ዮሐንስ 5:25-47

ዮሐንስ 5:25-47 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“እው​ነት እው​ነት እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ ሙታን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ልጅ ቃል የሚ​ሰ​ሙ​በት ሰዓት ይመ​ጣል፤ እር​ሱም አሁን ነው፤ የሚ​ሰ​ሙ​ትም ይድ​ናሉ። ለአብ በራሱ ሕይ​ወት እን​ዳ​ለው፥ እን​ዲ​ሁም ደግሞ ለወ​ልድ በራሱ ሕይ​ወት እን​ዲ​ኖ​ረው ሰጠው። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅ የሰው ልጅ ነውና ይፈ​ርድ ዘንድ ሥል​ጣ​ንን ሰጠው። “በመ​ቃ​ብር ያሉ ሁሉ ቃሉን የሚ​ሰ​ሙ​ባት ጊዜ ትመ​ጣ​ለ​ችና ስለ​ዚህ አታ​ድ​ንቁ። መል​ካም የሠሩ ለሕ​ይ​ወት ትን​ሣኤ፥ ክፉ የሠ​ሩም ለፍ​ርድ ትን​ሣኤ ይነ​ሣሉ። እኔ ከራሴ አን​ዳች አደ​ርግ ዘንድ አል​ች​ልም፤ እንደ ሰማሁ እፈ​ር​ዳ​ለሁ እንጂ፤ ፍር​ዴም እው​ነት ነው፤ የላ​ከ​ኝን ፈቃድ እንጂ የእ​ኔን ፈቃድ አል​ሻ​ምና። “እኔ ለራሴ ብመ​ሰ​ክር ምስ​ክ​ር​ነቴ እው​ነት አይ​ደ​ለም። ነገር ግን ለእኔ የሚ​መ​ሰ​ክር ሌላ ነው፤ ስለ እኔ የመ​ሰ​ከ​ረው ምስ​ክ​ር​ነ​ቱም እው​ነት እን​ደ​ሆነ አው​ቃ​ለሁ። እና​ንተ ወደ ዮሐ​ንስ ልካ​ችሁ አል​ነ​በ​ረ​ምን? እር​ሱም ምስ​ክ​ር​ነ​ቱን በእ​ው​ነት ነገ​ራ​ችሁ። እኔ ግን የሰ​ውን ምስ​ክ​ር​ነት የምሻ አይ​ደ​ለ​ሁም፤ ነገር ግን እና​ንተ ትድኑ ዘንድ ይህን እላ​ለሁ። እርሱ የሚ​ነ​ድና የሚ​ያ​በራ መብ​ራት ነበረ፤ እና​ን​ተም አን​ዲት ሰዓት በብ​ር​ሃኑ ደስ ሊላ​ችሁ ወደ​ዳ​ችሁ። እኔ ግን ከዮ​ሐ​ንስ ምስ​ክ​ር​ነት የሚ​በ​ልጥ ምስ​ክር አለኝ፤ ልሠ​ራ​ውና ልፈ​ጽ​መው አባቴ የሰ​ጠኝ ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ያ የም​ሠ​ራው ሥራ ምስ​ክሬ ነውና። የላ​ከኝ አብም ስለ እኔ መስ​ክ​ሮ​አል፤ ከሆ​ነም ጀምሮ ቃሉን አል​ሰ​ማ​ች​ሁም፤ መል​ኩ​ንም አላ​ያ​ች​ሁም። ቃሉም የላ​ች​ሁም፤ በእ​ና​ንተ ዘን​ድም አይ​ኖ​ርም፤ እርሱ የላ​ከ​ውን አላ​መ​ና​ች​ሁ​ምና። መጻ​ሕ​ፍ​ትን መር​ምሩ፤ በእ​ነ​ርሱ የዘ​ለ​ዓ​ለም ሕይ​ወ​ትን የም​ታ​ገኙ ይመ​ስ​ላ​ች​ኋ​ልና፤ እነ​ር​ሱም የእኔ ምስ​ክ​ሮች ናቸው። ሕይ​ወ​ትን ታገኙ ዘንድ ወደ እኔ ልት​መጡ አት​ወ​ዱም። እኔ ከሰው ክብ​ርን ልቀ​በል አል​ሻም። ነገር ግን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፍቅር በእ​ና​ንተ እን​ደ​ሌ​ለ​ባ​ችሁ ዐወ​ቅሁ። እኔ በአ​ባቴ ስም መጣሁ፥ አል​ተ​ቀ​በ​ላ​ች​ሁ​ኝ​ምም፤ ሌላው ግን በራሱ ስም ቢመጣ እር​ሱን ትቀ​በ​ሉ​ታ​ላ​ችሁ። ከባ​ል​ን​ጀ​ራ​ችሁ ክብ​ርን የም​ት​መ​ርጡ፥ ከአ​ንድ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ክብ​ርን የማ​ትሹ እና​ንተ እን​ዴት ልታ​ምኑ ትች​ላ​ላ​ችሁ? እኔ በአብ ዘንድ የም​ከ​ስ​ሳ​ችሁ አይ​ም​ሰ​ላ​ችሁ፤ የሚ​ከ​ስ​ሳ​ች​ሁስ አለ፤ እር​ሱም እና​ንተ ተስፋ የም​ታ​ደ​ር​ጉት ሙሴ ነው። ሙሴ​ንስ አም​ና​ች​ሁት ቢሆን እኔ​ንም ባመ​ና​ች​ሁኝ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎ​አ​ልና። ሙሴ የጻ​ፈ​ውን ካላ​መ​ና​ችሁ ግን የእ​ኔን ቃል እን​ዴት ታም​ና​ላ​ችሁ?”

