ያዕቆብ 1:1-26 - Compare All Versions

ያዕቆብ 1:1-26 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የሆነው ያዕቆብ፤ ለተበተኑ ለዐሥራ ሁለቱ ነገዶች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞቼ ሆይ፤ ልዩ ልዩ መከራ ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት፤ ምክንያቱም የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ። ምንም የማይጐድላችሁ ፍጹማንና ምሉኣን እንድትሆኑ ትዕግሥት ሥራውን ይፈጽም። ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጐድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉም የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለርሱም ይሰጠዋል። ዳሩ ግን ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ ምክንያቱም የሚጠራጠር ሰው በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚናወጥ የባሕር ማዕበል ነው። ያ ሰው፣ ከጌታ አንዳች ነገር አገኛለሁ ብሎ አያስብ፤ እርሱ በሁለት ሐሳብ የተያዘና በመንገዱ ሁሉ የሚወላውል ነው። ዝቅ ያለው ወንድም ከፍ በማለቱ ይመካ። ባለጠጋውም ዝቅ በማለቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ይረግፋልና። ፀሓይ በነዲድ ሙቀቷ ወጥታ ሣሩን ታጠወልጋለችና፤ አበባው ይረግፋል፤ ውበቱም ይጠፋል፤ እንዲሁም ባለጠጋ ሰው፣ በዕለት ተግባሩ ሲዋትት ሳለ ይጠፋል። በፈተና የሚጸና ሰው ብፁዕ ነው፤ ምክንያቱም ፈተናን ሲቋቋም እግዚአብሔር ለሚወድዱት የሰጠውን ተስፋ፣ የሕይወትን አክሊል ያገኛል። ማንም ሲፈተን፣ “እግዚአብሔር ፈተነኝ” አይበል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፤ እርሱም ማንንም አይፈትንም፤ ነገር ግን እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞትም ከፀነሰች በኋላ ኀጢአትን ትወልዳለች፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ አትታለሉ። በጎ ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከላይ፣ ከሰማይ ብርሃናት አባት ይወርዳሉ፤ በርሱ ዘንድ መለዋወጥ፣ ከመዞር የተነሣ የሚያርፍ ጥላም የለም። የፍጥረቱ በኵራት እንድንሆን በገዛ ፈቃዱ በእውነት ቃል ወለደን። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ይህን አስተውሉ፤ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ፣ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያመጣምና። ስለዚህ ርኩሰትንና ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ክፋትን አስወግዳችሁ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን፣ በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በትሕትና ተቀበሉ። ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ ሆናችሁ ራሳችሁን አታታልሉ። ቃሉን የሚሰማ፣ ነገር ግን የሚለውን የማይፈጽም ሰው ፊቱን በመስተዋት እንደሚያይ ሰው ነው፤ ራሱንም አይቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል፤ ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ ተመልክቶ የሚጸና፣ የሰማውን የሚያደርግና የማይረሳ ሰው በሥራው ብሩክ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ፣ ልቡን እያሳተ ሃይማኖተኛ ነኝ የሚል ሰው፣ ራሱን ያታልላል፤ ሃይማኖቱም ከንቱ ነው።

ያዕቆብ 1:1-26 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

በዓለም ሁሉ ለተበተኑ ለዐሥራ ሁለቱ ነገዶች የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ከሆነው ከያዕቆብ የተላከ መልእክት፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞቼ ሆይ! ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ ደስ የሚያሰኙ ነገሮችን እንዳገኛችሁ አድርጋችሁ ቊጠሩ። የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥት የሚያስገኝላችሁ መሆኑን ታውቃላችሁ። በትዕግሥት መጽናታችሁ ምንም ሳይጐድልባችሁ ፍጹምና ሙሉ እንድትሆኑ የሚያበቃችሁ ይሁን። ከእናንተ መካከል ጥበብ የጐደለው ሰው ቢኖር እግዚአብሔርን ይለምን፤ እግዚአብሔርም ይሰጠዋል፤ እርሱ ምንም ቅር ሳይለው ለሁሉም በልግሥና የሚሰጥ ቸር አምላክ ነው። ነገር ግን ሰው ምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተናወጠ የባሕር ማዕበል ይመስላል። እንዲህ ዐይነቱ ሰው ከጌታ ምንም ነገር የሚያገኝ አይምሰለው። ይህም የሚሆነው ሁለት ሐሳብ ስላለውና በመንገዱም ስለሚያወላውል ነው። በኑሮው ዝቅተኛ የሆነ ወንድም እግዚአብሔር ከፍ ስለሚያደርገው ደስ ይበለው። የሰው ሀብት እንደ ሣር አበባ ስለሚረግፍ በኑሮው ከፍ ያለ ወንድም እግዚአብሔር በኑሮው ዝቅ ቢያደርገውም ደስ ይበለው፤ ፀሐይ ከሙቀቱ ጋር ሲወጣ ሣሩን ያደርቀዋል አበባውም ይረግፋል፤ ውበቱም ይጠፋል፤ እንዲሁም ሀብታም ሰው በሥራው ሲባክን ይጠፋል። ጌታ በቃል ኪዳኑ መሠረት ለወዳጆቹ የሚሰጠውን የሕይወት አክሊል ስለሚቀበል ፈተናን ታግሦ የሚጸና ሰው የተባረከ ነው። እግዚአብሔር በክፉ ነገር ስለማይፈተንና እንዲሁም እርሱ ማንንም ስለማይፈትን ሰው በሚፈተንበት ጊዜ “እግዚአብሔር ፈተነኝ” አይበል። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው የሚፈተነው በገዛ ራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ከዚህ በኋላ ምኞት ስትፀንስ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ስታድግ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! አትታለሉ! መልካም ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህም የሚመጣው እንደ ጥላ መዘዋወር ወይም መለዋወጥ ከሌለበት ከብርሃን አባት ከእግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር የፍጥረቱ ሁሉ መጀመሪያ እንድንሆን በገዛ ፈቃዱ በእውነት ቃል ወለደን። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ይህን አትርሱ፤ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፥ ለመናገርና ለቊጣም የዘገየ ይሁን። የሰው ቊጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያስገኝም። ስለዚህ ርኲሰትንና የክፋትንም ብዛት ሁሉ አስወግዳችሁ እግዚአብሔር በልባችሁ የተከለውንና ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን ቃል በትሕትና ተቀበሉ። ቃሉን በሥራ ላይ የምታውሉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያታለላችሁ ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ። ቃሉን ሰምቶ በሥራ ላይ የማያውለው ሰው የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት እንደሚያይ ሰው ነው፤ ይህ ሰው ፊቱን በመስተዋት ካየ በኋላ ይሄዳል፤ እንዴት እንደ ሆነም ወዲያውኑ ይረሳዋል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ መርምሮ በእርሱ የሚጸና፥ እርሱንም ሰምቶ መርሳት ሳይሆን፥ በሥራ ላይ የሚያውለው ሰው በሥራው የተባረከ ይሆናል። አንደበቱን ሳይቈጣጠር እግዚአብሔርን አመልካለሁ የሚል ሰው ራሱን ያታልላል፤ የእርሱም አምልኮ ከንቱ ነው።

ያዕቆብ 1:1-26 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))

የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለዐሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞቼ ሆይ! የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት፤ ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው። የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ያልፋልና። ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል። በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና። ማንም ሲፈተን “በእግዚአብሔር እፈተናለሁ፤” አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኀጢአትን ትወልዳለች፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! አትሳቱ። በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፤ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። ለፍጥረቱ የበኵራት ዐይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን። ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና። ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፤ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው።

ያዕቆብ 1:1-26 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው። የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ያልፋልና። ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል። በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና። ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ። በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን። ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና። ስለዚህ ርኵሰትና ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው።

ያዕቆብ 1:1-26 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))

የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ያዕቆብ ለተበተኑ ለዐሥራ ሁለቱ ነገዶች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞቼ ሆይ! ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ደስታ አድርጋችሁ ቁጠሩት፤ ምክንያቱም የእምነታችሁ መፈተን እንደሚያጸናችሁ ታውቃላችሁ፥ ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን እንድትሆኑ ጽናትም ሥራውን ይፈጽም። ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ ምክንያቱም የሚጠራጠር ሰው በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚነዋወጥ የባሕርን ማዕበል ነው። ያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች አገኛለሁ ብሎ ሊያስብ አይገባውም። በመንገዱ ሁሉ የሚወላውል ሁለት ሐሳብ ያለው ሰው ነው። ዝቅ ያለው ወንድም ከፍ በማለቱ ይመካ፥ ሀብታምም እንደ ሣር አበባ ስለሚረግፍ በውርደቱ ይመካ። የፀሐይ ቃጠሎ በንዳዱ ሲወጣ ሣሩን ያደርቀዋል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የመልኩም ውበት ይጠፋል፤ እንዲሁ ሀብታም ሰው በመንገዱ ይዝላል። ጌታ ለሚወዱት ተስፋ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ተፈትኖ ይቀበላልና፥ በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው። ማንም ሲፈተን “እግዚአብሔር ፈተነኝ፤” አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! አትታለሉ! መልካም ስጦታ ሁሉ፥ ፍጹምም በረከት ሁሉ፥ እንደ ጥላ መዘዋወር ወይም መለዋወጥ ከሌለበት ከላይ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። ለፍጥረቱ የበኵራት እንድንሆን በገዛ ፈቃዱ በእውነት ቃል ወለደን። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ይህን አትርሱ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፥ ለመናገርም የዘገየ፥ ለቁጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቁጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና። ስለዚህ ርኩሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያታለላችሁ፥ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማና የማያደርግ ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ፥ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው።