ኢሳይያስ 16:1-14
ኢሳይያስ 16:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የጽዮን ሴት ልጅ ተራራ ምድረ በዳ አይደለችምን? ጫጩቶችዋን አሳድጋ እንደ ተወች ወፍ ሆናለችና፤ የሞዓብ ሴት ልጅም እንደ ሰባ የበግ ጠቦት ሆነች። አርኖንም በምትኖርበት ምሽግ መጠለያን ትሠራ ዘንድ ብዙ ትመክራለች፤ በቀትር ጊዜ እንደ ሌሊት ደንግጠው ይሸሻሉ፤ ወደ እናንተም አታስገቡአቸው። ከሚከቧችሁ ጋር ጠላቶች እንዳይሆኗችሁ ከሞዓብ የተሰደዱትን ከእናንተ ጋር አታስቀምጡ፤ ሰልፈኞች አልቀዋልና፤ በሀገሪቱ ሁሉ የነበረውም አለቃ ጠፍቶአልና። ዙፋን በምሕረት ይጸናል፥ በዚያም ላይ በዳዊት ቤት ፍርድን የሚሻ ጽድቅንም የሚያፋጥን ፈራጅ በእውነት ይቀመጣል፤ ይፈርዳልም። የሞዓብን ትዕቢትና እጅግ መኵራቱን ሰምተናል፤ ትዕቢቱንም አስወገድሁ፤ ጥንቈላህ እንዲህ አይደለምና፥ እንዲህም አይደለም፤ ሞዓብ ዋይ በሉ፤ ሁሉም በሞዓብ ዋይ ይላሉና፤ በዴሴት የሚኖሩም አያመልጡም፤ ጠብን ያጭራሉ፤ ያፍራሉም። የሐሴቦን እርሻዎችና የሴባማ ወይን ግንዶች አዝነዋል። የአሕዛብ አለቆች የሰባበሩአቸው ቅርንጫፎች እስከ ኢያዜር ደርሰው ወደ ምድረ በዳ ወጥተው ነበር፤ ቍጥቋጦቹም ተዘርግተው ባሕርን ተሻግረው ነበር። ስለዚህ በኢያዜር ልቅሶ ስለ ሴባማ ወይን ግንድ አለቅሳለሁ፤ ሐሴቦንና ኤልያሊ ሆይ፥ ዛፎችሽ ወድቀዋል፤ የዛፍሽን ፍሬና የወይንሽን መከር እረግጣለሁ፤ ተክሎችሽ ሁሉ ይወድቃሉ። ደስታና ሐሤትም ከወይን ቦታሽ ተወስዶአል፤ በወይንሽም ቦታዎች ፈጽመው ደስ አይላቸውም፤ በመጥመቂያውም ወይንን አይረግጡም፤ ረጋጮቹን አጥፍቻለሁና። ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ እንደ መሰንቆ ትጮኻለች። አጥንቶችም እንደ ተመረገ ግድግዳ ይሆናሉ። ለኀፍረት ይሆንብሃል፤ ሞዓብ በመሠዊያዎችዋ ደክማለችና፤ ለጸሎትም ወደ ጣዖቶችዋ ትሄዳለች፤ ሊያድኑአትም አይችሉም። እግዚአብሔር በሞዓብ ላይ በድሮ ዘመን የተናገረው ነገር ይህ ነው። አሁንም እንዲህ እላለሁ፤ በሦስት ዓመት ውስጥ እንደ ምንደኛ ዓመት የሞዓብ ክብር ከብዙ ሀብትዋ ጋር ይዋረዳል፤ በቍጥርም ጥቂት ይቀራል፤ ክብርዋም አይገኝም።
ኢሳይያስ 16:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከምድረ በዳው ማዶ ካለችው ከሴላ፣ ለምድሪቱ ገዥ፣ ወደ ጽዮን ሴት ልጅ ተራራ የበግ ጠቦት ግብር ላኩ። ከጐጇቸው ተባርረው ግራ እንደ ተጋቡ ወፎች፣ የሞዓብ ሴቶችም በአርኖን ወንዝ መሻገሪያ እንዲሁ ይሆናሉ። “ምክር ለግሱን፤ ውሳኔ ስጡን፤ በቀትር ጥላችሁን እንደ ሌሊት አጥሉብን፤ የሸሹትን ደብቁ፤ ስደተኞችን አሳልፋችሁ አትስጡ። የሞዓባውያን ስደተኞች ከእናንተ ጋራ ይቈዩ፤ እናንተም ከአጥፊው መጠጊያ ሁኗቸው።” የጨቋኙ ፍጻሜ ይመጣል፤ ጥፋቱ ያከትማል፤ እብሪተኛም ከምድር ገጽ ይጠፋል። ዙፋን በፍቅር ይመሠረታል፤ ከዳዊት ቤት የሆነ፣ በፍርድ ፍትሕን የሚሻ፣ ጽድቅንም የሚያፋጥን፣ አንድ ሰው በታማኝነት በላዩ ይቀመጣል። የሞዓብን