ኢሳይያስ 1:10-20
ኢሳይያስ 1:10-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እናንተ የሰዶም አለቆች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ሕግ አድምጡ። “የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምንድን ነው?” ይላል እግዚአብሔር፤ “የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤአለሁ፤ የበሬና የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም። በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ፥ ይህን ከእጃችሁ የሚሻ ማን ነው? እንግዲህ አደባባዬን ደግማችሁ አትረግጡም። መልካሙን የስንዴ ዱቄት ብታመጡ እንኳ ከንቱ ነው፤ ዕጣናችሁ በእኔ ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ መባቻዎቻችሁንና ሰንበቶቻችሁን፥ ታላቋን፥ ቀናችሁን፥ ጾማችሁንና ሥራ መፍታታችሁን አልወድም። መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ አስጸያፊ ሆናችሁብኛል፤ ኀጢአታችሁንም ይቅር አልልም። እጃችሁን ወደ እኔ ብትዘረጉ፥ ዐይኖችን ከእናንተ እመልሳለሁ፤ ምህላንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደምን ተሞልተዋልና። ታጠቡ፤ ንጹሓንም ሁኑ፤ የሰውነታችሁን ክፋት ከዐይኖች ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግንም ተዉ፤ መልካም መሥራትን ተማሩ፤ ፍርድን ፈልጉ፤ የተገፋውን አድኑ፤ ለድሃአደጉ ፍረዱለት፤ ስለ መበለቲቱም ተሙአገቱ።” “ኑና እንዋቀስ” ይላል እግዚአብሔር፤ ኀጢአታችሁ እንደ አለላ ቢሆን እንደ በረዶ አነጻዋለሁ፤ እንደ ደምም ቢቀላ እንደ ባዘቶ አጠራዋለሁ። እሽ ብትሉና ብትሰሙኝ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብትሉና ባትሰሙኝ ግን ሰይፍ ትበላችኋለች፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።
ኢሳይያስ 1:10-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እናንተ የሰዶም ገዦች፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሰዎች፤ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ። “የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምኔ ነው?” ይላል እግዚአብሔር። “የሚቃጠለውን የአውራ በግና የሠቡ እንስሳትን ሥብ ጠግቤአለሁ፤ በበሬ፣ በበግ ጠቦትና በፍየል ደም ደስ አልሰኝም። በፊቴ ለመቅረብ ስትመጡ፣ ይህን ሁሉ እንድታመጡ፣ የመቅደሴን ደጅ እንድትረግጡ ማን ጠየቃችሁ? ከንቱውን መባ አታቅርቡ፤ ዕጣናችሁን እጸየፋለሁ፤ የወር መባቻ በዓላችሁን፣ ሰንበቶቻችሁን፣ ጉባኤያችሁንና በክፋት የተሞላውን ስብሰባችሁን መታገሥ አልቻልሁም። የወር መባቻችሁንና በዓላታችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፤ መታገሥም አልቻልሁም። እጆቻቸሁን ለጸሎት ወደ እኔ ስትዘረጉ፣ ዐይኖቼን ከእናንተ እሰውራለሁ፤ አብዝታችሁ ብትጸልዩም እንኳ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ በደም ተበክለዋል፤ ታጠቡ፤ ራሳችሁንም አንጹ፤ ክፉ ሥራችሁን ከፊቴ አርቁ፤ ክፉ ማድረጋችሁን ተዉ፤ መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን እሹ፣ የተገፉትን አጽናኑ፤ አባት ለሌላቸው ቁሙላቸው፤ ለመበለቶችም ተሟገቱ። “ኑና እንዋቀሥ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ኀጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ፣ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደም ቢቀላም፣ እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል። ዕሺ ብትሉ፣ ብትታዘዙም የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብላችሁ ብታምፁ ግን ሰይፍ ይበላችኋል።” የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሯልና።
ኢሳይያስ 1:10-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እናንተ የሰዶም አለቆች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፥ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ። የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር፥ የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፥ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም። በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃችሁ የሚሻ ማን ነው? ምናምንቴውን ቍርባን ጨምራችሁ አታምጡ፥ እጣን በእኔ ዘንድ አጸያፊ ነው፥ መባቻችሁንና ሰንበታችሁን በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድድም፥ በደልንም የተቀደሰውንም ጉባኤ አልታገሥም። መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፥ ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሳቸውም ደክሜያለሁ። እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፥ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል። ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፥ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፥ ክፉ ማድረግን ተዉ፥ መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ። ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፥ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፥ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች። እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፥ እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።
ኢሳይያስ 1:10-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እናንተ የሰዶም ገዢዎች ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ! የአምላካችንን ትምህርት አድምጡ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይረባኛል? እስከ አሁን ያቀረባችሁልኝ የአውራ በግ፥ የተቃጠለ መሥዋዕትና የፍሪዳ ስብ በቅቶኛል፤ በኰርማና በበግ ጠቦት፥ በአውራ ፍየልም ደም አልደሰትም። እኔን ለመገናኘት እንድትመጡና የመቅደሴን አደባባይ እንድትረግጡ ማን ጠየቃችሁ? ይህን ዐይነት ከንቱ መባ ከእንግዲህ ወዲህ አታቅርቡ፤ የምታጥኑት ዕጣን በፊቴ አጸያፊ ነው፤ አዲስ ጨረቃ የምትወጣበት የወር መባቻችሁና ሰንበቶቻችሁ፥ መንፈሳዊ ስብሰባዎቻችሁም በኃጢአት የተበከሉ ስለ ሆኑ አልወደድሁላችሁም። አዲስ ጨረቃ የምትወጣበትን የወር መባቻችሁንና በዓሎቻችሁን ጠልቻለሁ፤ እነርሱ እንደ ከባድ ሸክም ስለ ሆኑብኝ ልታገሣቸው አልችልም። “እጆቻችሁን ወደ እኔ ለጸሎት ብትዘረጉ፥ ወደ እናንተ አልመለከትም፤ እጆቻችሁ በደም የተበከሉ ስለ ሆኑ የቱንም ያኽል ልመና ብታበዙ አልሰማችሁም፤ ይልቁንስ ታጥባችሁ ንጹሕ ሁኑ፤ ክፉ ሥራችሁን ሁሉ ከፊቴ አስወግዱ፤ በደል መፈጸማችሁንም ተዉ። መልካም ማድረግንም ተማሩ፤ ፍትሕ እንዳይጓደል አድርጉ፤ የተጨቈኑትን ታደጉ፤ አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች መብት ጠብቁ፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸውንም ሴቶች አቤቱታ ስሙ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እስቲ ኑና እንወያይ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ቢቀላ እኔ አጥቤ እንደ በረዶ ይጸዳል፤ እንደ ደም የቀላ ቢሆን እንደ ባዘቶ ይነጣል። እሺ ብላችሁ ብትታዘዙኝ ምድር የምታስገኘውን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉኝና ብታምፁ ግን ሰይፍ ይበላችኋል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ራሴ እግዚአብሔር ነኝ።”
ኢሳይያስ 1:10-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እናንተ የሰዶም ገዦች፤ የጌታን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሰዎች፤ የእግዚአብሔርን ሕግ አድምጡ። “የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምኔ ነው?” ይላል ጌታ። የሚቃጠለውን የአውራ በግና የሰቡ እንስሳትን ስብ ጠግቤአለሁ፤ በበሬ፤ በበግ ጠቦትና በፍየል ደም ደስ አልሰኝም። በፊቴ ለመቅረብ ስትመጡ፤ ይህን ሁሉ እንድታመጡ፤ የመቅደሴን ደጅ እንድትረግጡ ማን ጠየቃችሁ? ከንቱውን መባ አታቅርቡ፤ ዕጣናችሁን እጸየፋለሁ፤ የወር መባቻ በዓላችሁን፤ ሰንበቶቻችሁን፤ ጉባኤያችሁንና በክፋት የተሞላውን ስብሰባችሁን መታገሥ አልቻልሁም። የወር መባቻችሁንና የተደነገጉ በዓሎቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፤ መታገሥም አልቻልሁም። እጆቻቸሁን ለጸሎት ወደ እኔ ስትዘረጉ፤ ዐይኖቼን ከእናንተ እሰውራለሁ፤ አብዝታችሁ ብትጸልዩም እንኳ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ በደም ተበክለዋል፤ ታጠቡ፤ ራሳችሁንም አንጹ፤ ክፉ ሥራችሁን ከፊቴ አርቁ፤ ክፉ ማድረጋችሁን ተዉ፤ መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን እሹ፤ የተገፉትን አጽናኑ፤ አባት ለሌላቸው ቁሙላቸው፤ ለመበለቶችም ተሟገቱ። “ኑና፤ እንዋቀስ” ይላል ጌታ፤ “ኀጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደም ቢቀላም እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል። እሺ ብትሉ፤ ብትታዘዙም የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብላችሁ ብታምፁ ግን ሰይፍ ይበላችኋል።” የጌታ አፍ ይህን ተናግሮአልና።