ሆሴዕ 9:1-17

ሆሴዕ 9:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እስ​ራ​ኤል ሆይ! ከአ​ም​ላ​ክህ ርቀህ አመ​ን​ዝ​ረ​ሃ​ልና እንደ አሕ​ዛብ ደስ አይ​በ​ልህ፤ ሐሴ​ት​ንም አታ​ድ​ርግ፤ ከእ​ህ​ሉና ከወ​ይኑ አው​ድማ ሁሉ ይልቅ የግ​ል​ሙ​ትና ዋጋን ወድ​ደ​ሃል። የእ​ህሉ አው​ድ​ማና የወ​ይኑ መጭ​መ​ቂያ አላ​ወ​ቃ​ቸ​ውም፤ ወይ​ኑም ጐደ​ለ​ባ​ቸው። በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ምድር ላይ አይ​ቀ​መ​ጡም፤ ኤፍ​ሬ​ምም በግ​ብፅ ይቀ​መ​ጣል፤ በአ​ሦ​ርም ርኩስ ነገ​ርን ይበ​ላሉ። ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የወ​ይን ጠጅን ቍር​ባን አያ​ቀ​ር​ቡም፤ መሥ​ዋ​ዕ​ታ​ቸ​ውም ደስ አያ​ሰ​ኘ​ውም፤ እንደ ኀዘ​ንም እን​ጀራ ይሆ​ን​ባ​ቸ​ዋል፤ የሚ​በ​ላ​ውም ሁሉ ይረ​ክ​ሳል፤ እን​ጀ​ራ​ቸ​ውም ለሰ​ው​ነ​ታ​ቸው ይሆ​ናል እንጂ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤት አይ​ገ​ባም። በዓ​መት በዓል ቀንና በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በዓል ቀን ምን ታደ​ር​ጋ​ላ​ችሁ? ስለ​ዚህ እነሆ ከግ​ብፅ ጕስ​ቍ​ልና የተ​ነሣ ሸሽ​ተው ይሄ​ዳሉ፤ ሜም​ፎ​ስም ትቀ​በ​ላ​ቸ​ዋ​ለች፤ በማ​ከ​ማ​ስም ይቀ​ብ​ሩ​አ​ቸ​ዋል፤ ጥፋ​ትም ወር​ቃ​ቸ​ውን ይወ​ር​ሳል፥ እሾ​ህም በድ​ን​ኳ​ኖ​ቻ​ቸው ውስጥ ይበ​ቅ​ላል። የበ​ቀል ወራት መጥ​ቶ​አል፤ የፍ​ዳም ወራት ደር​ሶ​አል፤ እስ​ራ​ኤ​ልም እንደ አበደ ነቢ​ይና ርኩስ መን​ፈስ እንደ አለ​በት ሰው ይታ​መ​ማል፤ ከኀ​ጢ​አ​ት​ህና ከጠ​ላ​ት​ነ​ትህ ብዛት የተ​ነ​ሣም ቍጣ​ህን አበ​ዛህ። ኤፍ​ሬም ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጋር ጉበኛ ነበረ፤ አሁን ግን ነቢዩ በመ​ን​ገዱ ሁሉ ላይ ክፉ ወጥ​መድ ሆነ፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ቤት ርኵ​ሰ​ትን አደ​ረጉ። በጊ​ብዓ ዘመን እንደ ነበረ እጅግ ረከሱ፤ እር​ሱም በደ​ላ​ቸ​ውን ያስ​ባል፤ ኀጢ​አ​ታ​ቸ​ው​ንም ይበ​ቀ​ላል። እስ​ራ​ኤ​ልን በም​ድረ በዳ እንደ አለ ወይን ሆኖ አገ​ኘ​ሁት፤ አባ​ቶ​ቻ​ች​ሁ​ንም በመ​ጀ​መ​ሪ​ያዋ ዓመት እንደ በለስ በኵ​ራት ሆነው አየ​ኋ​ቸው፤ እነ​ርሱ ግን ወደ ብዔ​ል​ፌ​ጎር መጡ፤ ለነ​ው​ርም ተለዩ፤ እንደ ወደ​ዱ​ትም ርኩስ ሆኑ። ኤፍ​ሬ​ምም እንደ ወፍ በረረ፤ ክብ​ራ​ቸው ከመ​ፅ​ነ​ስና ከመ​ው​ለድ፥ ከማ​ማ​ጥም ነበር። ልጆ​ቻ​ቸ​ው​ንም ቢያ​ሳ​ድጉ ከሰው ለይች ልጅ አልባ አደ​ር​ጋ​ቸ​ዋ​ለሁ፤ ሥጋዬ ከእ​ነ​ርሱ ነውና ወዮ​ላ​ቸው! እኔ እንደ አየሁ የኤ​ፍ​ሬም ልጆች ለወ​ጥ​መድ ተሰ​ጥ​ተ​ዋል፤ ኤፍ​ሬ​ምም ልጆ​ቹን ወደ ገዳ​ዮች አወጣ። አቤቱ! ስጣ​ቸው፤ ምን ትሰ​ጣ​ቸ​ዋ​ለህ? መካን ማኅ​ፀ​ንን፥ የደ​ረ​ቁ​ት​ንም ጡቶች ስጣ​ቸው። ክፋ​ታ​ቸ​ውም ሁሉ በጌ​ል​ገላ አለ፤ በዚያ ጠል​ቻ​ቸ​ዋ​ለሁ፤ ስለ ሠሩት ክፋት ከቤቴ አሳ​ድ​ዳ​ቸ​ዋ​ለሁ፤ ከእ​ን​ግ​ዲህ ወዲያ አል​ወ​ድ​ዳ​ቸ​ውም፤ አለ​ቆ​ቻ​ቸው ሁሉ ዐመ​ፀ​ኞች ናቸ​ውና። ኤፍ​ሬም ታመመ፤ ሥሩም ደረቀ፤ ከእ​ን​ግ​ዲ​ህም ወዲህ ፍሬ አያ​ፈ​ራም፤ ደግ​ሞም ቢወ​ልዱ የተ​ወ​ደ​ደ​ውን የማ​ኅ​ፀ​ና​ቸ​ውን ፍሬ እገ​ድ​ላ​ለሁ። አል​ሰ​ሙ​ት​ምና እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይጥ​ላ​ቸ​ዋል፤ በአ​ሕ​ዛ​ብም መካ​ከል ተቅ​በ​ዝ​ባ​ዦች ይሆ​ናሉ።

ሆሴዕ 9:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እስራኤል ሆይ፤ ደስ አይበልሽ፤ እንደ ሌሎችም ሕዝቦች ሐሤት አታድርጊ፤ በአምላክሽ ላይ አመንዝረሻልና፤ በየእህል ዐውድማውም ላይ፣ ለጋለሞታ የሚከፈለውን ዋጋ ወድደሻል። የእህል ዐውድማዎችና የወይን መጭመቂያዎች ሕዝቡን አይመግቡም፤ አዲሱም የወይን ጠጅ ይጐድልባቸዋል። በእግዚአብሔር ምድር አይቀመጡም፤ ኤፍሬም ወደ ግብጽ ይመለሳል፤ የረከሰውንም ምግብ በአሦር ይበላል። የወይን ጠጅን ቍርባን ለእግዚአብሔር አያፈስሱም፤ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሠኘውም፤ እንዲህ ዐይነቱ መሥዋዕት ለእነርሱ የሐዘንተኞች እንጀራ ይሆንባቸዋል፤ የሚበሉትም ሁሉ ይረክሳሉ። ይህ ምግብ ለገዛ ራሳቸው ይሆናል፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ አይገባም። በእግዚአብሔር የበዓል ቀናት፣ በዓመት በዓሎቻችሁም ቀን ምን ታደርጋላችሁ? ከጥፋት ቢያመልጡም እንኳ፣ ግብጽ ትሰበስባቸዋለች፤ ሜምፎስም ትቀብራቸዋለች። የብር ሀብታቸውን ዳዋ ያለብሰዋል፤ ድንኳኖቻቸውንም እሾኽ ይወርሳቸዋል። የቅጣት ቀን መጥቷል፤ የፍርድም ቀን ቀርቧል፤ እስራኤልም ይህን ይወቅ! ኀጢአታችሁ ብዙ፣ ጠላትነታችሁም ታላቅ ስለ ሆነ፣ ነቢዩ እንደ ቂል፣ መንፈሳዊውም ሰው እንደ እብድ ተቈጥሯል። ነቢዩ ከአምላኬ ጋራ ሆኖ፣ የኤፍሬም ጠባቂ ነው፤ ዳሩ ግን በመንገዱ ሁሉ ወጥመድ፣ በአምላኩም ቤት ጠላትነት ይጠብቀዋል። በጊብዓ እንደ ነበረው፣ በርኩሰት ውስጥ ተዘፍቀዋል፤ እግዚአብሔር ክፋታቸውን ያስባል፤ ስለ ኀጢአታቸውም ይቀጣቸዋል። “እስራኤልን ማግኘቴ፣ የወይንን ፍሬ በምድረ በዳ የማግኘት ያህል ነበር፤ አባቶቻችሁንም ማየቴ፣ የመጀመሪያውን የበለስ ፍሬ የማየት ያህል ነበር፤ ወደ በኣል ፌጎር በመጡ ጊዜ ግን፣ ለዚያ አሳፋሪ ጣዖት ራሳቸውን ለዩ፤ እንደ ወደዱትም ጣዖት የረከሱ ሆኑ። የኤፍሬም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፤ መውለድ፣ ማርገዝና መፀነስ የለም። ልጆችን ቢያሳድጉ እንኳ፣ ልጅ አልባ እስኪሆኑ ድረስ እነጥቃቸዋለሁ፤ ፊቴን ከእነርሱ በመለስሁ ጊዜ፣ ወዮ ለእነርሱ! ኤፍሬምን እንደ ጢሮስ፣ በመልካም ስፍራ ተተክሎ አየሁት፤ አሁን ግን ኤፍሬም ልጆቹን፣ ለነፍሰ ገዳዮች አሳልፎ ይሰጣል።” እግዚአብሔር ሆይ፤ ስጣቸው፤ ምን ትሰጣቸዋለህ? የሚጨነግፉ ማሕፀኖችን፣ የደረቁ ጡቶችን ስጣቸው። “በጌልገላ ካደረጉት ክፋታቸው ሁሉ የተነሣ፣ እኔ በዚያ ጠላኋቸው፤ ስለ ሠሩት ኀጢአት፣ ከቤቴ አሳድዳቸዋለሁ፤ ከእንግዲህም አልወድዳቸውም፤ መሪዎቻቸው ሁሉ ዐመፀኞች ናቸው። ኤፍሬም ተመታ፤ ሥራቸው ደረቀ፤ ፍሬም አያፈሩም፤ ልጆች ቢወልዱም እንኳ፣ ተንከባክበው ያሳደጓቸውን ልጆቻቸውን እገድላለሁ።” ባለመታዘዛቸው ምክንያት፣ አምላኬ ይጥላቸዋል፤ በአሕዛብም መካከል ተንከራታች ይሆናሉ።

ሆሴዕ 9:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እስራኤል ሆይ፥ ከአምላክህ ተለይተህ አመንዝረሃልና እንደ አሕዛብ ደስ አይበልህ፥ ሐሴትንም አታድርግ፥ በእህሉ አውድማ ሁሉ ላይ የግልሙትናን ዋጋ ወድደሃል። አውድማውና መጥመቂያው አይመግባቸውም፥ ጉሽ ጠጅም ይጐድልባታል። በእግዚአብሔር ምድር ላይ አይቀመጡም፥ ኤፍሬምም ወደ ግብጽ ይመለሳል፥ በአሦርም ርኵስን ነገር ይበላሉ። ለእግዚአብሔርም የወይን ጠጅን ቍርባን አያፈስሱም፥ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሰኘውም፥ የኀዘንም እንጀራ ይሆንላቸዋል፥ የሚበላውም ሁሉ ይረክሳል፥ እንጀራቸውም ለሰውነታቸው ይሆናል እንጂ ወደ እግዚአብሔር ቤት አይገባም። በዓመት በዓል ቀንና በእግዚአብሔር በዓል ቀን ምን ታደርጋላችሁ? እነሆ፥ ከጥፋት ሸሽተው ሄዱ፥ ግብጽም ትሰበስባቸዋለች፥ ሜምፎስም ትቀብራቸዋለች፥ ሳማም የብራቸውን ጌጥ ይወርሳል፥ እሾህም በድንኳኖቻቸው ውስጥ ይበቅላል። የበቀል ወራት መጥቶአል፥ የፍዳም ወራት ደርሶአል፥ እስራኤልም ያውቃል፥ ከኃጢአትህና ከጠላትነትህ ብዛት የተነሣ ነቢዩ ሰንፎአል፥ መንፈስም ያለበት ሰው አብዶአል። ኤፍሬም ከአምላኬ ጋር ተመልካች ነበረ፥ አሁን ግን ነቢዩ በመንገዱ ሁሉ ላይ የወፍ ወጥመድ ሆነ፥ በአምላኩም ቤት ጠላትነት አለ። በጊብዓ ዘመን እንደ ነበረ እጅግ ረከሱ፥ እርሱም በደላቸውን ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይበቀላል። እስራኤልን በምድረ በዳ እንዳለ ወይን ሆኖ አገኘሁት፥ አባቶቻችሁንም ከመጀመሪያዋ ዓመት እንደ በለስ በኵራት ሆነው አየኋቸው፥ እነርሱ ግን ወደ ብዔልፌጎር መጡ፥ ለነውርም ተለዩ፥ እንደ ወደዱትም ርኩስ ሆኑ፥ የኤፍሬምም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፥ መውለድና መፅነስ ማርገዝም አይሆንላቸውም። ልጆቻቸውንም ቢያሳድጉ ሰው እንዳይቀርላቸው ልጅ አልባ አደረጋቸዋለሁ፥ ከእነርሱም በራቅሁ ጊዜ ወዮላቸው! እኔ እንዳየሁ የኤፍሬም ልጆች ለምርኮ ተሰጥተዋል፥ ኤፍሬምም ልጆቹን ወደ ገዳዩች ያወጣል። አቤቱ፥ ስጣቸው፥ ምን ትሰጣቸዋለህ? የሚጨነግፍን ማኅፀን የደረቀውንም ጡት ስጣቸው። ክፋታቸው ሁሉ በጌልገላ አለ፥ በዚያ ጠልቻቸዋለሁ፥ ስለ ሠሩት ክፋት ከቤቴ አሳድዳቸዋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲያ አልወድዳቸውም፥ አለቆቻቸው ሁሉ ዓመፀኞች ናቸው። ኤፍሬም ተመታ፥ ሥሩም ደረቀ፥ ፍሬም አያፈራም፥ ደግሞም ቢወልዱ የማኅፀናቸውን ፍሬ እገድላለሁ። አልሰሙትምና አምላኬ ይጥላቸዋል፥ በአሕዛብም መካከል ተቅበዝባዦች ይሆናሉ።

ሆሴዕ 9:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በየዐውድማው የሚገኘውን የዝሙት ዋጋ ከበዓል የሚሰጥ በረከት መስሎአችሁ፥ ትወዱታላችሁ፤ ይህን በማድረጋችሁ ለአምላካችሁ ታማኞች ሆናችሁ አልተገኛችሁም፤ ስለዚህ እንደ ሌሎች ሕዝቦች መደሰታችሁንና ሐሴት ማድረጋችሁን ተዉ! ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ከዐውድማችሁ እህልን፥ ከመጭመቂያችሁም የወይን ጠጅን ከቶ አታገኙም፤ አዲስ የወይን ጠጅም አይገኝም። የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር በሰጣቸው ምድር አይኖሩም፤ ነገር ግን ተገደው ወደ ግብጽ ይመለሳሉ፤ ወደ አሦርም ሄደው በሥርዓት ንጹሕ ያልሆነ ምግብ ይበላሉ። በዚያም ለእግዚአብሔር የወይን ጠጅ መባ ማቅረብ አይችሉም፤ መሥዋዕታቸውም እግዚአብሔርን አያስደስትም፤ የእነርሱ እንጀራ ሲርባቸው የሚበሉት እንጂ ወደ እግዚአብሔር ቤት መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርብ አይደለም፤ ስለዚህ ለእነርሱ የእዝን እንጀራ ይሆናል፤ እርሱንም የሚመገብ ሁሉ ይረክሳል። እንግዲህ ለእግዚአብሔር ክብር በተወሰኑት የዓመት በዓላት ምን ታደርጋላችሁ? እነሆ ከጥፋት ለማምለጥ ሲሸሹ ግብጽ ትሰበስባቸዋለች፤ ሜምፊስ ትቀብራቸዋለች፤ ያከማቹት የብር ሀብት ሁሉ ሳማ ለብሶ ይቀራል፤ መኖሪያቸውም እሾኽ ይበቅልበታል። የቅጣት ቀን ደርሶአል፤ እስራኤላውያንም የበቀል ቀን መቃረቡን ይወቁ፤ በእናንተ በደልና ጥላቻ ምክንያት ነቢይን እንደ ሞኝ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበትን ሰው እንደ ዕብድ ትቈጥሩታላችሁ። እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ነቢዩ ጠባቂ እንዲሆን አድርጎታል፤ ሆኖም በመንገዱ ሁሉ ወጥመድ ተዘርግቶበታል፤ በአምላኩም ቤተ መቅደስ ጥላቻ ይጠብቀዋል። የእስራኤል ሕዝብ በገባዖን ዘመን እንደ ነበሩት ሰዎች በጣም ረክሰዋል፤ እግዚአብሔርም በደላቸውን አስቦ ስለ ኃጢአታቸው ይቀጣቸዋል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እስራኤልን ባገኘሁ ጊዜ የወይን ዘለላን ከምድረ በዳ እንደ ማግኘት ነበር፤ የቀድሞ አባቶቻችሁን ባየሁ ጊዜ ቀድሞ የጐመራውን የበለስ ፍሬ እንደማየት ነበር፤ ወደ በዓል ጴዖር በደረሱ ጊዜ ግን ራሳቸውን ለዚያ አሳፋሪ ጣዖት ለይተው አቀረቡ፤ እነርሱም እንደዚያ እንደሚወዱት ጣዖት የረከሱ ሆኑ። የእስራኤል ሕዝብ ታላቅነት እንደ ወፍ በሮ ይጠፋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ መፅነስ የለም፤ ማርገዝ የለም፤ መውለድም የለም። ልጆች ወልደው ቢያሳድጉም ሁሉንም ስለምቀሥፋቸው ልጅ አልባ ሆነው ይቀራሉ፤ እኔ ከእነርሱ በራቅሁ ጊዜ ወዮላቸው!” እስራኤልን በመልካም መሬት ላይ እንደ ተተከለች የዘንባባ ዛፍ ሆና አየኋት፤ እስራኤላውያን ግን ልጆቻቸውን ለዕርድ አቀረቡ። ጌታ ሆይ! ለዚህ ሕዝብ ምን ትሰጠው፤ የሚጨነግፍ ማሕፀንና ደረቅ ጡት ስጣቸው! እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ገና በጌልገላ ሳሉ ክፉ ሥራቸው ተገለጠ፤ እኔም በዚያ የእነርሱን ሥራ መጥላት ጀመርኩ፤ ስለ ሠሩትም ክፉ ሥራ ከሰጠኋቸው ምድር አስወጣቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ለእነርሱ ፍቅር አላሳያቸውም፤ መሪዎቻቸው ሁሉ ዐመፀኞች ሆነዋል። የእስራኤል ሕዝብ ነፋስ እንደ መታው፥ ሥሩ እንደ ደረቀና ማፍራት እንደማይችል ዛፍ ያለ ፍሬ ይቀራሉ፤ ልጆች ቢወልዱም እጅግ የሚወዱአቸውን ልጆቻቸውን እገድላለሁ።” እርሱን ስላልታዘዙ አምላኬ ይጥላቸዋል፤ እነርሱም በአሕዛብ መካከል በመንከራተት ይኖራሉ።

