ያዕቆብ 1:9-16
ያዕቆብ 1:9-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ያልፋልና። ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል። በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና። ማንም ሲፈተን “በእግዚአብሔር እፈተናለሁ፤” አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኀጢአትን ትወልዳለች፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! አትሳቱ።
ያዕቆብ 1:9-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዝቅ ያለው ወንድም ከፍ በማለቱ ይመካ። ባለጠጋውም ዝቅ በማለቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ይረግፋልና። ፀሓይ በነዲድ ሙቀቷ ወጥታ ሣሩን ታጠወልጋለችና፤ አበባው ይረግፋል፤ ውበቱም ይጠፋል፤ እንዲሁም ባለጠጋ ሰው፣ በዕለት ተግባሩ ሲዋትት ሳለ ይጠፋል። በፈተና የሚጸና ሰው ብፁዕ ነው፤ ምክንያቱም ፈተናን ሲቋቋም እግዚአብሔር ለሚወድዱት የሰጠውን ተስፋ፣ የሕይወትን አክሊል ያገኛል። ማንም ሲፈተን፣ “እግዚአብሔር ፈተነኝ” አይበል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፤ እርሱም ማንንም አይፈትንም፤ ነገር ግን እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞትም ከፀነሰች በኋላ ኀጢአትን ትወልዳለች፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ አትታለሉ።
ያዕቆብ 1:9-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ያልፋልና። ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል። በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና። ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ።
ያዕቆብ 1:9-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በኑሮው ዝቅተኛ የሆነ ወንድም እግዚአብሔር ከፍ ስለሚያደርገው ደስ ይበለው። የሰው ሀብት እንደ ሣር አበባ ስለሚረግፍ በኑሮው ከፍ ያለ ወንድም እግዚአብሔር በኑሮው ዝቅ ቢያደርገውም ደስ ይበለው፤ ፀሐይ ከሙቀቱ ጋር ሲወጣ ሣሩን ያደርቀዋል አበባውም ይረግፋል፤ ውበቱም ይጠፋል፤ እንዲሁም ሀብታም ሰው በሥራው ሲባክን ይጠፋል። ጌታ በቃል ኪዳኑ መሠረት ለወዳጆቹ የሚሰጠውን የሕይወት አክሊል ስለሚቀበል ፈተናን ታግሦ የሚጸና ሰው የተባረከ ነው። እግዚአብሔር በክፉ ነገር ስለማይፈተንና እንዲሁም እርሱ ማንንም ስለማይፈትን ሰው በሚፈተንበት ጊዜ “እግዚአብሔር ፈተነኝ” አይበል። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው የሚፈተነው በገዛ ራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ከዚህ በኋላ ምኞት ስትፀንስ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ስታድግ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! አትታለሉ!
ያዕቆብ 1:9-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዝቅ ያለው ወንድም ከፍ በማለቱ ይመካ፥ ሀብታምም እንደ ሣር አበባ ስለሚረግፍ በውርደቱ ይመካ። የፀሐይ ቃጠሎ በንዳዱ ሲወጣ ሣሩን ያደርቀዋል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የመልኩም ውበት ይጠፋል፤ እንዲሁ ሀብታም ሰው በመንገዱ ይዝላል። ጌታ ለሚወዱት ተስፋ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ተፈትኖ ይቀበላልና፥ በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው። ማንም ሲፈተን “እግዚአብሔር ፈተነኝ፤” አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! አትታለሉ!