ዮሐንስ 2:1-10
ዮሐንስ 2:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በሦስተኛውም ቀን የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና ሰርግ ሆነ፤ የጌታችን የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች። ጌታችን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጃቸውም ባለቀ ጊዜ እናቱ ጌታችን ኢየሱስን፥ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “አንቺ ሆይ ካንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት። እናቱም ለአሳላፊዎቹ፥ “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው። በዚያም እንደ አይሁድ ልማድ የሚያነጹባቸው ስድስት የድንጋይ ጋኖች ነበሩ፤ ከእነርሱም እያንዳንዱ ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው” አላቸው፤ እስከ አፋቸውም እስከ ላይ ሞሉአቸው። “አሁንም ቅዱና ወስዳችሁ ለአሳዳሪው ስጡት” አላቸው፤ ወስደውም ሰጡት። አሳዳሪውም ያን የወይን ጠጅ የሆነውን ውኃ ቀምሶ አደነቀ፤ ከወዴት እንደ መጣም አላወቀም፤ የቀዱት አሳላፊዎች ግን የወይን ጠጅ የሆነውን ያን ውኃ ያውቁ ነበር። ውኃዉን የሞሉ እነርሱ ነበሩና። አሳዳሪውም ሙሽራውን ጠርቶ፥ “ሰው ሁሉ መልካሙን የወይን ጠጅ አስቀድሞ ያጠጣል፤ ከጠገቡ በኋላም ተርታውን ያመጣል፤ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስካሁን አቈየህ” አለው።
ዮሐንስ 2:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በሦስተኛው ቀን፣ በገሊላ አውራጃ፣ በቃና ከተማ ሰርግ ነበር፤ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ተጠርተው ነበር። የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜም የኢየሱስ እናት፣ “የወይን ጠጅ እኮ ዐለቀባቸው” አለችው። ኢየሱስም፣ “አንቺ ሴት ሆይ፤ ምን አድርግ ትይኛለሽ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት። እናቱም በዚያ የነበሩትን አገልጋዮች፣ “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው። በአይሁድ የመንጻት ሥርዐት መሠረት፣ ከሰባ ዐምስት እስከ አንድ መቶ ዐሥራ ዐምስት ሊትር የሚይዙ ከድንጋይ የተሠሩ ስድስት ጋኖች በዚያ ነበሩ። ኢየሱስ አገልጋዮቹን፣ “ጋኖቹን ውሃ ሙሏቸው” አላቸው፤ እነርሱም፣ ጋኖቹን እስከ አፋቸው ሞሏቸው። እርሱም፣ “ከላዩ ቀድታችሁ ለድግሱ ኀላፊ ስጡት” አላቸው። እነርሱም እንዳዘዛቸው አደረጉ። የድግሱ ኀላፊም ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን ውሃ ቀመሰ፤ ሆኖም ከየት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውሃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር። እርሱም ሙሽራውን ለብቻው ጠርቶ፣ “ሰው ሁሉ በመጀመሪያ የሚያቀርበው ጥሩውን የወይን ጠጅ ነው፤ እንግዶቹም ብዙ ከጠጡ በኋላ መናኛውን የወይን ጠጅ ያቀርባል፤ አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቈይተሃል” አለው።
ዮሐንስ 2:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት፦ የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት። እናቱም ለአገልጋዮቹ፦ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም፦ ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ፦ ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው።
ዮሐንስ 2:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በሦስተኛው ቀን፥ በገሊላ ምድር በምትገኘው ቃና በምትባል ከተማ ሠርግ ነበረ፤ የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሠርጉ ተጠርተው ነበር። በሠርጉ ግብዣ ላይ የወይን ጠጁ ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት ኢየሱስን፦ “የወይን ጠጅ እኮ አልቆባቸዋል!” አለችው። ኢየሱስም “እናቴ ሆይ! ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት። በዚያን ጊዜ እናቱ እዚያ ለነበሩት አገልጋዮች፦ “እርሱ የሚላችሁን አድርጉ” አለቻቸው። አይሁድ የመንጻት ሥርዓት ስለ ነበራቸው ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ነበሩ፤ እያንዳንዱ ጋን ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ውሃ ለመያዝ ይችል ነበር። ኢየሱስ አገልጋዮቹን “ጋኖቹን ውሃ ሙሉአቸው” አላቸው፤ እነርሱም እስከ አፋቸው ሞሉአቸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አገልጋዮቹን፦ “በሉ አሁን ቀድታችሁ ለግብዣው ኀላፊ ስጡት” አላቸው፤ እነርሱም ወስደው ሰጡት። የግብዣው ኀላፊ ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ፥ ከየት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውሃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ ስለዚህ የግብዣው ኀላፊ፥ ሙሽራውን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ሰው ሁሉ አስቀድሞ የሚያቀርበው ጥሩውን የወይን ጠጅ ነው፤ ተጋባዦቹ ከጠጡ በኋላ መናኛውን ያቀርባል፤ አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቈየህ።”
ዮሐንስ 2:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፤ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም፤” አለችው። ኢየሱስም “አንቺ ሴት ሆይ፦ ይህ ጉዳይ ለእኔ ምንድነው? ጊዜዬ ገና አልደረሰም፤” አላት። እናቱም ለአገልጋዮቹ “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ፤” አለቻቸው። አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፤ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም “ጋኖቹን ውሃ ሙሉአቸው፤” አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። “አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት፤” አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደመጣ አላወቀም፤ ውሃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ “ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፤ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል፤” አለው።