ኢሳይያስ 37:1-7 - Compare All Versions

ኢሳይያስ 37:1-7 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን ሲሰማ፣ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለበሰ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ገባ። ከዚያም የቤተ መንግሥቱን አዛዥ ኤልያቄምን፣ ጸሓፊውን ሳምናስንና ከካህናቱ ዋና ዋናዎቹን ማቅ ለብሰው ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ላካቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፤ ‘ይህ ቀን የጭንቀት፣ የተግሣጽና የውርደት ቀን ነው፤ ልጆች ሊወለዱ ሲሉ ብርታት እንደሚታጣበት ቀን ሆኗል። ምናልባት ሕያው አምላክን ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የጦር አዛዡን ቃል እግዚአብሔር አምላክህ ይሰማ ይሆናል፤ እግዚአብሔር አምላክህም ሰምቶ ይገሥጸው ይሆናል፤ ስለዚህ አንተም በሕይወት ለተረፉት ቅሬታዎች ጸልይ።’ ” የንጉሡ የሕዝቅያስ ባሪያዎች ወደ ኢሳይያስ መጡ፤ ኢሳይያስም እንዲህ አላቸው፤ “ጌታችሁን እንዲህ በሉት፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች እኔን ስለ ሰደቡኝ፣ በሰማኸው ቃል አትሸበር። እነሆ፤ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፤ ወሬም ሰምቶ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ በገዛ አገሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።’ ”

ኢሳይያስ 37:1-7 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደ። የቤተ መንግሥቱን አዛዥ ኤልያቄምን፥ የቤተ መንግሥቱን ዋና ጸሐፊ ሼብናንና ከካህናት መካከል ታዋቂዎች የሆኑትን ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ላከ፤ እነርሱም ማቅ ለብሰው ነበር። እነርሱም ከሕዝቅያስ ተቀብለው ለኢሳይያስ የነገሩት መልእክት ይህ ነበር፦ “ዛሬ የታላቅ መከራ ቀን ነው፤ የሚያሳፍር ቅጣትና ውርደት እየደረሰብን ነው፤ የምትወልድበት ጊዜ ደርሶ ለማማጥ አቅም እንዳነሣት ሴት ሆነናል፤ የአሦር ንጉሥ ሕያው እግዚአብሔርን እንዲሰድብለት ከፍተኛ ባለሥልጣኑን ልኮአል፤ አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ስድብ ሰምቶ ተሳዳቢውን ይቀጣ ይሆናል፤ ስለዚህ ከሕዝባችን መካከል በሕይወት ስለሚተርፉት እባክህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ።” ኢሳይያስም ንጉሥ ሕዝቅያስ የላከውን መልእክት ሰምቶ፥ ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ላከ፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች እኔን የሰደቡበትን የስድብ ቃል በመስማትህ አትፍራ።’ በሀገሩ ስላለ ጉዳይ በሹክሹክታ ወሬ እንዲሸበርና ወደ ሀገሩ ተመልሶ በሰይፍ እንዲገደል አደርገዋለሁ።”

ኢሳይያስ 37:1-7 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))

