ኤርምያስ 13:1-27

ኤርምያስ 13:1-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይለ​ኛል፦ ሂድ፥ ከተ​ልባ እግር የተ​ሠ​ራ​ችን መታ​ጠ​ቂያ ለአ​ንተ ግዛ፤ ወገ​ብ​ህ​ንም ታጠ​ቅ​ባት፤ በው​ኃ​ውም ውስጥ አት​ን​ከ​ራት። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም እን​ዳ​ለኝ የተ​ልባ እግር መታ​ጠ​ቂ​ያን ገዛሁ፤ ወገ​ቤ​ንም ታጠ​ቅ​ሁ​ባት። ዳግ​መ​ኛም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ብሎ ተና​ገ​ረኝ፦ “ለወ​ገ​ብህ የገ​ዛ​ሃ​ትን ያቺን መታ​ጠ​ቂያ ወስ​ደህ ተነሥ፤ ወደ ኤፍ​ራ​ጥ​ስም ሂድ፤ በዚ​ያም በተ​ሰ​ነ​ጠቀ ዓለት ውስጥ ሸሽ​ጋት።” እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም እን​ዳ​ዘ​ዘኝ ሄድሁ፤ በኤ​ፍ​ራ​ጥ​ስም ወንዝ አጠ​ገብ ሸሸ​ግ​ኋት። ከብዙ ቀንም በኋላ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፥ “ተነ​ሥ​ተህ ወደ ኤፍ​ራ​ጥስ ሂድ፥ በዚ​ያም ትሸ​ሽ​ጋት ዘንድ ያዘ​ዝ​ሁ​ህን መታ​ጠ​ቂያ ከዚያ ውስጥ ውሰድ” አለኝ። እኔም ወደ ኤፍ​ራ​ጥስ ወንዝ ሄድሁ፤ ቈፈ​ር​ሁም፤ ከቀ​በ​ር​ሁ​በ​ትም ስፍራ መታ​ጠ​ቂ​ያ​ዪ​ቱን ወሰ​ድሁ። እነ​ሆም መታ​ጠ​ቂ​ያ​ዪቱ ተበ​ላ​ሽታ ነበር፤ ለም​ንም አል​ረ​ባ​ችም። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ቃል ወደ እኔ እን​ዲህ ሲል መጣ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፥ “እን​ዲሁ የይ​ሁ​ዳን ትዕ​ቢት፥ ታላ​ቁ​ንም የኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምን ትዕ​ቢት አበ​ላ​ሻ​ለሁ። ቃሌን ይሰሙ ዘንድ እንቢ የሚሉ፥ በክፉ ልባ​ቸ​ውም እል​ከ​ኝ​ነት የሚ​ሄዱ፥ ያገ​ለ​ግ​ሏ​ቸ​ውና ይሰ​ግ​ዱ​ላ​ቸው ዘንድ ሌሎ​ችን አማ​ል​ክት ተከ​ት​ለው የሚ​ሄዱ እነ​ዚህ ክፉ ሕዝብ አን​ዳች እን​ደ​ማ​ት​ረባ እን​ደ​ዚች መታ​ጠ​ቂያ ይሆ​ናሉ። መታ​ጠ​ቂያ በሰው ወገብ ላይ እን​ደ​ም​ት​ጣ​በቅ፥ እን​ዲሁ ለስም፥ ለመ​መ​ኪ​ያና ለክ​ብር ሕዝብ ይሆ​ኑ​ልኝ ዘንድ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ቤት ሁሉ፥ የይ​ሁ​ዳ​ንም ቤት ሁሉ ከእኔ ጋር አጣ​ብ​ቄ​አ​ለሁ፥ ይላል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፤ ነገር ግን አል​ሰ​ሙም።” ስለ​ዚህ፦ የእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፥ “ማድጋ ሁሉ የወ​ይን ጠጅ ይሞ​ላል” ብለህ ትነ​ግ​ራ​ቸ​ዋ​ለህ፤ እነ​ር​ሱም፥ “ማድጋ ሁሉ የወ​ይን ጠጅ እን​ዲ​ሞላ በውኑ እኛ አና​ው​ቅ​ምን?” ቢሉህ፤ አን​ተም እን​ዲህ ትላ​ቸ​ዋ​ለህ፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፦ እነሆ በዚ​ህች ምድር የሚ​ኖ​ሩ​ትን ሁሉ፥ በዳ​ዊት ዙፋን የሚ​ቀ​መ​ጡ​ትን ነገ​ሥ​ታት፥ ካህ​ና​ቱ​ንም፥ ነቢ​ያ​ቱ​ንም፥ በይ​ሁ​ዳና በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም የተ​ቀ​መ​ጡ​ትን ሁሉ በስ​ካር እሞ​ላ​ቸ​ዋ​ለሁ። ሰው​ንና ወን​ድ​ሙን፥ አባ​ቶ​ች​ንና ልጆ​ችን በአ​ንድ ላይ እበ​ት​ና​ቸ​ዋ​ለሁ፥ ይላል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፤ አጠ​ፋ​ቸ​ዋ​ለሁ እንጂ አል​ራ​ራ​ላ​ቸ​ውም፤ አላ​ዝ​ን​ላ​ቸ​ውም፤ አል​ም​ራ​ቸ​ው​ምም።” ስሙ፤ አድ​ምጡ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ተና​ግ​ሮ​አ​ልና አት​ታ​በዩ። ሳይ​ጨ​ል​ም​ባ​ችሁ፥ ጨለ​ማም ባለ​ባ​ቸው ተራ​ሮች እግ​ሮ​ቻ​ችሁ ሳይ​ሰ​ነ​ካ​ከሉ ለአ​ም​ላ​ካ​ችሁ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ክብ​ርን ስጡ፤ በዚ​ያም የሞት ጥላ አለና በጨ​ለ​ማ​ውም ውስጥ ያኖ​ራ​ች​ኋ​ልና ብር​ሃ​ንን ተስፋ ታደ​ር​ጋ​ላ​ችሁ። ይህን ባት​ሰሙ ነፍሴ ስለ ትዕ​ቢ​ታ​ችሁ በስ​ውር ታለ​ቅ​ሳ​ለች፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መንጋ ተሰ​ብ​ሮ​አ​ልና ዐይኔ ታነ​ባ​ለች፤ እን​ባ​ንም ታፈ​ስ​ሳ​ለች። ለነ​ገ​ሥ​ታ​ቱና ለመ​ኳ​ን​ንቱ፦ የክ​ብ​ራ​ችሁ አክ​ሊል ከራ​ሳ​ችሁ ወር​ዶ​አ​ልና ራሳ​ች​ሁን አዋ​ር​ዳ​ችሁ ተቀ​መጡ በላ​ቸው። የደ​ቡብ ከተ​ሞች ተዘ​ግ​ተ​ዋል፤ የሚ​ከ​ፍ​ታ​ቸ​ውም የለም፤ ይሁዳ ሁሉ ተሰ​ድ​ዶ​አል፤ ፈጽ​ሞም ተሰ​ድ​ዶ​አል። ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም ሆይ! ዐይ​ን​ሽን አን​ሥ​ተሽ እነ​ዚ​ህን ከሰ​ሜን የሚ​መ​ጡ​ትን ተመ​ል​ከቺ፤ ለአ​ንቺ የሰ​ጠ​ሁሽ መንጋ፤ የክ​ብር በጎ​ችሽ ወዴት አሉ? አንቺ ትም​ህ​ርት ያስ​ተ​ማ​ር​ሻ​ቸው አለ​ቆ​ችሽ ሆነው በጐ​በ​ኙሽ ጊዜ ምን ትያ​ለሽ? እንደ ወላድ ሴት ምጥ አይ​ዝ​ሽ​ምን? በል​ብ​ሽም፦ እን​ዲህ ያለ ነገር ስለ ምን ደረ​ሰ​ብኝ? ብትዪ፥ ከኀ​ጢ​አ​ትሽ ብዛት የተ​ነሣ ልብ​ስሽ በስ​ተ​ኋ​ላሽ ተገ​ፎ​አል፤ ተረ​ከ​ዝ​ሽም ተገ​ል​ጦ​አል። በውኑ ኢት​ዮ​ጵ​ያዊ መል​ኩን ወይስ ነብር