ዮሐንስ 17:1-26

ዮሐንስ 17:1-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ይህን ነገር ተና​ግሮ ዐይ​ኖ​ቹን ወደ ሰማይ አነ​ሣና እን​ዲህ አለ፥ “አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደር​ሶ​አ​ልና ልጅህ ያከ​ብ​ርህ ዘንድ ልጅ​ህን አክ​ብ​ረው፤ ሥጋ በለ​በ​ሰው ሁሉ ላይ ሥል​ጣ​ንን እንደ ሰጠ​ኸው መጠን ለሰ​ጠ​ኸው ሁሉ የዘ​ለ​ዓ​ለም ሕይ​ወ​ትን ይሰ​ጣ​ቸው ዘንድ። ብቻ​ህን እው​ነ​ተኛ አም​ላክ የሆ​ንህ አን​ተን፥ የላ​ክ​ኸ​ው​ንም ኢየ​ሱስ ክር​ስ​ቶ​ስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘ​ለ​ዓ​ለም ሕይ​ወት ናት። እኔ ልሠ​ራው የሰ​ጠ​ኸ​ኝን ሥራ ፈጽሜ በም​ድር ላይ አከ​በ​ር​ሁህ። አሁ​ንም አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይ​ፈ​ጠር ከአ​ንተ ጋር በነ​በ​ረኝ ክብር በአ​ንተ ዘንድ አክ​ብ​ረኝ። “ከዓ​ለም ለይ​ተህ ለሰ​ጠ​ኸኝ ሰዎች ስም​ህን ገለ​ጥሁ፤ ያንተ ነበሩ፤ እነ​ር​ሱ​ንም ለእኔ ሰጥ​ተ​ኸ​ኛል፤ ቃል​ህ​ንም ጠበቁ። የሰ​ጠ​ኸ​ኝም ሁሉ ከአ​ንተ እንደ ሆነ ዛሬ ዐወቁ። የሰ​ጠ​ኽ​ኝን ቃል ሰጥ​ቻ​ቸ​ዋ​ለ​ሁና፤ እነ​ር​ሱም ተቀ​ብ​ለው ከአ​ንተ እንደ ወጣሁ በእ​ው​ነት ዐወቁ፤ አን​ተም እንደ ላክ​ኸኝ አመኑ። እኔ ስለ እነ​ርሱ እለ​ም​ና​ለሁ፤ የም​ለ​ም​ንህ ስለ ዓለም አይ​ደ​ለም፤ ስለ ሰጠ​ኸኝ ነው እንጂ፤ ያንተ ናቸ​ውና። የእ​ኔም የሆነ ሁሉ የአ​ንተ ነው፤ የአ​ን​ተም የሆነ የእኔ ነው፤ እኔም በእ​ነ​ርሱ ከብ​ሬ​አ​ለሁ። እን​ግ​ዲህ በዓ​ለም አል​ኖ​ርም፤ እነ​ርሱ ግን በዓ​ለም ይኖ​ራሉ፤ እኔም ወደ አንተ እመ​ጣ​ለሁ፤ ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነ​ዚ​ህን የሰ​ጠ​ኸ​ኝን እንደ እኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ በስ​ምህ ጠብ​ቃ​ቸው፤ እኔ በዓ​ለም ከእ​ነ​ርሱ ጋር ሳለሁ ግን የሰ​ጠ​ኸ​ኝን በስ​ምህ እጠ​ብ​ቃ​ቸው ነበር፤ ጠበ​ቅ​ኋ​ቸ​ውም፤ የመ​ጽ​ሐ​ፉም ቃል ይፈ​ጸም ዘንድ ከጥ​ፋት ልጅ በቀር ከእ​ነ​ርሱ አንድ ስን​ኳን አል​ጠ​ፋም። አሁን ግን ወደ አንተ እመ​ጣ​ለሁ፤ በእ​ነ​ር​ሱም ደስ​ታዬ ፍጹም ይሆን ዘንድ ይህን በዓ​ለም እና​ገ​ራ​ለሁ። እኔ ቃል​ህን ሰጠ​ኋ​ቸው፤ ዓለም ግን ጠላ​ቸው፤ እኔ ከዓ​ለም እን​ዳ​ይ​ደ​ለሁ እነ​ርሱ ከዓ​ለም አይ​ደ​ሉ​ምና። ከክፉ ነገር እን​ድ​ት​ጠ​ብ​ቃ​ቸው ነው እንጂ ከዓ​ለም እን​ድ​ት​ለ​ያ​ቸው አል​ለ​ም​ንም። እኔ ከዓ​ለም እን​ዳ​ይ​ደ​ለሁ ከዓ​ለም አይ​ደ​ሉ​ምና። በእ​ው​ነ​ትህ ቀድ​ሳ​ቸው፤ ቃልህ እው​ነት ነውና። አንተ እኔን ወደ ዓለም እንደ ላክ​ኸኝ እኔም እነ​ር​ሱን ወደ ዓለም ላክ​ኋ​ቸው። እነ​ር​ሱም በእ​ው​ነት ቅዱ​ሳን ይሆኑ ዘንድ ስለ እነ​ርሱ እኔ ራሴን እቀ​ድ​ሳ​ለሁ። “የም​ለ​ም​ን​ህም ስለ እነ​ዚህ ብቻ አይ​ደ​ለም፤ በቃ​ላ​ቸው ስለ​ሚ​ያ​ም​ኑ​ብ​ኝም ነው እንጂ፤ ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ አንተ አብ በእኔ እን​ዳ​ለህ፥ እኔም በአ​ንተ እን​ዳ​ለሁ፥ እነ​ር​ሱም እንደ እኛ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ አን​ተም እንደ ላክ​ኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ። እኔም የሰ​ጠ​ኸ​ኝን ክብር ሰጠ​ኋ​ቸው፤ እኛ አንድ እን​ደ​ሆን እነ​ር​ሱም እንደ እኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ። እኔ በእ​ነ​ርሱ እኖ​ራ​ለሁ፤ አን​ተም በእኔ፤ በአ​ንድ ፍጹ​ማን ይሆኑ ዘንድ፤ አን​ተም እንደ ላክ​ኸ​ኝና እንደ ወደ​ድ​ኸኝ እኔም እነ​ር​ሱን እንደ ወደ​ድ​ኋ​ቸው። አባት ሆይ፥ የሰ​ጠ​ኸኝ እነ​ዚህ እኔ ባለ​ሁ​በት አብ​ረ​ውኝ ይኖሩ ዘን​ድና የሰ​ጠ​ኸ​ኝን ክብ​ሬን ያዩ ዘንድ እወ​ድ​ዳ​ለሁ፤ ዓለም ሳይ​ፈ​ጠር ወድ​ደ​ኸ​ኛ​ልና። ጻድቅ አባት ሆይ፥ ዓለም አላ​ወ​ቀ​ህም፤ እኔ ግን ዐወ​ቅ​ሁህ፤ እነ​ዚ​ህም አንተ እንደ ላክ​ኸኝ ዐወቁ። እኔን የወ​ደ​ድ​ህ​በት ፍቅር በእ​ነ​ርሱ ይኖር ዘንድ፥ እኔም በእ​ነ​ርሱ እኖር ዘንድ ስም​ህን ነገ​ር​ኋ​ቸው፤ ደግ​ሞም እነ​ግ​ራ​ቸ​ዋ​ለሁ፤”

