ኢሳይያስ 64:1-4
ኢሳይያስ 64:1-4 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሰማይን ብትከፍት ከአንተ የተነሣ ተራሮች ይንቀጠቀጣሉ፤ ይቀልጣሉም። አደሮ ማር በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ እንዲሁ ጠላቶችህን እሳት ትበላቸዋለች፤ ስምህም በእነርሱ ላይ ይታወቃል፤ አሕዛብም በፊትህ ይደነግጣሉ። የክብርህንም ሥራ ባደረግህ ጊዜ፥ ተራሮች በፊትህ ተንቀጠቀጡ። ከጥንት ጀምሮ ይቅርታህን ለሚጠባበቁ ምሕረትን ከምታደርግላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ አላየንም፤ አልሰማንምም።
ኢሳይያስ 64:1-4 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አቤቱ፤ ሰማያትን ቀድደህ ምነው በወረድህ! ምነዋ ተራሮች በፊትህ በተናወጡ! እሳት ሲለኰስ ጭራሮን እንደሚያቀጣጥል፣ ውሃንም እንደሚያፈላ፣ ስምህ በጠላቶችህ ዘንድ እንዲታወቅ ውረድ፤ መንግሥታትም በፊትህ እንዲንቀጠቀጡ አድርግ! እኛ ያልጠበቅነውን አስፈሪ ነገር ባደረግህ ጊዜ፣ አንተ ወረድህ፤ ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ። ከጥንት ጀምሮ፣ በተስፋ ለሚጠባበቁት የሚደርስላቸው፣ ከአንተ በቀር አምላክ እንዳለ ያየ ዐይን የለም፤ የሰማም ጆሮ የለም።
ኢሳይያስ 64:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ! እሳት ጭራሮውን እንደሚያቃጥል፥ እሳትም ውኃውን እንደሚያፈላ፥ ስምህ ለጠላቶችህ ይገለጥ ዘንድ፥ አህዛብም በፊትህ ይንቀጠቀጡ ዘንድ። ያልተጠባበቅነውን የክብርህን ሥራ ባደረግህ ጊዜ፥ ወረድህ ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ። ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላችው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክን አልሰሙም በጆሮአቸውም አልተቀበሉም ዓይንም አላየችም።
ኢሳይያስ 64:1-4 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ምነው ሰማያትን ከፍተህ ብትወርድ፤ ተራራዎችም አንተን አይተው ምነው በተንቀጠቀጡ፤ እሳት ደረቁን እንጨት በሚያጋይ ጊዜ ፍሙ የተጣደውን ውሃ እንደሚያፍለቀልቀው፥ ሕዝቦችም በአንተ መገለጥ እንዲንቀጠቀጡ ወርደህ ስምህ በጠላቶችህ ዘንድ እንዲታወቅ አድርግ! ከዚህ በፊትም መጥተህ እኛ ያልጠበቅናቸውን እጅግ አስፈሪ የሆኑ ነገሮችን በፈጸምክበት ጊዜ ተራራዎች አንተን አይተው በፍርሃት ተንቀጠቀጡ። ከጥንት ጀምሮ ተስፋቸውን በእርሱ አድርገው ለሚተማመኑበት ወገኖች እነዚያን ሁሉ ድንቅ ነገሮች ያደረገ አምላክ ከአንተ በቀር አልተሰማም፤ አልታየም፤ የተረዳም የለም።
ኢሳይያስ 64:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ምነው ሰማያትን ቀደህ ብትወርድ! ምነው ተራሮችም ቢናወጡ! እሳት ጭራሮውን እንደሚያቃጥል፥ እሳትም ውኃውን እንደሚያፈላ፥ ስምህ ለጠላቶችህ እንዲገለጥ፥ አሕዛብም በፊትህ እንዲንቀጠቀጡ፤ ያልተጠባበቅነውን የክብርህን ሥራ ባደረግህ ጊዜ፥ አንተ ወረድህ፥ ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ። ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ማንም አልሰሙም፥ የትኛውም ጆሮ አልተቀበለውም፥ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላችው ከአንተ አምላካችን በቀር ሌላ ማንም አላየውም።