ያዕቆብ 5:1-19
ያዕቆብ 5:1-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አሁንም እናንተ ባለጠጎች! ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፤ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል። ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፤ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል። ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል። እነሆ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፤ የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ጸባዖት ጆሮ ገብቶአል። በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል፤ በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል። ጻድቁን ኰንናችሁታል፤ ገድላችሁትማል፤ እናንተን አይቃወምም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል። እናንተ ደግሞ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና። ወንድሞች ሆይ! እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል። ወንድሞች ሆይ! የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ። እነሆ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፤ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና። ከሁሉም በፊት ወንድሞቼ ሆይ! በሰማይም ቢሆን በምድርም ቢሆን በሌላ መሐላም ቢሆን በምንም አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ ነገራችሁ አዎን ቢሆን አዎን ይሁን፤ አይደለምም ቢሆን አይደለም ይሁን። ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር። ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል፤ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል። እርስ በርሳችሁ በኀጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኀይል ታደርጋለች። ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፤ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፤ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ፤ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች። ወንድሞች ሆይ! ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው፥
ያዕቆብ 5:1-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ እናንተ ሀብታሞች ስሙ፤ ስለሚደርስባችሁ መከራ አልቅሱ፤ ዋይ ዋይም በሉ። ሀብታችሁ ሻግቷል፤ ልብሳችሁንም ብል በልቶታል። ወርቃችሁና ብራችሁ ዝጓል፤ ዝገቱም በእናንተ ላይ ይመሰክራል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላዋል፤ ለመጨረሻው ዘመን ሀብትን አከማችታችኋል። ልብ በሉ፤ ዕርሻችሁን ሲያጭዱ ለዋሉ ሠራተኞች ያልከፈላችሁት ደመወዝ በእናንተ ላይ ይጮኻል፤ የዐጫጆቹም ጩኸት ሁሉን ቻይ ወደ ሆነው ጌታ ጆሮ ደርሷል። በምድርም ላይ በምቾትና በመቀማጠል ኖራችኋል፤ ለዕርድ ቀን ልባችሁን አወፍራችኋል። እናንተን ያልተቃወሙትን ንጹሓን ሰዎች ኰንናችኋል፤ ገድላችኋልም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ታገሡ። ገበሬ መሬቱ መልካምን ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ እንዴት እንደሚታገሥ፣ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እንዴት እንደሚጠባበቅ አስተውሉ። እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቧል። ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አታጕረምርሙ፤ አለዚያ ይፈረድባችኋል፤ እነሆ፤ ፈራጁ በበር ላይ ቆሟል። ወንድሞች ሆይ፤ በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ። በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው። ከሁሉም በላይ ወንድሞቼ ሆይ፤ በሰማይ ወይም በምድር ወይም በማናቸውም ነገር ቢሆን አትማሉ፤ “አዎ” ቢሆን አዎ ይሁን፤ “አይደለም” ቢሆን አይደለም ይሁን፤ አለዚያ ይፈረድባችኋል። ከእናንተ መካከል በመከራ ውስጥ ያለ አለ? እርሱ ይጸልይ፤ የተደሰተ አለ? የምስጋና መዝሙር ይዘምር። ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ይጥራ፤ እነርሱም በጌታ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትም ሠርቶ ከሆነ፣ ይቅር ይባላል። ስለዚህ ኀጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ለሌላው ይጸልይ። የጻድቅ ሰው ጸሎት ኀይል አለው፤ ታላቅ ነገርም ያደርጋል። ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ፤ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ተኩል ዝናብ አልዘነበም። እንደ ገናም ጸለየ፤ ዝናብም ከሰማይ ዘነበ፤ ምድርም ፍሬዋን ሰጠች። ወንድሞቼ ሆይ፤ ከእናንተ አንዱ ከእውነት ቢስትና ሌላው ቢመልሰው፣
ያዕቆብ 5:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፥ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፥ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል። ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፥ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል። ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል። እነሆ፥ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፥ የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ፀባዖት ጆሮ ገብቶአል። በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል። ጻድቁን ኵኦንናችሁታል ገድላችሁትማል፤ እናንተን አይቃወምም። እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል። እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና። ወንድሞች ሆይ፥ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ፥ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል። ወንድሞች ሆይ፥ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ። እነሆ፥ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፤ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና። ከሁሉም በፊት፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በሰማይ ቢሆን በምድርም ቢሆን በሌላ መሐላም ቢሆን በምንም አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ ነገራችሁ አዎን ቢሆን አዎን ይሁን፥ አይደለምም ቢሆን አይደለም ይሁን። ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር። ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል። እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች። ወንድሞች ሆይ፥ ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው፥
ያዕቆብ 5:1-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አሁን ደግሞ እናንተ ሀብታሞች! ኑ አድምጡ፤ አሠቃቂ መከራ ስለሚመጣባችሁ እየጮኻችሁ አልቅሱ። ሀብታችሁ ሁሉ በስብሶአል። ልብሳችሁንም ብል በልቶታል። ወርቃችሁና ብራችሁ ዝጎአል፤ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላዋል፤ በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ብዙ ሀብት አከማችታችኋል። ይሁን እንጂ በእርሻችሁ ሲያጭዱ ለዋሉት ሠራተኞች ዋጋቸውን ስላልከፈላችሁ እነሆ፥ የተቃውሞ ጩኸታቸው ይሰማል፤ የመከር ሰብሳቢዎቹንም ጩኸት የሠራዊት ጌታ ሰምቶአል። በምቾትና በደስታ በመኖር ልባችሁን ለዕርድ እንደ ተዘጋጀ ከብት አወፍራችኋል። ጻድቁን በሐሰት ፈረዳችሁበት፤ ገደላችሁትም፤ እርሱም አይቃወማችሁም። ወንድሞች ሆይ! እንግዲህ ጌታ እስኪመጣ ድረስ በትዕግሥት ጠብቁ፤ ገበሬ መሬቱ የመጀመሪያውንና የኋለኛውን ዝናብ እስከሚያገኝ እየታገሠ ክቡር ዋጋ ያለውን የመሬቱን ፍሬ ይጠባበቃል። እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ የጌታ መምጫ ጊዜ ስለ ተቃረበ በተስፋ ጽኑ። ወንድሞች ሆይ! በእናንተም ላይ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አትጨቃጨቁ፤ እነሆ ፈራጁ የሚመጣበት ጊዜ ደርሶአል። ወንድሞች ሆይ፥ በጌታ ስም የተናገሩት ነቢያት መከራን በትዕግሥት በመቀበል ምሳሌ መሆናቸውን ዕወቁ። ደግሞም እነዚያን በትዕግሥት የጸኑትን “የተባረኩ ናቸው” እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንዴት እንደ ታገሠ ሰምታችኋል። ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን መልካም ነገር አይታችኋል፤ በዚህም ጌታ መሐሪና ርኅሩኅ መሆኑን ተመልክታችኋል። ወንድሞቼ ሆይ! ከሁሉም በላይ በሰማይ ወይም በምድር ወይም በሌላ በምንም ነገር አትማሉ፤ ንግግራችሁ አዎ ከሆነ በእውነት አዎ ይሁን፤ አይደለም ከሆነም በእውነት አይደለም ይሁን፤ እንዲህ ካልሆነ ግን ይፈረድባችኋል። ከእናንተ መካከል ችግር የደረሰበት ሰው ቢኖር ይጸልይ፤ ደስ ያለው ሰውም ቢኖር እግዚአብሔርን በማመስገን ይዘምር። ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው ቢኖር የቤተ ክርስቲያን ካህናትን (ሽማግሌዎችን) ወደ እርሱ ይጥራ፤ እነርሱም በሽተኛውን በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። እንዲህ ዐይነቱ በእምነት ላይ የተመሠረተ ጸሎት በሽተኛውን ያድነዋል፤ ጌታም ከበሽታው ይፈውሰዋል፤ የሠራው ኃጢአትም ቢኖር ይቅር ይባልለታል። ስለዚህ እንድትፈወሱ ኃጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ እያንዳንዱም ለሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት ብዙ ውጤት የሚያስገኝ ታላቅ ኀይል አለው፤ ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ፤ ነገር ግን ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ በጸለየ ጊዜ ለሦስት ዓመት ተኩል በምድር ላይ ምንም ዝናብ አልዘነበም። እንደገና በጸለየም ጊዜ ሰማይ ዝናብ ሰጠ፤ ምድርም እንደገና ፍሬን ሰጠች። ወንድሞቼ ሆይ! ከእናንተ አንዱ ከእውነት መንገድ ቢወጣና ሌላው ወደ እውነት መንገድ ቢመልሰው
ያዕቆብ 5:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አሁንም እናንተ ሀብታሞች ኑ! ስለሚደርስባችሁ መከራ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፤ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል። ወርቃችሁና ብራችሁ ዝጎአል፤ ዝገቱም በእናንተ ላይ ይመሰክራል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላዋል፤ ለመጨረሻው ዘመን ሀብትን አከማችታችኋል። እነሆ፥ እርሻችሁን ሲያጭዱ ለዋሉ ሠራተኞች ያልከፈላችሁት ደመወዝ በእናንተ ላይ ይጮኻል፤ የአጫጆቹም ጩኸት የሠራዊት ጌታ ጆሮ ደርሶአል። በምድርም ላይ በምቾትና በመቀማጠል በመኖር ለዕርድ ቀን እንደሚዘጋጅ ልባችሁን አወፍራችኋል። እናንተን ያልተቃወመውን ጻድቁን ሰው ፈረዳችሁበት፤ ገደላችሁትም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ ገበሬ መሬቱ መልካምን ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ እንዴት እንደሚታገሥ፥ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እንዴት እንደሚጠባበቅ አስተውሉ። እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቦአልና። ወንድሞች ሆይ! እንዳይፈረድባችሁ፥ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ ፈራጁ በበር ላይ ቆሞአል። ወንድሞች ሆይ! በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ። በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው። ከሁሉም በላይ ወንድሞቼ ሆይ! በሰማይ ወይም በምድር ወይም በማናቸውም ነገር ቢሆን አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ፥ ነገራችሁ “አዎ” ቢሆን አዎ ይሁን፤ “አይደለም” ቢሆን አይደለም ይሁን። ከእናንተ መካከል በመከራ ውስጥ ያለ አለ? እርሱ ይጸልይ፤ የተደሰተ አለ? የምስጋና መዝሙር ይዘምር። ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ይጥራ፤ እነርሱም በጌታ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትም ሠርቶ ከሆነ፥ ይቅር ይባላል። ስለዚህ ኀጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ለሌላው ይጸልይ። የጻድቅ ሰው ጸሎት ኃይል አለው፤ ታላቅ ነገርም ያደርጋል። ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ፤ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ተኩል ዝናብ አልዘነበም። እንደገና በጸለየም ጊዜ ሰማይ ዝናብ ሰጠ፤ ምድርም ፍሬን ሰጠች። ወንድሞቼ ሆይ! ከእናንተ አንዱ ከእውነት ቢስትና ሌላው ቢመልሰው፥