ኤርምያስ 33:14-26
ኤርምያስ 33:14-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“እነሆ ስለ እስራኤል ቤትና ስለ ይሁዳ ቤት የሰጠሁትን መልካም የተስፋ ቃል የምፈጽምበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። በዚያም ዘመን በዚያም ጊዜ ለዳዊት የጽድቅን ቍጥቋጥ አበቅልለታለሁ፤ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር ያደርጋል። በዚያም ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ ኢየሩሳሌምም ተዘልላ ትቀመጣለች፤ የምትጠራበትም ስም፦ እግዚአብሔር ጽድቃችን ተብሎ ነው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከዳዊት ዘንድ አይታጣም። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የሚያቀርብ፥ የእህሉንም ቍርባን የሚያቃጥል፥ ሁልጊዜም የሚሠዋ ሰው ከሌዋውያን ካህናት ዘንድ በእኔ ፊት አይታጣም።” የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ቀንና ሌሊት በወራታቸው እንዳይሆኑ የቀን ቃል ኪዳኔንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ፥ በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ልጅ እንዳይሆንለት ከባሪያዬ ከዳዊት ጋር፥ ከአገልጋዮችም ከሌዋውያን ካህናት ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ደግሞ ይፈርሳል። የሰማይን ሠራዊት መቍጠር፥ የባሕርንም አሸዋ መስፈር እንደማይቻል፥ እንዲሁ የባሪያዬን የዳዊትን ዘርና የሚያገለግሉኝን ሌዋውያንን አበዛለሁ።” የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “ይህ ሕዝብ፦ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሁለቱን ወገን ጥሎአቸዋል፥ እንዲሁ በፊታቸው ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝብ እንዳይሆን ሕዝቤን አቃልለዋል ያለውን ነገር አትመለከትምን? እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የቀንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን የሰማይንና የምድርንም ሥርዐት ያላጸናሁ እንደ ሆነ፥ እኔም ደግሞ በአብርሃምና በይስሐቅ በያዕቆብም ዘር ላይ ገዢዎች ይሆኑ ዘንድ ከዘሩ እንዳላስነሣ፥ የያዕቆብንና የባሪያዬን የዳዊትን ዘር እጥላለሁ፤ ምርኮአቸውን እመልሳለሁና፥ እምራቸውማለሁና።”
ኤርምያስ 33:14-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ ‘ለእስራኤል ቤትና ለይሁዳ ቤት የገባሁትን የተስፋ ቃል የምፈጽምበት ጊዜ ይመጣል’ ይላል እግዚአብሔር። “ ‘በዚያ ዘመንና በዚያ ጊዜ፣ ከዳዊት ቤት ጻድቅ ቅርንጫፍ አበቅላለሁ፤ በምድሪቱም ፍትሕንና ጽድቅን ያደርጋል። በዚያ ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ ኢየሩሳሌም ያለ ሥጋት ትኖራለች፤ የምትጠራበትም ስም፣ “እግዚአብሔር ጽድቃችን” የሚል ይሆናል።’ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘ከዳዊት ዘር በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አይታጣም፤ ሌዋውያን ከሆኑት ካህናትም የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ፣ የእህል ቍርባን ለማቃጠልና ሌላውንም መሥዋዕት ለመሠዋት ሁልጊዜ በፊቴ የሚቆም ሰው አይታጣም።’ ” የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለቀንና ለሌሊት የወሰንሁትን ሥርዐት በማፋለስ ቀንና ሌሊት በተወሰነላቸው ጊዜ እንዳይፈራረቁ ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ፣ በዚያ ጊዜ ከአገልጋዬ ከዳዊት ጋራ የገባሁትን ኪዳን፣ እንዲሁም በፊቴ በክህነት ከሚያገለግሉት ሌዋውያን ጋራ የገባሁትን ኪዳን ማፍረስ ይቻላል፤ ዳዊትም ከእንግዲህ በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ዘር አይኖረውም። የአገልጋዬን የዳዊትን ዘር እንዲሁም በፊቴ የሚቆሙትን ሌዋውያን እንደማይቈጠሩ እንደ ሰማይ ከዋክብትና እንደማይሰፈር የባሕር አሸዋ አበዛቸዋለሁ።’ ” የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ “ይህ ሕዝብ፣ ‘እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሁለቱን መንግሥታት ጥሏል’ እንደሚሉ አላስተዋልህምን? ሕዝቤን ንቀዋል፤ እንደ ሕዝብም አልቈጠሯቸውም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የቀንና የሌሊት ኪዳኔን፣ የሰማይንና የምድርንም ሥርዐት ያጸናሁ እኔ ካልሆንሁ፣ የያዕቆብንና የአገልጋዬን የዳዊትን ዘር እጥላለሁ፤ ከልጆቹም በአብርሃም፣ በይሥሐቅና በያዕቆብ ዘር ላይ ገዥ እንዲሆኑ አልመርጥም፤ ይህንም የምለው ምርኳቸውን ስለምመልስና ስለምራራላቸው ነው።’ ”
ኤርምያስ 33:14-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እነሆ፥ ስለ እስራኤል ቤትና ስለ ይሁዳ ቤት የተናገርሁትን መልካም ቃል የምፈጽምበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። በዚያም ዘመን በዚያም ጊዜ ለዳዊት የጽድቅን ቍጥቋጥ አበቅልለታለሁ፥ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር ያደርጋል። በዚያም ዘመን ይሁዳ ይድናል ኢየሩሳሌምም ተዘልላ ትቀመጣለች፥ የምትጠራበትም ስም፦ እግዚአብሔር ጽድቃችን ተብሎ ነው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከዳዊት ዘንድ አይታጣም፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የሚያቀርብ የእህሉንም ቍርባን የሚያቃጥል ሁልጊዜም የሚሠዋ ሰው ከሌዋውያን ካህናት ዘንድ በእኔ ፊት አይታጣም። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ቀንና ሌሊት በወራቱ እንዳይሆን የቀን ቃል ኪዳኔንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ፥ በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ልጅ እንዳይሆንለት ከባሪያዬ ከዳዊት ጋር፥ ከአገልጋዮቼም ከሌዋውያን ካህናት ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ደግሞ ይፈርሳል። የሰማይን ሠራዊት መቍጠር የባሕርንም አሸዋ መስፈር እንደማይቻል፥ እንዲሁ የባሪያዬን የዳዊትን ዘርና የሚያገለግሉኝን ሌዋውያንን አበዛለሁ። የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ ይህ ሕዝብ፦ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሁለቱን ወገን ጥሎአቸዋል ያለውን ነገር አትመለከትምን? እንዲሁ በፊታቸው ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝብ እንዳይሆን ሕዝቤን አቃልለዋል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የቀንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን የሰማይንና የምድርንም ሥርዓት ያላጸናሁ እንደሆነ፥ እኔም ደግሞ በአብርሃምና በይስሐቅ በያዕቆብም ዘር ላይ ገዦች ይሆኑ ዘንድ ከዘሩ እንዳልወስድ፥ የያዕቆብንና የባሪያዬን የዳዊትን ዘር እጥላለሁ፥ ምርኮአቸውን እመልሳለሁና፥ እምራቸውማለሁና።
ኤርምያስ 33:14-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ለእስራኤልና ለይሁዳ ሕዝብ የተስፋ ቃል የምፈጽምበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ በዚያን ጊዜ የዳዊት ዘር ቅርንጫፍ የሆነ አንድ ጻድቅ ንጉሥ እመርጣለሁ፤ ያም ንጉሥ በአገሪቱ ላይ ቅን የሆነውን ነገር ያደርጋል፤ ትክክለኛ ፍርድም ይሰጣል። የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ከጠላት እጅ ድነው በሰላም ይኖራሉ። ከተማይቱም ‘እግዚአብሔር ጽድቃችን ነው’ ተብላ ትጠራለች፤ ከዳዊት ዘር በእስራኤል ላይ የሚነግሥ ንጉሥ ከቶ እንደማይጠፋ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ እንዲሁም የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል መሥዋዕትና ሌላውንም መሥዋዕት በማቅረብ የሚያገለግሉኝ ካህናት ከሌዊ ወገን ከቶ አይጠፉም።” እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ለአገልጋዬ ለዳዊት ዙፋን የሚወርስ ልጅ እንደምሰጠው የገባሁት ቃል ኪዳንና ለአገልጋዮቼ ለሌዋውያን ስለሚሰጡኝ አገልግሎት ያቆምኩላቸው ቃል ኪዳን ሊፈርሱ የሚችሉት ቀንና ሌሊት በተወሰነላቸው ጊዜ እንዲመጡ ያቆምኩላቸውን ሥርዓት ከእናንተ መካከል ለማፍረስ የሚችል ሰው የተገኘ ከሆነው ነው። ስለዚህ የአገልጋዬን የዳዊትን ዘርና ከሌዊ ወገን የሆኑትን ካህናት ቊጥር አበዛለሁ፤ ብዛታቸውም ሊቈጠር እንደማይችል እንደ ባሕር አሸዋና እንደ ሰማይ ከዋክብት ይሆናል።” እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ ሕዝቦች፦ ‘እግዚአብሔር የመረጣቸውን እነዚያን ሁለት መንግሥታት ትቶአቸዋል’ ብለው ሕዝቤን በመናቅ በሕዝብነት እንደማያውቁአቸው አላስተዋልክምን?” ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ለቀንና ለሌሊት መፈራረቅ፥ ለሰማይና ለምድር ቋሚ ሥርዓት የሰጠሁበትን ቃል ኪዳን ያልመሠረትሁ ከሆነ፥ የያዕቆብና የአገልጋዬን የዳዊትን ዘሮች ትቼአለሁ ማለት ነው፤ ይህም ማለት ለአገልጋዬ ለዳዊት በአብርሃም፥ በይስሐቅና በያዕቆብ ዘሮች ላይ የሚነግሥ አንድም ተወላጅ አላስነሣለትም ማለት ነው። እኔ ግን ምሕረት አደርግላቸዋለሁ፤ ንብረታቸውን እመልስላቸዋለሁ።”
ኤርምያስ 33:14-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“እነሆ፥ ስለ እስራኤል ቤትና ስለ ይሁዳ ቤት የተናገርሁትን መልካም ቃል የምፈጽምበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ። በዚያም ዘመን በዚያም ጊዜ ለዳዊት የጽድቅን ቁጥቋጥ አበቅልለታለሁ፤ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር ያደርጋል። በዚያም ዘመን ይሁዳ ይድናል ኢየሩሳሌምም በደኅንነት ትቀመጣለች፤ እርሷም፦ ‘ጌታ ጽድቃችን ነው’ በሚለው ስም ትጠራለች። ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ዳዊት በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አያጣም፤ እንዲሁም ሌዋውያን ካህናት በእኔ ፊት የሚቃጠለውን መሥዋዕት የሚያቀርብ፥ የእህሉንም ቁርባን የሚያቃጥል፥ ሁልጊዜም የሚሠዋ ሰው ፈጽሞ አያጡም።” የጌታም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ቀንና ሌሊት በተመደበላቸው ጊዜ እንዳይሆኑ የቀን ቃል ኪዳኔንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ፥ በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ልጅ እንዳይሆንለት ከአገልጋዬ ከዳዊት ጋር፥ ከአገልጋዮቼም ከሌዋውያን ካህናት ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ደግሞ ይፈርሳል። የሰማይን ሠራዊት መቁጠር የባሕርንም አሸዋ መስፈር እንደማይቻል፥ እንዲሁ የባርያዬን የዳዊትን ዘርና የሚያገለግሉኝን ሌዋውያንን አበዛለሁ።” የጌታ ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “ይህ ሕዝብ፦ ‘ጌታ የመረጣቸውን ሁለቱን ወገን ጥሎአቸዋል’ ያለውን ነገር አትመለከትምን? እንዲሁ በፊታቸው ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝብ ባለመሆኑ ሕዝቤን አቃልለዋል። ጌታ እንዲህ ይላል፦ የቀንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን የሰማይንና የምድርንም ሥርዓት ያላጸናሁ እንደሆነ፥ በአብርሃምና በይስሐቅ በያዕቆብም ዘር ላይ ገዦች እንዲሆኑ ከዘሩ ላለመውሰድ፥ የያዕቆብንና የባርያዬን የዳዊትን ዘር እኔ ደግሞ እጥላለሁ። እኔ ምርኮአቸውን እመልሳለሁና፥ እምራቸዋለሁምና።”