ዝን​ጕ​ር​ጕ​ር​ነ​ቱን ይለ​ውጥ ዘንድ ይች​ላ​ልን? በዚያ ጊዜ ክፋ​ትን የለ​መ​ዳ​ችሁ እና​ንተ ደግሞ በጎ ለማ​ድ​ረግ ትች​ላ​ላ​ች​ሁን? ነፋስ በም​ድረ በዳ እን​ደ​ሚ​በ​ት​ነው እብቅ እበ​ት​ና​ች​ኋ​ለሁ። ረስ​ተ​ሽ​ኛ​ልና፥ በሐ​ሰ​ትም ታም​ነ​ሻ​ልና ዕጣ​ሽና እድል ፈን​ታሽ ይህ ነው፥ ይላል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር። ስለ​ዚ​ህም የል​ብ​ስ​ሽን ዘርፍ በስ​ተ​ኋ​ላሽ ወደ ፊትሽ እገ​ል​ጣ​ለሁ እፍ​ረ​ት​ሽም ይታ​ያል። አስ​ጸ​ያፊ ሥራ​ሽን፥ ምን​ዝ​ር​ና​ሽን፥ ማሽ​ካ​ካ​ት​ሽን፥ የዝ​ሙ​ት​ሽ​ንም መዳ​ራት በኮ​ረ​ብ​ቶች ላይ፥ በሜ​ዳም ላይ አይ​ቻ​ለሁ። ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም ሆይ! ወዮ​ልሽ! ለመ​ን​ጻት እንቢ ብለ​ሻል፤ ይህስ እስከ መቼ ነው?

ኤርምያስ 13:1-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር፣ “ሄደህ ከተልባ እግር የተሠራ መቀነት ግዛ፤ ወገብህንም ታጠቅበት፤ ነገር ግን ውሃ አታስነካው” አለኝ። ስለዚህ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ መቀነቱን ገዛሁ፤ ወገቤንም ታጠቅሁበት። ለሁለተኛም ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ “ገዝተህ የታጠቅህበትን መቀነት ይዘህ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፤ በዚያም በዐለት ንቃቃት ውስጥ ሸሽገው።” ስለዚህ እግዚአብሔር በነገረኝ መሠረት ወደ ኤፍራጥስ ሄጄ ሸሸግሁት። ከብዙ ቀን በኋላም እግዚአብሔር፣ “ተነሥተህ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፤ በዚያ እንድትሸሽገው የነገርሁህን መቀነት አምጣ” አለኝ። እኔም ወደ ኤፍራጥስ ሄጄ፣ መታጠቂያውን ከሸሸግሁበት ቦታ ቈፍሬ አወጣሁ፤ መታጠቂያውም ተበላሽቶ፣ ከጥቅም ውጭም ሆኖ ነበር። ከዚያም የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የይሁዳን ትዕቢትና የኢየሩሳሌምን እብሪት እንደዚሁ አጠፋለሁ። ቃሌን መስማት እንቢ ብለው በልባቸው እልኸኝነት በመሄድ ሊያመልኳቸውና ሊሰግዱላቸው ሌሎችን ጣዖቶች የሚከተሉ እነዚህ ክፉ ሕዝቦች ከጥቅም ውጭ እንደ ሆነው እንደዚህ መቀነት ይበላሻሉ። መቀነት በሰው ወገብ ላይ እንደሚታሰር፣ መላው የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ከእኔ ጋራ ተጣብቆ ለስሜ ምስጋናና ክብር፣ የእኔ ሕዝብ እንዲሆንልኝ አድርጌው ነበር፤ ሕዝቤ ግን አልሰማም’ ይላል እግዚአብሔር። “እንዲህ በላቸው፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ማድጋ ሁሉ በወይን ጠጅ ይሞላል’፤ እነርሱም፣ ‘ማድጋ ሁሉ በወይን ጠጅ እንደሚሞላ እኛ አናውቅምን?’ ቢሉህ፣ እንዲህ በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትን፣ ካህናትን፣ ነቢያትን እንዲሁም በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሁሉ ጨምሮ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ። አንዱን ሰው ከሌላው ጋራ፣ አባትንና ወንድ ልጅን እርስ በእርስ አጋጫለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር፤ ያለ ሐዘኔታ፣ ያለ ምሕረትና ያለ ርኅራኄ አጠፋቸዋለሁ።’ ” እግዚአብሔር ተናግሯልና፣ ስሙ፤ ልብ በሉ፤ ትዕቢተኛም አትሁኑ። ጨለማን ሳያመጣ፣ በሚጨልሙትም ተራሮች ላይ፣ እግሮቻችሁ ሳይሰናከሉ፣ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ። ብርሃንን ተስፋ ታደርጋላችሁ፤ እርሱ ወደ ጨለማ ይለውጠዋል፤ ድቅድቅ ጨለማም ያደርገዋል። ባትሰሙ ግን፣ ነፍሴ ስለ ትዕቢታችሁ፣ በስውር ታለቅሳለች፤ የእግዚአብሔር መንጋ ተማርኳልና፣ ዐይኔ አምርሮ ያለቅሳል፤ እንባዬም እንደ ጐርፍ ይወርዳል። ለንጉሡና ለእናቱ ለእቴጌዪቱ፣ “የክብር ዘውዳችሁ ከራሳችሁ ይወድቃልና፣ ከዙፋናችሁ ውረዱ” በላቸው። በኔጌብ ያሉ ከተሞች ይዘጋሉ፤ የሚከፍታቸውም አይኖርም። ይሁዳ ሁሉ ተማርኮ ይሄዳል፤ ሙሉ በሙሉም ይዘጋል። ዐይኖቻችሁን ከፍታችሁ፣ ከሰሜን የሚመጡትን እዩ። ለአንቺ የተሰጠው መንጋ፣ የተመካሽባቸው በጎች የት አሉ? ልዩ ወዳጆች እንዲሆኑሽ ያስተማርሻቸው፣ ባለሥልጣን ሲሆኑብሽ ምን ትያለሽ? እንደምትወልድ ሴት፣ ምጥ አይዝሽምን? “ይህ ለምን ደረሰብኝ?” ብለሽ ራስሽን ብትጠይቂ፣ ልብስሽን ተገልበሽ የተገፈተርሽው፣ በሰውም እጅ የተንገላታሽው፣ ከኀጢአትሽ ብዛት የተነሣ ነው። ኢትዮጵያዊ መልኩን፣ ነብርስ ዝንጕርጕርነቱን መለወጥ ይችላልን? እናንተ ክፉ ማድረግ የለመዳችሁትም፣ መልካም ማድረግ አትችሉም። “የበረሓ ነፋስ ብትንትኑን እንደሚያወጣው ገለባ፣ እንዲሁ እበታትናችኋለሁ። እኔን ረስተሽ፣ በከንቱ አማልክት ስለ ታመንሽ፣ ያወጅሁልሽ ድርሻሽ፣ ዕጣ ፈንታሽ ይህ ነው፤” ይላል እግዚአብሔር፤ “ኀፍረትሽ እንዲገለጥ፣ ልብስሽን ፊትሽ ድረስ እገልባለሁ፤ በኰረብቶችና በሜዳዎች ላይ፣ አስጸያፊ ተግባርሽን፣ ምንዝርናሽንና ማሽካካትሽን፣ ኀፍረተ ቢስ ግልሙትናሽን አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ወዮልሽ! ከርኩሰትሽ የማትጸጂው እስከ መቼ ነው?”

ኤርምያስ 13:1-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል፦ ሂድ፥ ከተልባ እግር የተሠራችን መታጠቂያ ለአንተ ግዛ፥ ወገብህንም ታጠቅባት፥ በውኃውም ውስጥ አትንከራት። እንደ እግዚአብሔርም ቃል መታጠቂያን ገዛሁ ወገቤንም ታጠቅሁባት። ሁለተኛም ጊዜ፦ የገዛሃትን በወገብህ ያለችውን መታጠቂያ ወስደህ ተነሥ፥ ወደ ኤፍራጥስም ሂድ፥ በዚያም በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ ሸሽጋት የሚል የእግዚአብሔር ቃል መጣልኝ። እግዚአብሔርም እንዳዘዘኝ ሄድሁ በኤፍራጥስም አጠገብ ሸሸግኋት። ከብዙ ቀንም በኋላ እግዚአብሔር፦ ተነሥተህ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፥ በዚያም ትሸሽጋት ዘንድ ያዘዝሁህን መታጠቂያ ከዚያ ውስጥ ውሰድ አለኝ። እኔም ወደ ኤፍራጥስ ሄድሁ ቆፈርሁም፥ ከሸሸግሁበትም ስፍራ መታጠቂያይቱን ወሰድሁ። እነሆም፥ መታጠቂያይቱ ተበላሽታ ነበር፥ ለምንም አልረባችም። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንዲሁ የይሁዳን ትዕቢት ታላቁንም የኢየሩሳሌምን ትዕቢት አበላሻለሁ። ቃሌን ይሰሙ ዘንድ እንቢ የሚሉ፥ በልባቸውም እልከኝነት የሚሄዱ፥ ያመልኩአቸውና ይሰግዱላቸው ዘንድ ሌሎችን አማልክት የሚከተሉ እነዚህ ክፉ ሕዝብ አንዳች እንዳማትረባ እንደዚች መታጠቂያ ይሆናሉ። መታጠቂያ በሰው ወገብ ላይ እንደምትጣበቅ፥ እንዲሁ ሕዝብና ስም ምስጋናና ክብር ይሆኑልኝ ዘንድ የእስራኤልን ቤት ሁሉ የይሁዳንም ቤት ሁሉ ከእኔ ጋር አጣብቄአለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ነገር ግን አልሰሙም። ስለዚህ፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ ይሞላል ብለህ ትነግራቸዋለህ፥ እነርሱም፦ ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ እንዲሞላ በውኑ እኛ አናውቅምን? ይሉሃል። አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡትን ነገሥታት ካህናቱንም ነቢያቱንም በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ። ሰውንም በሰው ላይ፥ አባቶችንና ልጆችን በአንድ ላይ፥ እቀጠቅጣቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ አጠፋቸዋለሁ እንጂ አልራራም፥ አላዝንም፥ አልምርም። ስሙ፥ አድምጡ፥ እግዚአብሔር ተናግሮአልና አትታበዩ። ሳትጨልም እግራችሁም በጨለመችው ተራራ ላይ ሳትሰናከል፥ በተስፋ የምትጠባበቁትን ብርሃን ለሞት ጥላና ለድቅድቅ ጨልማ ሳይለውጠው ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ። ይህን ባትሰሙ ነፍሴ ስለ ትዕቢታችሁ በስውር ታለቅሳለች፥ የእግዚአብሔርም መንጋ ተማርኮአልና ዓይኔ ታነባለች፥ እንባንም ታፈስሳለች። ለንጉሡና ለንጉሥ እናት ለእቴጌይቱ፦ የክብራችሁ አክሊል ከራሳችሁ ወርዶአልና ተዋርዳችሁ ተቀመጡ በል። የደቡብ ከተሞች ተዘግተዋል፥ የሚከፍታቸውም የለም፥ ይሁዳ ሁሉ ተማርኮአል፥ ፈጽሞ ተማርኮአል። ዓይናችሁን አንሥታችሁ እነዚህን ከሰሜን የሚመጡትን ተመልከቱ፥ ለአንቺ የተሰጠ መንጋ፥ የተዋበ መንጋሽ፥ ወዴት አለ? ወዳጆችሽ እንዲሆኑ ያስተማርሻቸውን በራስሽ ላይ አለቆች ባደረጋቸው ጊዜ ምን ትያለሽ? እንደ ወላድ ሴት ምጥ አይዝሽምን? በልብሽም፦ እንዲህ ያለ ነገር ስለ ምን ደረሰብኝ? ብትዪ፥ ከኃጢአትሽ ብዛት የተነሣ የልብስሽ ዘርፍ ተገልጦአል ተረከዝሽም ተገፍፎአል። በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ። ስለዚህ እንደሚያልፍ እብቅ በምድረ በዳ ነፋስ እበትናቸዋለሁ። ረስተሽኛልና፥ በሐሰትም ታምነሻልና ዕጣሽ የለካሁልሽም እድል ፈንታ ይህ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህም የልብስሽን ዘርፍ በፊትሽ እገልጣለሁ እፍረትሽም ይታያል። አስጸያፊ ሥራሽን፥ ምንዝርናሽን፥ ማሽካካትሽን፥ የግልሙትናሽንም መዳራት በኮረብቶች ላይ በሜዳም አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ወዮልሽ! ለመንጻት እንቢ ብለሻል፥ ይህስ እስከ መቼ ነው?

