መሳፍንት 6:12-16
መሳፍንት 6:12-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእግዚአብሔርም መልአክ ለእርሱ ተገልጦ፥ “አንተ ጽኑዕ ኀያል ሰው! እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴዎንም፥ “ጌታዬ ሆይ! እሺ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ፦ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራት ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፤ በምድያም እጅም አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ እርሱ ተመለከተና፥ “በዚህ በጕልበትህ ሂድ፤ እስራኤልንም ከምድያም እጅ ታድናቸዋለህ፤ እነሆ፥ ልኬሃለሁ” አለው። እርሱም፥ “ጌታ ሆይ! እሺ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ በምናሴ ነገድ ዘንድ ጥቂቶች ናቸው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ” አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ፥ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ታጠፋለህ” አለው።
መሳፍንት 6:12-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ፣ “አንተ ኀያል ጦረኛ እነሆ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነው” አለው። ጌዴዎን መልሶ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ? ‘እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር አውጥቶናል’ በማለት አባቶቻችን የነገሩን ታምራት የት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፤ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፣ “ሂድ፤ ባለህ ኀይል እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ እንድታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን?” አለው። ጌዴዎንም፣ “ጌታ ሆይ፤ የእኔ ጐሣ ከምናሴ ነገድ እጅግ ደካማ ነው፤ ከቤተ ሰቤም እኔ የመጨረሻ ነኝ፤ ታዲያ እንዴት እኔ እስራኤልን ላድን እችላለሁ?” አለ። እግዚአብሔርም፣ “በርግጥ እኔ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ” አለው።
መሳፍንት 6:12-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእግዚአብሔርም መልአክ ለእርሱ ተገልጦ፦ አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው። ጌዴዎንም፦ ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ፦ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ? ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል አለው። እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፦ በዚህ በጉልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን፥ እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው። እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፥ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ አለው። እግዚአብሔርም፦ በእርግጥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታለህ አለው።
መሳፍንት 6:12-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና “አንተ ኀያልና ብርቱ ሰው! እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴዎንም እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ሆይ! ታዲያ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ ችግር እንዴት ሊደርስብን ቻለ? አባቶቻችን እንደ ነገሩን እግዚአብሔር ያደርገው የነበረ ድንቅ ሥራ ሁሉ ዛሬ የት አለ? ከግብጽ እንዴት እንዳወጣቸውም ነግረውን ነበር፤ ዛሬ ግን እግዚአብሔር እኛን በመተው እንደ ፈለጉ ያደርጉን ዘንድ ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጥቶናል።” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ሂድ፤ በዚህ ባለህ ብርቱ ኀይል ሁሉ በመጠቀም እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ አውጣ፤ እነሆ እኔ ራሴ ልኬሃለሁ” ሲል አዘዘው። ጌዴዎንም “ታዲያ እኔ እንዴት አድርጌ እስራኤልን ላድን እችላለሁ? ወገኔም ከምናሴ ነገድ መካከል እጅግ ደካማ ነው፤ እኔም ከቤተሰቤ መካከል በጣም አነስተኛ ነኝ” ሲል መለሰ። እግዚአብሔርም “እኔ ስለምረዳህ ይህን ማድረግ ትችላለህ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው ያኽል አድርገህ ታደቃቸዋለህ” አለው።
መሳፍንት 6:12-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የጌታ መልአክ ተገልጦለት “አንተ ኃያል ጦረኛ! እነሆ፥ ጌታ ከአንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴዎን መልሶ፥ “ጌታዬ ሆይ ጌታ ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ? ‘ጌታ ከግብጽ ምድር አውጥቶናል’ በማለት አባቶቻችን የነገሩን ታምራት የት አለ? አሁን ግን ጌታ ትቶናል፤ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው። በዚህ ጊዜ ጌታ ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፥ “ባለህ ኃይል ሂድ፤ እስራኤውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ እንድታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን? አለው” ጌዴዎንም፥ “ጌታ ሆይ የእኔ ጐሣ ከምናሴ ነገድ እጅግ ደካማ ነው፤ ከቤተሰቤም እኔ የመጨረሻ ነኝ፤ ታዲያ እንዴት እኔ እስራኤልን ላድን እችላለሁ?” አለ። ጌታም፥ “በእርግጥ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ” አለው።