ዮሐንስ 5:25-47 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቷል፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው ሁሉ፣ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና፤ ወልድ የሰው ልጅ ስለ ሆነም እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል። “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ። እኔ ብቻዬን ከራሴ ምንም ማድረግ አልችልም፤ የምፈርደው የምሰማውን ብቻ ነው፤ የላከኝን እንጂ የራሴን ፈቃድ ስለማልሻም ፍርዴ ትክክል ነው። “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር፣ ምስክርነቴ ተቀባይነት አይኖረውም። ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ አለ፤ እርሱ ስለ እኔ የሚሰጠውም ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ ዐውቃለሁ። “ወደ ዮሐንስ ልካችሁ ነበር፤ እርሱም ስለ እውነት መስክሯል፤ እኔ የሰው ምስክርነት የምቀበል አይደለሁም፤ ይህን የምናገረው ግን እናንተ እንድትድኑ ነው። ዮሐንስ እየነደደ ብርሃን የሚሰጥ መብራት ነበረ፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በብርሃኑ ደስ ልትሠኙ ወደዳችሁ። “እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የላቀ ምስክር አለኝ፤ እንድፈጽመው አብ የሰጠኝ፣ እኔም የምሠራው ሥራ አብ እንደ ላከኝ ይመሰክራል። የላከኝ አብ ራሱ ስለ እኔ መስክሯል፤ እናንተም ከቶ ድምፁን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፤ የላከውንም ስላላመናችሁ ቃሉ በእናንተ አይኖርም። በእነርሱ የዘላለም ሕይወትን የምታገኙ እየመሰላችሁ፣ መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ እነዚሁ መጻሕፍት ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ እናንተ ግን፣ ሕይወት እንዲኖራችሁ ወደ እኔ መምጣት አትፈልጉም። “እኔ ከሰው ክብር አልቀበልም፤ ነገር ግን እናንተን ዐውቃችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርም ፍቅር በልባችሁ እንደሌለ ዐውቃለሁ። እኔ በአባቴ ስም መጥቼ አልተቀበላችሁኝም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ ግን ትቀበሉታላችሁ። እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትሰጣጡ፣ ነገር ግን ከአንዱ አምላክ የሚመጣውን ክብር የማትፈልጉ ከሆነ፣ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? “ከሳሻችሁ ተስፋ የጣላችሁበት ሙሴ እንጂ፣ እኔ በአብ ፊት የምከስሳችሁ አይምሰላችሁ፤ ሙሴን ብታምኑ ኖሮ፣ እኔን ባመናችሁ ነበር፤ ምክንያቱም እርሱ የጻፈው ስለ እኔ ነው። እርሱ የጻፈውን ካላመናችሁ፣ እኔ የምናገረውን እንዴት ታምናላችሁ?”

ዮሐንስ 5:25-47 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔር ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲሆረው ሰጥቶታልና። የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ። እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና። እኔ ስለ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክሬ እውነት አይደለም፤ ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፥ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክር እውነት እንደ ሆነ አውቃለሁ። እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችኋል እርሱም ለእውነት መስክሮአል። እኔ ግን ከሰው ምስክር አልቀበልም፥ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ። እርሱ የሚያድንና የሚያበራ መብራት ነበረ፥ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ። እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና። የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል። ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፥ መልኩንም አላያችሁም፤ እርሱም የላከውን እናንተ አታምኑምና በእናንተ ዘንድ የሚኖር ቃሉ የላችሁም። እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በራሳችሁ እንደ ሌላችሁ አውቃችኋለሁ። እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ። እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ አለ፤ እርሱም ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው። ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?

ዮሐንስ 5:25-47 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ የሞቱ ሰዎች የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ ጊዜውም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም ሁሉ በሕይወት ይኖራሉ። አብ ራሱ የሕይወት ምንጭ እንዲሆን አድርጎታል። የሰው ልጅ በመሆኑም ፍርድ እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል። በዚህ ነገር አትደነቁ፤ በመቃብር ውስጥ ያሉት ሁሉ የእርሱን ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል። መልካም የሠሩ ከሞት ተነሥተው በሕይወት ይኖራሉ፤ ክፉ የሠሩ ግን ከሞት ተነሥተው ይፈረድባቸዋል። “እኔ በራሴ ሥልጣን ምንም ማድረግ አልችልም፤ ነገር ግን ከአብ የሰማሁትን እፈርዳለሁ፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ የራሴን ፈቃድ ስለማላደርግ ፍርዴ ትክክል ነው። “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክርነቴ እውነት አይደለም። ነገር ግን ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ አለ፤ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክርነት እውነት መሆኑን ዐውቃለሁ። እናንተ ወደ ዮሐንስ መልእክተኞች ልካችሁ ነበር፤ እርሱም ስለ እውነት መስክሮአል። ይህንንም ማለቴ እንድትድኑ ነው እንጂ እኔ የሰው ምስክርነት ስላስፈለገኝ አይደለም። ዮሐንስ እንደሚነድና እንደሚበራ መብራት ነበረ፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በእርሱ ብርሃን ለመደሰት ፈለጋችሁ። እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የበለጠ ምስክር አለኝ፤ ምስክሬም አባቴ እንድሠራው የሰጠኝ ሥራ ነው፤ ይህም የምሠራው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራል። የላከኝም አብ፥ ራሱ ስለ እኔ መስክሮአል፤ እናንተ ግን ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፤ መልኩንም ከቶ አላያችሁም። እርሱ የላከውን ስለማታምኑ የእርሱ ቃል በእናንተ ዘንድ አይኖርም። እናንተ በቅዱሳት መጻሕፍት የዘለዓለምን ሕይወት የምታገኙ ስለሚመስላችሁ እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው። ይሁን እንጂ እናንተ ሕይወትን ለማግኘት ወደ እኔ መምጣት አትፈልጉም። “እኔ ክብርን ከሰው አልፈልግም። እናንተ ከልባችሁ እግዚአብሔርን የማታፈቅሩ መሆናችሁን ዐውቃለሁ። እኔ በአባቴ ስም መጣሁ፤ እናንተ ግን አልተቀበላችሁኝም፤ ሌላ በራሱ ስም ቢመጣ ግን ትቀበሉታላችሁ። እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብርን የምትፈልጉ ከአንዱ ከእግዚአብሔር የሚገኘውን ክብር ግን የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? እኔ በአባቴ ፊት የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ፥ ተስፋ የምታደርጉበት ሙሴ ነው። ሙሴን ብታምኑ ኖሮ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና እኔንም ባመናችሁ ነበር። እርሱ የጻፈውን ካላመናችሁ ግን የእኔን ቃል እንዴት ታምናላችሁ?”

ዮሐንስ 5:25-47 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በእራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በእራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና። የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። በዚህ አታድንቁ፤ በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና። “እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ፤ ፍርዴም ቅን ነው፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና። እኔ ለእራሴ ብመሰክር ምስክርነቴ እውነት አይደለም፤ ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፤ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክር እውነት እንደሆነ አውቃለሁ። እናንተ ወደ ዮሐንስ መልክተኞችን ልካችኋል፥ እርሱም ለእውነት መስክሮአል። እኔ ግን የሰው ምስክር የሚያስፈልገኝ አይደለሁም፤ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ። እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፤ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ። እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ እንድፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና። የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል። ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፤ እርሱ የላከውንም እናንተ አታምኑምና፤ በእናንተ ዘንድ የሚኖር ቃሉ የላችሁም። እናንተ መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ በእነርሱም የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችሁ ታስባላችሁና፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። የሰው ክብር አያስፈልገኝም፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በውስጣችሁ እንደሌላችሁ ዐወቅሁ። እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ፤ አትቀበሉኝምም፤ ሌላው በእራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ። እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ፥ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ብቻ የሚገኘውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ አለ፤ እርሱም ተስፋ የምታደርጉበት ሙሴ ነው። ሙሴንስ ብታምኑት እኔንም ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። የእርሱን ጽሑፎች ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?”