መሳፍንት 2:10-15

መሳፍንት 2:10-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ትው​ልድ ሁሉ ደግሞ ወደ አባ​ቶ​ቻ​ቸው ተጨ​መሩ፤ ከእ​ነ​ዚ​ያም በኋላ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንና ለእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ያደ​ረ​ገ​ውን ሥራ ያላ​ወቀ ሌላ ትው​ልድ ተነሣ። የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ክፉ አደ​ረጉ፤ በዓ​ሊ​ም​ንም አመ​ለኩ። ከግ​ብፅ ምድ​ርም ያወ​ጣ​ቸ​ውን የአ​ባ​ቶ​ቻ​ቸ​ውን አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ተዉ፤ ሌሎ​ች​ንም በዙ​ሪ​ያ​ቸው ያሉ የአ​ሕ​ዛ​ብን አማ​ል​ክት ተከ​ተሉ፤ ሰገ​ዱ​ላ​ቸ​ውም፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም አስ​ቈ​ጡት። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም ትተው በዓ​ል​ንና አስ​ታ​ሮ​ትን አመ​ለኩ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ ተቈጣ፤ ወደ ማረ​ኳ​ቸ​ውም ማራ​ኪ​ዎች እጅ አሳ​ልፎ ሰጣ​ቸው፤ ማረ​ኩ​አ​ቸ​ውም፤ በዙ​ሪ​ያ​ቸ​ውም ባሉት በጠ​ላ​ቶ​ቻ​ቸው እጅ አሳ​ልፎ ሰጣ​ቸው፤ ከዚ​ያም ወዲያ ጠላ​ቶ​ቻ​ቸ​ውን ሊቋ​ቋሙ አል​ቻ​ሉም። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም እንደ ተና​ገረ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በእ​ነ​ርሱ ላይ እንደ ማለ፥ ወደ ወጡ​በት ሁሉ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እጅ ትከ​ፋ​ባ​ቸው ነበ​ረች፤ እጅ​ግም ተጨ​ነቁ።

መሳፍንት 2:10-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ያ ትውልድ በሙሉ ሞተ፤ ከዚያ ቀጥሎ እግዚአብሔርንና ለእስራኤል ያደረገውን መልካም ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሣ። ከዚህ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ክፉ ሥራ በመሥራት እግዚአብሔርን በደሉ። በዓሊም ተብለው የሚጠሩትን ባዕዳን አማልክት አመለኩ፤ ከግብጽ ያወጣቸውን የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ማገልገል ተዉ፤ በዚህም ፈንታ በዙሪያቸው ያሉ ሕዝቦች የሚያመልኩአቸውን የውሸት አማልክትን ማገልገል ጀመሩ፤ ለእነርሱም በመስገድ እግዚአብሔርን አስቈጡት። እግዚአብሔርን ማምለክ ትተው “ባዓልና ዐስታሮት” ተብለው የሚጠሩትን ባዕዳን አማልክት አመለኩ፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በጣም ተቈጣ፤ እንዲዘርፉአቸውም ለወራሪዎች አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዙሪያቸው ያሉ ጠላቶቻቸውም እንዲበረቱባቸው አደረገ። ከዚያም በኋላ እስራኤላውያን ከጠላቶቻቸው ወረራ ራሳቸውን መከላከል ተሳናቸው። ወደ ጦርነት በሄዱም ቊጥር ቀደም ብሎ በመሐላ በተናገረው መሠረት እግዚአብሔር ራሱ ይቃወማቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ እነርሱ በብርቱ ጭንቀት ላይ ወደቁ።