ዮሐንስ 20:1-10
ዮሐንስ 20:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከሳምንቱም በመጀመሪያዉ ቀን ማርያም መግደላዊት በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ ወደ መቃብር መጣች፤ ድንጋዩንም ከመቃብሩ አፍ ተነሥቶ አገኘችው። ፈጥናም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ጌታችን ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደዚያ ወደ ሌላዉ ደቀ መዝሙር መጥታ፥ “ጌታዬን ከመቃብር ወስደውታል፤ ወዴትም እንደ ወሰዱት አላውቅም” አለቻቸው። ጴጥሮስና ያ ሌላዉ ደቀ መዝሙርም ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም በአንድነት ሲሮጡ ያ ሌላዉ ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን ቀድሞት ወደ መቃብሩ ደረሰ። ጐንበስ ብሎም ሲመለከት በፍታዉን ተቀምጦ አየ፤ ነገር ግን ወደ ውስጥ አልገባም። ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት ደረሰና ወደ መቃብሩ ገባ፤ በፍታዉንም በአንድ ወገን ተቀምጦ አየ፤ በራሱ ላይ የነበረው መጠምጠሚያም ሳይቃወስ ለብቻው ተጠቅልሎ አየ፤ ከበፍታዉ ጋርም አልነበረም። ከዚህም በኋላ አስቀድሞ ወደ መቃብሩ የደረሰው ሌላዉ ደቀ መዝሙር ገባ፤ አይቶም አመነ፤ ከሙታን ተለይቶ ይነሣ ዘንድ እንደ አለው በመጻሕፍት የተጻፈውን ገና አላወቁም ነበርና። ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው ወደ ቤታቸው ገቡ።
ዮሐንስ 20:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን፣ በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ፣ መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ሄደች፤ ድንጋዩም ከመቃብሩ ተንከባልሎ አየች። ስለዚህም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወድደው ወደ ነበረው ሌላው ደቀ መዝሙር እየሮጠች መጥታ፣ “ጌታን ከመቃብር አውጥተው ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም!” አለቻቸው። ከዚያም ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም ይሮጡ ነበር፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ጴጥሮስን ቀድሞት ከመቃብሩ ደረሰ። ጐንበስ ብሎ ወደ ውስጥ ሲመለከት፣ በፍታውን ብቻ ተቀምጦ አየ፤ ወደ መቃብሩ ግን አልገባም። ይከተለው የነበረው ስምዖን ጴጥሮስ ደረሰና ወደ መቃብሩ ገባ፤ እርሱም ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን አየ፤ እንዲሁም በኢየሱስ ራስ ላይ ተጠምጥሞ የነበረውን ጨርቅ አየ፤ ይህም ጨርቅ ከከፈኑ ተለይቶ እንደ ተጠቀለለ ነበር። ከዚያም አስቀድሞ ከመቃብሩ የደረሰው ሌላው ደቀ መዝሙር ወደ ውስጥ ገባ፤ አይቶም አመነ፤ ይኸውም ኢየሱስ ከሙታን መነሣት እንዳለበት ገና ከመጽሐፍ ስላልተረዱ ነበር። ከዚያም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው ወደ የቤታቸው ሄዱ።
ዮሐንስ 20:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች። እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ፦ “ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም” አለቻቸው። ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርትም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፤ ዝቅም ብሎ ቢመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ነገር ግን አልገባ። ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ። በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውንም ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፥ አየም፥ አመነም፤ ከሙታን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም ነበርና። ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቤታቸው ደግሞ ሄዱ።
ዮሐንስ 20:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እሑድ ጠዋት በማለዳ፥ ገና ጎሕ ሳይቀድ፥ መግደላዊት ማርያም ወደ ኢየሱስ መቃብር ሄደች፤ እዚያም እንደ ደረሰች መቃብሩ ተዘግቶበት የነበረው ድንጋይ ከመቃብሩ በር ላይ ተነሥቶ አየች። ስለዚህ እርስዋ ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ወደሚወደው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር እየሮጠች ሄደችና “ጌታን ከመቃብሩ አውጥተው ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩት አናውቅም” አለቻቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጡና ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም አብረው ይሮጡ ነበር፤ ነገር ግን ሌላው ደቀ መዝሙር ከጴጥሮስ ይበልጥ ፈጥኖ ሮጠና ቀድሞ ወደ መቃብሩ ደረሰ። ጐንበስ ብሎም ወደ መቃብሩ ቢመለከት የከፈኑ ጨርቅ እዚያ ተቀምጦ አየ፤ ነገር ግን ወደ ውስጥ አልገባም። ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣና ወደ መቃብሩ ውስጥ ገባ፤ እርሱም የከፈኑን ጨርቅ እዚያ ተቀምጦ አየ፤ የኢየሱስ ራስ ተጠምጥሞ የነበረበት ጨርቅ ከከፈኑ ጨርቅ ጋር ሳይሆን ለብቻው በሌላ ስፍራ ተጠቅሎ እንደ ተቀመጠ አየ። ቀጥሎም ያ ቀድሞ የደረሰው ደቀ መዝሙር ወደ መቃብሩ ውስጥ ገብቶ አየና አመነ። “ከሞት መነሣት ይገባዋል” የሚለውን የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ገና አልተገነዘቡም ነበር። ከዚህ በኋላ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ተመልሰው ወደ ቤታቸው ሄዱ።
ዮሐንስ 20:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለሞ ሳለ በማለዳ ወደ መቃብር መጣች፤ ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች። እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደነበረው ወደ ሌላው ደቀመዝሙር መጥታ “ጌታን ከመቃብር ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው። ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀመዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና ቀድሞ ወደ መቃብሩ ደረሰ፤ ዝቅም ብሎ ሲመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፤ ነገር ግን አልገባም። ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ፤ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፤ እንዲሁም በራሱ ላይ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ። በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀመዝሙር ገባ፤ አየም፤ አመነም፤ “ከሙታን መነሣት ይገባዋል” የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም ነበርና። ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቤታቸው ሄዱ።