ያዕቆብ 2:1-26

ያዕቆብ 2:1-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ወንድሞቼ ሆይ! በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድኻ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ “አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ፤” ብትሉት፥ ድኻውንም “አንተስ ወደዚያ ቁም” ወይም “ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ፤” ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ። ባለ ጠጎቹ የሚያስጨንቁአችሁ አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤትም የሚጎትቱአችሁ እነርሱ አይደሉምን? የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን? ነገር ግን መጽሐፍ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤” እንደሚል የንጉሥን ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ፤ ለሰው ፊት ግን ብታደሉ ኀጢአትን ትሠራላችሁ፤ ሕግም እንደ ተላላፊዎች ይወቅሳችኋል። ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ፥ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል፤ “አታመንዝር” ያለው ደግሞ “አትግደል” ብሎአልና፤ ባታመነዝርም፥ ነገር ግን ብትገድል፥ ሕግን ተላላፊ ሆነሃል። በነጻነት ሕግ ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው ሰዎች እንዲህ ተናገሩ፤ እንዲህም አድርጉ። ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና፤ ምሕረትም በፍርድ ላይ ይመካል። ወንድሞቼ ሆይ! እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥ ከእናንተ አንዱም “በደኅና ሂዱ፤ እሳት ሙቁ፤ ጥገቡም፤” ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው “አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ፤” ይላል። እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጡማል። አንተ ከንቱ ሰው! እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን? መጽሐፍም “አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት፤” ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ። ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።

ያዕቆብ 2:1-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ወንድሞቼ ሆይ፤ ክቡር በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ እንደ መሆናችሁ አድልዎ አታድርጉ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና ያማረ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢመጣ እንዲሁም ያደፈ ልብስ የለበሰ ድኻ ሰው ቢገባ፣ ያማረ ልብስ ለለበሰው የተለየ አክብሮት በማሳየት፣ “ለአንተ የሚሆን መልካም ስፍራ ይኸውልህ” ብትሉትና ድኻውን ሰው ግን፣ “አንተ በዚያ ቁም” ወይም “ከእግሬ በታች በወለሉ ላይ ተቀመጥ” ብትሉት፣ በመካከላችሁ አድልዎ ማድረጋችሁ አይደለምን? ደግሞስ በክፉ ሐሳብ የተያዛችሁ ፈራጆች መሆናችሁ አይደለምን? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጠጋ እንዲሆኑና እርሱን ለሚወድዱም ተስፋ የተሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ፤ እናንተን የሚያስጨንቋችሁ ሀብታሞች አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ እነርሱ አይደሉምን? በእናንተ የተጠራውን ክቡር የሆነውን ስም የሚሳደቡ እነርሱ አይደሉምን? በመጽሐፍ፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” ተብሎ የተጻፈውን ክቡር ሕግ ብትፈጽሙ፣ መልካም እያደረጋችሁ ነው። አድልዎ ብታደርጉ ግን ኀጢአት መሥራታችሁ ነው፤ በሕግም ፊት እንደ ሕግ ተላላፊዎች ትቈጠራላችሁ፤ ምክንያቱም ሕግን ሁሉ የሚፈጽም ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ቢኖር፣ ሁሉን እንደ ተላለፈ ይቈጠራል። “አታመንዝር” ያለ እርሱ ራሱ “አትግደልም” ብሏልና። ባታመነዝር፣ ነገር ግን ብትገድል፣ ሕግ ተላላፊ ሆነሃል። ስትናገሩም ሆነ ስታደርጉ ነጻነት በሚሰጠው ሕግ እንደሚፈረድባቸው ሰዎች ሁኑ፤ ምክንያቱም ምሕረት ያላደረገ ሁሉ ያለ ምሕረት ይፈረድበታል፤ ምሕረት በፍርድ ላይ ያይላል። ወንድሞቼ ሆይ፤ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል፣ ሥራ ግን ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው ይችላልን? አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ ዐጥተው፣ ከእናንተ መካከል አንዱ፣ “በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ” ቢላቸው፣ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፣ ምን ይጠቅማቸዋል? እንዲሁ ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው “አንተ እምነት አለህ፤ እኔ ሥራ አለኝ።” እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል። አንድ እግዚአብሔር እንዳለ ታምናለህ፤ መልካም ነው፤ አጋንንትም ይህንኑ ያምናሉ፤ በፍርሀትም ይንቀጠቀጣሉ። አንተ ከንቱ ሰው! እምነት ያለ ሥራ ዋጋ የሌለው መሆኑን ለማወቅ ማስረጃ ትፈልጋለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይሥሐቅን በመሠዊያው ላይ ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? በዚህም፣ እምነት ከሥራው ጋራ ዐብሮ ይሠራ እንደ ነበር ታያለህ፤ እምነትም በሥራ ፍጹም ሆነ። “አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ተፈጸመ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ። እንግዲህ ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። እንዲሁም ጋለሞታዪቱ ረዓብ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ፣ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው።

