ኢሳይያስ 53:3-12
ኢሳይያስ 53:3-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
መልኩም የተናቀ፥ ከሰውም ልጆች ሁሉ የተዋረደ፥ የተገረፈ ሰው፥ መከራንም የተቀበለ ነው፤ ፊቱንም መልሶአልና አቃለሉት፥ አላከበሩትምም። እርሱ ግን በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ ስለ እኛም ታመመ፤ እኛም እንደ ታመመ፥ እንደ ተገረፈም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ ኀጢአታችን ቈሰለ፤ ስለ በደላችንም ታመመ፤ የሰላማችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፤ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም ስለ ኀጢአታችን ለሞት አሳልፎ ሰጠው። እርሱ ግን በመከራው ጊዜ አፉን አልከፈተም፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዷልና ልደቱን ማን ይናገራል? ስለ ሕዝቤ ኀጢአት ለሞት ደረሰ። ክፉዎችንም ስለ መቃብሩ፥ ባለጸጎችንም ስለ ሞቱ እሰጣለሁ፤ ኀጢአትን አላደረገምና፥ ከአፉም ሐሰት አልተገኘበትምና። እግዚአብሔር ከግርፋቱ ያነጻው ዘንድ ፈቀደ፤ ስለ ኀጢአት መሥዋዕትን ብታቀርቡ ሰውነታችሁ ረዥም ዕድሜ ያለውን ዘር ታያለች። እግዚአብሔርም ከሰውነቱ ሕማምን ያርቅ ዘንድ ይወዳል፤ ብርሃንንም ያሳየዋል፤ በጥበቡም ይለየዋል፤ ለጽድቅና ለበጎ ነገር የሚገዛውን ጻድቁን ያጸድቀዋል። የብዙዎችንም ኀጢአታቸውን እርሱ ይደመስሳል። ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፤ ከኀያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዐመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ተሸከመ፤ ስለ ኀጢአታቸውም ተሰጠ።
ኢሳይያስ 53:3-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በሰዎች የተናቀና የተጠላ፣ የሕማም ሰውና ሥቃይ ያልተለየው ነበር። ሰዎች ፊታቸውን እንደሚያዞሩበት ዐይነት፣ የተናቀ ነበር፤ እኛም አላከበርነውም። በርግጥ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ እኛ ግን በእግዚአብሔር እንደ ተመታ፣ እንደ ተቀሠፈ፣ እንደ ተሠቃየም ቈጠርነው። ነገር ግን እርሱ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ በርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤ በርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጐድን፤ እግዚአብሔርም፣ የሁላችንን በደል በርሱ ላይ ጫነው። ተጨነቀ፤ ተሠቃየም፤ ነገር ግን አፉን አልከፈተም፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ በሸላቾች ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኀጢአት ተመትቶ፣ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ፣ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? በአፉም ሳያታልል፣ ዐመፃም ሳያደርግ፣ አሟሟቱ ከክፉዎች፣ መቃብሩም ከባለጠጎች ጋራ ሆነ። መድቀቁና መሠቃየቱ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፤ እግዚአብሔር ነፍሱን የኀጢአት መሥዋዕት ቢያደርገውም እንኳ፣ ዘሩን ያያል፤ ዕድሜውም ይረዝማል፤ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ሥቃይ በኋላ፣ የሕይወት ብርሃን ያያል፤ ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬ በዕውቀቱ ብዙዎቹን ያጸድቃል፤ መተላለፋቸውንም ይሸከማል። ስለዚህ ድርሻውን ከታላላቆች ጋራ እሰጠዋለሁ፤ ምርኮውን ከኀያላን ጋራ ይካፈላል፤ እስከ ሞት ድረስ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠቱ፣ ከክፉ አድራጊዎችም ጋራ በመቈጠሩ፣ የብዙዎችን ኀጢአት ተሸከመ፤ ስለ ዐመፀኞችም ማለደ።
ኢሳይያስ 53:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፥ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም። በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፥ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፥ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፥ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፥ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ። ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፥ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፥ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ፥ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር። እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፥ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፥ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውንም ይሸከማል። ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፥ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፥ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።
ኢሳይያስ 53:3-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እርሱም በሌሎች የተናቀና የተጠላ ነበር፤ እርሱ የመከራና የሐዘን ሰው ነበር። ሰዎች ፊታቸውን እስኪያዞሩበት ድረስ እርሱ የተናቀ፥ እኛም ያላከበርነው ሰው ነበር። “በእውነት እርሱ ደዌአችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ እኛ ግን በእግዚአብሔር ተመትቶ እንደ ወደቀና እንደ ቈሰለ አድርገን ቈጠርነው። እርሱ ግን ተወግቶ የቈሰለው ስለ መተላለፋችን ነው፤ የደቀቀውም ስለ በደላችን ነው፤ እኛ የዳንነው እርሱ በተቀበለው ቅጣት ነው፤ በእርሱም ቊስል እኛ ተፈወስን። ሁላችንም እንደ በጎች ባዝነን ነበር፤ ሁላችንም ወደ ራሳችን መንገድ ሄደን ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሁላችንንም በደል በእርሱ ላይ አኖረ። “እርሱ ግፍና ችግር ደረሰበት፤ ይሁን እንጂ ምንም አልተናገረም፤ ለመታረድ እንደሚወሰድ ጠቦትና በሸላቾቹ ፊት ጸጥ እንደሚል በግ ዝም አለ እንጂ ምንም አልተናገረም። በእርሱ ላይ የተዛባ ፍርድ ተወስኖበት ተወሰደ፤ የወደፊትስ ሁኔታውን ማስተዋል የሚችል ማነው? ሆኖም ስለ ሕዝቤ መተላለፍ ተመታ፤ ከሕያዋንም ዓለም ተወገደ። ምንም ዐመፅ ሳይፈጽም፥ በአንደበቱም ሐሰት ሳይገኝበት፥ በሞቱ ከክፉ አድራጊዎች ጋር ተቈጠረ፤ በባለጸጋም መቃብር ተቀበረ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ይሁን እንጂ በሕማም አደቀው ዘንድ የእኔ ፈቃድ ነበር፤ ሕይወቱን የበደል መሥዋዕት አድርጎ በሚያቀርብበት ጊዜ ዘመኑ ተራዝሞ ብዙ ትውልድ ያያል፤ በእርሱም አማካይነት የእኔ ፈቃድ ይፈጸማል። ጻድቁ አገልጋዬ ከሥቃዩ በኋላ የሕይወትን ብርሃን አይቶ ይረካል፤ በዕውቀቱም ብዙዎችን ያጸድቃል፤ በደላቸውንም ይሸከማል። ሕይወቱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ፤ ከክፉ አድራጊዎችም ጋር ተቈጠረ፤ ይሁን እንጂ እርሱ የብዙዎችን ኃጢአት ተሸከመ፤ ለበደለኞችም ማለደ፤ ስለዚህ እኔ ከታላላቆቹ ጋር ድርሻ እንዲኖረውና ከኀያላን ጋር ምርኮን እንዲካፈል አደርገዋለሁ።”
ኢሳይያስ 53:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው፥ ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚያዞርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም። በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ እኛ ግን እንደ ተመታ፥ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ፥ እንደ ስቃይተኛም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፤ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ ጌታም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ። ተጨነቀ፥ ተሰቀየም፥ አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? አሟሟቱን ከክፉዎችም ጋር፥ መቃብሩን ከባለጠጎችም ጋር አደረጉ፤ ግፍ ግን አላደረገም ነበር፤ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር። ጌታም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የጌታም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ሥቃይ ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ አገልጋዬ በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፤ ኃጢአታቸውንም ይሸከማል። ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአል፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአል፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።