እን​ዲ​ህም ሆነ፤ ንጉሡ ሕዝ​ቅ​ያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብ​ሱን ቀደደ፤ ማቅም ለበሰ፤ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ቤት ገባ። የቤ​ቱ​ንም አዛዥ ኤል​ያ​ቄ​ምን፥ ጸሓ​ፊ​ው​ንም ሳም​ና​ስን፥ የካ​ህ​ና​ቱ​ንም ሽማ​ግ​ሌ​ዎች ማቅ ለብ​ሰው ወደ ነቢዩ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ኢሳ​ይ​ያስ ይሄዱ ዘንድ ላካ​ቸው። እነ​ር​ሱም፥ “ሕዝ​ቅ​ያስ እን​ዲህ ይላል፦ ይህ ቀን የመ​ከ​ራና የተ​ግ​ሣጽ፥ የዘ​ለ​ፋም ቀን ነው፤ ልጆች የሚ​ወ​ለ​ዱ​በት ጊዜ ደር​ሶ​አል፤ ለመ​ው​ለ​ድም ኀይል የለም። ምና​ል​ባት በሕ​ያው አም​ላክ ላይ ይገ​ዳ​ደር ዘንድ ጌታው የአ​ሦር ንጉሥ የላ​ከ​ውን የራ​ፋ​ስ​ቂ​ስን ቃል አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይሰማ እንደ ሆነ፥ አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ስለ ሰማው ቃል ይገ​ሥ​ጸው እንደ ሆነ፥ ስለ​ዚህ ለቀ​ረው ቅሬታ ጸልይ” አሉት። እን​ዲሁ የን​ጉሡ የሕ​ዝ​ቅ​ያስ ብላ​ቴ​ኖች ወደ ኢሳ​ይ​ያስ በመጡ ጊዜ፥ ኢሳ​ይ​ያስ፥ “ለጌ​ታ​ችሁ፦ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፦ የአ​ሦር ንጉሥ ባሪ​ያ​ዎች ስለ ሰደ​ቡኝ፥ ስለ ሰማ​ኸው ቃል አት​ፍራ። እነሆ፥ መን​ፈ​ስን በላዩ እሰ​ድ​ዳ​ለሁ፤ ወሬ​ንም ይሰ​ማል፤ ወደ ምድ​ሩም ይመ​ለ​ሳል፤ በም​ድ​ሩም በሰ​ይፍ እን​ዲ​ወ​ድቅ አደ​ር​ጋ​ለሁ በሉት” አላ​ቸው።

ኢሳይያስ 37:1-7 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

እንዲህም ሆነ፥ ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፥ ማቅም ለበሰ፥ ወደ እግዚአብሔርም ገባ። የቤቱንም አዛዥ ኤልያቄምን ጸሐፊውንም ሳምናስን የካህናቱንም ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ ነቢዩ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ኢሳይያስ ይሄዱ ዘንድ ላካቸው። እነርሱም፦ ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፦ ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ የዘለፋም ቀን ነው፥ ልጆች የሚወለዱበት ጊዜ ደርሶአል ለመውለድም ኃይል የለም። ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል አምላክህ እግዚአብሔር ይሰማ እንደ ሆነ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደ ሆነ፥ ስለዚህ ለቀረው ቅሬታ ጸልይ አሉት። እንዲሁ የንጉሡ የሕዝቅያስ ባሪያዎች ወደ ኢሳይያስ መጡ። ኢሳይያስም፦ ለጌታችሁ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች ስለ ሰደቡኝ፥ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ። እነሆ፥ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፥ ወሬንም ይሰማል፥ ወደ ምድሩም ይመለሳል፥ በምድሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ በሉት አላቸው።

ኢሳይያስ 37:1-7 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))

ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፥ ማቅም ለበሰ፥ ወደ ጌታም ቤት ገባ። የቤቱንም አዛዥ ኤልያቄምን ጸሐፊውንም ሳምናስን የካህናቱንም ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ ነቢዩ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ላካቸው። እነርሱም፦ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፦ ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ የዘለፋም ቀን ነው፤ ልጆች የሚወለዱበት ጊዜ ደርሶአል ለመውለድም ብርታቱ የለም። ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ አለቃው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል አምላክህ ጌታ ሰምቶ እንደሆነ፥ አምላክህ ጌታም ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደሆን፥ ስለዚህ አንተም በሕይወት ስለተረፉት ቅሬታ ጸልይ አሉት።” ከዚያም የንጉሡ የሕዝቅያስ አገልጋዮች ወደ ኢሳይያስ መጡ። ኢሳይያስም፥ “ለአለቃችሁ፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች ስለ ሰደቡኝ፥ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ። እነሆ፥ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፥ ወሬም ይሰማል፥ ወደ ምድሩም ይመለሳል፤ በምድሩም ላይ በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ በሉት’ ” አላቸው።