ዮሐንስ 17:1-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “አባት ሆይ፤ ጊዜው ደርሷል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤ ከአንተ ለተቀበላቸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት እንዲሰጥ፣ በሰው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥተኸዋልና። እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። የሰጠኸኝን ሥራ በመፈጸም በምድር አከበርሁህ። እንግዲህ አባት ሆይ፤ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋራ በነበረኝ ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ። “ለእነዚህ ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። የአንተ ነበሩ ለእኔ ሰጠኸኝ፤ እነርሱም ቃልህን ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ አሁን ዐውቀዋል፤ ምክንያቱም የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸው ተቀብለዋል፤ እኔም ከአንተ እንደ ወጣሁ በርግጥ ዐውቀዋል፤ አንተ እንደ ላክኸኝም አምነዋል፤ እነርሱ የአንተ ስለ ሆኑ እጸልይላቸዋለሁ፤ ለሰጠኸኝና የአንተ ለሆኑት እንጂ ለዓለም አልጸልይም። የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም ሁሉ የእኔ ነው፤ በእነርሱም ከብሬአለሁ። ከእንግዲህ እኔ በዓለም አልቈይም፤ እነርሱ ግን በዓለም ውስጥ ናቸው፤ እኔም ወደ አንተ መምጣቴ ነው። ቅዱስ አባት ሆይ፤ እኛ አንድ እንደ ሆንን፣ እነርሱም አንድ እንዲሆኑ በሰጠኸኝ በስምህ ጠብቃቸው። እኔ ከእነርሱ ጋራ ሳለሁ፣ በሰጠኸኝ ስም ከለልኋቸው፤ ጠበቅኋቸውም፤ የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ከአንዱ ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም። “አሁን ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ ነገር ግን ደስታዬ በእነርሱ ዘንድ የተሟላ እንዲሆን፣ አሁን በዓለም እያለሁ ይህን እናገራለሁ። ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ፣ እነርሱም ከዓለም ባለመሆናቸው ዓለም ጠልቷቸዋል። የምለምንህም ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ፣ ከዓለም እንድታወጣቸው አይደለም። እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ፣ እነርሱም ከዓለም አይደሉም። ቃልህ እውነት ነው፤ በእውነትህ ቀድሳቸው። አንተ ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እኔም ወደ ዓለም ልኬአቸዋለሁ። እነርሱ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ፣ ራሴን ስለ እነርሱ ቀድሻለሁ።” “የእነርሱን ትምህርት ተቀብለው በእኔ ለሚያምኑ ጭምር እንጂ ለእነዚህ ብቻ አልጸልይም፤ ይህም፣ አባት ሆይ፤ አንተ በእኔ፣ እኔም በአንተ እንዳለሁ ሁሉም አንድ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም አንተ እኔን እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፣ እነርሱም በእኛ እንዲሆኑ ነው። እኛ አንድ እንደ ሆንን እነርሱም አንድ እንዲሆኑ፣ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ። ይህም እኔ በእነርሱ፣ አንተም በእኔ መሆንህ ነው። አንተ እንደ ላክኸኝና እኔን በወደድኸኝ መጠን እነርሱንም እንደ ወደድሃቸው ዓለም ያውቅ ዘንድ፣ አንድነታቸው ፍጹም ይሁን። “አባት ሆይ፤ እነዚህ የሰጠኸኝ እኔ ባለሁበት እንዲሆኑ፣ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝንም ክብሬን እንዲያዩ እፈልጋለሁ። “ጻድቅ አባት ሆይ፤ ዓለም ባያውቅህም፣ እኔ ዐውቅሃለሁ፤ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ ያውቃሉ። ለእኔ ያለህ ፍቅር በእነርሱ እንዲሆን፣ እኔም በእነርሱ እንድሆን፣ ስምህን እንዲያወቁ አድርጌአለሁ፤ እንዲያውቁትም አደርጋለሁ።”