መዘባነን፣ እጅግ መታበዩንና ኵራቱን፣ እብሪቱንና ስድነቱን ሰምተናል፤ ትምክሕቱ ግን ከንቱ ነው! ስለዚህ ሞዓባውያን ዋይ ይላሉ፤ በአንድነትም ስለ ሞዓብ ዋይታ ያሰማሉ፤ ስለ ቂርሐራሴት ከተማ ሰዎች ትዝታ፣ በሐዘን ያለቅሳሉ። የሐሴቦን ዕርሻ፣ የሴባማም የወይን ተክል ጠውልጓል፤ የአሕዛብ ገዦች፣ ኢያዜርን ዐልፈው፣ ምድረ በዳውን ዘልቀው፣ ሥሮቻቸውን እስከ ባሕር ሰድደው የነበሩትን የተመረጡ የወይን ተክሎችን ረጋግጠዋል። ስለዚህ ስለ ሴባማ የወይን ተክል፣ ኢያዜር እንዳለቀሰች፣ እኔም አለቅሳለሁ፤ ሐሴቦን ሆይ፤ ኤልያሊ ሆይ፤ በእንባዬ አርስሻለሁ! ፍሬ ባፈራሽበት ወቅት የነበረው ሆታ፣ መከርሽም ሲደርስ የነበረው ደስታ ተቋርጧልና። ደስታና ሐሤትም ከአትክልቱ ቦታ ተወግዷል፤ በወይን ተክልም ቦታ ዝማሬ የለም፤ እልልታም ቀርቷል። በወይን መጭመቂያ ቦታ የሚረግጥ የለም፤ የረጋጮችን ሆታ አጥፍቻለሁና። ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ እንደ በገና የሐዘን እንጕርጕሮ ታሰማለች፤ አንጀቴም ስለ ቂርሔሬስ ታለቅሳለች፤ ሞዓብ ወደ ኰረብታዋ ብትወጣ፣ ትርፏ ድካም ብቻ ነው፤ ለጸሎት ወደ መቅደሷ ብትገባም፣ ዋጋ የለውም። እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለ ሞዓብ የተናገረው ቃል ይህ ነው። አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የተቀጠረ ሠራተኛ ቀን እንደሚቈጥር፣ የሞዓብ ክብርና የሕዝቧ ብዛት በሦስት ዓመት ውስጥ ይዋረዳል፤ የሚቀረውም ሕዝብ ጥቂትና ደካማ ይሆናል።”
ኢሳይያስ 16:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በምድር ላይ ለሰለጠነ አለቃ የበግ ጠቦቶችን በምድረ በዳ ካለችው ከሴላ ወደ ጽዮን ሴት ልጅ ተራራ ስደዱ። እንደሚበርር ወፍ እንደተበተኑም ጫጩቶች እንዲሁ የሞዓብ ሴቶች ልጆች በአርኖን መሻገሪያዎች ይሆናሉ። ምክርን ምከሪ፥ ፍርድን አድርጊ፥ በቀትር ጊዜ ጥላሽን እንደ ሌሊት አድርጊ፥ የተሰደዱትን ሸሽጊ፥ የሸሹትን አትግለጪ። ከሞዓብ የተሰደዱት ከአንቺ ጋር ይቀመጡ፥ ከሚያጠፋቸው ፊት መጋረጃ ሁኛቸው። የሚያስጨንቁ አልቀዋል፥ ጥፋትም ቀርቷል፥ ይጨቍኑ የነበሩ ከምድር ጠፍተዋል። ዙፋኑም በምሕረት ይቀናል፥ በዚያም ላይ በዳዊት ድንኳን ፍርድን የሚሻ ጽድቅንም የሚያፈጥን ፈራጅ በእውነት ይቀመጣል። ስለ ሞዓብ ትዕቢት እጅግ ስለ መታበዩ፥ ስለ ኵራቱና ስለ ትዕቢቱ ስለ ቍጣውም ሰምተናል፥ ትምክሕቱ ከንቱ ነው። ስለዚህ ሞዓብ ስለ ሞዓብ ዋይ ይላል፥ ሁሉም ዋይ ይላል፥ ስለ ቂርሐራሴት መሠራት በጥልቅ ኀዘን ታለቅሳላችሁ። የሐሴቦን እርሻዎችና የሴባማ ወይን ግንዶች አዝነዋል። የአሕዛብ አለቆች የሰባበሩአቸው ቅርንጫፎች እስከ ኢያዜር ደርሰው ወደ ምድረ በዳ ወጥተው ነበር፥ ቍጥቋጦቹም ተዘርግተው ባሕርን ተሻግረው ነበር። ስለዚህ በኢያዜር ልቅሶ ስለ ሴባማ የወይን ግንድ አለቅሳለሁ፥ ሐሴቦንና ኤልያሊ ሆይ፥ በዛፍሽ ፍሬና በወይንሽ መከር የጦር ጩኸት ወድቆአልና በእንባዬ አረካሻለሁ። ደስታና ሐሴትም ከፍሬያማው እርሻ ተወስዶአል፥ በወይኑም ቦታዎች ዝማሬና እልልታ የለም፥ በመጥመቂያም ወይን የሚረግጥ የለም፥ የረጋጮቹን እልልታ አጥፍቻለሁ። ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ አንጀቴም ስለ ቂርሔሬስ እንደ መሰንቆ ትጮኻለች። ሞዓም መጥቶ በኮረብታ መስገጃ ላይ በደከመና ለጸሎት ወደ መቅደሱ በገባ ጊዜ አያሸንፍም። እግዚአብሔር በሞዓብ ላይ በድሮ ዘመን የተናገረው ነገር ይህ ነው። አሁን ግን እግዚአብሔር፦ በሦስት ዓመት ውስጥ እንደ ምንደኛ ዓመት የሞዓብ ክብርና የሕዝቡ ሁሉ ብዛት ይዋረዳል፥ ቅሬታውም እጅግ ያነሰና የተጠቃ ይሆናል ይላል።
ኢሳይያስ 16:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የሞአብ ሕዝብ ሆይ! በጽዮን ተራራ ላይ ለሚገኘው ለሀገሪቱ መሪ ከሴላ በበረሓው በኩል ጠቦቶችን እጅ መንሻ አድርጋችሁ ላኩለት። የአርኖንን ወንዝ የሚሻገሩ የሞአብ ሴቶች ከጎጆዎቻቸው ተበታትነው ክንፎቻቸውን እያራገቡ ወዲያና ወዲህ እንደሚንከራተቱ የወፍ መንጋዎች ናቸው። የሞአብ መልእክተኞች ለይሁዳ ሕዝብ እንዲህ ይላሉ፦ “ምን ማድረግ እንደሚገባን ምከሩን፤ በቀትር ጊዜ የእናንተ ጥላ እንደ ሌሊት ጨለማ ይከልለን። የሞአብ ስደተኞች በመካከላችሁ ይኑሩ፤ ሊያጠፉአቸው ከሚፈልጉ ወገኖች መጠጊያ ሁኑአቸው።” ጨቋኞች ከእንግዲህ ወዲያ አይኖሩም፤ ያገር መፈራረስም ያከትማል። ወራሪዎችም ይወገዳሉ። በዚያን ጊዜ አንድ መንግሥት በዘለዓለማዊ ፍቅር ይመሠረታል፤ በዙፋኑም ላይ ከዳዊት ዘር አንድ ታማኝ የሆነ፥ ፍትሕን የሚፈልግና ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ፈጣን የሆነ ንጉሥ ይቀመጥበታል። የይሁዳ ሕዝብ እንዲህ ይላሉ፦ “የሞአብ ሕዝብ ምን ያኽል ኩራተኛ መሆኑን፥ ትዕቢተኛነቱን፥ ዕብሪተኛነቱንና ንቀቱን ሰምተናል፤ ነገር ግን ፉከራው ሁሉ ከንቱ ነው።” ስለዚህ ሞአብ ታልቅስ፤ ሰዎችም ሁሉ ስለ ሞአብ ያልቅሱ፤ በቂርሔሬስ ከተማ የነበረው ምርጥ ምግብ ትዝ እያላቸው በታላቅ ሐዘን ያለቅሳሉ። የሀሴቦን እርሻዎችና የሲብማ የወይን ተክል ቦታዎች ተደምስሰዋል፤ እነዚህ የወይን ተክል ቦታዎች የአሕዛብ መሪዎችን የሚያሰክር የወይን ጠጅ ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ነበሩ፤ ከዚያ በፊት የእነዚያ የወይን ተክሎች ሐረግ እስከ ያዕዜር ከተማ ድረስ የተንሰራፋ ነበር፤ እንዲሁም በስተ ምዕራብ እስከ ሙት ባሕር ማዶና በስተ ምሥራቅም እስከ በረሓው ይደርስ ነበር። ስለ ያዕዜር እንደማለቅስ ስለ ሲብማ የወይን ሐረጎችም አለቅሳለሁ፤ ስለ ሐሴቦንና ስለ ኤልዓሌ እንባዬ ይረግፋል፤ ሕዝቡ የሚደሰትበት መከር አልተገኘባቸውም፤ እነሆ በፍሬያማው የእርሻ ቦታ አንድ እንኳ ደስተኛ የለም፤ በወይን ተክል ቦታዎች የእልልታና የዝማሬ ድምፅ አይሰማም፤ የወይን ጠጅ ለመጥመቅ የወይን ፍሬ የሚጨምቅ የለም፤ እግዚአብሔር የደስታ እልልታን ሁሉ እንዲቆም