ዮሐንስ 10:1-8
ዮሐንስ 10:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች ስፍራ በበሩ የማይገባ፥ በሌላም በኩል የሚገባ ሌባ፥ ወንበዴም ነው። በበሩ የሚገባ ግን የበጎች ጠባቂ ነው። ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፤ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ አውጥቶም ያሰማራቸዋል። ሁሉንም አውጥቶ ባሰማራቸው ጊዜ በፊት በፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ይከተሉታል፤ ቃሉን ያውቃሉና። ሌላውን ግን ይሸሹታል እንጂ አይከተሉትም፤ የሌላውን ቃሉን አያውቁምና።” ጌታችን ኢየሱስም ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸውን አላወቁም። ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የበጎች በር እኔ ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ነገር ግን፤ በጎች አልሰሙአቸውም።
ዮሐንስ 10:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች ጕረኖ በበሩ ሳይሆን፣ በሌላ በኩል ዘልሎ የሚገባ ሌባና ነጣቂ ነው። በበሩ የሚገባ ግን እርሱ የበጎቹ እረኛ ነው፤ በር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱንም በጎች በየስማቸው እየጠራ ያወጣቸዋል። የራሱ የሆኑትንም ሁሉ ካወጣ በኋላ ፊት ፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። እንግዳ የሆነውን ግን ድምፁን ስለማያውቁ ከርሱ ይሸሻሉ እንጂ ፈጽሞ አይከተሉትም።” ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን ምን እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም። ስለዚህ ኢየሱስ ዳግም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የበጎች በር እኔ ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡት ሁሉ ሌቦችና ቀማኞች ነበሩ፤ በጎቹ ግን አልሰሟቸውም።
ዮሐንስ 10:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
“እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና።” ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነሩስ ግን የነገራቸው ምን እንደ ሆነ አላስተዋሉም። ኢየሱስም ደግሞ አላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም።
ዮሐንስ 10:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች በረት በበር ሳይሆን በሌላ በኩል የሚገባ ሰው ሌባና ወንበዴ ነው። በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ለእርሱ የበር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹ ድምፁን ይሰማሉ፤ እርሱም የራሱን በጎች በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ እየመራም ወደ ውጪ ያወጣቸዋል። የራሱን በጎች ካስወጣ በኋላም እፊት እፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። የሌላውን ድምፅ ግን ስለማያውቁ ከእርሱ ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉም።” ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የተናገረውን አላስተዋሉም። ስለዚህ ኢየሱስ እንደገና እንዲህ አላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የበጎች በር ነኝ፤ ከእኔ በፊት የመጡት ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ በጎቹ ግን አልሰሙአቸውም።
ዮሐንስ 10:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች በረት በበሩ ሳይሆን የማይገባ በሌላ መንገድ የሚገባ እርሱ ሌባና ወንበዴ ነው፤ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ለእርሱ በር ጠባቂው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፤ የእራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። የእራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፤ የሌሎቹን ድምፅ አያውቁምና።” ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸው ምን እንደሆነ አላስተዋሉም። ኢየሱስም ደግሞ አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የበጎች በር ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም።