ሆሴዕ 8:1-14

ሆሴዕ 8:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በብ​ብ​ታ​ቸው እንደ መሬት፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ቤት እንደ ንስር ይመ​ጣል። ቃል ኪዳ​ኔን ተላ​ል​ፈ​ዋ​ልና፥ በሕ​ጌም ላይ ዐም​ፀ​ዋ​ልና። አም​ላክ ሆይ! እኛ እስ​ራ​ኤል ዐወ​ቅ​ንህ ብለው ወደ እኔ ይጮ​ኻሉ። እስ​ራ​ኤል ደግ​ነ​ቱን ጥሎ​አ​ልና፤ ጠላ​ትም ያሳ​ድ​ደ​ዋ​ልና። ራሳ​ቸ​ውን አነ​ገሡ፤ ከእ​ኔም ዘንድ አይ​ደ​ለም፤ አለ​ቆ​ች​ንም አደ​ረጉ፤ እኔም አላ​ወ​ቅ​ሁም፤ ለጥ​ፋ​ታ​ቸ​ውም ከብ​ራ​ቸ​ውና ከወ​ር​ቃ​ቸው ጣዖ​ታ​ትን ለራ​ሳ​ቸው አደ​ረጉ። ሰማ​ርያ ሆይ! እም​ቦ​ሳ​ሽን መልሺ፤ ቍጣ​ዬም በላ​ያ​ቸው ነድ​ዶ​አል፤ እስከ መቼም ድረስ ንጹሕ ሊሆኑ አይ​ች​ሉም። ይህ ደግሞ በእ​ስ​ራ​ኤል ዘንድ ነው፤ ሠራ​ተኛ ሠራው፤ እር​ሱም አም​ላክ አይ​ደ​ለም፤ ሰማ​ርያ ሆይ! እን​ቦ​ሳሽ ተቅ​በ​ዝ​ብ​ዞ​አ​ልና። ነፋ​ስን ዘር​ተ​ዋ​ልና ዐውሎ ነፋ​ስን አጨዱ፤ ለነ​ዶ​አ​ቸ​ውም ኀይል የለ​ውም፤ ከፍ​ሬ​ውም ዱቄት አይ​ገ​ኝም፤ ቢገ​ኝም ጠላት ይበ​ላ​ዋል። እስ​ራ​ኤል ተው​ጦ​አል፤ በአ​ሕ​ዛ​ብም መካ​ከል ዛሬ እንደ ግትቻ ዕቃ ሆኖ​አል። ለብ​ቻ​ውም እን​ደ​ሚ​ቀ​መጥ እንደ ምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ወጥ​ተ​ዋል፤ ኤፍ​ሬ​ምም እንደ ገና ለመ​ለመ፤ እጅ መን​ሻ​ንም ወደደ። ስለ​ዚህ ለአ​ሕ​ዛብ አል​ፈው ይሰ​ጣሉ፤ እኔም አሁን እቀ​በ​ላ​ቸ​ዋ​ለሁ፤ ንጉ​ሥ​ንና አለ​ቆ​ች​ንም ይቀቡ ዘንድ ፈጽ​መው ያን​ሣሉ። ኤፍ​ሬም መሠ​ዊ​ያን አብ​ዝ​ቶ​አ​ልና የወ​ደ​ደው መሠ​ዊያ ለኀ​ጢ​አት ሆነ​በት። ብዙ ሕጎ​ችን እጽ​ፍ​ለ​ታ​ለሁ፤ ነገር ግን ሥር​ዐ​ቱና የተ​ወ​ደ​ደው መሠ​ዊ​ያው እንደ እን​ግዳ ነገር ተቈ​ጠሩ። መሥ​ዋ​ዕ​ት​ንም ቢሠዉ፥ ሥጋ​ንም ቢበሉ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አይ​ቀ​በ​ላ​ቸ​ውም፤ አሁ​ንም በደ​ላ​ቸ​ውን ያስ​ባል፤ በኀ​ጢ​አ​ታ​ቸ​ውም ይበ​ቀ​ላ​ቸ​ዋል፤ እነ​ር​ሱም ወደ ግብፅ ይመ​ለ​ሳሉ፤ በአ​ሦ​ርም ርኩስ ነገ​ርን ይበ​ላሉ። እስ​ራ​ኤል ፈጣ​ሪ​ውን ረስ​ቶ​አል፤ መስ​ገ​ጃ​ዎ​ች​ንም ሠር​ቶ​አል፤ ይሁ​ዳም የተ​መ​ሸ​ጉ​ትን ከተ​ሞች አብ​ዝ​ቶ​አል፤ እኔ ግን በከ​ተ​ሞች ላይ እሳ​ትን እሰ​ድ​ዳ​ለሁ፤ መሠ​ረ​ቶ​ቻ​ቸ​ው​ንም ትበ​ላ​ለች።

ሆሴዕ 8:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“መለከትን በአፍህ ላይ አድርግ! ሕዝቡ ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና፣ በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና፣ ንስር በእግዚአብሔር ቤት ላይ ነው፤ እስራኤልም፣ ‘አምላካችን ሆይ፤ እኛ እናውቅሃለን!’ እያሉ፣ ወደ እኔ ይጮኻሉ። ነገር ግን እስራኤል በጎ የሆነውን ነገር ናቁ፤ ጠላትም ያሳድዳቸዋል። ያለ እኔ ፈቃድ ነገሥታትን አነገሡ፤ እኔንም ሳይጠይቁ አለቆችን መረጡ፤ በብራቸውና በወርቃቸው፣ ለገዛ ጥፋታቸው፣ ጣዖታትን ለራሳቸው ሠሩ። ሰማርያ ሆይ፤ የጥጃ ጣዖትሽን ጣዪ! ቍጣዬ በእነርሱ ላይ ነድዷል፤ የማይነጹት እስከ መቼ ነው? ይህም በእስራኤል ሆነ! የእጅ ጥበብ ባለሙያ የሠራው ይህ ጥጃ፣ አምላክ አይደለም፤ ያ የሰማርያ ጥጃ፣ ተሰባብሮ ይደቅቃል። “ነፋስን ይዘራሉ፤ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ፤ አገዳው ዛላ የለውም፤ ዱቄትም አይገኝበትም፤ እህል አፍርቶ ቢገኝም፣ ባዕዳን ይበሉታል። እስራኤል ተውጠዋል፤ በአሕዛብም መካከል፣ ዋጋ እንደሌለው ዕቃ ሆነዋል። ለብቻው እንደሚባዝን የዱር አህያ፣ ወደ አሦር ሄደዋልና፤ ኤፍሬም በእጅ መንሻ ወዳጅ አበጀ። በአሕዛብ መካከል ራሳቸውን ቢሸጡም፣ እኔ አሁን እሰበስባቸዋለሁ፤ በንጉሥና በአለቆች ጭቈና ሥር፣ እየመነመኑ ይሄዳሉ። “ኤፍሬም ለኀጢአት ማስተስረያ ብዙ መሠዊያዎችን ቢሠራም፣ እነርሱ የኀጢአት መሥሪያ መሠዊያዎች ሆነውበታል። በሕጌ ውስጥ ያለውን ብዙውን ነገር ጻፍሁላቸው፤ እነርሱ ግን እንደ እንግዳ ነገር ቈጠሩት። ለእኔ የሚገባውን መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ሥጋውንም ይበላሉ፤ እግዚአብሔር ግን በእነርሱ አልተደሰተም፤ ስለዚህ ክፋታቸውን ያስታውሳል፤ ኀጢአታቸውን ይቀጣል፤ ወደ ግብጽም ይመለሳሉ። እስራኤል ፈጣሪውን ረሳ፤ ቤተ መንግሥቶችንም ሠራ፤ ይሁዳም የተመሸጉ ከተሞችን አበዛ፤ እኔ ግን በከተሞቻቸው ላይ እሳትን እለቃለሁ፤ ምሽጎቻቸውንም ይበላል።”