ያዕቆብ 2:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ፦ አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም፦ አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድሆችን አዋረዳችሁ። ባለ ጠጎቹ የሚያስጨንቁአችሁ አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤትም የሚጎትቱአችሁ እነርሱ አይደሉምን? የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን? ነገር ግን መጽሐፍ፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ እንደሚል የንጉሥን ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ፤ ለሰው ፊት ግን ብታደሉ ኃጢአትን ትሠራላችሁ፥ ሕግም እንደ ተላላፊዎች ይወቅሳችኋል። ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ፥ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል፤ አታመንዝር ያለው ደግሞ፦ አትግደል ብሎአልና፤ ባታመነዝርም፥ ነገር ግን ብትገድል፥ ሕግን ተላላፊ ሆነሃል። በነጻነት ሕግ ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው ሰዎች እንዲህ ተናገሩ፥ እንዲህም አድርጉ። ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና፤ ምሕረትም በፍርድ ላይ ይመካል። ወንድሞቼ ሆይ፥ እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥ ከእናንተ አንዱም፦ በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው፦ አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፥ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል። እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል። አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን? መጽሐፍም፦ አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ። ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።

ያዕቆብ 2:1-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ወንድሞቼ ሆይ! በክብር ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ ከሆናችሁ አንዱ ከሌላው ይበልጣል በማለት በሰው መካከል አድልዎ አታድርጉ። ለምሳሌ ሁለት ሰዎች ወደምትሰበሰቡበት ቦታ ይመጣሉ፤ አንደኛው በጣቱ የወርቅ ቀለበት ያደረገና የሚያምር ጌጠኛ ልብስ የለበሰ ሀብታም ነው፤ ሌላው ያደፈ አሮጌ ልብስ የለበሰ ድኻ ነው፤ የሚያምር ጌጠኛ ልብስ የለበሰውን ሰው በማክበር “በዚህ በመልካሙ ቦታ ተቀመጥ” ትሉታላችሁ። ድኻውን ግን “አንተስ እዚያ ቁም፤ ወይም በእግሬ ሥር ተቀመጥ” ትሉታላችሁ፤ ታዲያ፥ በዚህ ዐይነት በመካከላችሁ ልዩነት እንደምታደርጉና የአድልዎ ፍርድ እንደምትፈርዱ አይታያችሁምን? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ሀብታሞች እንዲሆኑና እርሱን ለሚወዱት ተስፋ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድኾችን ትንቃላችሁ፤ የሚጨቊኑአችሁና ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ ሀብታሞች አይደሉምን? እናንተ የምትጠሩበትን ያን ክቡር ስም የሚሰድቡስ እነርሱ አይደሉምን? “ሰውን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ። በሰዎች መካከል ልዩነት ብታደርጉ ግን ኃጢአት ትሠራላችሁ፤ ሕግን በመተላለፋችሁም ትወቀሳላችሁ። ሰው ከትእዛዞች አንዱን አፍርሶ የቀሩትን ሁሉ ቢፈጽም እንኳ ሁሉንም እንዳፈረሰ ይቈጠራል። “አታመንዝር” ያለው ጌታ እንዲሁም “አትግደል” ብሎአል፤ ስለዚህ ባታመነዝርም እንኳ ከገደልክ ሕግን አፍርሰሃል። ነጻነትን በሚያስገኘው ሕግ ፊት ቀርበው እንደሚዳኙት ሰዎች ተናገሩ፤ እንዲሁም ሥሩ። የእግዚአብሔር ፍርድ ምሕረት ለማያደርግ ሰው ምሕረት አያደርግም፤ ሆኖም ምሕረት ፍርድን ያሸንፋል። ወንድሞቼ ሆይ! ሰው እምነት አለኝ ቢል፥ ነገር ግን እምነቱን በመልካም ሥራ ባይገልጥ ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ለምሳሌ የሚለብሱትና የሚመገቡት የሌላቸው ወንድሞችና እኅቶች ቢኖሩ፥ ከእናንተ አንዱ ለኑሮአቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሳይሰጣቸው “በሰላም ሂዱ! ይሙቃችሁ! ጥገቡ!” ቢላቸው ምን ይጠቅማቸዋል? ከመልካም ሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው። ነገር ግን “አንተ እምነት አለህ፤ እኔም መልካም ሥራ አለኝ” የሚል ቢኖር፥ “እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም በሥራዬ እምነቴን አሳይሃለሁ” እለዋለሁ። አንተ “አንድ እግዚአብሔር አለ” ብለህ ታምናለህ፤ ይህም መልካም ነው፤ ማመንማ አጋንንትም ያምናሉ፤ በፍርሃትም ይንቀጠቀጣሉ። አንተ ሞኝ! እምነት ያለ ሥራ ፍሬቢስ መሆኑን ታያለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበው ጊዜ የጸደቀው በሥራ አይደለምን? ስለዚህ እምነት ከሥራው ጋር አብሮ እንደ ነበርና እምነትም በሥራ ፍጹም እንደ ሆነ ታያለህን? በቅዱስ መጽሐፍ “አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ፤ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” የተባለው ቃል ተፈጸመ፤ በዚህ ሁኔታ አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ። እንግዲህ ሰው የሚጸድቀው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም ጭምር መሆኑን ታያለህ። አመንዝራይቱ ረዓብ የእስራኤልን መልእክተኞች በቤትዋ በተቀበለች ጊዜና በሌላም መንገድ እንዲሄዱ ባደረገቻቸው ጊዜ እርስዋስ በሥራዋ ጸድቃ የለምን? አካል ያለ ነፍስ የሞተ ነው፤ እንዲሁም ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።