ሆሴዕ 9:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እስራኤል ሆይ! ከአምላክህ ተለይተህ አመንዝረሃልና እንደ አሕዛብ ደስ አይበልህ፥ ሐሴትንም አታድርግ፤ በእህሉ አውድማ ሁሉ ላይ የዝሙትን ዋጋ ወድደሃል። አውድማውና ወይን ጠጅ መጥመቂያው አይመግባቸውም፥ በመጥመቂያውም ውስጥ አዲስ የወይን ጠጅ ጐድሏል። በጌታ ምድር ላይ አይቀመጡም፤ ኤፍሬምም ወደ ግብጽ ይመለሳል፥ በአሦርም ርኩስን ነገር ይበላሉ። ለጌታም የወይን ጠጅን ቁርባን አያፈስሱም፥ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሰኘውም፤ እንደ ኀዘን እንጀራም ይሆንባቸዋል፥ የሚበሉትም ሁሉ ይረክሳሉ፤ እንጀራቸውም ለሆዳቸው ይሆናል እንጂ ወደ ጌታ ቤት አይገባም። በዓመት በዓል ቀንና በጌታ በዓል ቀን ምን ታደርጋላችሁ? እነሆ፥ ከጥፋት ሸሽተው ቢሄዱ እንኳ ግብጽ ትሰበስባቸዋለች፥ ሜምፎስም ትቀብራቸዋለች፤ ሳማም የብራቸውን ጌጥ ይወርሰዋል፥ እሾኽም በድንኳኖቻቸው ውስጥ ይበቅላል። የበቀል ወራት መጥቷል፥ የፍዳም ወራት ደርሶአል፥ እስራኤልም ይወቀው፤ ከበደልህና ከጥላቻህ ብዛት የተነሣ ነቢዩ ሞኝ ሆኗል፥ መንፈስም ያለበት ሰው አብዶአል። ነቢዩ ከአምላኬ ጋር በኤፍሬም ላይ ጠባቂ ነው፤ አሁን ግን በመንገዱ ሁሉ ላይ የወፍ ወጥመድ፥ በአምላኩም ቤት ጥላቻ አለ። በጊብዓ ዘመን እንደነበረው ርኩሰት እነርሱም እንዲሁ እጅግ ረከሱ፤ እርሱም በደላቸውን ያስታውሳል፥ ስለ ኃጢአታቸውም ይቀጣቸዋል። እስራኤልን በምድረ በዳ እንዳለ እንደ ወይን ዘለላ ሆኖ አገኘሁት፤ አባቶቻችሁንም በወቅቱ መጀመሪያ ላይ እንዳለ እንደ በለስ በኵራት በበለስ ዛፍ ላይ ሆነው አየኋቸው፤ እነርሱ ግን ወደ ባዓል-ፌዖር መጡ፥ ለእፍረትም ነገር ራሳቸውን ለዩ፥ እንደ ወደዱትም ርኩስ ሆኑ፥ የኤፍሬምም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፤ መውለድና መፅነስ ማርገዝም አይሆንላቸውም። ልጆቻቸውንም ቢያሳድጉ እንኳ አንድም ሰው ሳላስቀር ልጅ አልባ አደረጋቸዋለሁ፤ ከእነርሱም በራቅሁ ጊዜ ወዮላቸው! ኤፍሬምን እንደ ጢሮስ በለመለመ መስክ ተተክሎ አየሁት፤ አሁን ግን ኤፍሬም ልጆቹን ወደ ገዳዩች ያወጣል። ጌታ ሆይ! ስጣቸው፤ ምን ትሰጣቸዋለህ? የሚጨነግፍን ማኅፀን የደረቀውንም ጡት ስጣቸው። ክፋታቸው ሁሉ በጌልገላ አለ፤ በዚያ ሳሉ ጠላኋቸው፤ ስለ ሥራዎቻቸውም ክፋት ከቤቴ አስወጣቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ አልወድዳቸውም፤ አለቆቻቸው ሁሉ ዓመፀኞች ናቸው። ኤፍሬም ተመታ፥ ሥሩም ደረቀ፥ ፍሬም አያፈራም፤ ደግሞም ቢወልዱ እንኳ እጅግ የሚወዱአቸውን የማኅፀናቸውን ፍሬ እገድላለሁ። እርሱን አልሰሙትምና አምላኬ ይጥላቸዋል፤ በአሕዛብም መካከል ተቅበዝባዦች ይሆናሉ።