ያዕቆብ 3:1-18

ያዕቆብ 3:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ወንድሞቼ ሆይ! ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፤ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና። ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው። እነሆ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናገባለን፤ ሥጋቸውንም ሁሉ እንመራለን። እነሆ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ። እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ የአካል ክፍል ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል። አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በሰውነታችን ክፍሎች መካከል ዐመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፤ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፤ በገሃነምም ይቃጠላል። የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል፤ ደግሞ ተገርቶአል፤ ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም፤ የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው። በእርሱ ጌታንና አብን እናመሰግናለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤ ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ! ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም። ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውሃ ያመነጫልን? ወንድሞቼ ሆይ! በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውሃም ጣፋጭ ውሃ አይወጣም። ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ሥራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ፤ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፤ የሥጋም ነው፤ የአጋንንትም ነው፤ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉና። ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ፥ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።

ያዕቆብ 3:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ወንድሞቼ ሆይ፤ ከእናንተ ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ፤ ምክንያቱም እኛ አስተማሪዎች የሆንን የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል ታውቃላችሁ። ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለን፤ በንግግሩ የማይሰናከል ማንም ሰው ቢኖር፣ እርሱ ሰውነቱን ሁሉ መቈጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው። ፈረሶች እንዲታዘዙልን ልጓም በአፋቸው ውስጥ ስናስገባ፣ መላ ሰውነታቸውን መምራት እንችላለን። ወይም መርከቦችን ተመልከቱ፤ ምንም እንኳ እጅግ ትልቅና በኀይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም፣ የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ይመራቸዋል። እንዲሁም ምላስ ትንሽ የሰውነት ክፍል ሆና ሳለ በታላላቅ ነገሮች ትኵራራለች፤ ትልቅ ጫካ በትንሽ እሳት እንዴት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ አስተውሉ፤ ምላስም እንደ እሳት ናት፤ በሰውነት ክፍሎቻችን መካከል የምትገኝ የክፋት ዓለም ናት፤ ሰውነትን ሁሉ ታረክሳለች፤ ደግሞም የፍጥረትን ሩጫ ታቃጥላለች፤ ራሷም በገሃነም ትቃጠላለች። ማንኛውም ዐይነት እንስሳ፣ አዕዋፍ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡና፣ በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ መገራት ችለዋል፤ በሰውም ተገርተዋል። ነገር ግን ምላስን መግራት የሚችል ማንም ሰው የለም፤ የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት። በምላሳችን ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በርሷም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣል። ወንድሞቼ ሆይ፤ ይህ ሊሆን አይገባም። ከአንድ ምንጭ ጣፋጭ ውሃና መራራ ውሃ ይመነጫልን? ወንድሞቼ ሆይ፤ በለስ ወይራን ወይንም በለስን ሊያፈራ ይችላልን? እንዲሁም ከጨው ውሃ ጣፋጭ ውሃ ሊገኝ አይችልም። ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ የሆነ ሰው ማን ነው? ሥራውን ከጥበብ በሆነ በመልካም አኗኗር ያሳይ። ነገር ግን መራራ ቅናትና ራስ ወዳድነት በልባችሁ ቢኖር ኵራት አይሰማችሁ፤ እውነትንም አትካዱ። እንዲህ ያለችዋ ጥበብ ከላይ አይደለችም፤ ነገር ግን ከምድር፣ ከሥጋና ከአጋንንት ናት። ቅናትና ራስ ወዳድነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ ይገኛሉ። ከሰማይ የሆነችው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ሰላም ወዳድ፣ ታጋሽ፣ ዕሺ ባይ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬ የሞላባት፣ አድልዎና ግብዝነት የሌለባት ናት። የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉ በሰላም ይዘራል።

ያዕቆብ 3:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና። ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው። እነሆ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናገባለን፥ ሥጋቸውንም ሁሉ እንመራለን። እነሆ፥ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ። እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል። አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል። የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል፥ ደግሞ ተገርቶአል፤ ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም፤ የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው። በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤ ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም። ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን? ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም ጣፋጭ ውኃ አይወጣም። ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።

ያዕቆብ 3:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ወንድሞቼ ሆይ! እኛ አስተማሪዎች የሆንን የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል ታውቃላችሁና ከእናንተ ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ። እኛ ሁላችን ብዙ ጊዜ እንሳሳታለን፤ በንግግሩ የማይሳሳት እርሱ ሰውነቱን መቈጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው። ፈረስ እንዲታዘዝልን በአፉ ውስጥ ልጓም እናገባለን፤ ፈረሱንም ወደምንፈልገው ቦታ እንመራዋለን። መርከብ ምንም ትልቅ ቢሆንና በኀይለኛ ነፋስ የሚገፋ ቢሆንም፥ የመርከቡ ነጂ በትንሽ መቅዘፊያ ወደ ፈለገው ቦታ ይነዳዋል። እንዲሁም ምላስ ትንሽ የአካል ክፍል ስትሆን በታላላቅ ነገሮች ትመካለች፤ ትልቅ ጫካ የሚቃጠለው በትንሽ እሳት ነው። ምላስም እንደ እሳት ናት፤ ምላስ በአካል ክፍሎቻችን መካከል የምትገኝ ክፉ ዓለም ናት፤ አካላችንን ትበክላለች፤ ከገሃነም እንደሚወጣ እሳትም የኑሮአችንን ሂደት ሁሉ ታቃጥላለች። የምድር አውሬዎችና ወፎች፥ በመሬት የሚሳቡና በባሕር የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች ሁሉ በሰው ሊገሩ ይችላሉ፤ ደግሞም ተገርተዋል። ነገር ግን ምላስን ሊገራ የሚችል ማንም የለም፤ የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት። በእርስዋ አባታችንን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፤ እንዲሁም በእርስዋ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። ከአንድ አፍ ምስጋናና ርግማን ይወጣሉ፤ ወንድሞቼ ሆይ! ይህ ሊሆን አይገባም። ከአንድ ምንጭ ለመጠጥ የሚሆን ጣፋጭ ውሃና መራራ ውሃ ሊፈልቅ ይችላልን? ወንድሞቼ ሆይ፥ የበለስ ዛፍ የወይራን ፍሬ ሊያፈራ ይችላልን? ወይስ የወይን ተክል የበለስ ፍሬ ሊያፈራ ይችላልን? እንዲሁም ከመራራ ውሃ ጣፋጭ ውሃ ሊገኝ ይችላልን? ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ ሰው ማን ነው? በጥበብና በትሕትና የፈጸመውን ሥራ በመልካም አኗኗሩ ያሳይ። ነገር ግን መራራ ቅናትና ራስ ወዳድነት በልባችሁ ቢኖር አትመኩ፤ በእውነትም ላይ አትዋሹ። እንዲህ ዐይነቱ ጥበብ የሚገኘው ከዓለም፥ ከሥጋ፥ ከሰይጣን ነው እንጂ ከእግዚአብሔር አይደለም። ቅናትና ራስ ወዳድነት ባሉበት ስፍራ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ ይኖራሉ። ነገር ግን ከእግዚአብሔር የሚገኘው ጥበብ በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ቀጥሎም ሰላም ወዳድ፥ ደግ፥ ታዛዥ፥ ምሕረት አድራጊ፥ ጥሩ ፍሬ የሞላበት፥ አድልዎና ግብዝነት የሌለበት ነው። ሰላም ወዳድ ሰዎች ሰላምን ዘርተው የጽድቅን ፍሬ ይሰበስባሉ።

ያዕቆብ 3:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ወንድሞቼ ሆይ! ከእናንተ ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ፤ ምክንያቱም አስተማሪዎች የሆንን የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል ታውቃላችሁ። ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በንግግሩ የማይሰናከል ማንም ሰው ቢኖር እርሱ ሰውነቱን ሁሉ መቈጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው። ፈረሶች እንዲታዘዙልን ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናስገባለን፤ መላ ሰውነታቸውንም መምራት እንችላለን። መርከቦችንም ተመልከቱ፤ ምንም እንኳ እጅግ ትልቅና በኀይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ይመራቸዋል። እንዲሁም ምላስ ትንሽ የሰውነት ክፍል ሆና ሳለች በታላላቅ ነገሮች ትኩራራለች፤ ትልቅ ጫካ በትንሽ እሳት እንዴት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ አስተውሉ፤ ምላስም እንደ እሳት ናት፤ በሰውነት ክፍሎቻችን መካከል የምትገኝ የክፋት ዓለም ናት፤ ሰውነትን ሁሉ ታረክሳለች፤ ደግሞም የፍጥረትን ሩጫ ታቃጥላለች፤ ራሷም በገሃነም ትቃጠላለች። ማናቸውም ዓይነት አውሬ፥ አዕዋፍ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡና በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ መገራት ችለዋል፤ በሰውም ተገርተዋል። ነገር ግን ምላስን መግራት የሚችል ማንም ሰው የለም፤ የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት። በምላሳችን ጌታንና አብን እንባርካለን፥ በእርሷም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ፤ ወንድሞቼ ሆይ! ይህ ሊሆን አይገባም። ከአንድ ምንጭ ጣፋጭ ውሃና መራራ ውሃ ይመነጫልን? ወንድሞቼ ሆይ! የበለስ ዛፍ የወይራን ፍሬ ሊያፈራ ይችላልን? ወይስ የወይን ተክል የበለስ ፍሬ ሊያፈራ ይችላልን? እንዲሁም ከጨው ውሃ ጣፋጭ ውሃ ሊገኝ አይችልም። ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ የሆነ ማን ነው? በመልካም አኗኗር ሥራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። ነገር ግን መራራ ቅናትና ራስ ወዳድነት በልባችሁ ቢኖር ኩራት አይሰማችሁ፤ በእውነትም ላይ አትዋሹ። እንዲህ ያለችዋ ጥበብ ከላይ አይደለችም፤ ነገር ግን ምድራዊ፥ ሥጋዊና አጋንንታዊ ናት። ቅናትና ራስ ወዳድነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ ይኖራሉ። ከላይ የሆነችው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ ቀጥሎም ሰላም ወዳድ፥ ደግ፥ እሺ ባይ፥ ምሕረትና መልካም ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉ በሰላም ይዘራል።