ዮሐንስ 11:41-44
ዮሐንስ 11:41-44 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ድንጋዩንም አነሡ፤ ጌታችን ኢየሱስም ዐይኖቹን አቅንቶ እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ፥ ሰምተኸኛልና አመሰግንሃለሁ። እኔም ዘወትር እንደምትሰማኝ አውቃለሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ቆመው ስላሉት ሰዎች ይህን እናገራለሁ።” ይህንም ብሎ በታላቅ ቃል ጮኸና፥ “አልዓዛር፥ ና፤ ወደ ውጭ ውጣ” አለ። ሞቶ የነበረውም እንደ ተገነዘ፥ እጁንና እግሩንም እንደ ታሰረ፥ ፊቱም በሰበን እንደ ተጠቀለለ ወጣ፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እንግዲህስ ፍቱትና ተዉት ይሂድ” አላቸው።
ዮሐንስ 11:41-44 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ ድንጋዩን አነሡ። ኢየሱስም ወደ ላይ ተመልክቶ አንዲህ አለ፤ “አባት ሆይ፤ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፤ ይህን መናገሬ ግን በዚህ የቆሙ ሰዎች አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ ነው።” ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ በታላቅ ድምፅ፣ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” ብሎ ተጣራ። የሞተውም ሰው እጅና እግሩ በቀጭን ስስ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ፣ ፊቱም በሻሽ እንደ ተጠመጠመ ወጣ። ኢየሱስም “መግነዙን ፍቱለትና ይሂድ” አላቸው።
ዮሐንስ 11:41-44 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ፦ “አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ” አለ። ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ፦ “አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና” ብሎ ጮኸ። የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር። ኢየሱስም፦ “ፍቱትና ይሂድ ተዉት” አላቸው።
ዮሐንስ 11:41-44 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሰዎቹም ድንጋዩን አነሡት፤ ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ላይ ተመልክቶ፥ “አባት ሆይ! ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ይህን ያልኩት፥ እዚህ የቆሙት ሰዎች አንተ እንደ ላክኸኝ እንዲያምኑ ብዬ ነው” አለ። ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ “አልዓዛር! ና ውጣ!” ብሎ በታላቅ ድምፅ ተናገረ። ሟቹ አልዓዛርም እጆቹና እግሮቹ በመገነዣ እንደ ተገነዙ ከመቃብሩ ወጣ፤ ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር፤ ኢየሱስም “ፍቱትና ተዉት ይሂድ!” አላቸው።
ዮሐንስ 11:41-44 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዐይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ! ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ፤” ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ “አልዓዛር ሆይ! ና፥ ወደ ውጭ ውጣ፤” ብሎ ጮኸ። ሞቶ የነበረውም ሰው እጆቹና እግሮቹ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ። ኢየሱስም “ፍቱትና ይሂድ፤ ተዉት፤” አላቸው።