ሆሴዕ 9:9-12
ሆሴዕ 9:9-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በጊብዓ ዘመን እንደ ነበረ እጅግ ረከሱ፤ እርሱም በደላቸውን ያስባል፤ ኀጢአታቸውንም ይበቀላል። እስራኤልን በምድረ በዳ እንደ አለ ወይን ሆኖ አገኘሁት፤ አባቶቻችሁንም በመጀመሪያዋ ዓመት እንደ በለስ በኵራት ሆነው አየኋቸው፤ እነርሱ ግን ወደ ብዔልፌጎር መጡ፤ ለነውርም ተለዩ፤ እንደ ወደዱትም ርኩስ ሆኑ። ኤፍሬምም እንደ ወፍ በረረ፤ ክብራቸው ከመፅነስና ከመውለድ፥ ከማማጥም ነበር። ልጆቻቸውንም ቢያሳድጉ ከሰው ለይች ልጅ አልባ አደርጋቸዋለሁ፤ ሥጋዬ ከእነርሱ ነውና ወዮላቸው!
ሆሴዕ 9:9-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በጊብዓ እንደ ነበረው፣ በርኩሰት ውስጥ ተዘፍቀዋል፤ እግዚአብሔር ክፋታቸውን ያስባል፤ ስለ ኀጢአታቸውም ይቀጣቸዋል። “እስራኤልን ማግኘቴ፣ የወይንን ፍሬ በምድረ በዳ የማግኘት ያህል ነበር፤ አባቶቻችሁንም ማየቴ፣ የመጀመሪያውን የበለስ ፍሬ የማየት ያህል ነበር፤ ወደ በኣል ፌጎር በመጡ ጊዜ ግን፣ ለዚያ አሳፋሪ ጣዖት ራሳቸውን ለዩ፤ እንደ ወደዱትም ጣዖት የረከሱ ሆኑ። የኤፍሬም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፤ መውለድ፣ ማርገዝና መፀነስ የለም። ልጆችን ቢያሳድጉ እንኳ፣ ልጅ አልባ እስኪሆኑ ድረስ እነጥቃቸዋለሁ፤ ፊቴን ከእነርሱ በመለስሁ ጊዜ፣ ወዮ ለእነርሱ!
ሆሴዕ 9:9-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በጊብዓ ዘመን እንደ ነበረ እጅግ ረከሱ፥ እርሱም በደላቸውን ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይበቀላል። እስራኤልን በምድረ በዳ እንዳለ ወይን ሆኖ አገኘሁት፥ አባቶቻችሁንም ከመጀመሪያዋ ዓመት እንደ በለስ በኵራት ሆነው አየኋቸው፥ እነርሱ ግን ወደ ብዔልፌጎር መጡ፥ ለነውርም ተለዩ፥ እንደ ወደዱትም ርኩስ ሆኑ፥ የኤፍሬምም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፥ መውለድና መፅነስ ማርገዝም አይሆንላቸውም። ልጆቻቸውንም ቢያሳድጉ ሰው እንዳይቀርላቸው ልጅ አልባ አደረጋቸዋለሁ፥ ከእነርሱም በራቅሁ ጊዜ ወዮላቸው!
ሆሴዕ 9:9-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእስራኤል ሕዝብ በገባዖን ዘመን እንደ ነበሩት ሰዎች በጣም ረክሰዋል፤ እግዚአብሔርም በደላቸውን አስቦ ስለ ኃጢአታቸው ይቀጣቸዋል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እስራኤልን ባገኘሁ ጊዜ የወይን ዘለላን ከምድረ በዳ እንደ ማግኘት ነበር፤ የቀድሞ አባቶቻችሁን ባየሁ ጊዜ ቀድሞ የጐመራውን የበለስ ፍሬ እንደማየት ነበር፤ ወደ በዓል ጴዖር በደረሱ ጊዜ ግን ራሳቸውን ለዚያ አሳፋሪ ጣዖት ለይተው አቀረቡ፤ እነርሱም እንደዚያ እንደሚወዱት ጣዖት የረከሱ ሆኑ። የእስራኤል ሕዝብ ታላቅነት እንደ ወፍ በሮ ይጠፋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ መፅነስ የለም፤ ማርገዝ የለም፤ መውለድም የለም። ልጆች ወልደው ቢያሳድጉም ሁሉንም ስለምቀሥፋቸው ልጅ አልባ ሆነው ይቀራሉ፤ እኔ ከእነርሱ በራቅሁ ጊዜ ወዮላቸው!”
ሆሴዕ 9:9-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በጊብዓ ዘመን እንደነበረው ርኩሰት እነርሱም እንዲሁ እጅግ ረከሱ፤ እርሱም በደላቸውን ያስታውሳል፥ ስለ ኃጢአታቸውም ይቀጣቸዋል። እስራኤልን በምድረ በዳ እንዳለ እንደ ወይን ዘለላ ሆኖ አገኘሁት፤ አባቶቻችሁንም በወቅቱ መጀመሪያ ላይ እንዳለ እንደ በለስ በኵራት በበለስ ዛፍ ላይ ሆነው አየኋቸው፤ እነርሱ ግን ወደ ባዓል-ፌዖር መጡ፥ ለእፍረትም ነገር ራሳቸውን ለዩ፥ እንደ ወደዱትም ርኩስ ሆኑ፥ የኤፍሬምም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፤ መውለድና መፅነስ ማርገዝም አይሆንላቸውም። ልጆቻቸውንም ቢያሳድጉ እንኳ አንድም ሰው ሳላስቀር ልጅ አልባ አደረጋቸዋለሁ፤ ከእነርሱም በራቅሁ ጊዜ ወዮላቸው!