ኤርምያስ 13:1-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ከበፍታ የተሠራ መታጠቂያ ገዝተህ ታጠቀው፤ ውሃ ግን አታስነካው።” ስለዚህ እግዚአብሔር ባዘዘኝ መሠረት መታጠቂያውን ገዝቼ ታጠቅሁት፤ እግዚአብሔርም እንደገና እንዲህ አለኝ፦ “ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ሂድና መታጠቂያውን በአለት ንቃቃት ውስጥ ደብቀው።” ስለዚህ እግዚአብሔር ባዘዘኝ መሠረት ሄጄ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ መታጠቂያውን ደበቅሁት። ከብዙ ቀኖች በኋላም እግዚአብሔር፥ “ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ተመልሰህ ሂድና መታጠቂያውን ውሰድ” አለኝ። እኔም ሄጄ መታጠቂያውን የደበቅሁበትን ስፍራ አገኘሁ፤ መታጠቂያውንም ባየሁት ጊዜ ተበላሽቶና ከጥቅም ውጪ ሆኖ አገኘሁት። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የይሁዳን ኲራትና የኢየሩሳሌምን ታላቅ ትዕቢት የማስወግደው በዚህ ዐይነት ነው፤ እነዚህ በክፋት የተሞሉ ሕዝብ ለእኔ መታዘዝን እምቢ ብለዋል፤ ከምንጊዜውም ይልቅ እልኸኞች ሆነዋል፤ ባዕዳን አማልክትን በማምለክ ያገለግላሉ፤ ከዚህም የተነሣ እነርሱ ዋጋቢስ ሆኖ እንደ ቀረው እንደዚያ መታጠቂያ ይሆናሉ። መታጠቂያ በወገብ ዙሪያ ተጣብቆ እንደሚገኝ፥ የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ ከእኔ ጋር እንዲጣበቁ ዐቅጄ ነበር፤ ይህንንም ያደረግኹት ሕዝቤ እንዲሆኑና ለስሜ ምስጋናና ክብር እንዲያስገኙ ነበር፤ እነርሱ ግን አልሰሙኝም።” እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ አለኝ፦ “ኤርምያስ ሆይ! ‘እያንዳንዱ ማድጋ በወይን ጠጅ የተሞላ ይሆናል’ ብለህ ለእስራኤል ሕዝብ ንገር፤ በዚያን ጊዜ እነርሱ ‘ማድጋ በወይን ጠጅ መሞላቱን የማናውቅ ይመስልሃልን?’ ይሉሃል። ከዚህ በኋላ እኔ እግዚአብሔር በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ እስከሚሰክሩ ድረስ በወይን ጠጅ ልሞላቸው እንዳቀድኩ ንገራቸው፤ በዚያን ጊዜ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡ ነገሥታትን፥ ካህናትን፥ ነቢያትንና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችን ሁሉ በወይን ጠጅ አሰክራቸዋለሁ። ያን ጊዜ አባቶችንና ልጆቻቸውን ሁሉንም እንደ ማድጋ እርስ በርሳቸው አጋጫቸዋለሁ፤ ምንም ዐይነት ሐዘኔታ፥ ርኅራኄ ወይም ምሕረት እነርሱን ከማጥፋት ሊያግደኝ አይችልም።” እግዚአብሔር ተናግሮአልና፤ ትዕቢታችሁን አስወግዳችሁ ስሙት፤ በጥንቃቄም አድምጡት። ጨለማን አምጥቶ በተራራዎች ከመሰናከላችሁ በፊት ተስፋ ያደረጋችኹትን ብርሃን ወደ ድቅድቅ ጨለማና ወደ ጥልቅ ጭጋግ ከመለወጡ በፊት አምላካችሁን እግዚአብሔርን አክብሩ። አናዳምጥም ብትሉ ግን ስለ ትዕቢታችሁ ተደብቄ አለቅሳለሁ፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ ምርኮኞች ሆነው በመወሰዳቸውም ምርር ብዬ አለቅሳለሁ፤ እንባዬም ባለማቋረጥ ይፈስሳል። እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የተከበረ ዘውዳቸው ከራሳቸው ስለ ወደቀ ንጉሡና ንግሥት እናቱ ከዙፋናቸው እንዲወርዱ ንገራቸው። በደቡብ ይሁዳ ያሉት ከተሞች በጠላት ስለ ተከበቡ ማንም ወደ እነርሱ ሊሄድ አይችልም፤ መላው የይሁዳ ሕዝብ ተማርከው ይወሰዳሉ።” ኢየሩሳሌም ሆይ! ከሰሜን በኩል የጠላቶችሽን አመጣጥ ተመልከቺ፤ ስትንከባከቢያቸው የነበርሽና መመኪያዎችሽ የነበሩ ሕዝብ የት ደረሱ? ወዳጆች ብለሽ ያቀረብሻቸው ወራሪዎችሽና ገዢዎችሽ ሲሆኑ ምን ትያለሽ? በምጥ ላይ እንዳለች ሴት ሕመም አይሰማሽምን? ይህ ሁሉ የደረሰብኝ ለምንድነው? “ልብሴስ ተቀዶ የተደፈርኩት ስለምንድነው?” ብለሽ ብትጠይቂ፤ ይህ ሁሉ የደረሰብሽ ኃጢአትሽ እጅግ የከፋ በመሆኑ ምክንያት እንደ ሆነ ዕወቂ። ኢትዮጵያዊ መልኩን፥ ነብርም ዝንጒርጒርነቱን መለወጥ አይችልም፤ እንዲሁም እናንተ ክፉ ነገር ማድረግን ስለ ለመዳችሁ ደግ ሥራ መሥራት አይሆንላችሁም። አሁን ግን እግዚአብሔር የበረሓ ነፋስ ጠራርጎ እንደሚወስደው ገለባ ይበታትናችኋል። ዕድል ፈንታችሁም ይህ እንደሚሆን እግዚአብሔር ተናግሮአል። እርሱን ረስታችሁ በሐሰተኞች አማልክት ስለ ታመናችሁ በእናንተ ላይ ይህን ለማድረግ ወስኖአል። እግዚአብሔር ራሱ ልብሳችሁን ገፎ ኀፍረተ ሥጋችሁ እንዲጋለጥ ያደርጋል። እርሱ የሚጠላውን ነገር ስታደርጉ አይቶአችኋል፤ ከባልንጀራው ሚስት ጋር ለማመንዘር እንደሚጐመጅ ሰውና ባዝራ እንደሚፈልግ ሰንጋ ፈረስ፥ እናንተም የአሕዛብ አማልክትን ተከትላችሁ በየኰረብታው ራስና በየሜዳው ስትኳትኑ አይቶአችኋል። የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፥ ወዮላችሁ፥ ከቶ ንጹሕ መሆን የምትችሉት መቼ ይሆን?

ኤርምያስ 13:1-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ጌታ እንዲህ ይለኛል፦ “ሂድ፥ ከተልባ እግር የተሠራን መታጠቂያ ለእራስህ ግዛ፥ ወገብህንም ታጠቀው፤ በውኃም ውስጥ አትንከረው።” እንደ ጌታም ቃል መታጠቂያን ገዛሁ ወገቤንም ታጠቅሁት። የጌታ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እኔ መጣ እንዲህም አለኝ፦ “የገዛኸውን በወገብህ ያለውን መታጠቂያ ወስድ፥ ተነሣም፥ ወደ ኤፍራጥስም ሂድ፥ በዚያም በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ ሸሽጋት።” ጌታም እንዳዘዘኝ ሄድሁ በኤፍራጥስም አጠገብ ሸሸግሁት። ከብዙ ቀንም በኋላ ጌታ፦ “ተነሣ፥ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፥ በዚያም እንድትሸሽገው ያዘዝሁህን መታጠቂያ ከዚያ ውስጥ ውሰድ” አለኝ። እኔም ወደ ኤፍራጥስ ሄድሁ ቆፈርሁም፥ ከዚያ ከሸሸግሁበትም ስፍራ መታጠቂያውን ወሰድሁ። እነሆም፥ መታጠቂያው ተበላሽቶ ነበር፥ ለምንም አይረባም። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ እንዲሁ የይሁዳን ትዕቢት ታላቁንም የኢየሩሳሌምን ትዕቢት አጠፋለሁ። ቃሌን ለመስማት እንቢ የሚሉ፥ በልባቸውም እልከኝነት የሚሄዱ፥ ሊያገለግሉአቸውና ሊሰግዱላቸው ሌሎችን አማልክት የሚከተሉ፥ እነዚህ ክፉ ሕዝብ አንዳች እንደማይረባ እንደዚህ መታጠቂያ ይሆናሉ። መታጠቂያ በሰው ወገብ ላይ እንደሚጣበቅ፥ እንዲሁ ሕዝብና ስም፥ ምስጋናና ክብር እንዲሆኑልኝ የእስራኤልን ቤት ሁሉ የይሁዳንም ቤት ሁሉ ከእኔ ጋር አጣብቄአለሁ፥ ይላል ጌታ፤ ነገር ግን አልሰሙም።” ስለዚህ፦ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ ይሞላል” ብለህ ይህን ቃል ትነግራቸዋለህ፤ እነርሱም፦ “ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ እንደሚሞላ በእርግጥ እኛ አናውቅምን?” ይሉሃል። አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡትን ነገሥታት ካህናቱንም ነቢያቱንም በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ። ሰውንም ከሰው ጋር፥ አባቶችንና ልጆችን በአንድ ላይ፥ አላትማቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ አጠፋቸዋለሁ እንጂ አልራራም፥ አላዝንም፥ አልምርም።” ስሙ፥ አድምጡም፤ ጌታ ተናግሮአልና አትታበዩ። ሳትጨልም እግራችሁም በጨለሙት ተራሮች ላይ ሳትሰናከል፥ በተስፋ የምትጠባበቁትን ብርሃን ለሞት ጥላና ለድቅድቅ ጨልማ ሳይለውጠው፥ ለአምላካችሁ ለጌታ ክብርን ስጡ። ይህን ባትሰሙ ነፍሴ ስለ ትዕቢታችሁ በስውር ታለቅሳለች፤ የጌታም መንጋ ተማርኮአልና ዓይኔ እጅግ ታነባለች፥ እንባንም ታፈስሳለች። ለንጉሡና ለንጉሥ እናት ለእቴጌይቱ፦ “የክብራችሁ አክሊል ከራሳችሁ ወርዶአልና ተዋርዳችሁ ተቀመጡ” በል። የደቡብ ከተሞች ተዘግተዋል፥ የሚከፍታቸውም የለም፤ ይሁዳ ሁሉ ተማርኮአል፥ ፈጽሞ ተማርኮአል። “ዓይናችሁን አንሥታችሁ እነዚህን ከሰሜን የሚመጡትን ተመልከቱ፤ ለአንቺ የተሰጠ መንጋ፥ የተዋበ መንጋሽ፥ ወዴት አለ? ወዳጆችሽ እንዲሆኑ ያስተማርሻቸውን በራስሽ ላይ አለቆች ባደረጋቸው ጊዜ ምን ትያለሽ? እንደ ወላድ ሴት ምጥ አይዝሽምን? በልብሽም፦ ‘እነዚህ ነገሮች ስለምን ደረሱብኝ?’ ብትዪ፥ ከኃጢአትሽ ብዛት የተነሣ የልብስሽ ዘርፍ ተገልጦአል ተረከዝሽም ተገፍፎአል። በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጉርጉርነቱን መለወጥ ይችላልን? እናንተ ክፋትን የለመዳችሁ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ። ስለዚህ እንደሚያልፍ እብቅ በምድረ በዳ ነፋስ እበትናቸዋለሁ። ረስተሽኛልና፥ በሐሰትም ታምነሻልና ዕጣሽ፥ የለካሁልሽም ድርሻሽ ይህ ነው፥ ይላል ጌታ። ስለዚህም የልብስሽን ዘርፍ በፊትሽ እገልጣለሁ እፍረትሽም ይታያል። አስጸያፊ ሥራሽን፥ ምንዝርናሽን፥ ማሽካካትሽን፥ የአመንዝራነትሽንም መዳራት በኮረብቶች ላይ፥ በሜዳም አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ወዮልሽ! ለመንጻት እንቢ ብለሻል፤ ይህስ እስከ መቼ ነው?”