ኢሳይያስ 18:1-5
ኢሳይያስ 18:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ ላለች፥ ክንፍ ያላቸው መርከቦች ላሉባት ምድር ወዮላት! መልእክተኞችን በባሕር ላይ፥ ደብዳቤዎችንም በውኃ ላይ ይልካል። ፈጣኖች መልእክተኞች ወደ ረዥምና ወደ ባዕድ፥ ወደ ክፉም ሕዝብ ይሄዳሉና፤ ተስፋ የቈረጡና የተረገጡ ሕዝብ እነማን ናቸው? ዛሬ ግን የምድር ወንዞች ሁሉ፥ ሰዎች እንደሚኖሩባት ሀገር ይኖራሉ። በየሀገራቸው ይቀመጣሉ፤ ከተራሮች ራሶችም እንደ ዓላማ ይይዙታል፤ እንደ መለከት ድምፅም ይሰማል። እግዚአብሔር፥ “እንደ ቀትር ብርሃን፥ በአጨዳም ወራት እንደ ጠል ደመና በማደሪያዬ ጸጥታ ይሆናል” ብሎኛልና። እርሱ ከመከር በፊት አበባ በረገፈ ጊዜ የወይንም ፍሬ ጨርቋ ሲይዝ የወይኑን ቀጫጭን ዘንግ በማጭድ ይቈርጣል፤ ጫፎቹንም ይመለምላል፤ ያስወግድማል።
ኢሳይያስ 18:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በኢትዮጵያ ወንዞች ዳር ለምትገኝ፣ ፉር ፉር የሚሉ ክንፎች ላሉባት ምድር ወዮላት! ይህችውም መልእክተኞችን በባሕር፣ ከወንዞች ማዶ በደንገል ጀልባ የምትልክ ናት። እናንተ ፈጣን መልእክተኞች ረዣዥምና ቈዳው ወደ ለሰለሰ፣ ከቅርብም ከሩቅም ወደሚፈራ ሕዝብ፣ ኀያልና ቋንቋው ወደማይገባ፣ ወንዞች ምድሩን ወደሚከፍሉት መንግሥት፣ ሂዱ! እናንተ የዓለም ሕዝቦች፣ በምድርም የምትኖሩ ሁሉ፣ በተራሮች ላይ ምልክት ሲሰቀል ታዩታላችሁ፤ መለከትም ሲነፋ ትሰሙታላችሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ብሎኛል፤ “ጸጥ ብዬ እቀመጣለሁ፤ ከማደሪያዬም በፀሓይ ሐሩር እንደሚያስፈልጋችሁ ብርቅርቅ ትኵሳት፣ በመከርም ሙቀት እንደ ደመና ጠል ሆኜ እመለከታለሁ።” ከመከር በፊት የአበባው ወቅት ሲያልፍ፣ አበባው የጐመራ የወይን ፍሬ ሲሆን፣ የወይን ሐረጉን ተቀጥላ በመግረዣ ይገርዘዋል፤ የተንሰራፋውንም ቅርንጫፍ ቈራርጦ ያስወግደዋልና።
ኢሳይያስ 18:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ ላለች፥ ክንፍ ያላቸው መርከቦች ላሉባት፥ መልእክተኞችን በባሕር ላይ የደንገል መርከቦችንም በውኃ ላይ ለምትልክ ምድር ወዮላት! እናንተ ፈጣኖች መልእክተኞች ሆይ፥ ወደ ረጅምና ወደ ለስላሳ ሕዝብ፥ ከመጀመሪያው አስደንጋጭ ወደ ሆነው ወገን፥ ወደሚሰፍርና ወደሚረግጥ፥ ወንዞችም ምድራቸውን ወደሚከፍሉት ሕዝብ ሂዱ። በዓለም የምትኖሩ ሁሉና በምድር የምትቀመጡ ሆይ፥ ምልክት በተራሮች ላይ በተነሣ ጊዜ እዩ፥ መለከትም በተነፋ ጊዜ ስሙ። እግዚአብሔር፦ በፀሐይ ጮራ እንደ ደረቅ ትኩሳት በአጨዳም ወራት እንደ ጠል ደመና ሆኜ በማደሪያዬ በጸጥታ ተቀምጬ እመለከታለሁ ብሎኛልና። እርሱ ከመከር በፊት አበባ በረገፈ ጊዜ የወይንም ፍሬ ጨርቋ ሲይዝ የወይኑን ዘንግ በማጭድ ይቈርጣል፥ ጫፎቹንም ይመለምላል ያስወግድማል።
ኢሳይያስ 18:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የክንፎች ድምፅ ለሚሰማባት አገር ወዮላት! ያቺ አገር መልእክተኞችን ከደንገል በተሠራ ጀልባ በአባይ ወንዝ ላይ ትልካለች፤ ሕዝብዋ ረጃጅሞችና ቆዳቸው ለስላሳ፥ አገራቸው በወንዞች የተከፋፈለች፥ ጠንካሮችና ኀያላን በመሆናቸው በዓለም ሁሉ ወደሚፈሩት ሕዝቦች እናንት ፈጣን መልእክተኞች ሂዱ! በምድር የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ! በተራሮች ጫፍ ላይ የተተከለ የሰንደቅ ዓላማ ምልክት ሲውለበለብ አስተውሉ! መለከት ሲነፋ ስሙ! እግዚአብሔር እንዲህ ብሎኛል፦ “በቀትር ጊዜ በጸጥታ እንደምታበራ ፀሐይ፥ በመከርም ወራት በሞቃት ሌሊት እንደሚታይ ጤዛ ከሰማያዊ መኖሪያዬ ጸጥ ባለ መንፈስ ቊልቊል እመለከታለሁ። የወይን መከር ከመሰብሰቡ በፊት አበቦች ረግፈው የወይን ፍሬ በሚበስልበት ጊዜ የወይን ሐረግ ቅርንጫፎች በስለት ተቈርጠው እንደሚጣሉ እርሱ የዚያችን አገር ሕዝብ ያጠፋል።
ኢሳይያስ 18:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ ላለች፥ ክንፍ ያላቸው መርከቦች ላሉባት፥ መልእክተኞችን በባሕር ላይ፥ የደንገል መርከቦችንም በውኃ ላይ ለምትልክ ምድር ወዮላት! እናንተ ፈጣን መልእክተኞች ሆይ፥ ወደ ረጅምና ወደ ለስላሳ ሕዝብ፥ ከቅርብም ከሩቅም አስፈሪ ወደ ሆነ ሕዝብ፥ ኀያል ወደሆነና ወደሚገዛ፥ ወንዞችም ምድራቸውን ወደሚከፍሉት ሕዝብ ሂዱ። እናንት በዓለም ውስጥ ያላችሁና በምድር የምትኖሩ ሕዝቦች ሆይ፥ ምልክት በተራሮች ላይ በሚወጣ ጊዜ ተመልከቱ! መለከትም በተነፋ ጊዜ ስሙ! ጌታ፥ “በፀሐይ ጮራ እንደ ደረቅ ትኩሳት፥ በአጨዳም ወራት እንደ ጠል ደመና ሆኜ በማደሪያዬ በጸጥታ ተቀምጬ እመለከታለሁ” ብሎኛል። እርሱ ከመከር በፊት አበባ በረገፈ ጊዜ፥ አበባው ያበበ የወይንም ፍሬ ሲይዝ፥ የወይኑን ዘንግ በመግረዣ ይገርዘዋል፤ ጫፎቹንም መልምሎ ያስወግዳል።