ኤርምያስ 9:3-9

ኤርምያስ 9:3-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“ምላ​ሳ​ቸ​ውን ለሐ​ሰት እንደ ቀስት ገተሩ፤ በም​ድ​ርም በረቱ፤ ነገር ግን ለእ​ው​ነት አይ​ደ​ለም፤ ከክ​ፋት ወደ ክፋት ይሄ​ዳ​ሉና፥ እኔ​ንም አላ​ወ​ቁ​ምና፥” ይላል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር። ወን​ድ​ምም ሁሉ ያሰ​ና​ክ​ላ​ልና፥ ባል​ን​ጀ​ራም ሁሉ በጠ​ማ​ማ​ነት ይሄ​ዳ​ልና እና​ንተ ሁሉ ከባ​ል​ን​ጀ​ሮ​ቻ​ችሁ ተጠ​ን​ቀቁ፤ በወ​ን​ድ​ሞ​ቻ​ች​ሁም አት​ታ​መኑ። እያ​ን​ዳ​ንዱ በባ​ል​ን​ጀ​ራው ላይ ይሣ​ለ​ቃል በእ​ው​ነ​ትም አይ​ና​ገ​ርም፤ ሐሰት መና​ገ​ር​ንም ምላ​ሳ​ቸው ተም​ሮ​አል፤ በደሉ መመ​ለ​ስ​ንም እንቢ አሉ። አራ​ጣ​ንም በአ​ራጣ ላይ ይቀ​በ​ላሉ፤ ተን​ኰ​ልን በተ​ን​ኰል ላይ ይሠ​ራሉ፤ “እኔ​ንም ያው​ቁኝ ዘንድ እንቢ ብለ​ዋል፥” ይላል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር። ስለ​ዚህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፦ እነሆ፥ አቀ​ል​ጣ​ቸ​ዋ​ለሁ፤ እፈ​ት​ና​ቸ​ው​ማ​ለሁ፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ክፋት እን​ደ​ዚሁ አደ​ር​ጋ​ለ​ሁና። ምላ​ሳ​ቸው የተ​ሳለ ፍላጻ ነው፤ ንግ​ግ​ራ​ቸው ሽን​ገላ ነው፤ ለባ​ል​ን​ጀ​ራ​ቸው ሰላ​ምን ይና​ገ​ራሉ፤ በል​ባ​ቸው ግን ጥላ​ቻን ይይ​ዛሉ። በውኑ ስለ​ዚህ ነገር በመ​ቅ​ሠ​ፍት አል​ጐ​በ​ኝ​ምን? ይላል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፤ ነፍ​ሴስ እን​ደ​ዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አት​በ​ቀ​ል​ምን?

ኤርምያስ 9:3-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“ሐሰትን ለመናገር፣ ምላሳቸውን እንደ ቀስት ገተሩ፤ በእውነት ሳይሆን፣ በሐሰት በምድሪቱ ገነኑ፤ ከክፋት ወደ ክፋት ሄዱ፤ እኔንም አላወቁኝም፤” ይላል እግዚአብሔር። “እያንዳንዱ ወንድም አታላይ፣ ባልንጀራም ሁሉ ሐሜተኛ ስለ ሆነ፣ ወንድም ከወንድሙ ይጠንቀቅ፤ ባልንጀራም በጓደኛው አይታመን። ባልንጀራ ባልንጀራውን ያታልላል፤ እውነትን የሚናገር የለም፤ ሐሰትን ይናገሩ ዘንድ ምላሳቸውን አሠልጥነዋል፤ ኀጢአትንም በማድረግ ራሳቸውን አድክመዋል። መኖሪያህ በሽንገላ መካከል ነው፤ ከሽንገላቸውም የተነሣ ሊያውቁኝ አልፈቀዱም፤” ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ እንደ ብረት አነጥራቸዋለሁ፤ እፈትናቸዋለሁም፤ ስለ ሕዝቤ ኀጢአት፣ ከዚህ የተለየ ምን ማድረግ እችላለሁ? ምላሳቸው የሚገድል ቀስት ነው፤ በሽንገላ ይናገራል፤ ሁሉም ከባልንጀራው ጋራ በሰላም ይናገራል፤ በልቡ ግን ያደባበታል። ታዲያ ስለ እነዚህ ነገሮች ልቀጣቸው አይገባኝምን?” ይላል እግዚአብሔር፤ “እንደዚህ ዐይነቱንስ ሕዝብ፣ አልበቀልምን?”

