መሳፍንት 2:1-6
መሳፍንት 2:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእግዚአብሔርም መልአክ ከገልገላ ወደ ቀላውትምኖስ ወደ ቤቴል ወደ እስራኤል ቤት ወጥቶ እንዲህ አላቸው፥ “እግዚአብሔር እኔ ከግብፅ አውጥቼአችኋለሁ፤ እሰጣችሁም ዘንድ ለአባቶቻችሁ ወደ ማልሁላቸው ምድር አግብቻችኋለሁ፤ እኔም፦ ከእናንተ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ለዘለዓለም አላፈርስም፤ እናንተም በዚች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ፤ ለአማልክቶቻቸውም አትስገዱላቸው፤ ምስሎቻቸውንም ስበሩ፤ መሠዊያቸውንም አፍርሱ አልሁ። እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም፤ ይህንስ ለምን አደረጋችሁ? ስለዚህም እኔ አሕዛብን ከፊታችሁ አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ያስጨንቋችኋል፤ አማልክቶቻቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል” አልሁ። የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ድምፃቸውን አንሥተው አለቀሱ። የዚያም ስፍራ ስም “መካነ ብካይ” ተብሎ ተጠራ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር ሠዉ። ኢያሱም ሕዝቡን ባሰናበተ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ምድሪቱን ሊወርሱ ወደየርስታቸው ገቡ።
መሳፍንት 2:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የእግዚአብሔር መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ፤ “ከግብጽ ምድር አወጣኋችሁ፤ ለቀደሙትም አባቶቻችሁ ልሰጣቸው ወደ ማልሁላቸው ምድር አመጣኋችሁ፤ እንዲህም አልሁ፤ ‘ከእናንተ ጋራ የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አላፈርስም፤ እናንተም ከዚህች ምድር ነዋሪዎች ጋራ ቃል ኪዳን አታድርጉ፤ መሠዊያቸውንም አፍርሱ፤’ እናንተ ግን አልታዘዛችሁኝም፤ ይህን ያደረጋችሁት ለምንድን ነው? ስለዚህ አሁንም ከፊታችሁ አሳድጄ እንደማላስወጣቸው እነግራችኋለሁ፤ ነገር ግን እነርሱ የጐን ውጋት፣ አማልክታቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል።” የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤላውያን ሁሉ በተናገረ ጊዜ፣ ሕዝቡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ያን ስፍራ ቦኪም ብለው ጠሩት፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ። ኢያሱ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ምድሪቱን ለመውረስ ወደየርስቱ ሄደ።
መሳፍንት 2:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእግዚአብሔርም መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ፦ እኔ ከግብፅ አውጥቻችኋለሁ፥ ለአባቶቻችሁም ወደ ማልሁላቸው ምድር አግብቻችኋለሁ፥ እኔም፦ ከእናንተ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ለዘላለም አላፈርስም፥ እናንተም መሠዊያቸውን አፍርሱ እንጂ በዚህች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ አልሁ። እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም፥ ይህንስ ለምን አደረጋችሁ? ስለዚህም፦ ከፊታችሁ አላወጣቸውም፥ ነገር ግን ያስጨንቋችኋል፥ አማልክቶቻቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል አልሁ። የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ድምፃቸውን አንሥተው አለቀሱ። የዚያንም ስፍራ ስም ቦኪም ብለው ጠሩት፥ በዚያም ለእግዚአብሔር ሠዉ። ኢያሱም ሕዝቡን ባሰናበተ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ምድሪቱን ሊወርሱ ወደ እየርስታቸው ሄዱ።
መሳፍንት 2:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእግዚአብሔር መልአክ ከጌልጌላ ወደ ቦኪም ሄዶ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ከግብጽ ምድር አውጥቼ ለቀድሞ አባቶቻችሁ ልሰጣቸው ቃል ወደገባሁላቸው ምድር አመጣኋችሁ፤ እንዲህም አልኩ፦ ‘ከእናንተ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ከቶ አላፈርስም፤ እናንተ በዚች ምድር ከሚኖሩ ሕዝብ ጋር ምንም ዐይነት ቃል ኪዳን አታድርጉ፤ መሠዊያዎቻቸውንም አፍርሱ፤’ እናንተ ግን አልታዘዛችሁኝም፤ ይህንስ ያደረጋችኹት ለምንድን ነው? ስለዚህ አሁን እነዚህን ሕዝቦች ከፊታችሁ እንደማላስወጣቸው እነግራችኋለሁ፤ እነርሱ ለእናንተ ጠላቶች ይሆናሉ፤ ባዕዳን አማልክታቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል።” የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን በተናገረ ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ያ ስፍራ “ቦኪም” ተብሎ የተጠራውም በዚህ ምክንያት ነው፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ። ኢያሱ ሕዝቡን ባሰናበተ ጊዜ እስራኤላውያን ሁሉ የየራሳቸውን ድርሻ ለመያዝ ወደየተመደበላቸው ርስት ሄዱ።
መሳፍንት 2:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የጌታ መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ፤ “ከግብጽ ምድር አወጣኋችሁ፤ ለቀደሙትም አባቶቻችሁ ልሰጣቸው ወደ ማልሁላቸው ምድር አመጣኋችሁ፤ እንዲህም አልሁ፤ ከእናንተ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አላፈርስም፤ እናንተም ከዚህች ምድር ነዋሪዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ፤ መሠዊያቸውንም አፍርሱ፤ እናንተ ግን አልታዘዛችሁኝም፤ ይህን ያደረጋችሁት ለምንድነው? ስለዚህ አሁንም ከፊታችሁ አሳድጄ እንደማላስወጣቸው እነግራችኋለሁ፤ ነገር ግን እነርሱ የጐን ውጋት፥ አማልክቶቻቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል።” የጌታም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ድምፃቸውን አንሥተው አለቀሱ። ያንን ስፍራ ቦኪምሠ ብለው ጠሩት፤ በዚያም ለጌታ መሥዋዕት አቀረቡ። ኢያሱ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ምድሪቱን ለመውረስ ወደ የርስቱ ሄደ።