ዮሐንስ 17:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ ዓኖቹን አነሣና እንዲህ አለ፦ “አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፥ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው። እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤ አሁንም፥ አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ። ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ አሁን ያውቃሉ፤ የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፥ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ። እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ፤ ስለ ዓለም አልለምንም ስለ ሰጠኸኝ እንጂ፤ የአንተ ናቸውና፤ የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው የአንተውም የእኔ ነው፤ እኔም ስለ እነርሱ ከብሬአለሁ። ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፥ እነርሱም በዓለም ናቸው፥ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው። ከእነርሱ ጋር በዓለም ሳለሁ የሰጠኸኝን በስምህ እኔ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም መጽሐፉም እንዲፈጸም ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልተፋም። አሁንም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በእነርሱም ዘንድ ደስታዬ የተፈጸመ እንዲሆንላቸው ይህን በዓለም እናገራለሁ። እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም። በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እንዲሁ እኔ ወደ ዓለም ላክኋቸው፤ እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ። ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ። እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ። ጻድቅ አባት ሆይ፥ ዓለም አላወቀህም፥ እኔ ግን አወቅሁህ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ አወቁ፤ እኔንም የወደድህበት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፥ ስምህም አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ።”

ዮሐንስ 17:1-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ ቀና ብሎ ወደ ሰማይ እያየ እንዲህ አለ፦ “አባት ሆይ! እነሆ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ እንዲያከብርህ ልጅህን አክብረው፤ የምታከብረውም ለሰጠኸው ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲሰጥ በሰዎች ሁሉ ላይ ሥልጣን ስለ ሰጠኸው ነው። የዘለዓለም ሕይወትም አንተ ብቻ እውነተኛውን አምላክና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው። እኔ የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርኩህ። አባት ሆይ! ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር አሁንም በአንተ ዘንድ አክብረኝ። “ከዓለም ውስጥ መርጠህ ለሰጠኸኝ ሰዎች የአንተን ማንነት ገለጥኩላቸው፤ እነርሱ የአንተ ነበሩ፤ አንተ እነርሱን ለእኔ ሰጠኸኝ፤ እነርሱም ቃልህን ጠብቀዋል፤ የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ እነርሱ አሁን ዐውቀዋል። የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁ፤ እነርሱም ተቀብለውታል፤ ከአንተ ዘንድ መጥቼ መምጣቴንም በእውነት ዐውቀዋል፤ አንተ እንደ ላክኸኝም አምነዋል። “እኔ የምጸልየው ለእነርሱ ነው፤ እነዚህ የሰጠኸኝ የአንተ ስለ ሆኑ ለእነርሱ እጸልያለሁ፤ ለዓለም አልጸልይም። የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው የአንተም የሆነው የእኔ ነው፤ እኔም በእነርሱ እከብራለሁ። እኔ ከእንግዲህ ወዲህ በዓለም ላይ አልኖርም፤ እነርሱ ግን በዓለም ናቸው። እኔ ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህ የሰጠኸኝ እንደእኛ አንድ እንዲሆኑ ለእኔ በሰጠኸኝ ስምህ ጠብቃቸው። ይላሉ” እኔ አብሬአቸው በነበርኩ ጊዜ በሰጠኸኝ ስምህ ጠብቄአቸዋለሁ፤ እኔ ጠበቅኋቸው፤ ስለዚህ የቅዱስ መጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ከዚያ ከጥፋት ልጅ በቀር ከቶ ከእነርሱ ማንም አልጠፋም። አሁን እኔ ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ በዓለም ላይ ሳለሁ ይህን የምናገረው ደስታዬ በእነርሱ ዘንድ ፍጹም እንዲሆን ነው። እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነርሱም ከዓለም አይደሉም፤ ስለዚህ ዓለም ጠላቸው። ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም ውጪ እንድትወስዳቸው አለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነርሱም ከዓለም አይደሉም። በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። አንተ እኔን ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እኔም እነርሱን ወደ ዓለም ላክኋቸው። እነርሱ በእውነት ቅዱሳን እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ ቅዱስ አደርጋለሁ። “በእነርሱ ቃል አማካይነት በእኔ ስለሚያምኑትም እለምናለሁ እንጂ ለእነርሱ ብቻ አለምንም። እኔም የምለምነው ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ እንዲሁም አባት ሆይ! አንተ በእኔ እንዳለህ፥ እኔም በአንተ እንዳለሁ፥ እነርሱም በእኛ እንዲኖሩ ነው፤ አንተ እንደ ላክኸኝም ዓለም እንዲያምን ነው። እኛ አንድ እንደ ሆንን እነርሱም አንድ እንዲሆኑ ለእኔ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ። እኔ የምለምነው እኔ በእነርሱ አንተም በእኔ እንደ ሆንክ እነርሱም በፍጹም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ እንዲሁም እኔን እንደ ላክኸኝና እኔን በወደድከኝ መጠን እነርሱንም እንደ ወደድካቸው ዓለም እንዲያውቅ ነው። “አባት ሆይ! ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድከኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እነዚህ አንተ የሰጠኸኝም እኔ ባለሁበት ከእኔ ጋር እንዲኖሩ እወዳለሁ። ጻድቅ አባት ሆይ! ዓለም አላወቀህም፤ እኔ ግን ዐውቅሃለሁ፤ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ ዐውቀዋል። አንተ እኔን የወደድክበት ፍቅር በእነርሱ ላይ እንዲሆንና እኔም በእነርሱ እንድሆን እነርሱ አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ፤ ደግሞም እንዲያውቁ አደርጋቸዋለሁ።”

ዮሐንስ 17:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ ዐይኖቹን አነሣና እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ! ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤ ይህም በሥጋ ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘለዓለምን ሕይወት እንዲሰጣቸው ነው። የዘለዓለም ሕይወትም ይህች ናት፤ እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንከውን አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ነው። እኔ እንዳደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርሁህ፤ አሁንም፥ አባት ሆይ! ዓለም ሳይፈጠር በፊት በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር፥ በራስህ ዘንድ አንተ አክብረኝ። “ከዓለም ወስጥ ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ፤ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደሆነ አሁን ያውቃሉ፤ የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፤ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፤ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ። እኔ ስለ እነርሱ እለምናለሁ፤ ስለ ሰጠኸኝ ስለ እነርሱ እንጂ ስለ ዓለም አልለምንም፤ እነርሱ የአንተ ናቸውና፤ የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም የእኔ ነው፤ እኔም በእነርሱ ከብሬአለሁ። ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፤ እነርሱ ግን በዓለም ናቸው፤ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ! እነዚህን የሰጠኸኝ እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው። ከእነርሱ ጋር በዓለም ሳለሁ የሰጠኸኝን እኔ በስምህ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም፤ የመጽሐፉም ቃል እንዲፈጸም ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም። አሁንም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በእነርሱም ዘንድ ደስታዬ የተፈጸመ እንዲሆንላቸው ይህን በዓለም እናገራለሁ። እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ እነርሱም ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ እነርሱም ከዓለም አይደሉም። በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ ሁሉ እኔም ወደ ዓለም ላክኋቸው፤ እነርሱም ደግሞ በእውነትህ የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ።” በእነርሱ ቃል አማካይነት በእኔ ስለሚያምኑትም ጭምር እንጂ ስለ እነርሱ ብቻ አልለምንም፤ ይህም ሁሉም አንድ እንዲሆኑ፥ አንተም፥ አባት ሆይ! በእኔ እንዳለህና እኔም በአንተ እንዳለሁ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ እንዲሆኑ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ ዓለም እንዲያምን ነው። እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ፤ ይህም እኔ በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በፍጹም አንድ እንዲሆኑ፥ እንዲሁም አንተ እንደ ላክኸኝና በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ዓለም እንዲያውቅ ነው። አባት ሆይ! ዓለም ሳይፈጠር በፊት ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ፥ የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ እኔ ባለሁበት ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ። ጻድቅ አባት ሆይ! ዓለም አላወቀህም፤ እኔ ግን ዐውቅሃለሁ፤ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ አወቁ፤ እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን፥ እኔም በእነርሱ እንድሆን፥ ስምህን አስታወቅኋቸው፤ አስታውቃቸውማለሁ።