።” ስለዚህ ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አላሳረፈበትም፤ ሆኖም ከሕዝቡ ብዙዎች በርሱ አምነው፣ “ታዲያ፣ ክርስቶስ ሲመጣ ይህ ሰው ከሚሠራቸው ታምራዊ ምልክቶች የበለጠ ያደርጋል?” አሉ። ፈሪሳውያን፣ ሕዝቡ ስለ እርሱ በጕምጕምታ የሚነጋገረውን ነገር ሰሙ፤ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም እንዲይዙት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችን ላኳቸው። ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ከእናንተ ጋራ የምቈየው ጥቂት ጊዜ ነው፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ እኔ ወዳለሁበትም ልትመጡ አትችሉም።” አይሁድም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “ይህ ሰው፣ ልናገኘው የማንችለው ወዴት ለመሄድ ቢያስብ ነው? በግሪኮች መካከል ተበታትነው ወደሚኖሩት ወገኖቻችን ሄዶ ግሪኮችን ሊያስተምር ፈልጎ ይሆን? ‘ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ እኔ ወዳለሁበትም ልትመጡ አትችሉም’ ሲል ምን ማለቱ ይሆን?” የበዓሉ መጨረሻ በሆነው በታላቁ ቀን፣ ኢየሱስ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፤ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፤ በእኔ የሚያምን፣ መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውሃ ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል።” ይህን ያለው በርሱ የሚያምኑ ስለሚቀበሉት መንፈስ ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ አልተሰጠም ነበር። ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ቃሉን ሰምተው፣ “ይህ ሰው በርግጥ ነቢዩ ነው” አሉ። ሌሎችም፣ “እርሱ ክርስቶስ ነው” አሉ። ሌሎች ደግሞ እንዲህ አሉ፤ “ክርስቶስ ከገሊላ እንዴት ሊመጣ ይችላል? መጽሐፍ፣ ክርስቶስ ከዳዊት ዘር፣ ዳዊትም ከኖረበት ከቤተ ልሔም እንደሚመጣ ይናገር የለምን?” ስለዚህም በኢየሱስ ምክንያት በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤ አንዳንዶቹም ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ማንም እጁን አላሳረፈበትም። በመጨረሻም የቤተ መቅደስ ጠባቂዎቹ፣ ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን ተመልሰው ሄዱ፤ እነርሱም ጠባቂዎቹን፣ “ለምን አላመጣችሁትም?” አሏቸው። ጠባቂዎቹም፣ “እንደዚህ ሰው፣ ከቶ ማንም ተናግሮ አያውቅም” ሲሉ መለሱ። ፈሪሳውያንም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “እናንተም ተታልላችኋል ማለት ነው? ለመሆኑ ከባለሥልጣኖችና ከፈሪሳውያን በርሱ ያመነ አለ? ሕጉን የማያውቅ ይህ ሕዝብ ግን የተረገመ ነው።” ከዚህ ቀደም ወደ ኢየሱስ ሄዶ የነበረውና ከእነርሱ አንዱ የሆነው ኒቆዲሞስ እንዲህ አላቸው፤ “ሕጋችን፣ አስቀድሞ አንድን ሰው ሳይሰማና ምን እንዳደረገ ሳይረዳ ይፈርድበታልን?” እነርሱም፣ “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንደማይነሣ መርምር፤ ትደርስበታለህ” ብለው መለሱለት። [ከዚህ በኋላ ሁሉም ወደ የቤታቸው ሄዱ።
ዮሐንስ 7:1-53 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበርና በገሊላ ይመላለስ ነበር። የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር። እንግዲህ ወንድሞቹ፦ “ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፤ ራሱ ሊገልጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለምና። እነዚህን ብታደርግ ራስህን ለዓለም ግለጥ” አሉት። ወንድሞቹ ስንኳ አላመኑበትም ነበርና። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ጊዜዬ ገና አልደረሰም፥ ጊዜያችሁ ግን ዘወትር የተመቸ ነው። ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል። እናንተ ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል ገና አልወጣም።” ይህንም አላቸውና በገሊላ ቀረ። ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ በዚያን ጊዜ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ። አይሁድም፦ “እርሱ ወዴት ነው?” እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ነበር። በሕዝቡም መካከል ስለ እርሱ ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዱም፦ “ደግ ሰው ነው፤” ሌሎች ግን፦ “አይደለም፥ ሕዝቡን ግን ያስታል” ይሉ ነበር። ዳሩ ግን አይሁድን ስለ ፈሩ ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አይናገርም ነበር። አሁንም በበዓሉ እኩሌታ ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ነበር። አይሁድም፦ “ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል?” ብለው ይደነቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፦ “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤ ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም። ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ከእናንተ ግን ሕግን የሚያደርግ አንድ ስንኳ የለም። ልትገድሉኝ ስለ ምን ትፈልጋላችሁ?” ሕዝቡ መለሱና፦ “ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል?” አሉት። ኢየሱስ መለሰ አላቸውም፦ “አንድ ሥራ አደረግሁ ሁላችሁም ታደንቃላችሁ። ስለዚህ ሙሴ መገረዝን ሰጣችሁ፤ ከአባቶችም ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ በሰንበትም ሰውን ትገርዛላችሁ። የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት መገረዝን የሚቀበል ከሆነስ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ጤናማ ስላደረግሁ ትቈጡኛላችሁን? ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ።” እንግዲህ ከኢየሩሳሌም ሰዎች እንዳንዶቹ እንዲህ አሉ፦ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን? እነሆም፥ በግልጥ ይናገራል አንዳችም አይሉትም። አለቆቹ ይህ ሰው በእውነት ክርስቶስ እንደ ሆነ በእውነት አወቁን? ነገር ግን ይህን ከወዴት እንደ ሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም።” እንግዲህ ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር፦ “እኔንም ታውቁኛላችሁ ከወዴትም እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ እርሱም ልኮኛልና አውቀዋለሁ” ብሎ ጮኸ። ስለዚህ ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አልጫነበትም። ከሕዝቡ ግን ብዙዎች አመኑበትና፦ “ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ይህ ካደረጋቸው ምልክቶች ይልቅ ያደርጋልን?” አሉ። ፈሪሳውያን ሕዝቡ ሰለ እርሱ እንደዚህ ሲያንጐራጕሩ ሰሙ፤ የካህናት አለቆችም ፈሪሳውያም ሊይዙት ሎሌዎችን ላኩ። ኢየሱስም፦ “ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ ወደ ላከኝም እሄዳለሁ። ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም” አለ። እንግዲህ አይሁድ፦ “እኛ እንዳናገኘው ይህ ወዴት ይሄድ ዘንድ አለው? በግሪክ ሰዎች መካከል ተበትነው ወደሚኖሩት ሊሂድና የግሪክን ሰዎች ሊያስተምር አለውን” እርሱ፦ “ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም የሚለው ይህ ቃል ምንድር ነው?” ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ፦ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይመጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል” ብሎ ጮኸ። ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና። ስለዚህ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎች ይህን ቃል ሲሰሙ፦ “ይህ በእውነት ነቢዩ ነው” አሉ፤ ሌሎች፦ “ይህ ክርስቶስ ነው” አሉ፤ ሌሎች ግን፦ “ክርስቶስ በእውኑ ከገሊላ ይመጣልን? ክርስቶስ ከዳዊት ዘር ዳዊትም ከነበረባት መንደር ከቤተ ልሔም እንዲመጣ መጽሐፍ አላለምን?” አሉ። እንግዲህ ከእርሱ የተነሣ በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ሊይዙት ወደዱ ነገር ግን እጁን ማንም አልጫነበትም። ሌሎቹም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን መጡ፤ እነዚያም፦ “ያላመጣችሁት ስለ ምን ነው?” አሉአቸው። ሎሌዎቹ፦ “እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም” ብለው መለሱ። እንግዲህ ፈሪሳውያን፦ “እናንተ ደግሞ ሳታችሁን? ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን? ነገር ግን ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው” ብለው መለሱላቸው። ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀደሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ፦ “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ማንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” አላቸው። እነርሱም መለሱና፦ “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ” አሉት። እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።
