ኢሳይያስ 31:1-9
ኢሳይያስ 31:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ርዳታ ለመፈለግ ወደ ግብፅ ለሚወርዱ፥ በፈረሶችና በሰረገሎችም ለሚታመኑ ወዮላቸው! ፈረሰኞቹ ብዙዎች ናቸውና፤ በእስራኤልም ቅዱስ አልታመኑምና፤ እግዚአብሔርንም አልፈለጉምና። እርሱ ግን ጠቢብ ነው፤ ክፉንም ነገር በላያቸው ያመጣል፤ ቃሉንም አይመልስም፤ በክፉዎችም ሰዎች ቤት ላይ በከንቱ ተስፋቸውም ላይ ይነሣል። ግብፃውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ እጁን በዘረጋ ጊዜ፥ ረጂው ይሰናከላል፤ ተረጂውም ይወድቃል፤ ሁሉም በአንድ ላይ ይጠፋሉ። እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛልና፥ “አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል በንጥቂያው ላይ እንደሚያገሣ፥ ድምፁም ተራሮችን እስኪሞላ በእርሱ ላይ እንደሚጮህ፥ እረኞችም ሁሉ ሲጮሁበት ከብዛታቸው የተነሣ እንደማይፈራ፥ ከድምፃቸውም የተነሣ እንደማይደነግጥ፥ እነርሱም ከቍጣው ብዛት የተነሣ ድል እንደሚሆኑና እንደሚደነግጡ፥ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራና በኮረብታዋ ላይ ይዋጋ ዘንድ ይወርዳል። እንደሚበርር ወፍ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይጋርዳታል፤ ይከልላታልም፤ ይታደጋታል፤ አልፎም ያድናታል። ትበድሉ ዘንድ ጥልቅ ምክርን የምትመክሩ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ። በዚያም ቀን እያንዳንዳቸው እጆቻቸው የሠሩአቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቻቸውን ይጥላሉ። አሦርም ይወድቃል፤ የሚወድቀውም በሰው ሰይፍ አይደለም፤ የምትበላቸውም የሰው ሰይፍ አይደለችም፤ የሚሸሹም ከሰይፍ ፊት አይደለም ጐልማሶቻቸው ግን ይሸነፋሉ። ዓለትም ትውጣቸዋለች ድልም ይሆናሉ የሸሸም ይያዛል። በጽዮን ዘርእ፥ በኢየሩሳሌምም ቤቶች ያሉት ብፁዕ ነው” ይላል እግዚአብሔር።
ኢሳይያስ 31:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወደ እስራኤል ቅዱስ ለማይመለከቱ፣ ከእግዚአብሔርም ርዳታን ለማይሹ፣ ነገር ግን፤ ለርዳታ ብለው ወደ ግብጽ ለሚወርዱ፣ በፈረሶች ለሚታመኑ፣ በሠረገሎቻቸው ብዛት፣ በፈረሶቻቸውም ታላቅ ብርታት ለሚመኩ ወዮላቸው! እርሱም ግን ጠቢብ ነው፤ ጥፋትን ያመጣል፤ ቃሉን አያጥፍም። በክፉ አድራጊዎች ቤት ላይ፣ በደለኞችንም በሚረዱ ላይ ይነሣል። ግብጻውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔር እጁን ሲዘረጋ፣ ርዳታ ሰጪው ይሰናከላል፤ ተረጂውም ይወድቃል፤ ሁለቱም በአንድ ላይ ይጠፋሉ። እግዚአብሔር እንዲህ ብሎኛል፤ “አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል የሰበረውን ይዞ ሲያገሣ፣ ብዙ እረኞች ተጠራርተው ሲመጡበት፣ ጩኸታቸው እንደማያስፈራው፣ በድምፃቸውም እንደማይታወክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በጽዮን ተራራና በከፍታዎቿ ላይ ለውጊያ እንዲሁ ይወርዳል። በዐናት ላይ እንደሚያንዣብቡ ወፎች፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲሁ ይጋርዳታል፤ ይከልላታል፤ ይታደጋታል፤ በላይዋ ያልፋል፤ ያድናታልም።” እናንተ እስራኤላውያን ሆይ፤ እጅግ ወዳመፃችሁበት ወደ እርሱ ተመለሱ። በዚያ ቀን በኀጢአት የተሞላ እጃችሁ የሠራቸውን የወርቅና የብር ጣዖቶች ሁላችሁም ትጥላላችሁና። “አሦር የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃል፤ የሥጋ ለባሽ ያልሆነም ሰይፍ ይበላዋል። ከሰይፍ ፊት ይሸሻል፤ ጕልማሶቹም የግዳጅ ሥራ ይሠራሉ። ጠንካራ ምሽጉ በሽብር ምክንያት ይወድቃል፤ መሪዎቹም የጦር ዐርማ ሲያዩ በድንጋጤ ይዋጣሉ” ይላል እሳቱ በጽዮን፣ ማንደጃውም በኢየሩሳሌም የሆነ እግዚአብሔር።
ኢሳይያስ 31:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለ እርዳታ ወደ ግብጽ ለሚወርዱ በፈረሶችም ለሚደገፉ፥ ስለ ብዛታቸውም በሰረገሎች፥ እጅግ ብርቱዎችም ስለ ሆኑ በፈረሰኞች ለሚታመኑ፥ ወደ እስራኤልም ቅዱስ ለማይመለከቱ እግዚአብሔርንም ለማይፈልጉ ወዮላቸው! እርሱ ግን ደግሞ ጠቢብ ነው፥ ክፉንም ነገር ያመጣል፥ ቃሉንም አይመልስም፥ በክፉም አድራጊዎች ቤት ላይ በደልንም በሚሠሩ ረዳት ላይ ይነሣል። ግብጻውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፥ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፥ እግዚአብሔርም እጁን በዘረጋ ጊዜ፥ ረጂው ይሰናከላል ተረጂውም ይወድቃል፥ ሁሉም በአንድ ላይ ይጠፋሉ። እግዚአብሔርም እንዲህ ይለኛልና፦ አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል በንጥቂያው ላይ ሲያገሣ፥ ብዙ እረኞች ቢከማቹበት ከቃላቸው እንደማይፈራ ከድምፃቸውም እንደማይዋረድ፥ እንዱሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራና በኮረብታዋ ላይ ይዋጋ ዘንድ ይወርዳል። እንደሚበርር ወፍ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይጋርዳታል፥ ይከልላታል፥ ይታደጋታል፥ አልፎም ያድናታል። እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አጥብቃችሁ ወደ ዐመፃችሁበት ተመለሱ። በዚያም ቀን እያንዳንዳቸው እጆቻቸው ለኃጢአት የሠሩላቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቻቸውን ይጥላሉ። አሦርም የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃል፥ የሰውም ያልሆነ ሰይፍ ይበላዋል፥ ከሰይፍም ይሸሻል ጐበዛዝቱም ገባሮች ይሆናሉ። አምባው ከፍርሃት የተነሣ ያልፋል መሳፍንቱም ከዓላማው የተነሣ ይደነግጣሉ፥ ይላል እሳቱ በጽዮን እቶኑም በኢየሩሳሌም የሆነ እግዚአብሔር።
ኢሳይያስ 31:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ብዙ ፈረሶች፥ ሠረገሎችና ወታደሮች ባሉት ብርቱ በሆነው በግብጽ ሠራዊት ተማምነው ርዳታ ለማግኘት ወደ ግብጽ ለሚወርዱ ወዮላቸው! ነገር ግን የእስራኤልን ቅዱስ ርዳታ አይለምኑም፤ መመሪያውንም አይቀበሉም። ሆኖም እግዚአብሔር ጥበበኛ ነው፤ መቅሠፍትንም ያመጣል፤ ቃሉን አያጥፍም፤ በክፉ ሰዎች ቤት ላይና ክፉዎችን በሚረዱ ሰዎች ላይ ይነሣል። ግብጻውያን ሰዎች ናቸው እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ ለባሾች እንጂ የተለዩ መናፍስት አይደሉም፤ እግዚአብሔር በቊጣው በሚነሣበት ጊዜ ይህ የሌሎች ረዳት የሆነው መንግሥት ይደናቀፋል፤ እርሱ ይረዳው የነበረውም መንግሥት ተንኰታኲቶ ይወድቃል፤ ሁለቱም በአንድነት ተያይዘው ይጠፋሉ። እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “አንበሳ በገደለው እንስሳ ላይ በሚያገሣበት ጊዜ እረኞች ተጠራርተው የቱንም ያኽል ቢጮኹ የእነርሱ ጩኸት ምንም እንደማያስፈራው እኔም የሠራዊት አምላክ የጽዮንን ተራራና ኰረብቶቿን ለመከላከል የሚያግደኝ የለም። ወፍ በጎጆዋ ላይ ክንፍዋን ዘርግታ በማንጃበብ ጫጩቶችዋን እንደምትጠብቅ፥ እኔ የሠራዊት አምላክ ኢየሩሳሌምን እጋርዳታለሁ፤ እጠብቃታለሁ፤ አድናታለሁ፤ ከችግር አወጣታለሁ። “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ፈጽማችሁ ወደ ከዳችሁኝ ወደ እኔ ተመለሱ! በኃጢአተኛ እጃችሁ ከብርና ከወርቅ የሠራችኋቸውን ጣዖቶቻችሁን ሁሉ አሽቀንጥራችሁ የምትጥሉበት ጊዜ ይመጣል። ከዚያ በኋላ አሦራውያን የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃሉ። ሽብር በተነሣ ጊዜ ምሽጋቸው ይፈርሳል፤ የጦር መኰንኖቻቸውም አርማቸውን ትተው በመርበድበድ ይሸሻሉ”። እሳቱ በጽዮን፥ እቶኑ በኢየሩሳሌም የሆነው እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል።
ኢሳይያስ 31:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለ እርዳታ ወደ ግብጽ ለሚወርዱ በፈረሶችም ለሚደገፉ፥ ስለ ብዛታቸውም በሰረገሎች፥ እጅግ ብርቱዎችም ስለ ሆኑ በፈረሰኞች ለሚታመኑ፥ ወደ እስራኤልም ቅዱስ ለማይመለከቱ ጌታንም ለማይፈልጉ ወዮላቸው! እርሱ ግን ደግሞ ጠቢብ ነው፥ ክፉንም ነገር ያመጣል፥ ቃሉንም አይመልስም፥ በክፉም አድራጊዎች ቤት ላይ በደልንም በሚሠሩ ረዳት ላይ ይነሣል። ግብጻውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ ጌታ እጁን በሚዘረጋ ጊዜ፥ ረጂው ይሰናከላል ተረጂውም ይወድቃል፥ ሁሉም በአንድ ላይ ይጠፋሉ። ጌታም እንዲህ ይለኛልና፦ አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል በንጥቂያው ላይ ሲያገሣ፥ ብዙ እረኞች ቢከማቹበት ከቃላቸው እንደማይፈራ ከድምፃቸውም እንደማይዋረድ፥ እንደዚሁም የሠራዊት ጌታ በጽዮን ተራራና በኮረብታዋ ላይ ለመዋጋት ይወርዳል። እንደሚበር ወፍ እንደዚሁ የሠራዊት ጌታ ኢየሩሳሌምን ይጋርዳታል፤ ይከልላታል፤ ይታደጋታል፤ እንዲሁም ያድናታል። እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አጥብቃችሁ ወደ ዐመፃችሁበት ተመለሱ። በዚያም ቀን እያንዳንዳቸው እጆቻቸው ለኃጢአት የሠሩላቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቻቸውን ይጥላሉ። አሦርም የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃል፥ የሰውም ያልሆነ ሰይፍ ይበላዋል፤ ከሰይፍም ይሸሻል ጐበዛዝቱም ገባሮች ይሆናሉ። አምባው ከፍርሃት የተነሣ ያልፋል መሳፍንቱም ከዓላማው የተነሣ ይደነግጣሉ፥ ይላል እሳቱ በጽዮን እቶኑም በኢየሩሳሌም የሆነ ጌታ።