ያዕቆብ 2:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ወንድሞቼ ሆይ! ክቡር በሆነው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ በመሆናችሁ፥ አድልዎን አታድርጉ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና ያማረ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤያችሁ ቢመጣ እንዲሁም ያደፈ ልብስ የለበሰ ድኻ ሰው ቢገባ፥ ያማረ ልብስ ለለበሰው የተለየ አክብሮት በማሳየት፥ “ለአንተ የሚሆን መልካም መቀመጫ ይኸውልህ” ብትሉትና ድኻውን ሰው ግን፥ “አንተ በዚያ ቁም” ወይም “ከእግሬ በታች በወለሉ ላይ ተቀመጥ” ብትሉት፥ በመካከላችሁ አድልዎ ማድረጋችሁ አይደለምን? ደግሞስ በክፉ ሐሳብ የተያዛችሁ ፈራጆች መሆናችሁ አይደለምን? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጸጋ እንዲሆኑና እርሱን ለሚወዱም ተስፋ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ፤ እናንተን የሚያስጨንቋችሁ ሀብታሞች አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ እነርሱ አይደሉምን? እናንተ የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን? በመጽሐፍ፥ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ተብሎ የተጻፈውን ንጉሣዊ ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ። አድልዎ ብታደርጉ ግን ኃጢአት መሥራታችሁ ነው፤ እንደ ሕግ ተላላፊዎችም ትቈጠራላችሁ፤ ምክንያቱም ሕግን ሁሉ ብትፈጽሙ ነገር ግን በአንዱ ብትሰናከሉ፥ ሁሉን እንደ ተላለፋችሁ ይቈጠራል። “አታመንዝር” ያለ እርሱ ራሱ “አትግደል” ብሏል። ባታመነዝር፥ ነገር ግን ብትገድል፥ ሕግ ተላላፊ ሆነሃል። ስለዚህ ስትናገሩም ሆነ ስታደርጉ በነጻነት ሕግ እንደሚፈረድባቸው ሰዎች አድርጉ፤ ምሕረት ያላደረገ ሁሉ ያለ ምሕረት ይፈረድበታልና፤ ምሕረትም ፍርድን ያሸንፋል። ወንድሞቼ ሆይ! አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ ቢያጡና፥ ከእናንተ መካከል አንዱ፥ “በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ” ቢላቸው፥ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፥ ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ከሥራ የተለየ እምነት በራሱ የሞተ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው “አንተ እምነት አለህ፤ እኔ ሥራ አለኝ” ቢል፤ እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ። አንድ እግዚአብሔር እንዳለ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንትም ቢሆኑ ይህንኑ ያምናሉ፤ በፍርሃትም ይንቀጠቀጣሉ። አንተ ከንቱ ሰው! እምነት ያለ ሥራ ዋጋ የሌለው መሆኑን ለማወቅ ማስረጃ ትፈልጋለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ላይ ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? ስለዚህ እምነት ከሥራው ጋር አብሮ እንደ ነበርና እምነትም በሥራ ፍጹም እንደሆነ ታያለህን? “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ተፈጸመ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ። እንግዲህ ሰው የሚጸድቀው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም እንደሆነ ታያለህን? እንዲሁም አመንዝራይቱ ረዓብ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በላከቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ ሁሉ፥ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው።