ዮሐንስ 18:1-40
ዮሐንስ 18:1-40 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌታችን ኢየሱስም ይህን ተናግሮ አትክልት ወደ አለበት ስፍራ ወደ ቄድሮስ ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደዚያ ገባ። አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም ያን ስፍራ ያውቀው ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደዚያ ብዙ ጊዜ ይሄድ ነበርና። ይሁዳም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን ወታደሮችን ተቀበለ፤ ሎሌዎቻቸውንም በረዳትነት ወሰደ፤ ፋኖስና የችቦ መብራት፥ የጦር መሣሪያም ይዞ ወደዚያ ሄደ። ጌታችን ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወደ እነርሱ ወደ ውጭ ወጣና፥ “ማንን ትሻላችሁ?” አላቸው። “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ ነኝ” አላቸው፤ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም በዚያው አብሮአቸው ቆሞ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ፤ ወደ ኋላቸው ተመልሰው በምድር ላይ ወደቁ። ከዚህም በኋላ እንደገና፥ “ማንን ትሻላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፤ እነርሱም፥ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ ነኝ አልኋችሁ፤ እኔን የምትሹ ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አላቸው። ይህም፥ “ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንድ ስንኳ አልጠፋም” ያለው ቃሉ ይፈጸም ዘንድ ነው። ስምዖን ጴጥሮስም ሾተል ነበረው፤ ሾተሉንም መዝዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው፤ የዚህም አገልጋይ ስም ማልኮስ ይባል ነበር። ጌታችን ኢየሱስም ጴጥሮስን፥ “ሾተልህን ወደ አፎቷ መልስ፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ ሳልጠጣ እተወዋለሁን?” አለው። ጭፍሮችና የሺ አለቃው፥ የአይሁድም ሎሌዎች ጌታችን ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። አስቀድሞም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት የካህናት አለቃ ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና። ቀያፋም “ስለ ሕዝቡ ሁሉ አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል” ብሎ አይሁድን የመከራቸው ነበር። ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙርም ጌታችን ኢየሱስን ከሩቅ ተከተሉት፤ ያ ደቀ መዝሙር ግን በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበር፤ ከጌታችን ኢየሱስ ጋርም ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገባ። ጴጥሮስ ግን በስተውጭ በበሩ ቆሞ ነበር፤ ያም በሊቀ ካህናቱ ዘንድ ይታወቅ የነበረው ሌላው ደቀ መዝሙር ወጣና ለበረኛዪቱ ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው። በረኛዪቱ አገልጋይም፥ “አንተም ከዚያ ሰው ደቀ መዛሙርት ወገን አይደለህምን?” አለችው፤ እርሱም፥ “አይደለሁም” አላት። አገልጋዮችና ሎሌዎችም በዚያ ቆመው እሳት አንድደው ይሞቁ ነበር፤ የዚያች ሌሊት ብርድ ጽኑ ነበርና፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበረ። ሊቀ ካህናቱም ጌታችን ኢየሱስን፦ ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “እኔ ለዓለም በግልጥ ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብም፥ በቤተ መቅደስም ሁልጊዜ አስተማርሁ፤ በስውርም የተናገርሁት አንዳች ነገር የለም። እንግዲህ እኔን ለምን ትጠይቀኛለህ? የተናገርሁትን የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ እኔም የተናገርሁትን እነሆ፥ እነርሱ ያውቃሉ።” ይህንም ባለጊዜ ከቆሙት ሎሌዎች አንዱ፥ “ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልስለታለህን?” ብሎ ጌታችን ኢየሱስን በጥፊ መታው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክርብኝ፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ለምን ትመታኛለህ?” አለው። ሐናም ጌታችን ኢየሱስን እንደ ታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው። ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር፤ “አንተስ ከእርሱ ደቀ መዛሙርት ወገን አይደለህምን?” አሉት፤ እርሱም፥ “አይደለሁም” ብሎ ካደ። ጴጥሮስ ጆሮውን ከቈረጠው ሰው ዘመዶች ወገን የሆነ ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮችም አንድ ሰው፥ “እኔ በአትክልት ቦታ ውስጥ ከእርሱ ጋር አይችህ አልነበረምን?” አለው። ጴጥሮስም ደግሞ ካደ፤ ያንጊዜም ዶሮ ጮኸ። ጌታችን ኢየሱስንም ከቀያፋ ወደ ፍርድ አደባባይ ወሰዱት፤ አይሁድ ግን ፈጽሞ ስለ ነጋ የፋሲካውን በግ ሳይበሉ እንዳይረክሱ ወደ ፍርድ አደባባይ አልገቡም። ጲላጦስም ወደ እነርሱ ወደ ውጭ ወጥቶ፥ “ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደሉ ምንድነው?” አላቸው። እነርሱም፥ “ክፉ የሠራ ባይሆንስ ወደ አንተ አሳልፈን ባልሰጠነው ነበር” ብለው መለሱለት። ጲላጦስም፥ “እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት” አላቸው፤ አይሁድም፥ “እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም” አሉት። ይህም በምን ዐይነት ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት የተናገረው የጌታችን የኢየሱስ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ጲላጦስም እንደገና ወደ ፍርድ አደባባይ ገብቶ ጌታችን ኢየሱስን ጠራና፥ “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ይህን የምትናገር ከራስህ ነውን? ወይስ ስለ እኔ የነገረህ ሌላ አለን?” ብሎ መለሰለት። ጲላጦስም መልሶ፥ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ለእኔ አሳልፈው የሰጡህ ወገኖችህና ሊቃነ ካህናት አይደሉምን? Aረ ምን አድርገሃል?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ በዚህ ዓለም ብትሆን ኖሮ ለአይሁድ እንዳልሰጥ አሽከሮች በተዋጉልኝ ነበር፤ አሁንም መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” ብሎ መለሰለት። ጲላጦስም፥ “እንግዲያ አንተ ንጉሥ ነህን?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ራስህ ትላለህ፤ እኔ ስለዚህ ተወለድሁ፤ ስለዚህም ለእውነት ልመሰክር ወደ ዓለም መጣሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ቃሌን ይሰማኛል” አለው። ጲላጦስም፥ “እውነት ምንድነው?” አለው፤ ይህንም ተናግሮ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጣና እንዲህ አላቸው፥ “እኔ አንዲት ስንኳን በደል አላገኘሁበትም። ነገር ግን በየዓመቱ በፋሲካ በዓል ከእስረኞች አንድ እንድፈታላችሁ ልማድ አላችሁ፤ እንግዲህ የአይሁድን ንጉሥ ልፈታላችሁ ትወዳላችሁን?” አላቸው። ዳግመኛም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፥ “በርባንን እንጂ ይህን አይደለም፤” አሉ፤ በርባን ግን ወንበዴ ነበር።
ዮሐንስ 18:1-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ሆኖ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገረ፤ ማዶ ወደ ነበረውም የአትክልት ስፍራ ገቡ። ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ በዚያ ስለሚገናኝ፣ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ቦታውን ያውቅ ነበር። ይሁዳም ወታደሮችን እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩ አገልጋዮችን እየመራ ወደ አትክልቱ ስፍራ መጣ፤ እነርሱም ችቦ፣ ፋኖስና የጦር መሣሪያ ይዘው ነበር። ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወጣና፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” አላቸው። እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ከእነርሱ ጋራ ቆሞ ነበር። ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” ባለ ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወደቁ። እንደ ገናም፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስም መልሶ፣ “ ‘እርሱ እኔ ነኝ’ ብያችኋለሁ እኮ፤ እኔን የምትፈልጉ ከሆነ፣ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው” አለ፤ ይህ የሆነው፣ “ከሰጠኸኝ ከእነዚህ አንድም አልጠፋብኝም” ብሎ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው። ሰይፍ ይዞ የነበረው ስምዖን ጴጥሮስም፣ ሰይፉን መዝዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ ቀኝ ጆሮ ቈረጠ፤ የባሪያውም ስም ማልኮስ ይባል ነበር። ኢየሱስም ጴጥሮስን፣ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ! አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣምን?” አለው። ወታደሮቹም ከአዛዣቸውና ከአይሁድ አገልጋዮች ጋራ በመሆን ኢየሱስን ያዙት፤ አስረውም፣ በመጀመሪያ የቀያፋ አማት ወደ ነበረው ወደ ሐና አመጡት፤ ቀያፋም የዓመቱ ሊቀ ካህናት ነበር። ቀያፋም ለሕዝቡ ሲባል አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል ብሎ አይሁድን የመከረ ነበር። ስምዖን ጴጥሮስና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉት። ይህም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ይታወቅ ስለ ነበር፣ ከኢየሱስ ጋራ ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገባ፤ ጴጥሮስ ግን ከበሩ ውጭ ቀረ። በሊቀ ካህናቱ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙርም ተመለሰና በር ጠባቂዋን አነጋግሮ ጴጥሮስን ይዞት ገባ። በር ጠባቂዋም ጴጥሮስን፣ “አንተ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ። ብርድ ስለ ነበር ባሮቹና ጠባቂዎቹ ባያያዙት የከሰል ፍም ዙሪያ ለመሞቅ ቆመው ሳሉ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋራ ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር። በዚያ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ለዓለም በግልጽ ተናግሬአለሁ፤ አይሁድ በተሰበሰቡበት ምኵራብ፣ በቤተ መቅደስም ሁልጊዜ አስተምሬአለሁ፤ በስውር የተናገርሁት የለም። ለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ እነሆ፤ የተናገርሁትን እነርሱ ያውቃሉ።” ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ፣ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት ጠባቂዎች አንዱ፣ “ለሊቀ ካህናቱ የምትመልሰው እንዲህ ነውን?” ብሎ በጥፊ መታው። ኢየሱስም፣ “ክፉ ተናግሬ ከሆነ ክፉ መናገሬን መስክር፤ እውነት ከተናገርሁ ግን ለምን ትመታኛለህ?” አለው። ሐናም ኢየሱስ ታስሮ እንዳለ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው። ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ሲሞቅ፣ “አንተ ከርሱ ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አሉት። እርሱም፣ “እኔ አይደለሁም” ሲል ካደ። ከሊቀ ካህናቱ ባሮች አንዱ ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመድ፣ “በአትክልቱ ስፍራ አንተን ከርሱ ጋራ አላየሁህም?” ሲል ጠየቀው። ጴጥሮስም እንደ ገና ካደ፤ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። አይሁድም ኢየሱስን ከቀያፋ ወደ ሮማዊው ገዥ ግቢ ይዘውት ሄዱ፤ ጊዜውም ማለዳ ነበር። አይሁድም ፋሲካን መብላት እንዲችሉ፣ ላለመርከስ ወደ ገዥው ግቢ አልገቡም። ስለዚህ ጲላጦስ ወደ እነርሱ ወጥቶ፣ “በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ክስ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ይህ ሰው ወንጀለኛ ባይሆን ኖሮ፣ አንተ ፊት ባላቀረብነውም ነበር” ብለው መለሱለት። ጲላጦስም፣ “እናንተ ራሳችሁ ወስዳችሁ በሕጋችሁ መሠረት ፍረዱበት” አላቸው። አይሁድም፣ “እኛማ በማንም ላይ የሞት ፍርድ ለመፍረድ መብት የለንም” አሉት። ይህ የሆነው በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት ለማመልከት ሲል ኢየሱስ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው። ጲላጦስም ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን አስጠራና፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ይህ ሐሳብ የራስህ ነው? ወይስ ሌሎች ስለ እኔ የነገሩህ?” ሲል መለሰለት። ጲላጦስም መልሶ፣ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወደ እኔ የላኩህ የራስህ ወገኖችና የካህናት አለቆች ናቸው፤ ለመሆኑ ምን አድርገህ ነው?” አለው። ኢየሱስም፣ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም፤ ቢሆንማ ኖሮ አይሁድ እንዳይዙኝ አገልጋዮቼ በተከላከሉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም” አለው። ጲላጦስም፣ “ታዲያ፣ ንጉሥ ነህ ማለት ነዋ!” አለው። ኢየሱስም፣ “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ መናገርህ ትክክል ነው፤ የተወለድሁት፣ ወደዚህም ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ይሰማኛል” አለው። ጲላጦስም፣ “እውነት ምንድን ነው?” አለው፤ ይህን ከተናገረ በኋላም እንደ ገና ወደ አይሁድ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ የሚያስከስስ በደል አላገኘሁበትም፤ ነገር ግን በፋሲካ አንድ እስረኛ እንድፈታላችሁ ልማድ አላችሁ፤ ስለዚህ፣ ‘የአይሁድን ንጉሥ’ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?” እነርሱም እንደ ገና በመጮኽ፣ “የለም፤ እርሱን አይደለም! በርባንን ፍታልን!” አሉ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ።
ዮሐንስ 18:1-40 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም ይህን ብሎ አትክልት ወዳለበት ስፍራ ወደ ቄድሮን ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ እነርሱም ደቀ መዛሙርቱም በዚያ ገቡ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ጊዜ ወደዚያ ስለ ተሰበሰቡ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ደግሞ ስፍራውን ያውቅ ነበር። ስለዚህ ይሁዳ ጭፍሮችንና ካህናት አለቆች ከፈሪሳውያንም ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና በጋሻ ጦርም ወደዚያ መጣ። ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና፦ “ማንን ትፈልጋላችሁ” አላቸው። “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት። ኢየሱስ፦ “እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። እንግዲህ፦ እኔ ነኝ ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በምድር ወደቁ። ደግሞም፦ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፦ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስ መልሶ፦ “እኔ ነኝ አልኋችሁ፤ እንግዲህ እኔን ትፈልጉ እንደ ሆናችሁ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው” አለ፤ ይህም፦ “ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንዱን ስንኳ አላጠፋሁም” ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ስምዖን ጴጥሮስም ሰይፍ ስለ ነበረው መዘዘው፥ የሊቀ ካህናቱንም ባርያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የባርያውም ስም ማልኮስ ነበረ። ኢየሱስም ጴጥሮስን፦ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው ክተተው፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣምን?” አለው። እንግዲህ የሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት፥ አስቀድመውም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና። ቀያፋም፦ “አንድ ሰው ስለ ሕዝብ ይሞት ዘንድ ይሻላል” ብሎ ለአይሁድ የመከራቸው ነበረ። ስምዖን ጴጥሮስም ሌላውም ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀ መዝሙርት በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፥ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤ ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ ቆሞ ነበር። እንግዲህ በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙር ወጣ ለበረኛይቱም ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው። በረኛ የነበረችይቱም ገረድ ጴጥሮስን፦ “አንተ ደግሞ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱ፦ “አይደለሁም” አለ። ብርድ ነበረና ባሮችና ሎሌዎች የፍም እሳት አንድደው ቆሙ ይሞቁም ነበር፤ ጴጥሮስም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። ሊቀ ካህናቱም ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየስስም መልሶ፦ “እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ እኔ ሁልጊዜ አስተማርሁ፥ በስውርም ምንም አልተናገርሁም። ስለምን ትጠይቀኛለህ? ለእነርሱ የተናገርሁትን የሰሙትን ጠይቅ፤ እነሆ፥ እነዚህ እኔ የነገርሁትን ያውቃሉ” አለው። ይህንም ሲል በዚያ ቆሞ የነበረው ከሎሌዎች አንዱ፦ “ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን?” ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። ኢየሱስም መልሶ፦ “ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክር፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ሰለ ምን ትመታኛለህ?” አለው። ስለዚህ ሐና እንደ ታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ሰደደው። ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር። እንግዲህ፦ “አንተ ደግሞ ከደቀ መዛሙርቱ አይደለህምን?” አሉት። እርሱም፦ “አይደለሁም” ብሎ ካደ። ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ዘመድ የሆነ ከሊቀ ካህናቱ ባሮች አንዱ፦ “በአትክልቱ ከእርሱ ጋር እኔ አይቼህ አልነበረምን?” አለው። ጴጥሮስም እንደ ገና ካደ፥ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። ኢየስስንም ከቀያፋ ወደ ገዡ ግቢ ወሰዱት፤ ማለዳም ነበረ፤ እነርሱም የፋሲካ በግ ይበሉ ዘንድ እንጂ እንዳይረክሱ ወደ ገዡ ግቢ አልገቡም። ስለዚህ ጲላጦስ ወደ ውጭ ወደ እነርሱ ወጥቶ፦ “ይህን ሰው ስለ ምን ትከሱታላችሁ” አላቸው። እነርሱም መልሰው፦ “ይህስ ክፉ አድራጊ ባይሆን ወደ አንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር” አሉት። ጴላጦስም፦ “እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት” አላቸው። አይሁድም፦ “ለእኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም” አሉት፤ ኢየሱስ በምን ዓይነት ሞት ሊሞት እንዳለው ሲያመለክት የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ጲላጦስም እንደ ገና ወገ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ፦ “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ “አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህን?” አለው። ጲላጦስ መልሶ፦ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል?” አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” አለው። ጲላጦስም፦ “እንግዲያ ንጉሥ ነህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል” አለው። ጲላጦስ፦ “እውነት ምንድር ነው?” አለው። ይህንም ብሎ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጥቶ፦ “እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትም። ነገር ግን በፋሲካ አንድ ልፈታላችሁ ልማድ አላችሁ፤ እንግዲህ የአይሁድን ንጉሥ ልፈታላችሁ ትወዳላችሁን?” አላቸው። ሁሉም ደግመው፦ በርባንን እንጂ ይህን አይደለም እያሉ ጮኹ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ።
ዮሐንስ 18:1-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቄድሮን ሸለቆ ማዶ ሄደ፤ እዚያ ወደነበረውም የአትክልት ቦታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ገባ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እዚያ ቦታ ዘወትር ይሰበሰቡ ስለ ነበር አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ያን ቦታ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ይሁዳ አንድ የወታደሮች ጭፍራ፥ እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩትን የዘብ ኀላፊዎችን አስከትሎ ወደዚያ ቦታ መጣ፤ እነርሱም ፋኖስና ችቦ፥ የጦር መሣሪያም ይዘው ነበር። ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወደ እነርሱ ወጣ ብሎ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ እንፈልጋለን” አሉት። እርሱም “እኔ ነኝ!” አላቸው። አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። ኢየሱስ “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈገፈጉና በምድር ላይ ወደቁ። ኢየሱስም “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ሲል እንደገና ጠየቃቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ እንፈልጋለን” አሉ። እርሱም “እኔ ነኝ ብዬአችኋለሁ፤ እንግዲህ የምትፈልጉት እኔን ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አለ። ይህም የሆነው፥ “አባት ሆይ፥ ከሰጠኸኝ ሰዎች አንዱን እንኳ አላጠፋሁም” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው። ስምዖን ጴጥሮስ ሰይፍ ይዞ ስለ ነበረ መዘዘና የካህናት አለቃውን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የአገልጋዩም ስም “ማልኮስ” ይባል ነበር። ኢየሱስ ግን ጴጥሮስን፥ “ሰይፍህን ወደ አፎቱ ክተተው፤ አብ የሰጠኝን የመከራ ጽዋ የማልጠጣው ይመስልሃልን?” አለው። ከዚህ በኋላ ወታደሮቹና አዛዣቸው፥ የአይሁድ የዘብ ኀላፊዎችም ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። በመጀመሪያ ወደ ሐና ወሰዱት፤ ሐና በዚያ ዓመት የካህናት አለቃ ለነበረው ለቀያፋ ዐማቱ ነበር። ቀያፋ “አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት የተሻለ ነው” ሲል የአይሁድ ባለሥልጣኖችን የመከረ ነው። ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉት፤ ያ ሌላው ደቀ መዝሙር በካህናት አለቃው ዘንድ የታወቀ ነበር፤ ስለዚህ ከኢየሱስ ጋር ወደ ካህናት አለቃው ግቢ ገባ፤ ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ በካህናት አለቃው የታወቀው ደቀ መዝሙር መጣና ለበረኛይቱ ልጃገረድ ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው፤ በረኛይቱም ልጃገረድ ጴጥሮስን “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱ ግን “አይደለሁም” አለ። ጊዜው ብርድ ስለ ነበረ አገልጋዮቹና የዘብ ኀላፊዎች የከሰል እሳት አንድደው ቆመው ይሞቁ ነበር፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቃው ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ለሰው ሁሉ በግልጥ ተናገርኩ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኲራብም ሆነ በቤተ መቅደስ፥ ዘወትር አስተማርኩ፤ በስውር የተናገርኩት ምንም ነገር የለም፤ ታዲያ፥ ስለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? ስናገራቸው የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ የተናገርኩትን እነርሱ ያውቃሉ።” ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ እዚያ ቆመው ከነበሩት የዘብ ኀላፊዎች አንዱ፥ “ለካህናት አለቃው የምትመልሰው እንዲህ ነውን?” ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። ኢየሱስም “ክፉ ቃል ተናግሬ እንደ ሆነ ክፉ መናገሬን መስክር፤ የተናገርኩት ትክክል ከሆነ ግን ስለምን ትመታኛለህ?” አለው። ከዚህ በኋላ ሐና፥ ኢየሱስን እንደ ታሰረ ወደ ካህናት አለቃው ወደ ቀያፋ ሰደደው። የዚያን ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር፤ ሌሎች ሰዎችም “አንተስ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አሉት። እርሱም “አይደለሁም” ብሎ ካደ። ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመዱ የሆነው ከካህናት አለቃው ሎሌዎች አንዱ “በአትክልቱ ቦታ ከእነርሱ ጋር አይቼህ አልነበረምን?” አለው። ጴጥሮስም እንደገና ካደ፤ ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስን ከቀያፋ ቤት ወደ አገረ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ ጊዜውም ጠዋት ማለዳ ነበር፤ አይሁድ ለፋሲካ በዓል የሚታረደውን በግ መብላት ስለ ነበረባቸው እንዳይረክሱ በማለት ወደ አገረ ገዢው ግቢ ውስጥ አልገቡም። ስለዚህ ጲላጦስ ወደ እነርሱ ወጣና “በዚህ ሰው ላይ ያቀረባችሁት ክስ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ይህ ሰው ክፉ አድራጊ ባይሆን ኖሮ ለአንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር” ሲሉ መለሱለት። ጲላጦስም “እናንተ ራሳችሁ ወስዳችሁ በሕጋችሁ መሠረት ፍረዱበት” አላቸው። አይሁድም “እኛ ሰውን ለመግደል አልተፈቀደልንም” አሉት። ይህም የሆነው ኢየሱስ በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው። ጲላጦስ እንደገና ወደ ግቢው ተመልሶ ገባ፤ ኢየሱስንም ጠርቶ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስ “አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን? ወይስ ሌሎች ይህን ስለ እኔ ነግረውሃል?” አለው። ጲላጦስም “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? አንተን ለእኔ አሳልፈው የሰጡህ ወገኖችህና የካህናት አለቆች ናቸው፤ ምንድን ነው ያደረግኸው?” አለው። ኢየሱስ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴ ከዚህ ዓለም ብትሆን ኖሮ በአይሁድ ባለሥልጣኖች እጅ እንዳልወድቅ ሎሌዎቼ በተዋጉልኝ ነበር፤ መንግሥቴ ግን ከዚህ ዓለም አይደለችም” ሲል መለሰ። ጲላጦስም “ታዲያ፥ አንተ ንጉሥ ነኻ?” አለው። ኢየሱስም “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንኩ አንተ ትላለህ፤ እኔ የተወለድኩትና ወደ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ልመሰክር ነው፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ቃሌን ይሰማል” ሲል መለሰ። ጲላጦስም “እውነት ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ። ከዚህ በኋላ ጲላጦስ እንደገና ወደ አይሁድ ወጣና እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም፤ ነገር ግን እንደ ልማዳችሁ በፋሲካ በዓል ሁልጊዜ አንድ እስረኛ እፈታላችኋለሁ፤ ስለዚህ የአይሁድን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?” እነርሱ ግን “በርባንን ፍታልን እንጂ ይህን አይደለም!” እያሉ ጮኹ። በርባን ግን ወንበዴ ነበር።
ዮሐንስ 18:1-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስም ይህን ብሎ አትክልት ወዳለበት ስፍራ ወደ ቄድሮን ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ እርሱም ደቀ መዛሙርቱም በዚያ ገቡ። ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ ብዙ ጊዜ ወደዚያ ስለ ተሰበሰቡ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ስፍራውን ያውቅ ነበር። ስለዚህ ይሁዳ ወታደሮችን፥ እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና፥ በጦር መሣርያም ታጅቦ ወደዚያ መጣ። ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት። እርሱም “እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። ኢየሱስም “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመሬት ላይ ወደቁ። ዳግመኛ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስ መልሶ “እኔ ነኝ፤ አልኋችሁ፤ እንግዲህ እኔን ከሆነ የምትፈልጉት እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አለ፤ ይህም “ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንዱን እንኳን አላጠፋሁም” ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ስምዖን ጴጥሮስም ሰይፍ ይዞ ስለ ነበር መዘዘውና የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የአገልጋዩም ስም ማልኮስ ነበረ። ኢየሱስም ጴጥሮስን “ሰይፍህን ወደ ሰገባው ክተተው፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ ላልጠጣ ነውን?” አለው። እንግዲህ ወታደሮቹና አዛዣቸው፥ የአይሁድም ሎሌዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት፤ አስቀድመውም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና። ቀያፋም “ስለ ሕዝቡ ሲባል አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል” ሲል አይሁድን የመከራቸው ነበረ። ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀመዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀመዝሙር በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፤ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤ ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ ቆሞ ነበር። በሊቀ ካህናቱም ዘንድ የታወቀው ሌላው ደቀመዝሙር ወጣ፤ ለበረኛይቱም ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው። በር ጠባቂ አገልጋይቱም ጴጥሮስን “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱ “አይደለሁም” አለ። ይበርድ ነበረና አገልጋዮችና ሎሌዎች የከሰል እሳት አንድደው ቆመው ይሞቁ ነበር፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። ሊቀ ካህናቱም ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየሱስም መልሶ “እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ ሁልጊዜ አስተማርሁ፤ በስውርም ምንም አልተናገርሁም። ስለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? ስናገር የሰሙኝን ጠይቅ፤ እነሆ፥ እነርሱ እኔ የተናገርሁትን ያውቃሉ፤” አለው። ይህንን ባለ ጊዜ በዚያ ቆመው ከነበሩት ሎሌዎች አንዱ “ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን?” ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። ኢየሱስም መልሶ “ክፉ ተናግሬ እንደሆነ ስለ ክፉ መስክርብኝ፤ መልካም ተናግሬ እንደሆን ግን ስለምን ትመታኛለህ?” አለው። ሐናም እንደታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው። ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር። “አንተስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አይደለህምን?” አሉት። እርሱም “አይደለሁም፤” ብሎ ካደ። ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮች መካከል አንዱ፥ ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመድ፥ “በአትክልቱ ስፍራ ከእርሱ ጋር አይቼህ አልነበረምን?” አለው። ጴጥሮስም በድጋሚ ካደ፤ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። ኢየሱስንም ከቀያፋ ወደ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ ማለዳም ነበረ፤ እነርሱም እንዳይረክሱ፥ ይልቁንም የፋሲካን በግ እንዲበሉ በማለት ወደ ገዢው ግቢ አልገቡም። ስለዚህም ጲላጦስ ወደ ውጭ፥ ወደ እነርሱ ወጥቶ “በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ምን ዓይነት ክስ ነው አላቸው?” አላቸው። እነርሱም መልሰው “ይህ ሰው ክፉ አድራጊ ባይሆን ለአንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር” አሉት። ጲላጦስም “እናንተ ወስዳችሁ በሕጋችሁ ፍረዱበት” አላቸው። አይሁድም “እኛስ ማንንም ለመግደል አልተፈቀደልንም፤” አሉት፤ ይህም ኢየሱስ በምን ዓይነት ሞት እንደሚሞት ሲያመለክት የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነብር። ጲላጦስም እንደገና ወደ ገዢው ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን? ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህ?” አለው። ጲላጦስ መልሶ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴ ከዚህ ዓለም ብትሆን ኖሮ፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ ነገር ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” አለው። ጲላጦስም “እንግዲያውስ ንጉሥ ነህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “እኔ ንጉሥ እንደሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ተወልጃለሁ፤ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል” አለው። ጲላጦስ “እውነት ምንድነው?” አለው። ይህንንም ብሎ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጣና “እኔስ አንዲት በደል እንኳን አላገኘሁበትም። ነገር ግን በፋሲካ አንድ ሰው እንድፈታላችሁ ልማድ ሆኖአል፤ የአይሁድን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?” አላቸው። ሁሉም በድጋሚ “በርባንን እንጂ ይህን ሰው አይደለም” እያሉ ጮኹ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ።