መሳፍንት 3:7-11
መሳፍንት 3:7-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረጉ፤ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረስተው በዓሊምንና አስታሮትን አመለኩ። ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ፈጽሞ ተቈጣ፤ በወንዞችም መካከል ባለች በሶርያ ንጉሥ በኩሳርሳቴም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የእስራኤልም ልጆች ለኩሳርሳቴም ስምንት ዓመት ተገዙለት። የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። እግዚአብሔርም ለእስራኤል መድኀኒትን አስነሣላቸው። የካሌብ የታናሽ ወንድሙ የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያልም አዳናቸው፤ ለእርሱም ታዘዙለት። የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ አደረ፤ በእስራኤልም ላይ ይፈርድ ነበር፤ ለጦርነትም ወጣ፤ እግዚአብሔርም በወንዞች መካከል ያለች የሶርያ ንጉሥ ኩሳርሳቴምን በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ እጁም በኩሳርሳቴም ላይ በረታች። ምድሪቱም አርባ ዓመት ዐረፈች፤ የቄኔዝም ልጅ ጎቶንያል ሞተ።
መሳፍንት 3:7-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ እግዚአብሔር አምላካቸውንም ረሱ፤ የበኣልንና የአስታሮትን አማልክት አመለኩ። እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ስለዚህ ለመስጴጦምያ ንጉሥ ለኵስርስቴም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እስራኤላውያንም ስምንት ዓመት በባርነት ተገዙለት። እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ ግን የካሌብን ታናሽ ወንድም የቄኔዝን ልጅ ጎቶንያልን ታዳጊ አድርጎ አስነሣላቸው። የእግዚአብሔር መንፈስ በርሱ ላይ ወረደ፤ የእስራኤል መስፍን ሆኖ ወደ ጦርነትም ወጣ። እግዚአብሔር የአራም ንጉሥ ኵስርስቴምን አሳልፎ ስለ ሰጠው ድል አደረገ። የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ምድሪቱ ለአርባ ዓመት ሰላም አገኘች።
መሳፍንት 3:7-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር አደረጉ፥ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረስተው በኣሊምንና አስታሮትን አመለኩ። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በመስጴጦምያ ንጉሥ በኩሰርሰቴም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ የእስራኤልም ልጆች ለኩሰርሰቴም ስምንት ዓመት ተገዙለት። የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ እግዚአብሔርም የሚያድናቸውን አዳኝ የካሌብን የታናሽ ውንድሙን የቄኔዝን ልጅ ጎቶንያልን አስነሣላቸው። የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ መጣ፥ በእስራኤልም ላይ ይፈርድ ነበር፥ ለሰልፍ ወጣ፥ እግዚአብሔርም የመሰጴጦምያን ንጉሥ ኩሰርሰቴምን በእጁ አሳልፎ ሰጠው፥ እጁም በኩሰርሰቴም ላይ አሸነፈች። ምድሪቱም አርባ ዓመት ዐረፈች፥ የቄኔዝም ልጅ ጎቶንያል ሞተ።
መሳፍንት 3:7-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ አምላካቸውን እግዚአብሔርንም ትተው በዓልና አሼራን አመለኩ፤ ከዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር ቊጣ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ነደደ፤ ለመስጴጦምያው ንጉሥ ለኩሻን ፊሽዓታይም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለኩሻን ሪሽዓታይም ስምንት ዓመት ተገዙለት፤ ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም የሚያድናቸውን አዳኝ የካሌብ ታናሽ ወንድም ልጅ የሆነውን የቄኔዝን ልጅ ዖትኒኤልን አስነሣቸው። የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ ዐደረ፤ በእስራኤልም ላይ መሪ ሆነ፤ ለጦርነት በወጣ ጊዜ እግዚአብሔር የመስጴጦምያውን ንጉሥ ኩሻን ፊሽዓታይምን አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም ኩሻን ሪሽዓታይምን ድል አደረገው። በምድሪቱም ላይ ለአርባ ዓመት ያኽል ሰላም ሰፍኖ ከቈየ በኋላ የቄኔዝ ልጅ ዖትኒኤል ሞተ።
መሳፍንት 3:7-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እስራኤላውያን በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ አምላካቸውን ጌታንም ረሱ፤ በኣልንና አስታሮትን አመለኩ። ጌታ በእስራኤላውያን ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ስለዚህ ለመስጴጦምያ ንጉሥ ለኩሽን-ሪሽዓታይም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እስራኤላውያንም ለኩሽን-ሪሽዓታይም ስምንት ዓመት በባርነት ተገዙለት። እስራኤላውያን ወደ ጌታ በጮኹ ጊዜ ግን፥ ጌታ የካሌብን ታናሽ ወንድም የቄኔዝን ልጅ ዖትኒኤልን ታዳጊ አድርጎ አስነሣላቸው። የጌታም መንፈስ በእርሱ ላይ ዐደረ፤ በእስራኤልም ላይ መሪ ሆነ፤ ለጦርነት በወጣ ጊዜ ጌታ የመስጴጦምያውን ንጉሥ ኩሽን ሪሽዓታይምን አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም ኩሽን-ሪሽዓታይምን ድል አደረገው። የቄኔዝ ልጅ ዖትኒኤል እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ምድሪቱ ለአርባ ዓመት ሰላም አገኘች።