ያዕቆብ 2:5-8
ያዕቆብ 2:5-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ። ባለ ጠጎቹ የሚያስጨንቁአችሁ አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤትም የሚጎትቱአችሁ እነርሱ አይደሉምን? የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን? ነገር ግን መጽሐፍ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤” እንደሚል የንጉሥን ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ፤
ያዕቆብ 2:5-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጠጋ እንዲሆኑና እርሱን ለሚወድዱም ተስፋ የተሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ፤ እናንተን የሚያስጨንቋችሁ ሀብታሞች አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ እነርሱ አይደሉምን? በእናንተ የተጠራውን ክቡር የሆነውን ስም የሚሳደቡ እነርሱ አይደሉምን? በመጽሐፍ፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” ተብሎ የተጻፈውን ክቡር ሕግ ብትፈጽሙ፣ መልካም እያደረጋችሁ ነው።
ያዕቆብ 2:5-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድሆችን አዋረዳችሁ። ባለ ጠጎቹ የሚያስጨንቁአችሁ አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤትም የሚጎትቱአችሁ እነርሱ አይደሉምን? የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን? ነገር ግን መጽሐፍ፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ እንደሚል የንጉሥን ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ፤
ያዕቆብ 2:5-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ሀብታሞች እንዲሆኑና እርሱን ለሚወዱት ተስፋ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድኾችን ትንቃላችሁ፤ የሚጨቊኑአችሁና ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ ሀብታሞች አይደሉምን? እናንተ የምትጠሩበትን ያን ክቡር ስም የሚሰድቡስ እነርሱ አይደሉምን? “ሰውን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ።
ያዕቆብ 2:5-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጸጋ እንዲሆኑና እርሱን ለሚወዱም ተስፋ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ፤ እናንተን የሚያስጨንቋችሁ ሀብታሞች አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ እነርሱ አይደሉምን? እናንተ የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን? በመጽሐፍ፥ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ተብሎ የተጻፈውን ንጉሣዊ ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ።