ኢሳይያስ 41:17-20
ኢሳይያስ 41:17-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ድሆችና ምስኪኖች ውኃ ይሻሉ፤ አያገኙምም፤ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፤ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እሰማቸዋለሁ፤ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም። በተራሮች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፤ ምድረ በዳውን ለውኃ መቆሚያ፥ የተጠማችውንም ምድር ለውኃ መፍለቂያ አደርጋለሁ። በምድረ በዳ ዝግባውንና ግራሩን፥ ባርሰነቱንና የዘይቱን ዛፍ አበቅላለሁ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር እጅ ይህን ሁሉ እንደ ሠራ፥ የእስራኤልም ቅዱስ ይህን እንደ አሳየ ያውቁ ዘንድ፥ ያስተውሉም ዘንድ፥ ይረዱም ዘንድ፥ ያምኑም ዘንድ ነው።
ኢሳይያስ 41:17-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ ዳሩ ግን ምንም አያገኙም፤ ጕረሯቸው በውሃ ጥም ደርቋል። ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር እመልስላቸዋለሁ፤ እኔ የእስራኤል አምላክ አልተዋቸውም። በተራቈቱ ኰረብቶች ላይ ወንዞችን፣ በሸለቆዎች ውስጥ ምንጮችን አፈልቃለሁ። ምድረ በዳውን የውሃ ኵሬ፣ የተጠማውን ምድር የውሃ ምንጭ አደርጋለሁ። በምድረ በዳ፣ ዝግባን፣ ግራርን፣ ባርሰነትንና ወይራን አበቅላለሁ፤ በበረሓ፣ ጥድን፣ አስታንና ሸውሸዌን በአንድነት እተክላለሁ። ስለዚህ ሰዎች ያያሉ፤ ያውቃሉ፤ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ፣ የእስራኤል ቅዱስ እንደ ፈጠረው፣ በአንድነት ይገነዘባሉ፤ ያስተውላሉም።
ኢሳይያስ 41:17-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ድሆችና ምስኪኖችም ውኃ ይሻሉ አያገኙምም፥ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፥ እኔ እግዚአብሔር እሰማቸዋለሁ፥ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም። በወናዎቹ ኮረብቶች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆዎችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፥ ምድረ በዳውን ለውኃ መቆሚያ፥ የጥማትንም ምድር ለውሃ መፍለቂያ አደርጋለሁ። የእግዚዘብሔር እጅ ይህን እንደ ሠራች፥ የእስራኤልም ቅዱስ እንደ ፈጠረው ያዩ ዘንድ ያውቁም ዘንድ ያስቡም ዘንድ በአንድነትም ያስተውሉ ዘንድ፥ በምድረ በዳ ዝግባውንና ግራሩን ባርሰነቱንና የዘይቱን ዛፍ አበቅላለሁ፥ በበረሃውም ጥዱንና አስታውን ወይራውንም በአንድነት አኖራለሁ።
ኢሳይያስ 41:17-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ አያገኙም፤ ጒሮሮአቸው ከጥማት የተነሣ ሲደርቅ፥ እኔ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን እሰማለሁ፤ እኔም የእስራኤል አምላክ ከቶ አልተዋቸውም። በደረቁ ኰረብቶች ላይ ወንዞች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤ በሸለቆዎችም ውስጥ የውሃ ምንጮች ያልፋሉ፤ በረሓዎችንም የኲሬ ውሃ መከማቻ እንዲሆኑ አደርጋቸዋለሁ፤ ደረቁም ምድር የምንጭ ውሃ መፍሰሻ ይሆናል። የሊባኖስ ዛፎችን፥ የግራር እንጨቶችን፥ ባርሰነቱንና የወይራ ዛፎችን በበረሓ አበቅላለሁ፤ በምድረ በዳ ዝግባ፥ አስታና ጥድ፥ ወይራ የሞላበት ደን አበቅላለሁ። ይህን የማደርገው የእኔ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገና እኔም የእስራኤል ቅዱስ እንደ ፈጠርኩት ሁሉም አይተው ያውቁ ዘንድ፥ አስተውለውም ይረዱ ዘንድ ነው።”
ኢሳይያስ 41:17-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ድሆችና ምስኪኖችም ውኃ ይሻሉ አያገኙምም፥ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፤ እኔ ጌታ እሰማቸዋለሁ፥ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም። በወናዎቹ ኮረብቶች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆዎችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፤ ምድረ በዳውን ለውኃ ማከማቻ፥ የጥማትንም ምድር ለውሃ መፍለቂያ አደርጋለሁ። በምድረ በዳ፤ ዝግባን፤ ግራርን፤ ባርሰነትንና ወይራን አበቅላለሁ፤ በበረሃ፤ ጥድን፤ አስታንና ሸውሸዌን በአንድነት እተክላለሁ። ስለዚህ የጌታ እጅ ይህን እንዳደረገ፥ የእስራኤል ቅዱስ እንደፈጠረው፥ ሰዎች እንዲያዩና እንዲያውቁ፥ በአንድነት እንዲገነዘቡ፤ እንዲያስተውሉም።