ዮሐንስ 14:1-20
ዮሐንስ 14:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ልባችሁ አይደንግጥ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያና ማረፊያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ ቦታ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ እላችሁ ነበር። ከሄድሁና ቦታ ካዘጋጀሁላችሁም ዳግመኛ እመጣለሁ፤ እናንተም እኔ በአለሁበት ትኖሩ ዘንድ ወደ እኔ እወስዳችኋለሁ። ወዴትም እንደምሄድ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ መንገዱንም ታውቃላችሁ።” ቶማስም፥ “ጌታዬ ሆይ፥ የምትሄድበትን የማናውቅ እንግዲህ መንገዱን እንዴት እናውቃለን?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው፥ “የእውነትና የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔንስ ብታውቁኝ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን አውቃችሁታል፤ አይታችሁትማል።” ፊልጶስም፥ “ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው፥ “ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን አብሬአችሁ ስኖር አታወቀኝምን? እኔን ያየ አብን አየ፤ እንግዲህ እንዴት አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁ ይህ ቃልም ከራሴ የተናገርሁት አይደለም፤ በእኔ ያለ አብ እርሱ ይህን ሥራ ይሠራዋል እንጂ። እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤ ያለዚያም ስለ ሥራዬ እመኑኝ። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ሥራ እርሱም ይሠራል፤ ከዚያም የሚበልጥ ይሠራል፤ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና። አብ በወልድ ይከብር ዘንድ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ። በስሜ የምትለምኑት ነገር ቢኖር ያን አደርግላችኋለሁ። “ከወደዳችሁኝስ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምነዋለሁ፤ እርሱም ለዘለዓለም ከእናንተ ጋር ይኖር ዘንድ ሌላ አጽናኝ ይልክላችኋል። እርሱም ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ እናንተ ግን ታውቁታላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ ይኖራልና፤ ያድርባችሁማልና። “የሙት ልጆች ትሆኑ ዘንድ አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ገና ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንግዲህ ወዲህም ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና፤ እናንተም ሕያዋን ትሆናላችሁ። እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ፥ እናንተም በእኔ፥ እኔም በእናንተ እንዳለሁ ያንጊዜ ታውቃላችሁ።
ዮሐንስ 14:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ልባችሁ አይጨነቅ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ ይህ ባይሆንማ ኖሮ እነግራችሁ ነበር፤ የምሄደውም ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው። ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋራ እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ። እኔ ወደምሄድበትም ስፍራ የሚያደርሰውን መንገድ ታውቃላችሁ።” ቶማስም፣ “ጌታ ሆይ፤ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም፤ ታዲያ፣ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር። ከአሁን ጀምሮ ግን ታውቁታላችሁ፤ አይታችሁታልም።” ፊልጶስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንተ ፊልጶስ! ይህን ያህል ጊዜ ከእናንተ ጋራ ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቷል፤ እንዴትስ፣ ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ፣ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? የምነግራችሁ ቃል ከራሴ አይደለም፤ ነገር ግን ሥራውን የሚሠራው በእኔ የሚኖረው አብ ነው። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ስነግራችሁ እመኑኝ፤ ሌላው ቢቀር ስለ ድንቅ ሥራዎቹ እንኳ እመኑ። እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ፣ ከእነዚህም የሚበልጥ ያደርጋል። አብ በወልድ እንዲከብር፣ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፤ ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትለምኑኝ፣ እኔ አደርገዋለሁ። “ብትወድዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ። እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋራ ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም። እናንተ ግን፣ ዐብሯችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስለሚሆን ታውቁታላችሁ። ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ዓለም ከቶ አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ። እኔ ሕያው ስለ ሆንሁ እናንተም ሕያዋን ትሆናላችሁ። እኔ በአባቴ እንዳለሁ፣ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ፣ እኔም ደግሞ በእናንተ እንዳለሁ በዚያ ቀን ትረዳላችሁ።
ዮሐንስ 14:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
“ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ። ወደምሄድበትም ታውቃላችሁ፥ መንገዱንም ታውቃላችሁ።” ቶማስም፦ “ጌታ ሆይ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን?” አለው። ኢየሱስም፦ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። አሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል” አለው። ፊልጶስ፦ “ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። ኢየሱስም አለው፦ “አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ፦ ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነገራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና አብም ስለ ወልድ እንዲከብር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ። “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ በዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ። “ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ገና ጥቂት ዘመን አለ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ። እኔ በአባቴ እንዳለሁ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ።
ዮሐንስ 14:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ልባችሁ አይጨነቅ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም እመኑ፤ በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ አለበለዚያ ግን ‘የምትኖሩበትን ስፍራ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ’ ባልኳችሁ ነበር። ሄጄ ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ እኔ ባለሁበት እንድትኖሩ እንደገና መጥቼ እወስዳችኋለሁ። እኔ የምሄድበትንም መንገድ ታውቃላችሁ።” ቶማስ “ጌታ ሆይ! ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም፤ ታዲያ፥ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “መንገድና እውነት ሕይወትም እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ማንም ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔን ዐውቃችሁኝ ቢሆን ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ታውቁታላችሁ፤ አይታችሁታልም።” ፊልጶስም “ጌታ ሆይ! አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ፊልጶስ ሆይ! ይህን ያኽል ጊዜ ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አየ፤ ታዲያ፥ አንተ ‘አብን አሳየን’ እንዴት ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? ለእናንተ የምናገረውን ቃል የምናገረው በራሴ ሥልጣን አይደለም፤ ነገር ግን ሥራውን ሁሉ የሚሠራው፥ በእኔ የሚኖረው አብ ነው። እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤ አለበለዚያ በሥራዎቼ ምክንያት እመኑኝ። እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም ከዚህ የበለጠ ይሠራል፤ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁ። አብ በወልድ ምክንያት እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ። ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።” “የምትወዱኝ ከሆነ ትእዛዜን ጠብቁ፤ እኔ አብን እለምነዋለሁ፤ እርሱም ለዘለዓለም ከእናንተ ጋር የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል። ይህም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም፤ እናንተ ግን፥ እርሱ ከእናንተ ጋር ስለ ሆነና በውስጣችሁም ስላለ ታውቁታላችሁ። “እናትና አባት እንደሌላቸው ልጆች ብቻችሁን አልተዋችሁም፤ ተመልሼ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ስለ ሆንኩ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፤ እኔ በአብ እንዳለሁ፥ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ፥ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ።
ዮሐንስ 14:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ ስፍራ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ እላችሁ ነበርን? ሄጄም ስፍራ ሳዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትኖሩ ዳግምኛ እመጣለሁ፤ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ። የምሄድበትንም መንገድ ታውቃላችሁ።” ቶማስም “ጌታ ሆይ! ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን?” አለው። ኢየሱስም “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ ማንም ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር። ከአሁንም ጀምሮ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል፤” አለው። ፊልጶስ “ጌታ ሆይ! አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። ኢየሱስም አለው “አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነገራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ ሥራውን ይሠራል። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ይህም ካልሆነ ስለ ሥራዎቹ ስትሉ እመኑኝ። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውንም ሥራ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፤ አብ በወልድ እንዲከብር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።” “የምትወዱኝ ከሆነ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ። እኔም አብን እለምናለሁ፤ ለዘለዓለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ምክንያቱም ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ነው። ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ስለሚኖር፥ በውስጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቁታላችሁ። “ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ገና ጥቂት ዘመን አለ፤ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና፤ እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ። እኔ በአባቴ እንዳለሁ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ።