ኤርምያስ 16:2-9 - Compare All Versions
ኤርምያስ 16:2-9 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
“በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም አይኑሩህ፤” በዚህች ምድር ስለሚወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፣ እንዲሁም ስለ እናቶቻቸው ስለ አባቶቻቸው እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “በአደገኛ በሽታ ይሞታሉ፤ አይለቀስላቸውም፤ አይቀበሩም፤ በምድርም ላይ እንደ ጕድፍ ይጣላሉ። በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “በረከቴን፣ ፍቅሬንና ምሕረቴን ከዚህ ሕዝብ አርቄአለሁና፤ ልቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፤ ታለቅስና ታዝንም ዘንድ አትሂድ” ይላል እግዚአብሔር። “ታላላቆችና ታናናሾች በዚህች ምድር ይሞታሉ፤ አይቀበሩም፤ አይለቀስላቸውም፤ ሰውነቱን የሚቧጥጥላቸው፣ ጠጕሩንም የሚላጭላቸው አይገኝም፤ ሐዘንተኞችን ለማጽናናት የዕዝን እንጀራ የሚያመጣ አይኖርም፤ አባትም ሆነ እናት የሞተባቸውንም ለማጽናናት መጠጥ የሚያቀርብ አይገኝም። “ከእነርሱ ጋራ ተቀምጠህ ለመብላትና ለመጠጣት ድግስ ወዳለበት ቤት አትግባ፤ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘እነሆ፤ በዐይናችሁ ፊት፣ በዘመናችሁም የደስታና የሐሤት ድምፅ፣ የሙሽራውንና የሙሽራዪቱን ድምፅ ከዚህ ስፍራ አስወግዳለሁ።’
ኤርምያስ 16:2-9 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
“በዚህ ባለው ቦታ ሚስት አታግባ፤ ልጆችም አትውለድ፤ በዚህ ስፍራ በሚወለዱ ልጆችና እነርሱንም በሚወልዱአቸው ወላጆች ላይ የሚደርስባቸውን እነግርሃለሁ፤ ሁሉም በአሠቃቂ በሽታ ያልቃሉ፤ የሚያለቅስላቸውም ሆነ የሚቀብራቸው እንኳ አያገኙም፤ ሬሳቸው እንደ ጒድፍ በሜዳ ላይ ይከመራል፤ በጦርነትና በራብ ያልቃሉ፤ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ምግብ ይሆናል። “ለቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፤ ስለ ማንም ሐዘንህን አትግለጥ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝቤን በሰላም አልባርክም፤ ዘላቂ ፍቅርና ምሕረትም አላሳያቸውም፤ በዚህች ምድር የሚገኙ ሀብታሞችም ድኾችም ሁሉ ይሞታሉ፤ አልቅሶ የሚቀብራቸውም አያገኙም፤ ስለ እነርሱ ሐዘኑን ለመግለጥ ፊቱን የሚነጭም ሆነ ጠጒሩን የሚላጭ አይኖርም። ወዳጁ የሞተበትን ሰው ለማጽናናት የእዝን እንጀራ በመውሰድ አብሮት የሚበላና የሚጠጣ አይኖርም፤ ሌላው ቀርቶ እናትም አባትም የሞቱበትን የሚያጽናና አይገኝም። “ሰዎች ወደሚደሰቱበት ግብዣ ቤትም አትግባ፤ ለመብላትና ለመጠጣትም ከእነርሱ ጋር አትቀመጥ። እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ የምልህን አድምጥ፥ አንተ ባለህበት በዚህ ዘመን የደስታና የሐሤት፥ የሠርግ ዘፈን ድምፅ እንዳይሰማ አደርጋለሁ።
ኤርምያስ 16:2-9 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም አትውለድ። እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ስለ ተወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፥ ስለ ወለዱአቸውም ስለ እናቶቻቸው፥ በዚህችም ምድር ስለ ወለዱአቸው ስለ አባቶቻቸው እንዲህ ይላልና፦ “በክፉ ሞት ይሞታሉ፤ አይለቀስላቸውም፤ አይቀበሩምም፤ ነገር ግን በመሬት ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ፤ በሰይፍም ይወድቃሉ፤ በራብም ይጠፋሉ፤ ሬሳዎቻቸውም ለሰማይ ወፎችና ለዱር አራዊት መብል ይሆናሉ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሰላሜን፥ ቸርነቴንና ምሕረቴን፥ ከዚህ ሕዝብ አስወግጄአለሁና ልቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፤ ታለቅስና ታዝንም ዘንድ አትሂድ። ታላላቆችና ታናናሾች በዚች ምድር ይሞታሉ ፥ አይቀበሩም ሰዎችም አያለቅሱላቸውም፤ ስለ እነርሱም ፊት አይነጩላቸውም፤ ራስንም አይላጩላቸውም፤ ሰዎችም ስለ ሞቱት ለማጽናናት የእዝን እንጀራ አይቈርሱላቸውም፤ ስለ አባታቸውና ስለ እናታቸውም የመጽናናት ጽዋ አያጠጡአቸውም። ትበላና ትጠጣ ዘንድ ከእነርሱ ጋር ለመቀመጥ ወደ ግብዣ ቤት አትግባ።” ስለዚህም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በዐይናችሁ ፊት በዘመናችሁም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ ከዚህ ስፍራ አስቀራለሁ።
ኤርምያስ 16:2-9 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም አይሁኑልህ። እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ስለ ተወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፥ ስለወለዱአቸውም ስለ እናቶቻቸው፥ በዚህችም ምድር ስለ ወለዱአቸው ስለ አባቶቻቸው እንዲህ ይላልና፦ በክፉ ሞት ይሞታሉ፥ አይለቀስላቸውም አይቀበሩምም፥ በመሬትም ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ፥ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፥ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናሉ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰላሜን፥ ቸርነትና ምሕረትን፥ ከዚህ ሕዝብ አስወግጄአለሁና ልቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፥ ታለቅስም ታዝንም ዘንድ አትሂድ። ታላላቆችና ታናናሾች በዚህች ምድር ይሞታሉ፥ አይቀበሩም ሰዎችም አያለቅሱላቸውም ስለ እነርሱም ገላን አይነጩላቸውም ራስንም አይላጩላቸውም፥ ሰዎችም ስለ ሞቱት ለማጽናናት የእዝን እንጀራ አይቈርሱላቸውም፥ ስለ አባታቸውና ስለ እናታቸውም የመጽናናት ጽዋ አያጠጡአቸውም። ትበላና ትጠጣ ዘንድ ከእነርሱ ጋር ለመቀመጥ ወደ ግብዣ ቤት አትግባ። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ በዓይናችሁ ፊት በዘመናችሁም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ ከዚህ ስፍራ አስቀራለሁ።
ኤርምያስ 16:2-9 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
“በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም አይኑሩህ። ጌታ በዚህ ስፍራ በተወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፥ በወለዱአቸውም እናቶቻቸው፥ በዚህችም ምድር በወለዱአቸው አባቶቻቸው ላይ እንዲህ ይላልና፦ በክፉ በሽታ ይሞታሉ፤ አይለቀስላቸውም አይቀበሩምም፥ በመሬትም ላይ እንደ ጉድፍ ይሆናሉ፤ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፥ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል። “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሰላሜን፥ ቸርነትንና ጽኑ ፍቅርን፥ ከዚህ ሕዝብ አስወግጄአለሁና ልቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፥ ለማልቀስም ሆነ ለማዘን አትሂድ። ታላላቆችና ታናናሾች በዚህች ምድር ይሞታሉ፤ አይቀበሩም፥ ሰዎችም አያለቅሱላቸውም፥ ስለ እነርሱም ማንም ገላውን አይነጭም ራሱንም አይላጭም፤ ሰዎችም ስለ ሞቱት ለማጽናናት የኀዝን እንጀራ አይቈርሱላቸውም፥ ስለ አባታቸውና ስለ እናታቸውም የመጽናናት ጽዋ አያጠጡአቸውም። ለመብላትና ለመጠጣት፥ ከእነርሱም ጋር ለመቀመጥ ወደ ግብዣ ቤት አትግባ። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ በዓይናችሁ ፊት በዘመናችሁም፥ የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የሙሽራውን ድምፅና የሙሽራቱይን ድምፅ ከዚህ ስፍራ አስቀራለሁ።