ዮሐንስ 5:1-47
ዮሐንስ 5:1-47 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች፤ ስምዋንም በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ይሉአታል፤ አምስት እርከኖችም ነበሩአት። በዚያም ዕውሮችና አንካሶች፥ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃዉን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር። የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያዉ ወርዶ ውኃዉን በሚያናውጠው ጊዜ፥ ከውኃዉ መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበርና። በዚያም ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበር። ጌታችን ኢየሱስም ያን ሰው በአልጋዉ ተኝቶ ባየ ጊዜ በደዌ ብዙ ዘመን እንደ ቈየ ዐውቆ፥ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው። ድውዩም መልሶ፥ “አዎን ጌታዬ ሆይ፥ ነገር ግን ውኃዉ በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያዉ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው። ወዲያውኑም ያ ሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ያች ቀንም ሰንበት ነበረች። አይሁድም የዳነውን ሰው፥ “ዛሬ ሰንበት ነው፤ አልጋህን ልትሸከም አይገባህም” አሉት። እርሱም መልሶ፥ “ያዳነኝ እርሱ፦ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” አላቸው። አይሁድም፥ “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬው ማነው?” ብለው ጠየቁት። ያ የተፈወሰው ግን ያዳነው ማን እንደ ሆነ አላወቀም፤ ጌታችን ኢየሱስ በዚያ ቦታ በነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል ተሰውሮ ነበርና። ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ያን የዳነውን ሰው በቤተ መቅደስ አገኘውና፥ “እነሆ፥ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ” አለው። ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው። ስለዚህም አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን ያሳድዱትና ሊገድሉትም ይሹ ነበር፤ በሰንበት እንዲህ ያደርግ ነበርና። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ” አላቸው። ስለዚህም አይሁድ ሊገድሉት በጣም ይፈልጉ ነበር፤ “ሰንበትን የሚሽር ነው” በማለት ብቻ አይደለም፤ ደግሞም እግዚአብሔርን “አባቴ ነው ይላል፤ ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል” በማለት ነው እንጂ። ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወልድ ከራሱ ብቻ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ፤ ወልድም አብ የሚሠራውን ያንኑ እንዲሁ ይሠራል። አብ ልጁን ይወዳልና የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ታደንቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራን ያሳየዋል። አብ ሙታንን እንደሚያስነሣቸው፥ ሕይወትንም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድም ለሚወድዳቸው ሕይወትን ይሰጣል። አብ ከቶ በማንም አይፈርድም፤ ፍርዱን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ። ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩ ዘንድ፤ ወልድን የማያከብር ግን የላከውን አብን አያከብርም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ በላከኝም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛል፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይሄድም። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ቃል የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም ይድናሉ። ለአብ በራሱ ሕይወት እንዳለው፥ እንዲሁም ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጠው። የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ነውና ይፈርድ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠው። “በመቃብር ያሉ ሁሉ ቃሉን የሚሰሙባት ጊዜ ትመጣለችና ስለዚህ አታድንቁ። መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፥ ክፉ የሠሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ። እኔ ከራሴ አንዳች አደርግ ዘንድ አልችልም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ እንጂ፤ ፍርዴም እውነት ነው፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ የእኔን ፈቃድ አልሻምና። “እኔ ለራሴ ብመሰክር ምስክርነቴ እውነት አይደለም። ነገር ግን ለእኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፤ ስለ እኔ የመሰከረው ምስክርነቱም እውነት እንደሆነ አውቃለሁ። እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችሁ አልነበረምን? እርሱም ምስክርነቱን በእውነት ነገራችሁ። እኔ ግን የሰውን ምስክርነት የምሻ አይደለሁም፤ ነገር ግን እናንተ ትድኑ ዘንድ ይህን እላለሁ። እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፤ እናንተም አንዲት ሰዓት በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ። እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ ልሠራውና ልፈጽመው አባቴ የሰጠኝ ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ያ የምሠራው ሥራ ምስክሬ ነውና። የላከኝ አብም ስለ እኔ መስክሮአል፤ ከሆነም ጀምሮ ቃሉን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም። ቃሉም የላችሁም፤ በእናንተ ዘንድም አይኖርም፤ እርሱ የላከውን አላመናችሁምና። መጻሕፍትን መርምሩ፤ በእነርሱ የዘለዓለም ሕይወትን የምታገኙ ይመስላችኋልና፤ እነርሱም የእኔ ምስክሮች ናቸው። ሕይወትን ታገኙ ዘንድ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። እኔ ከሰው ክብርን ልቀበል አልሻም። ነገር ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በእናንተ እንደሌለባችሁ ዐወቅሁ። እኔ በአባቴ ስም መጣሁ፥ አልተቀበላችሁኝምም፤ ሌላው ግን በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ። ከባልንጀራችሁ ክብርን የምትመርጡ፥ ከአንድ እግዚአብሔርም ክብርን የማትሹ እናንተ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? እኔ በአብ ዘንድ የምከስሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከስሳችሁስ አለ፤ እርሱም እናንተ ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው። ሙሴንስ አምናችሁት ቢሆን እኔንም ባመናችሁኝ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። ሙሴ የጻፈውን ካላመናችሁ ግን የእኔን ቃል እንዴት ታምናላችሁ?”
ዮሐንስ 5:1-47 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌም፣ በበጎች በር አጠገብ፣ ዐምስት ባለመጠለያ መመላለሻዎች የነበሯት፣ በአራማይክ ቋንቋ ቤተ ሳይዳ የተባለች አንዲት መጠመቂያ አለች። በእነዚህም መመላለሻዎች ውስጥ ብዙ አካለ ስንኩላን፣ ዐይነ ስውሮች፣ ዐንካሶችና ሽባዎች ይተኙ ነበር። [የውሃውንም መንቀሳቀስ እየተጠባበቁ፣ ዐልፎ ዐልፎ የጌታ መልአክ ወርዶ ውሃውን በሚያናውጥበት ጊዜ፣ ቀድሞ ወደ መጠመቂያዪቱ የገባ ካደረበት ማንኛውም በሽታ ይፈወስ ነበር።] በዚያም ለሠላሳ ስምንት ዓመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ነበር። ኢየሱስም ይህን ሰው ተኝቶ ባገኘው ጊዜ፣ ለብዙ ጊዜ በዚህ ሁኔታ እንደ ነበር ዐውቆ “ልትድን ትፈልጋለህን?” አለው። ሕመምተኛውም መልሶ፣ “ጌታዬ፣ ውሃው በሚናወጥበት ጊዜ ወደ መጠመቂያዪቱ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ ለመግባትም ስሞክር ሌላው ይቀድመኛል” አለው። ኢየሱስም፣ “ተነሥ! መተኛህን ተሸክመህ ሂድ” አለው። ሰውየውም ወዲያው ተፈወሰ፤ መተኛውንም ተሸክሞ ሄደ። ይህም የሆነው በሰንበት ቀን ነበር። አይሁድም የተፈወሰውን ሰው፣ “ሰንበት ስለ ሆነ መተኛህን እንድትሸከም ሕጉ አይፈቅድልህም” አሉት። እርሱ ግን፣ “ያ የፈወሰኝ ሰው፣ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ብሎኛል” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም፣ “ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ያለህ እርሱ ማነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ወደ ሕዝብ መካከል ገብቶ ስለ ነበር፣ ሰውየው ማን እንደ ፈወሰው አላወቀም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው በቤተ መቅደስ አግኝቶ፣ “እነሆ፣ ተፈውሰሃል፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥራ፤ አለዚያ ከዚህ የባሰ ይደርስብሃል” አለው። ሰውየውም የፈወሰው ኢየሱስ መሆኑን ሄዶ ለአይሁድ ነገራቸው። አይሁድም፣ በሰንበት ቀን እነዚህን ድርጊቶች በመፈጸሙ፣ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር። ኢየሱስም፣ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ” አላቸው። እንግዲህ አይሁድ፣ ኢየሱስ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አባቱ በማድረግ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል በማድረጉ፣ ሊገድሉት አጥብቀው ይፈልጉት ነበር። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ አብ ሲሠራ ያየውን ብቻ እንጂ ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ያደርጋልና፤ አብ ወልድን ስለሚወድድ የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል፤ ትደነቁም ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ነገር ያሳየዋል። ምክንያቱም አብ ሙታንን እንደሚያስነሣ፣ ሕይወትንም እንደሚሰጥ፣ ወልድም ደግሞ ለሚፈቅደው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል። አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ ይኸውም፣ ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን አብንም አያከብርም። “እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ፣ በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቷል፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው ሁሉ፣ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና፤ ወልድ የሰው ልጅ ስለ ሆነም እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል። “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ። እኔ ብቻዬን ከራሴ ምንም ማድረግ አልችልም፤ የምፈርደው የምሰማውን ብቻ ነው፤ የላከኝን እንጂ የራሴን ፈቃድ ስለማልሻም ፍርዴ ትክክል ነው። “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር፣ ምስክርነቴ ተቀባይነት አይኖረውም። ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ አለ፤ እርሱ ስለ እኔ የሚሰጠውም ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ ዐውቃለሁ። “ወደ ዮሐንስ ልካችሁ ነበር፤ እርሱም ስለ እውነት መስክሯል፤ እኔ የሰው ምስክርነት የምቀበል አይደለሁም፤ ይህን የምናገረው ግን እናንተ እንድትድኑ ነው። ዮሐንስ እየነደደ ብርሃን የሚሰጥ መብራት ነበረ፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በብርሃኑ ደስ ልትሠኙ ወደዳችሁ። “እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የላቀ ምስክር አለኝ፤ እንድፈጽመው አብ የሰጠኝ፣ እኔም የምሠራው ሥራ አብ እንደ ላከኝ ይመሰክራል። የላከኝ አብ ራሱ ስለ እኔ መስክሯል፤ እናንተም ከቶ ድምፁን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፤ የላከውንም ስላላመናችሁ ቃሉ በእናንተ አይኖርም። በእነርሱ የዘላለም ሕይወትን የምታገኙ እየመሰላችሁ፣ መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ እነዚሁ መጻሕፍት ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ እናንተ ግን፣ ሕይወት እንዲኖራችሁ ወደ እኔ መምጣት አትፈልጉም። “እኔ ከሰው ክብር አልቀበልም፤ ነገር ግን እናንተን ዐውቃችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርም ፍቅር በልባችሁ እንደሌለ ዐውቃለሁ። እኔ በአባቴ ስም መጥቼ አልተቀበላችሁኝም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ ግን ትቀበሉታላችሁ። እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትሰጣጡ፣ ነገር ግን ከአንዱ አምላክ የሚመጣውን ክብር የማትፈልጉ ከሆነ፣ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? “ከሳሻችሁ ተስፋ የጣላችሁበት ሙሴ እንጂ፣ እኔ በአብ ፊት የምከስሳችሁ አይምሰላችሁ፤ ሙሴን ብታምኑ ኖሮ፣ እኔን ባመናችሁ ነበር፤ ምክንያቱም እርሱ የጻፈው ስለ እኔ ነው። እርሱ የጻፈውን ካላመናችሁ፣ እኔ የምናገረውን እንዴት ታምናላችሁ?”
ዮሐንስ 5:1-47 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር። በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ፦ ልትድን ትወዳለህን? አለው። ድውዩም፦ ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ፦ ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ያም ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው፦ ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም አሉት። እርሱ ግን፦ ያዳነኝ ያ ሰው፦ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ ብሎ መለሰላቸው። እነርሱም፦ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማን ነው? ብሎአው ጠየቁት። ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ሰለ ነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቀም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና፦ እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው። ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገረ። ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ግን፦ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ፦ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል። አብ ሙታንን ይንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔር ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲሆረው ሰጥቶታልና። የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ። እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና። እኔ ስለ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክሬ እውነት አይደለም፤ ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፥ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክር እውነት እንደ ሆነ አውቃለሁ። እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችኋል እርሱም ለእውነት መስክሮአል። እኔ ግን ከሰው ምስክር አልቀበልም፥ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ። እርሱ የሚያድንና የሚያበራ መብራት ነበረ፥ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ። እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና። የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል። ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፥ መልኩንም አላያችሁም፤ እርሱም የላከውን እናንተ አታምኑምና በእናንተ ዘንድ የሚኖር ቃሉ የላችሁም። እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በራሳችሁ እንደ ሌላችሁ አውቃችኋለሁ። እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ። እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ አለ፤ እርሱም ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው። ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?
ዮሐንስ 5:1-47 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ስለ ነበረ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ፥ በዕብራይስጥ ቋንቋ ቤተ ሳይዳ የሚባል አንድ የምንጭ ኲሬ ነበረ፤ በዙሪያውም አምስት ከላይ ክዳን ያላቸው መተላለፊያዎች ነበሩ። [በጣም ብዙ በሽተኞች፥ ዕውሮች አንካሶችና ሽባዎች በመተላለፊያዎቹ ተኝተው ነበር። እነዚህ የውሃውን መንቀሳቀስ ይጠባበቁ ነበር፤ አልፎ አልፎ የጌታ መልአክ ወደ ኲሬው ወርዶ ውሃውን ያናውጥ ነበር፤ ከውሃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ ወደ ኲሬው የሚገባ ካደረበት ከማንኛውም በሽታ ይፈወስ ነበር።] በዚያም ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ የታመመ አንድ ሰው ነበረ። ኢየሱስ ይህን ሰው እዚያ ተኝቶ አየውና ከብዙ ጊዜ ጀምሮ መታመሙን ዐውቆ፥ “መዳን ትፈልጋለህን?” አለው። በሽተኛውም “ጌታ ሆይ! ውሃው በሚንቀሳቀስበት ጊዜ እኔን ወስዶ ወደ ኲሬው የሚያስገባኝ ሰው የለኝም፤ እኔ ልሄድ ስል ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው። ኢየሱስም “ተነሥ! አልጋህን ተሸከምና ሂድ!” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ይህም የሆነው በሰንበት ቀን ነበር፤ ስለዚህ የአይሁድ ባለሥልጣኖች ያንን የዳነውን ሰው “ዛሬ ሰንበት ስለ ሆነ አልጋህን እንድትሸከም ሕግ አይፈቅድልህም” አሉት። እርሱ ግን “ያዳነኝ ሰው አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” ብሎኛል አላቸው። እነርሱም “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ሰውየው ግን ሕዝብ ስለ በዛና ኢየሱስም ከዚያ ራቅ ብሎ ስለ ሄደ ያዳነው ማን እንደ ሆነ አያውቅም ነበር። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሰውየውን በቤተ መቅደስ አገኘውና “እነሆ፥ አሁን ድነሃል፤ ከዚህ የባሰ ነገር እንዳይደርስብህ ከእንግዲህ ወዲህ ኃጢአት አትሥራ” አለው። ሰውየውም ሄደና ያዳነው ኢየሱስ መሆኑን ለአይሁድ ባለሥልጣኖች ነገረ። ይህን ነገር በሰንበት ስላደረገ የአይሁድ ባለሥልጣኖች ኢየሱስን ያሳድዱት ጀመር። ኢየሱስ ግን “አባቴ ሁልጊዜ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ” ሲል መለሰላቸው። ይህም አባባል የአይሁድን ባለሥልጣኖች ኢየሱስን እንዲገድሉት በይበልጥ አነሣሣቸው፤ ይህም የሆነው እርሱ ሰንበትን በመሻሩ ብቻ ሳይሆን “እግዚአብሔር አባቴ ነው” በማለት ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ስለ አስተካከለ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ አብ ሲሠራ ያየውን ከመሥራት በቀር ወልድ በራሱ ሥልጣን ምንም ሊሠራ አይችልም። አብ የሚያደርገውን ወልድም እንዲሁ ያደርጋል። አብ ወልድን ስለሚወድ የሚሠራውን ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም እንድትደነቁ ከዚህ የበለጠ ሥራም ያሳየዋል። አብ የሞቱትን እንደሚያስነሣና ሕይወትን እንደሚሰጣቸው፥ ወልድም እንዲሁ ለፈለገው ሰው ሕይወትን ይሰጠዋል። አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጥቶአል። ይህንንም ያደረገው ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ፥ እንዲሁም ወልድን እንዲያከብሩ ነው፤ ወልድን የማያከብር፥ ወልድን የላከውን አብን አያከብርም። “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማና በላከኝም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እርሱ ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገረ ስለ ሆነ አይፈረድበትም። እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ የሞቱ ሰዎች የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ ጊዜውም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም ሁሉ በሕይወት ይኖራሉ። አብ ራሱ የሕይወት ምንጭ እንዲሆን አድርጎታል። የሰው ልጅ በመሆኑም ፍርድ እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል። በዚህ ነገር አትደነቁ፤ በመቃብር ውስጥ ያሉት ሁሉ የእርሱን ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል። መልካም የሠሩ ከሞት ተነሥተው በሕይወት ይኖራሉ፤ ክፉ የሠሩ ግን ከሞት ተነሥተው ይፈረድባቸዋል። “እኔ በራሴ ሥልጣን ምንም ማድረግ አልችልም፤ ነገር ግን ከአብ የሰማሁትን እፈርዳለሁ፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ የራሴን ፈቃድ ስለማላደርግ ፍርዴ ትክክል ነው። “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክርነቴ እውነት አይደለም። ነገር ግን ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ አለ፤ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክርነት እውነት መሆኑን ዐውቃለሁ። እናንተ ወደ ዮሐንስ መልእክተኞች ልካችሁ ነበር፤ እርሱም ስለ እውነት መስክሮአል። ይህንንም ማለቴ እንድትድኑ ነው እንጂ እኔ የሰው ምስክርነት ስላስፈለገኝ አይደለም። ዮሐንስ እንደሚነድና እንደሚበራ መብራት ነበረ፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በእርሱ ብርሃን ለመደሰት ፈለጋችሁ። እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የበለጠ ምስክር አለኝ፤ ምስክሬም አባቴ እንድሠራው የሰጠኝ ሥራ ነው፤ ይህም የምሠራው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራል። የላከኝም አብ፥ ራሱ ስለ እኔ መስክሮአል፤ እናንተ ግን ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፤ መልኩንም ከቶ አላያችሁም። እርሱ የላከውን ስለማታምኑ የእርሱ ቃል በእናንተ ዘንድ አይኖርም። እናንተ በቅዱሳት መጻሕፍት የዘለዓለምን ሕይወት የምታገኙ ስለሚመስላችሁ እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው። ይሁን እንጂ እናንተ ሕይወትን ለማግኘት ወደ እኔ መምጣት አትፈልጉም። “እኔ ክብርን ከሰው አልፈልግም። እናንተ ከልባችሁ እግዚአብሔርን የማታፈቅሩ መሆናችሁን ዐውቃለሁ። እኔ በአባቴ ስም መጣሁ፤ እናንተ ግን አልተቀበላችሁኝም፤ ሌላ በራሱ ስም ቢመጣ ግን ትቀበሉታላችሁ። እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብርን የምትፈልጉ ከአንዱ ከእግዚአብሔር የሚገኘውን ክብር ግን የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? እኔ በአባቴ ፊት የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ፥ ተስፋ የምታደርጉበት ሙሴ ነው። ሙሴን ብታምኑ ኖሮ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና እኔንም ባመናችሁ ነበር። እርሱ የጻፈውን ካላመናችሁ ግን የእኔን ቃል እንዴት ታምናላችሁ?”
ዮሐንስ 5:1-47 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። በእነዚህም ውስጥ ብዙ ድኩማን፥ ዐይነ ሥውሮች፥ አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሰዎች ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውሃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውሃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ይፈወስ ይሆን ነበር። በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው። ሕመምተኛውም “ጌታ ሆይ! ውሃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ ነገር ግን እኔ በመምጣት ላይ እያለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል፤” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ “ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤” አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ያም ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው “ሰንበት ነው፥ አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም፤” አሉት። እርሱ ግን “ያዳነኝ ያ ሰው ‘አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤’ አለኝ፤” ብሎ መለሰላቸው። እነርሱም “‘አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤’ ያለህ ሰው ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። ዳሩ ግን የተፈወሰው ሰው ማን እንደሆነ አላወቀም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ስለ ነበርና፥ በዚያ ስፍራ ብዙ ሰዎች ሰለ ነበሩ ነው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ አገኘውና “እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ፤” አለው። ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደሆነ ለአይሁድ ነገረ። ስለዚህም አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር፤ በሰንበት ይህን አድርጎ ነበርና። ኢየሱስ ግን “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ፤” ብሎ መለሰላቸው። እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ደግሞ እራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ “እግዚአብሔር አባቴ ነው፤” ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ፤ እንዲህም አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከእራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። አብ ወልድን ይወዳልና፤ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል። አብ ሙታንን እንደሚያስነሣቸው፥ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። አብ ከቶ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ይልቁንም፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው። ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በእራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በእራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና። የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። በዚህ አታድንቁ፤ በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና። “እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ፤ ፍርዴም ቅን ነው፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና። እኔ ለእራሴ ብመሰክር ምስክርነቴ እውነት አይደለም፤ ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፤ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክር እውነት እንደሆነ አውቃለሁ። እናንተ ወደ ዮሐንስ መልክተኞችን ልካችኋል፥ እርሱም ለእውነት መስክሮአል። እኔ ግን የሰው ምስክር የሚያስፈልገኝ አይደለሁም፤ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ። እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፤ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ። እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ እንድፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና። የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል። ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፤ እርሱ የላከውንም እናንተ አታምኑምና፤ በእናንተ ዘንድ የሚኖር ቃሉ የላችሁም። እናንተ መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ በእነርሱም የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችሁ ታስባላችሁና፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። የሰው ክብር አያስፈልገኝም፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በውስጣችሁ እንደሌላችሁ ዐወቅሁ። እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ፤ አትቀበሉኝምም፤ ሌላው በእራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ። እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ፥ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ብቻ የሚገኘውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ አለ፤ እርሱም ተስፋ የምታደርጉበት ሙሴ ነው። ሙሴንስ ብታምኑት እኔንም ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። የእርሱን ጽሑፎች ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?”