አድርጎአል። ስለዚህ ልቤ ለሞአብ፥ ነፍሴም ለቂርሔሬስ ይታወካሉ። የሞአብ ሕዝቦች የጣዖት ቤተ መቅደሶቻቸውና መስገጃዎቻቸው ወደተሠሩበት ተራራ ለጸሎት በመመላለስ ሰውነታቸውን አድክመዋል፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ ምንም ውጤት አያስገኝላቸውም። እግዚአብሔር ስለ ሞአብ በቅድሚያ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የአንድ ጊዜያዊ የቅጥር ሠራተኛ የሥራ ጊዜ እንደሚቋረጥ የሞአብ ክብርና ብዙ ሕዝቦችዋ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይዋረዳል፤ ከሕዝቧ የተረፉትም በጣም ጥቂቶችና ደካሞች ይሆናሉ።”
ኢሳይያስ 16:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በምድረ በዳ ካለችው ከሴላ በምድር ላይ ገዢ ለሆነው ወደ ጽዮን ሴት ልጅ ተራራ የበግ ጠቦቶችን ስደዱ። ከጎጆቸው ተበትነው እንደሚበሩ ወፎች፥ የሞዓብ ሴቶችም በአርኖን መሻገሪያዎች እንዲሁ ይሆናሉ። ምክርን ለግሺ፥ ፍትህን አስፍኚ፥ በቀትር ጊዜ ጥላሽን እንደ ሌሊት አጢይ፤ ስደተኞችን ሸሽጊ፥ የሸሹትን አሳልፈሽ አትስጪ። ከሞዓብ የተሰደዱት ከአንቺ ዘንድ ይኑሩ፤ ስደተኞቹን ከሚሳድዷቸው መሸሸጊ ሁኛቸው። የሚያስጨንቁ አልቀዋል፥ ጥፋትም ቀርቷል፤ ጨቋኞች የነበሩ ከምድር ጠፍተዋል። ዙፋኑም በምሕረት ይቀናል፥ በዚያም በዳዊት ድንኳን ፍትህን የሚሻ ትክክል የሆነውን ለመፈጸም የሚፈጥን ፈራጅ በእውነት ይቀመጣል። የሞዓብን ኩራት፥ እጅግ መታበዩን! ስለ እብሪቱና ስለ ኩራቱ፥ ስለ ስድነቱም ሰምተናል፤ ትምክሕቱ ከንቱ ነው። ስለዚህ ሞዓብ ስለ ሞዓብ ዋይታ ያሰማ፤ ሁሉም ዋይታ ያሰማሉ፤ ስለ ቂርሐራሴት መሠራት በጥልቅ ኀዘን ታለቅሳላችሁ። የሐሴቦን እርሻዎችና የሴባማ ወይን ግንዶች አዝነዋል። የአሕዛብ አለቆች የሰባበሩአቸው ቅርንጫፎች ኢያዜርን አልፈው ወደ ምድረ በዳ ወጥተው ነበር፤ ቁጥቋጦቹም ተዘርግተው ባሕርን ተሻግረው ነበር። ስለዚህ ስለ ሴባማ የወይን ግንድ ከኢያዜር ልቅሶ ጋር አለቅሳለሁ፤ ሐሴቦንና ኤልያሊ ሆይ፥ በዛፍሽ ፍሬና በወይንሽ መከር የጦር ጩኸት ወድቆአልና በእንባዬ አርስሻለሁ። ደስታና ሐሴትም ከፍሬያማው እርሻ ተወስዶአል፤ በወይኑም ቦታዎች ዝማሬና እልልታ የለም፤ በመጥመቂያም ወይን የሚረግጥ የለም፤ የረጋጮቹን እልልታ አጥፍቻለሁ። ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ አንጀቴም ስለ ቂርሔሬስ እንደ በገና የኀዘን እንጉርጉሮ ታሰማለች። ሞዓም ወደ ኮረብታ ወጥቶ ራሱን ቢያደክም፥ ለጸሎት ወደ መቅደሱ ቢገባም በከንቱ ይደክማል እንጂ አያሸንፍም። ጌታ በሞዓብ ላይ አስቀድሞ የተናገረው ነገር ይህ ነው። አሁን ግን ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እንደ ተቀጣሪ ደሞዝተኛ የሞዓብ ክብር፥ ምንም ያህል ሕዝቡ ቢበዛ፥ በሦስት ዓመት ውስጥ ይዋረዳል፤ የሚተርፈውም ሕዝብ እጅግ ጥቂትና ደካማ ይሆናል።”