ዮሐንስ 18:3-6
ዮሐንስ 18:3-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይሁዳም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን ወታደሮችን ተቀበለ፤ ሎሌዎቻቸውንም በረዳትነት ወሰደ፤ ፋኖስና የችቦ መብራት፥ የጦር መሣሪያም ይዞ ወደዚያ ሄደ። ጌታችን ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወደ እነርሱ ወደ ውጭ ወጣና፥ “ማንን ትሻላችሁ?” አላቸው። “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ ነኝ” አላቸው፤ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም በዚያው አብሮአቸው ቆሞ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ፤ ወደ ኋላቸው ተመልሰው በምድር ላይ ወደቁ።
ዮሐንስ 18:3-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይሁዳም ወታደሮችን እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩ አገልጋዮችን እየመራ ወደ አትክልቱ ስፍራ መጣ፤ እነርሱም ችቦ፣ ፋኖስና የጦር መሣሪያ ይዘው ነበር። ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወጣና፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” አላቸው። እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ከእነርሱ ጋራ ቆሞ ነበር። ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” ባለ ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወደቁ።
ዮሐንስ 18:3-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ ይሁዳ ጭፍሮችንና ካህናት አለቆች ከፈሪሳውያንም ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና በጋሻ ጦርም ወደዚያ መጣ። ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና፦ “ማንን ትፈልጋላችሁ” አላቸው። “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት። ኢየሱስ፦ “እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። እንግዲህ፦ እኔ ነኝ ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በምድር ወደቁ።
ዮሐንስ 18:3-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ ይሁዳ አንድ የወታደሮች ጭፍራ፥ እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩትን የዘብ ኀላፊዎችን አስከትሎ ወደዚያ ቦታ መጣ፤ እነርሱም ፋኖስና ችቦ፥ የጦር መሣሪያም ይዘው ነበር። ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወደ እነርሱ ወጣ ብሎ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ እንፈልጋለን” አሉት። እርሱም “እኔ ነኝ!” አላቸው። አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። ኢየሱስ “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈገፈጉና በምድር ላይ ወደቁ።
ዮሐንስ 18:3-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ ይሁዳ ወታደሮችን፥ እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና፥ በጦር መሣርያም ታጅቦ ወደዚያ መጣ። ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት። እርሱም “እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። ኢየሱስም “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመሬት ላይ ወደቁ።