መሳፍንት 3:1-4
መሳፍንት 3:1-4 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የከነዓናውያንንም ጦርነት ሁሉ ያላወቁትን እስራኤልን በእነርሱ ይፈትናቸው ዘንድ እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ተዋቸው። ይህም ጦርነትን ያስተምሩአቸው ዘንድ ስለ እስራኤል ልጆች ትውልድ ብቻ ነው፤ ነገር ግን ከእነርሱ በፊት የነበሩት እነዚህን አላወቋቸውም ነበር፤ እነርሱም አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥ ከነዓናውያንም ሁሉ ፥ ሲዶናውያንም፥ ከበዓልሄርሞን ተራራ ጀምሮ እስከ ኤማት መግቢያ ድረስ በሊባኖስ ተራራ የሚኖሩትም ኤዌዎናውያን፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ለአባቶቻቸው ያዘዘውን ትእዛዝ መስማታቸው እንዲታወቅ እስራኤል ይፈተኑባቸው ዘንድ እነዚህ ቀሩ።
መሳፍንት 3:1-4 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ጊዜ በከነዓን ላይ በተደረጉት ጦርነቶች ተሳትፈው የማያውቁትን እስራኤላውያን ለመፈተን፣ እግዚአብሔር ባሉበት የተዋቸው ሕዝቦች እነዚህ ናቸው፤ ይህን ማድረጉ ቀደም ሲል በጦር ሜዳ ውለው የማያውቁትን የእስራኤል ልጆች የጦርነት ልምድ እንዲያገኙ ለማድረግ ብቻ ነው፤ እነዚህም አሕዛብ ዐምስቱ የፍልስጥኤም ገዦች፣ ከነዓናውያን በሙሉ፣ ሲዶናውያንና ከበኣል አርሞንዔም ተራራ እስከ ሐማት መግቢያ ባሉት የሊባኖስ ተራሮች የሚኖሩ ኤዊያውያን ነበሩ። እነዚህ፣ እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ለቀደሙ አባቶቻቸው የሰጠውን ትእዛዞች ማክበር አለማክበራቸውን ለማወቅ ለእስራኤል መፈተኛ እንዲሆኑ እዚያው የቀሩ ነበሩ።
መሳፍንት 3:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከከነዓናውያንም ጋር መዋጋት ያላወቁትን እስራኤልን በእነርሱ ይፈትናቸው ዘንድ፥ በፊትም ሰልፍን ያልለመዱ የእስራኤል ልጆች ትውልድ መዋጋትን ያውቁና ይማሩ ዘንድ እግዚአብሔር ያስቀራቸው አሕዛብ እነዚህ ናቸው፥ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥ ከነዓናውያንም ሁሉ፥ ሲዶናውያንም፥ ከበኣልአርሞንዔም ተራራ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ በሊባኖስ ተራራ የሚኖሩትም ኤዊያውያን። እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ለአባቶቻቸው ያዘዘውን ትእዛዝ መስማታቸው እንዲታወቅ እስራኤል ይፈተኑባቸው ዘንድ እነዚህ ቀሩ።
መሳፍንት 3:1-4 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በከነዓን ምድር ጦርነት ያልተለማመዱ እስራኤላውያንን ለመፈተን እግዚአብሔር በምድሪቱ የተዋቸው ሕዝቦች እነዚህ ናቸው። ይህንንም ማድረጉ ቀድሞ የጦርነት ልምድ ያልነበራቸውን የእስራኤልን ትውልድ የጦርነት ስልት ለማስተማር ብሎ ብቻ ነው። በምድሪቱ ላይ የቀሩትም፥ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መሪዎች፥ ከነዓናውያን በሙሉ፥ ሲዶናውያንና ከባዓልሔርሞን ተራራ አንሥቶ እስከ ሐማት ድረስ በሊባኖስ ተራራዎች የሚኖሩት ሒዋውያን ነበሩ። እነርሱም እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻቸው የሰጣቸውን ትእዛዞች እስራኤላውያን ያከብሩ ወይም አያከብሩ እንደ ሆነ ለማወቅ ለእስራኤል መፈተኛዎች ነበሩ።
መሳፍንት 3:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚህ ጊዜ በከነዓን ላይ በተደረጉት ጦርነቶች ተሳትፈው የማያውቁትን እስራኤላውያን ለመፈተን፥ ጌታ ባሉበት የተዋቸው ሕዝቦች እነዚህ ናቸው። ይህን ማድረጉ ቀደም ሲል በጦር ሜዳ ውለው የማያውቁትን የእስራኤል ልጆች የጦርነት ልምድ እንዲያገኙ ለማድረግ ብቻ ነው። እነዚህም አሕዛብ አምስቱ የፍልስጥኤም ገዦች፥ ከነዓናውያን በሙሉ፥ ሲዶናውያንና ከበኣል አርሞንዔም ተራራ እስከ ሐማትስ መግቢያ ባሉት የሊባኖስ ተራሮች የሚኖሩ ኤዊያውያን ነበሩ። እነርሱም ጌታ በሙሴ አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻቸው የሰጣቸውን ትእዛዞች እስራኤላውያን ያከብሩ ወይም አያከብሩ እንደሆነ ለማወቅ ለእስራኤል መፈተኛዎች ነበሩ።