ያዕቆብ 2:1-9

ያዕቆብ 2:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ወንድሞቼ ሆይ! በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድኻ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ “አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ፤” ብትሉት፥ ድኻውንም “አንተስ ወደዚያ ቁም” ወይም “ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ፤” ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ። ባለ ጠጎቹ የሚያስጨንቁአችሁ አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤትም የሚጎትቱአችሁ እነርሱ አይደሉምን? የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን? ነገር ግን መጽሐፍ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤” እንደሚል የንጉሥን ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ፤ ለሰው ፊት ግን ብታደሉ ኀጢአትን ትሠራላችሁ፤ ሕግም እንደ ተላላፊዎች ይወቅሳችኋል።

ያዕቆብ 2:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ወንድሞቼ ሆይ፤ ክቡር በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ እንደ መሆናችሁ አድልዎ አታድርጉ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና ያማረ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢመጣ እንዲሁም ያደፈ ልብስ የለበሰ ድኻ ሰው ቢገባ፣ ያማረ ልብስ ለለበሰው የተለየ አክብሮት በማሳየት፣ “ለአንተ የሚሆን መልካም ስፍራ ይኸውልህ” ብትሉትና ድኻውን ሰው ግን፣ “አንተ በዚያ ቁም” ወይም “ከእግሬ በታች በወለሉ ላይ ተቀመጥ” ብትሉት፣ በመካከላችሁ አድልዎ ማድረጋችሁ አይደለምን? ደግሞስ በክፉ ሐሳብ የተያዛችሁ ፈራጆች መሆናችሁ አይደለምን? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጠጋ እንዲሆኑና እርሱን ለሚወድዱም ተስፋ የተሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ፤ እናንተን የሚያስጨንቋችሁ ሀብታሞች አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ እነርሱ አይደሉምን? በእናንተ የተጠራውን ክቡር የሆነውን ስም የሚሳደቡ እነርሱ አይደሉምን? በመጽሐፍ፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” ተብሎ የተጻፈውን ክቡር ሕግ ብትፈጽሙ፣ መልካም እያደረጋችሁ ነው። አድልዎ ብታደርጉ ግን ኀጢአት መሥራታችሁ ነው፤ በሕግም ፊት እንደ ሕግ ተላላፊዎች ትቈጠራላችሁ፤

ያዕቆብ 2:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ፦ አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም፦ አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድሆችን አዋረዳችሁ። ባለ ጠጎቹ የሚያስጨንቁአችሁ አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤትም የሚጎትቱአችሁ እነርሱ አይደሉምን? የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን? ነገር ግን መጽሐፍ፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ እንደሚል የንጉሥን ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ፤ ለሰው ፊት ግን ብታደሉ ኃጢአትን ትሠራላችሁ፥ ሕግም እንደ ተላላፊዎች ይወቅሳችኋል።

ያዕቆብ 2:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ወንድሞቼ ሆይ! በክብር ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ ከሆናችሁ አንዱ ከሌላው ይበልጣል በማለት በሰው መካከል አድልዎ አታድርጉ። ለምሳሌ ሁለት ሰዎች ወደምትሰበሰቡበት ቦታ ይመጣሉ፤ አንደኛው በጣቱ የወርቅ ቀለበት ያደረገና የሚያምር ጌጠኛ ልብስ የለበሰ ሀብታም ነው፤ ሌላው ያደፈ አሮጌ ልብስ የለበሰ ድኻ ነው፤ የሚያምር ጌጠኛ ልብስ የለበሰውን ሰው በማክበር “በዚህ በመልካሙ ቦታ ተቀመጥ” ትሉታላችሁ። ድኻውን ግን “አንተስ እዚያ ቁም፤ ወይም በእግሬ ሥር ተቀመጥ” ትሉታላችሁ፤ ታዲያ፥ በዚህ ዐይነት በመካከላችሁ ልዩነት እንደምታደርጉና የአድልዎ ፍርድ እንደምትፈርዱ አይታያችሁምን? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ሀብታሞች እንዲሆኑና እርሱን ለሚወዱት ተስፋ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድኾችን ትንቃላችሁ፤ የሚጨቊኑአችሁና ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ ሀብታሞች አይደሉምን? እናንተ የምትጠሩበትን ያን ክቡር ስም የሚሰድቡስ እነርሱ አይደሉምን? “ሰውን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ። በሰዎች መካከል ልዩነት ብታደርጉ ግን ኃጢአት ትሠራላችሁ፤ ሕግን በመተላለፋችሁም ትወቀሳላችሁ።

ያዕቆብ 2:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ወንድሞቼ ሆይ! ክቡር በሆነው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ በመሆናችሁ፥ አድልዎን አታድርጉ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና ያማረ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤያችሁ ቢመጣ እንዲሁም ያደፈ ልብስ የለበሰ ድኻ ሰው ቢገባ፥ ያማረ ልብስ ለለበሰው የተለየ አክብሮት በማሳየት፥ “ለአንተ የሚሆን መልካም መቀመጫ ይኸውልህ” ብትሉትና ድኻውን ሰው ግን፥ “አንተ በዚያ ቁም” ወይም “ከእግሬ በታች በወለሉ ላይ ተቀመጥ” ብትሉት፥ በመካከላችሁ አድልዎ ማድረጋችሁ አይደለምን? ደግሞስ በክፉ ሐሳብ የተያዛችሁ ፈራጆች መሆናችሁ አይደለምን? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጸጋ እንዲሆኑና እርሱን ለሚወዱም ተስፋ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ፤ እናንተን የሚያስጨንቋችሁ ሀብታሞች አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ እነርሱ አይደሉምን? እናንተ የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን? በመጽሐፍ፥ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ተብሎ የተጻፈውን ንጉሣዊ ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ። አድልዎ ብታደርጉ ግን ኃጢአት መሥራታችሁ ነው፤ እንደ ሕግ ተላላፊዎችም ትቈጠራላችሁ፤