ዮሐንስ 7:1-53 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ይዘዋወር ነበር፤ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበረ ግን በይሁዳ ሊዘዋወር አልፈለገም፤ በዚያን ጊዜ የአይሁድ የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር። ስለዚህ ወንድሞቹ ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “ደቀ መዛሙርትህ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሥተህ ወደ ይሁዳ ምድር ሂድ፤ በግልጥ ለመታወቅ የሚፈልግ ሰው ሥራውን በስውር አያደርግም፤ አንተም እነዚህን ነገሮች ሁሉ ስታደርግ ራስህን ለዓለም ልትገልጥ ያስፈልጋል።” ይህንንም ያሉበት ምክንያት ወንድሞቹ እንኳ በእርሱ ስላላመኑ ነው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የእኔ ጊዜ ገና አልደረሰም፤ የእናንተ ጊዜ ግን ዘወትር የተመቸ ነው። ዓለም እናንተን ሊጠላ አይችልም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን ስለምመሰክርበት እኔን ይጠላኛል። እናንተ ወደ በዓሉ ሂዱ፤ እኔ ግን ጊዜዬ ገና ስላልደረሰ ወደዚህ በዓል አልሄድም።” ይህንንም ብሎ እርሱ በገሊላ ቀረ። ነገር ግን ወንድሞቹ ወደ በዓሉ ከሄዱ በኋላ እርሱ በይፋ ሳይሆን በስውር ወደ በዓሉ ሄደ። በበዓሉም ላይ “እርሱ የት ነው?” እያሉ አይሁድ ይፈልጉት ነበር። ሕዝቡም ስለ እርሱ በሹክሹክታ ይነጋገሩ ነበር፤ አንዳንዶቹ “እርሱ ደግ ሰው ነው” ሲሉ፥ ሌሎች ደግሞ “አይደለም፤ እርሱ ሕዝቡን ያስታል” ይሉ ነበር። ይሁን እንጂ የአይሁድን ባለ ሥልጣኖች በመፍራት ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አልተናገረም። በበዓሉም አጋማሽ ላይ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዶ ያስተምር ጀመር። አይሁድም፥ “ይህ ሰው ሳይማር ይህን ሁሉ እንዴት ሊያውቅ ቻለ?” እያሉ ይደነቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የእኔ ትምህርት ከላከኝ ከአብ የተገኘ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም። የላከኝን ፈቃድ ማድረግ የሚፈልግ ቢኖር ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር የተገኘ ወይም እኔ ከራሴ የተናገርኩት መሆኑን ያውቃል። ከገዛ ራሱ የሚናገር የገዛ ራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላኪውን ክብር የሚፈልግ ግን እውነተኛ ነው፤ ሐሰትም የለበትም። ሙሴ ሕግን ሰጥቶአችሁ የለምን? ነገር ግን ከእናንተ ሕግን የሚፈጽም ማንም የለም። እናንተ ለምን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ?” ሕዝቡም “አንተ ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ አንድ ሥራ ሠራሁ፤ እናንተም ሁላችሁ በዚህ ሥራ ትደነቃላችሁ። ሙሴ የግዝረትን ሥርዓት ሰጣችሁ፤ ይህም ሥርዓት የተገኘው፤ ከአባቶች ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ እናንተም እኮ በሰንበት ሰውን ትገርዛላችሁ። እንግዲህ በሙሴ አማካይነት የተሰጠው ሕግ እንዳይሻር በሰንበት ቀን ሰው የሚገረዝ ከሆነ ታዲያ፥ እኔ በሰንበት ቀን የሰውን ሁለንተና በመፈወሴ ስለምን ትቈጣላችሁ? ትክክለኛ ፍርድ ፍረዱ እንጂ የሰውን ፊት አይታችሁ በማዳላት አትፍረዱ።” ከኢየሩሳሌም ሰዎች አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ፦ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ሰው ይህ አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በግልጥ ይናገራል፤ እነርሱም ምንም አላሉትም፤ ይህ ሰው መሲሕ መሆኑን ባለሥልጣኖች በእውነት ዐውቀው ይሆን? ሆኖም ይህ ሰው ከወዴት እንደ ሆነ እኛ እናውቃለን፤ መሲሕ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ የሚያውቅ ማንም የለም።” ስለዚህ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሲያስተምር ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “እኔን ታውቁኛላችሁ፤ ከወዴትም እንደ መጣሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እኔ በራሴ ሥልጣን አልመጣሁም፤ የላከኝ እርሱ እውነተኛ ነው፤ እናንተ ግን አታውቁትም። እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ስለ መጣሁና እርሱ ስለ ላከኝ ዐውቀዋለሁ።” በዚያን ጊዜ ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም። ሆኖም ከሕዝቡ ብዙዎቹ በእርሱ አመኑ፤ እንዲህም አሉ፦ “መሲሕ በሚመጣበትስ ጊዜ ይህ ሰው ካደረጋቸው ተአምራት የበለጠ ያደርጋልን?” ሰዎቹ ስለ ኢየሱስ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ፈሪሳውያን ሰሙ፤ ስለዚህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለማስያዝ የቤተ መቅደስ ዘብ ጠባቂዎችን ላኩ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ከእናንተ ጋር ጥቂት ጊዜ እቈያለሁ፤ ከዚያ በኋላ ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ እኔ ወዳለሁበት፥ እናንተ መምጣት አትችሉም።” ስለዚህ የአይሁድ ባለ ሥልጣኖች እንዲህ ተባባሉ፦ “እኛ እንዳናገኘው ይህ ሰው ወዴት ሊሄድ ነው? ምናልባት በግሪኮች መካከል ወደ ተበተኑት አይሁድ ዘንድ ሄዶ አሕዛብን ያስተምር ይሆን? ‘ትፈልጉኛላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙኝም፤ እኔ ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም’ ሲል ምን ማለቱ ነው?” የበዓሉ መጨረሻ በሆነው በታላቁ ቀን ኢየሱስ ቆመና ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “ውሃ የጠማው ቢኖር ወደ እኔ መጥቶ ይጠጣ፤ በእኔ የሚያምን ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለው፥ የሕይወት ውሃ ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል።” ይህንንም የተናገረው በእርሱ የሚያምኑ ስለሚቀበሉት ስለ መንፈስ ቅዱስ ነበር፤ ኢየሱስ ገና ወደ ክብር ስላልወጣ መንፈስ ቅዱስ ገና አልተሰጠም ነበር። ስለዚህ ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ይህን ቃል በሰሙ ጊዜ፦ “ይመጣል የተባለው ነቢይ በእርግጥ ይህ ነው” አሉ። ሌሎች “ይህ መሲሕ ነው” አሉ። ሌሎቹ ግን “መሲሕ የሚመጣው ከገሊላ ነውን? መሲሕ ከዳዊት ዘር እንደሚወለድና ከዳዊት ከተማ ከቤተልሔም እንደሚመጣ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፎ የለምን?” አሉ። ስለዚህ በእርሱ ምክንያት በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ። አንዳንዶቹ ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ማንም አልያዘውም። ከዚህ በኋላ ዘብ ጠባቂዎቹ ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን ተመልሰው ሄዱ፤ እነርሱም “ስለምን አላመጣችሁትም?” አሉአቸው። ወታደሮቹም “ይህ ሰው እንደሚናገረው ዐይነት ማንም ተናግሮ አያውቅም” ሲሉ መለሱ። ፈሪሳውያን ግን እንዲህ አሉ፦ “እናንተም ደግሞ ተሳሳታችሁን? ለመሆኑ ከባለ ሥልጣኖች ወይም ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመኑ አሉን? ይህ የሙሴን ሕግ የማያውቅ ሕዝብ በእርግጥ የተረገመ ነው።” ከዚህ በፊት ወደ ኢየሱስ ሄዶ የነበረውና ከፈሪሳውያን አንዱ የሆነው ኒቆዲሞስ፥ “በሕጋችን መሠረት አንድ ሰው የክስ መልስ አስቀድሞ ሳይሰማለትና ምን እንዳደረገ ሳይታወቅ ይፈረድበታልን?” አላቸው። እነርሱም “አንተም ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንደማይነሣ መርምረህ ተረዳ” አሉት። እያንዳንዱም ወደየቤቱ ሄደ።
ዮሐንስ 7:1-53 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ይመላለስ ነበር። አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበር። የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር። ወንድሞቹም “ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፤ በይፋ መታወቅ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለምና። እነዚህን ነገሮች የምታደርግ ከሆነ እራስህን ለዓለም ግለጥ፤” አሉት። ወንድሞቹም እንኳን አላመኑበትም ነበርና። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “ጊዜዬ ገና አልደረሰም፤ ጊዜያችሁ ግን ዘወትር የተመቸ ነው። ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ይጠላኛል፤ ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና ነው። እናንተ ወደ በዓሉ ውጡ፤ እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል አልወጣም።” ይህንም አላቸውና በገሊላ ቀረ። ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ፥ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ። አይሁድም “እርሱ ወዴት ነው?” እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ነበር። በሕዝቡም መካከል በእርሱ ምክንያት ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዶቹ “ደግ ሰው ነው፤” ሌሎች ደግሞ “አይደለም፤ ሕዝቡን ያስታል እንጂ፤” ይሉ ነበር። ዳሩ ግን አይሁድን ስለ ፈሩ ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አይናገርም ነበር። በበዓሉ እኩሌታ ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ነበር። አይሁድም “ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል?” ብለው ይደነቁ ነበር። ስለዚህም ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ትምህርቴስ የላከኝ ነው እንጂ የእኔ አይደለም፤ ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር እንደሆነ ወይንም እኔ ከራሴ የምናገር እንደሆነ ያውቃል። ከገዛ እራሱ የሚናገር የገዛ እራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው፤ በእርሱም ዐመፃ የለበትም። ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ከእናንተ ግን ሕግን የሚፈጽም አንድ እንኳን የለም። ልትገድሉኝ ስለምን ትፈልጋላችሁ?” ሕዝቡ መለሱና “ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል?” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “አንድ ሥራ ፈጸምኩ፥ ሁላችሁም ትደነቃላችሁ። ሙሴ መገረዝን ሰጣችሁ፤ ከአባቶችም ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ በሰንበትም ሰውን ትገርዛላችሁ። የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት መገረዝን የሚቀበል ከሆነስ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ጤናማ ስላደረግሁ ትቈጡኛላችሁን? ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ።” ከኢየሩሳሌም ሰዎችም እንዳንዶቹ እንዲህ አሉ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን? እነሆ፥ በግልጥ ይናገራል፤ ነገር ግን ምንም አይሉትም። አለቆቹ ይህ ሰው ክርስቶስ እንደሆነ በእውነት አወቁን? ሆኖም ይህ ሰው ከወዴት እንደሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደሆነ ማንም አያውቅም።” እንግዲህ ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር “እኔንም ታውቁኛላችሁ፤ ከወዴትም እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ፤ እርሱም ልኮኛልና አውቀዋለሁ፤” ብሎ ጮኸ። ስለዚህ ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አልጫነበትም። ከሕዝቡ ግን ብዙዎች አመኑበትና፥ “ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ይህ ሰው ካደረጋቸው ምልክቶች የሚበልጥ ያደርጋልን?” አሉ። ፈሪሳውያን ሕዝቡ ስለ እርሱ እንደዚህ ሲያንጐራጉሩ ሰሙ፤ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ሊይዙት ዘቦችን ላኩ። ኢየሱስም “ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ። ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም፤” አለ። አይሁድም እንዲህ ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ “እኛ እንዳናገኘው ይህ ሰው ወዴት ሊሄድ ነው? በግሪክ ሰዎች መካከል ተበትነው ወደሚኖሩት ሄዶ የግሪክን ሰዎች ሊያስተምር ነውን? ‘ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም፤’ የሚለውስ ይህ አባባል ምን ማለት ነው?” ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን፥ መጽሐፍ እንዳለው፥ የሕይወት ውሃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል።” ይህንንም በእርሱ የሚያምኑ ስለሚቀበሉት መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና። ስለዚህ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎች ይህን ቃል ሲሰሙ “ይህ በእውነት ነቢዩ ነው፤” አሉ፤ ሌሎች “ይህ ክርስቶስ ነው፤” አሉ፤ ሌሎች ግን “ክርስቶስ በእውኑ ከገሊላ ይመጣልን? አሉ ክርስቶስ ከዳዊት ዘር፥ ዳዊትም ከነበረባት መንደር ከቤተልሔም እንደሚመጣ መጽሐፍ አልተናገረምን?” ስለዚህም ከእርሱ የተነሣ በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን እጁን ማንም አልጫነበትም። ዘቦቹም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን መጡ፤ እነርሱም “ለምንድነው ያላመጣችሁት?” አሉአቸው። ዘቦቹም “እንደዚህ ሰው ማንም ከቶ አልተናገረም፤” ብለው መለሱ። ፈሪሳውያንም እንዲህ ብለው መለሱላቸው፤ “እናንተ ደግሞ ሳታችሁን? ከአለቆች ወይም ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን? ነገር ግን ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው፤” ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስ እንዲህ አላቸው “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ፥ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” እነርሱም መለሱና “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንደማይነሣ መርምርና እይ፤” አሉት። እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።