ኤርምያስ 9:3-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ምላሳቸውን ስለ ሐሰት እንደ ቀስት ገተሩ፥ በምድር በረቱ ነገር ግን ለእውነት አይደለም፥ ከክፋት ወደ ክፋት ይሄዳሉና እኔንም አላወቁምና፥ ይላል እግዚአብሔር። ወንድምም ሁሉ ያሰናክላልና፥ ባልንጀራም ሁሉ ያማልና እናንተ ሁሉ ከባልንጀሮቻችሁ ተጠንቀቁ፥ በወንድሞቻችሁም አትታመኑ። ሰውም ሁሉ ባልንጀራውን ያታልላል በእውነትም አይናገርም፥ ሐሰትን መናገርንም ምላሳቸው ተምሮአል፥ ክፉንም ለማድረግ ይደክማሉ። ማደሪያህ በሽንገላ መካከል ነው፥ ከሽንገላም የተነሣ እኔን ያውቁኝ ዘንድ እንቢ ብለዋል፥ ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ አቀልጣቸዋለሁ እፈትናቸውማለሁ፥ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ክፋት ከዚህ ሌላ የማደርገው ምንድር ነው? ምላሳቸው የተሳለ ፍላጻ ነው፥ ሽንገላን ይናገራሉ ሰው ከባልንጀራው ጋር በሰላም ይናገራል፥ በልቡ ግን ያደባበታል። በውኑ ስለዚህ ነገር አልቀሥፍምን? ይላል እግዚአብሔር፥ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን?

ኤርምያስ 9:3-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እነርሱ በአንደበታቸው ሐሰት ለመናገር ዘወትር የተዘጋጁ ናቸው፤ ስለዚህም በምድሪቱ ላይ በእውነት ፈንታ ሐሰት ነግሦአል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤ ከአንዱ ኃጢአት ወደ ሌላው ኃጢአት ይተላለፋሉ፤ የእኔንም አምላክነት ዐውቀው አላከበሩኝም።” እያንዳንዱ ከባልንጀራው ተንኰል ይጠንቀቅ፤ ወንድሙን እንኳ ቢሆን ማመን የለበትም፤ ወንድም የተባለ ሁሉ (እንደ ያዕቆብ) አታላይ ሆኖአል፤ ወዳጅ የተባለም ሁሉ የባልንጀራውን ስም ያጠፋል። ሁሉም ባልንጀራውን በማሞኘት ያሳስታል፤ እውነት የሚናገርም የለም፤ አንደበታቸው ውሸት መናገርን እንዲለማመድ አድርገውታል፤ ኃጢአት በመሥራት ሰውነታቸውን ያደክማሉ። ግፍን በግፍ ላይ ማታለልንም በማታለል ላይ እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ “እኔም አምላካቸው መሆኔን ለመቀበል እምቢ ብለዋል” ይላል እግዚአብሔር። ከዚህም የተነሣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤን ለማጥራት እንደ ብረት እፈትናቸዋለሁ፤ ሕዝቤ ክፉ ነገር ስለ ፈጸሙ ይህን ከማድረግ በቀር ሌላ ምን አደርጋቸዋለሁ? አንደበታቸው ዘወትር ተንኰል ስለሚናገር፥ እንደ አደገኛ ፍላጻ ነው፤ እያንዳንዱ ባልንጀራውን በፍቅር ቃል ያነጋግረዋል፤ ነገር ግን በስውር ወጥመድ ይዘረጋበታል። ታዲያ በዚህ ሁሉ ነገር እነርሱን ልቀጣቸውና እንደነዚህ ያሉትንስ ሕዝብ ልበቀላቸው አይገባኝምን? እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

ኤርምያስ 9:3-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ምላሳቸውን ስለ ሐሰት እንደ ቀስት ገተሩ፤ በምድር በረቱ ነገር ግን ለእውነት አይደለም፤ ከክፋት ወደ ክፋት ይሄዳሉና፥ እኔንም አላወቁምና፥ ይላል ጌታ። ወንድምም ሁሉ ያሰናክላልና፥ ባልንጀራም ሁሉ ያማልና እናንተ ሁሉ ከባልንጀሮቻችሁ ተጠንቀቁ፥ በወንድሞቻችሁም አትታመኑ። ሰውም ሁሉ ባልንጀራውን ያታልላል በእውነትም አይናገሩም፤ ሐሰትን መናገርንም ምላሳቸው ተምሮአል፥ ክፉንም ለማድረግ ይደክማሉ። ማደሪያህ በሽንገላ መካከል ነው፥ ከሽንገላም የተነሣ እኔን ለማወቅ እንቢ ብለዋል፥ ይላል ጌታ። ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ አቀልጣቸዋለሁ እፈትናቸዋለሁም፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ክፋት ከዚህ ሌላ የማደርገው ምንድነው? ምላሳቸው የተሳለ ፍላጻ ነው፤ ሽንገላን ይናገራሉ፤ ሰው ከባልንጀራው ጋር በሰላም ይናገራል፥ በልቡ ግን ያደባበታል። በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀስፋቸውምን? ይላል ጌታ፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን?