ያዕቆብ 2:14-25

ያዕቆብ 2:14-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ወንድሞቼ ሆይ! እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥ ከእናንተ አንዱም “በደኅና ሂዱ፤ እሳት ሙቁ፤ ጥገቡም፤” ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው “አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ፤” ይላል። እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጡማል። አንተ ከንቱ ሰው! እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን? መጽሐፍም “አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት፤” ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ። ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?

ያዕቆብ 2:14-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ወንድሞቼ ሆይ፤ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል፣ ሥራ ግን ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው ይችላልን? አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ ዐጥተው፣ ከእናንተ መካከል አንዱ፣ “በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ” ቢላቸው፣ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፣ ምን ይጠቅማቸዋል? እንዲሁ ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው “አንተ እምነት አለህ፤ እኔ ሥራ አለኝ።” እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል። አንድ እግዚአብሔር እንዳለ ታምናለህ፤ መልካም ነው፤ አጋንንትም ይህንኑ ያምናሉ፤ በፍርሀትም ይንቀጠቀጣሉ። አንተ ከንቱ ሰው! እምነት ያለ ሥራ ዋጋ የሌለው መሆኑን ለማወቅ ማስረጃ ትፈልጋለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይሥሐቅን በመሠዊያው ላይ ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? በዚህም፣ እምነት ከሥራው ጋራ ዐብሮ ይሠራ እንደ ነበር ታያለህ፤ እምነትም በሥራ ፍጹም ሆነ። “አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ተፈጸመ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ። እንግዲህ ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። እንዲሁም ጋለሞታዪቱ ረዓብ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?

ያዕቆብ 2:14-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ወንድሞቼ ሆይ፥ እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥ ከእናንተ አንዱም፦ በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው፦ አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፥ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል። እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል። አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን? መጽሐፍም፦ አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ። ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?

ያዕቆብ 2:14-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ወንድሞቼ ሆይ! ሰው እምነት አለኝ ቢል፥ ነገር ግን እምነቱን በመልካም ሥራ ባይገልጥ ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ለምሳሌ የሚለብሱትና የሚመገቡት የሌላቸው ወንድሞችና እኅቶች ቢኖሩ፥ ከእናንተ አንዱ ለኑሮአቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሳይሰጣቸው “በሰላም ሂዱ! ይሙቃችሁ! ጥገቡ!” ቢላቸው ምን ይጠቅማቸዋል? ከመልካም ሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው። ነገር ግን “አንተ እምነት አለህ፤ እኔም መልካም ሥራ አለኝ” የሚል ቢኖር፥ “እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም በሥራዬ እምነቴን አሳይሃለሁ” እለዋለሁ። አንተ “አንድ እግዚአብሔር አለ” ብለህ ታምናለህ፤ ይህም መልካም ነው፤ ማመንማ አጋንንትም ያምናሉ፤ በፍርሃትም ይንቀጠቀጣሉ። አንተ ሞኝ! እምነት ያለ ሥራ ፍሬቢስ መሆኑን ታያለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበው ጊዜ የጸደቀው በሥራ አይደለምን? ስለዚህ እምነት ከሥራው ጋር አብሮ እንደ ነበርና እምነትም በሥራ ፍጹም እንደ ሆነ ታያለህን? በቅዱስ መጽሐፍ “አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ፤ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” የተባለው ቃል ተፈጸመ፤ በዚህ ሁኔታ አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ። እንግዲህ ሰው የሚጸድቀው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም ጭምር መሆኑን ታያለህ። አመንዝራይቱ ረዓብ የእስራኤልን መልእክተኞች በቤትዋ በተቀበለች ጊዜና በሌላም መንገድ እንዲሄዱ ባደረገቻቸው ጊዜ እርስዋስ በሥራዋ ጸድቃ የለምን?

ያዕቆብ 2:14-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ወንድሞቼ ሆይ! አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ ቢያጡና፥ ከእናንተ መካከል አንዱ፥ “በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ” ቢላቸው፥ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፥ ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ከሥራ የተለየ እምነት በራሱ የሞተ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው “አንተ እምነት አለህ፤ እኔ ሥራ አለኝ” ቢል፤ እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ። አንድ እግዚአብሔር እንዳለ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንትም ቢሆኑ ይህንኑ ያምናሉ፤ በፍርሃትም ይንቀጠቀጣሉ። አንተ ከንቱ ሰው! እምነት ያለ ሥራ ዋጋ የሌለው መሆኑን ለማወቅ ማስረጃ ትፈልጋለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ላይ ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? ስለዚህ እምነት ከሥራው ጋር አብሮ እንደ ነበርና እምነትም በሥራ ፍጹም እንደሆነ ታያለህን? “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ተፈጸመ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ። እንግዲህ ሰው የሚጸድቀው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም እንደሆነ ታያለህን? እንዲሁም አመንዝራይቱ ረዓብ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በላከቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?