ሆሴዕ 8:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

መለከትን ወደ አፍህ አቅርብ፥ ቃል ኪዳኔን ተላልፈዋልና፥ በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ንስር ይመጣል። እነርሱም፦ አምላክ ሆይ፥ እኛ እስራኤል አወቅንህ ብለው ወደ እኔ ይጮኻሉ። እስራኤል ደግነትን ጥሎአል፥ ጠላትም ያሳድዱታል። ለራሳቸው ነገሥታትን አነገሡ፥ ከእኔም ዘንድ አይደለም፥ አለቆችንም አደረጉ፥ እኔም አላወቅሁም፥ ለጥፋታቸውም ከብራቸውና ከወርቃቸው ጣዖታትን ለራሳቸው አደረጉ። ሰማርያ ሆይ፥ እምቦሳህን፥ ጥሎአል፥ ቍጣዬ በላያቸው ነድዶአል፥ እስከ መቼ ድረስ ንጹሕ ሊሆኑ አይችሉም? ይህ ደግሞ ከእስራኤል ዘንድ ነው፥ ሠራተኛ ሠራው፥ እርሱም አምላክ አይደለም፥ የሰማርያም እምቦሳ ይቈራረጣል። ነፋስን ዘርተዋል፥ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ፥ አገዳ የለውም፥ ከፍሬውም ዱቄት አይገኝም፥ ቢገኝም እንግዶች ይበሉታል። እስራኤል ተውጦአል፥ በአሕዛብ መካከል ዛሬ እንደ ረከሰ ዕቃ ሆኖአል። ለብቻውም እንደሚቀመጥ እንደ ምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ወጥተዋል፥ ኤፍሬምም ወዳጆቹን በእጅ መንሻ ገዛ። ነገር ግን ለአሕዛብ እጅ መንሻ ቢሰጡ እኔ አሁን እሰበስባቸዋለሁ፥ ከንጉሥና ከአለቆችም ሸክም የተነሣ ይደክማሉ። ኤፍሬም ኃጢአትን ለመሥራት መሠዊያ አብዝቶአልና መሠዊያ ለኃጢአት ይሆንለታል። የሕጌን ብዛት ጽፌለታለሁ፥ እነርሱ ግን እንደ እንግዳ ነገር ቈጥረውታል። መሥዋዕቴን ያቀርባሉ፥ ሥጋንም ያርዳሉ፥ ይበላሉም፥ እግዚአብሔር ግን አይቀበላቸውም፥ በደላቸውንም ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይቀጣል፥ እነርሱም ወደ ግብጽ ይመለሳሉ። እስራኤል ፈጣሪውን ረስቶአል፥ መስገጃዎችንም ሠርቶአል፥ ይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች አብዝቶአል፥ እኔ ግን በከተሞች ላይ እሳት እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችንም ትበላለች።

ሆሴዕ 8:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ቃል ኪዳኔን ስላፈረሱና ሕጌን ስለ ተላለፉ በቤቴ ላይ ጠላት እንደ ጆፌ አሞራ ያንዣበበ ስለ ሆነ የማስጠንቀቂያ መለከት ንፉ!” እነርሱም፥ “አምላክ ሆይ! እኛ ሕዝብህ እናውቅሃለን” እያሉ ወደ እኔ ይጮኻሉ፤ ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በጎ ነገርን ስለ ጠሉ ጠላት ያሳድዳቸዋል። “ያለ እኔ ፈቃድ ነገሥታትን አነገሡ፤ እኔን ሳይጠይቁ መሳፍንትን መርጠው ሾሙ፤ ከብራቸውና ከወርቃቸው ለገዛ ራሳቸው መጥፊያ የሆኑትን ጣዖቶችን ሠሩ። የሰማርያ ሕዝብ ሆይ! በጥጃ ምስል የተሠራ ጣዖታችሁን ተጸይፌአለሁ፤ ቊጣዬ በእናንተ ላይ እንደ እሳት ይነዳል፤ ከበደል የማትነጹት እስከ መቼ ነው? ይህ በጥጃ ምስል የተሠራ ጣዖት በአናጢ እጅ የተሠራ ስለ ሆነ አምላክ ሊሆን አይችልም፤ ስለዚህ በጥጃ ምስል የተሠራው የሰማርያ ጣዖት ተሰባብሮ ይወድቃል። እነርሱ ነፋስን ዘርቶ ዐውሎ ነፋስን እንደሚያጭድ ይሆናሉ፤ ዛላ የሌለው የእህል አገዳ ምግብ ሊሆን አይችልም፤ ፍሬ ቢኖረውም እንኳ የሚበሉት ባዕዳን በሆኑ ነበር። የእስራኤል ሕዝብ በአሕዛብ መካከል ተውጠው ቀርተዋል፤ ዋጋ እንደሌለው ዕቃም ሆነዋል። ብቻውን እንደሚንከራተት የምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ሄዱ፤ እንዲጠብቁአቸውም ዋጋ በመክፈል መንግሥታትን ተለማመጡ፤ መንግሥታትን ለመለማመጥ ዋጋ ቢከፍሉም እንኳ እኔ በአንድነት እሰበስበዋለሁ፤ ነገሥታትና መሳፍንት በሚያደርጉባቸው ጭቈና እየመነመኑ ይሄዳሉ። “የእስራኤል ሕዝብ ብዙ መሠዊያዎችን ለኃጢአት ማስተስረያ ብለው ሠርተዋል፤ ነገር ግን እነዚያ መሠዊያዎች የኃጢአት መሥሪያ ቦታዎች ሆኑ። እኔ ለእነርሱ ከሕጌ ብዙ መመሪያዎችን ጽፌ ሰጠኋቸው፤ እነርሱ ግን እንደ እንግዳ ነገር ቈጠሩት። እነርሱ ለእኔ ምርጥ መሥዋዕት ቢያቀርቡ፥ የመሥዋዕቱንም ሥጋ ቢበሉ እኔ እግዚአብሔር አልቀበላቸውም። አሁን በደላቸውን አስቤ በኃጢአታቸው እቀጣቸዋለሁ፤ ወደ ግብጽም ይመለሳሉ። “የእስራኤል ሕዝብ ለራሳቸው ታላላቅ ቤተ መንግሥቶች ሠርተዋል፤ እኔን ፈጣሪአቸውን ግን ረስተዋል፤ የይሁዳም ሕዝብ ብዙ የተመሸጉ ከተሞችን ሠርተዋል፤ ስለዚህ ከተሞቻቸውንና ምሽጎቻቸውን የሚያቃጥል እሳት እልክባቸዋለሁ።”

ሆሴዕ 8:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

መለከትን ወደ አፍህ አቅርብ፤ ቃል ኪዳኔን ተላልፈዋልና፥ በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና እንደ ንስር በጌታ ቤት ላይ እያንዣበበ ነው። እነርሱም፦ “አምላክ ሆይ! እኛ እስራኤል እናውቅሃለን!” ብለው ወደ እኔ ጮሁ። እስራኤል በጎነትን ጥሎአል፤ ጠላትም ያሳድደዋል። ለራሳቸው ነገሥታትን አነገሡ፥ ከእኔም ዘንድ አይደለም፤ አለቆችንም ሾሙ፥ እኔም አላወቅሁም፤ ለመጥፊያቸው ከብራቸውና ከወርቃቸው ጣዖታትን ለራሳቸው ሠሩ። ሰማርያ ሆይ! እምቦሳህን አስወግጃለሁ፤ ቁጣዬ በላያቸው ነድዶአል፤ መንጻት የማይቻላቸው እስከ መቼ ድረስ ነው? የተሠራው ነገር ከእስራኤል ዘንድ ነው፤ እርሱም በሞያተኛ የተሠራ ነው፤ እርሱም አምላክ አይደለም፤ የሰማርያም እምቦሳ ይሰባበራል። ነፋስን ዘሩ፥ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ፤ የቆመውም እህል ዛላ የለውም፥ ከእርሱም ዱቄት አይገኝም፤ ቢገኝም እንኳ ባዕዳን ይበሉታል። እስራኤል ተውጦአል፤ አሁን በአሕዛብ መካከል እንደ ረከሰ ዕቃ ሆነዋል። ብቻውን እንደሚንከራተት የምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ወጥተዋል፤ ኤፍሬምም ወዳጆችን በገንዘብ ቀጥሯል። ከአሕዛብ መካከል ወዳጆችን በገንዘብ ቢቀጥሩም እንኳ እኔ አሁን እሰበስባቸዋለሁ፤ ከንጉሥና ከአለቆችም ሸክም የተነሣ በቶሎ ይመነምናሉ። ኤፍሬም ኃጢአትን ለመሥራት መሠዊያዎችን አብዝቶአልና የኃጢአት መሥርያ መሠዊያዎች ሆነውለታል። በሺዎች የሚቆጠሩትን ሕጎቼን ጽፌለት እንኳ እንደ እንግዳ ነገር ተቆጠሩ። የተመረጠውን መሥዋዕቴን ያቀርባሉ፥ ሥጋንም ያርዳሉ፥ ይበላሉም፤ ጌታ ግን በእነርሱ ደስ አይሰኝም፤ በደላቸውን አሁን ያስታውሳል፥ ስለ ኃጢአታቸውም ይቀጣቸዋል፤ እነርሱም ወደ ግብጽ ይመለሳሉ። እስራኤል ፈጣሪውን ረስቶአል፥ ቤተ መንግሥቶችን ሠርቶአል፤ ይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች አብዝቶአል፤ እኔ ግን በእርሱ ከተሞች ላይ እሳት እልካለሁ፥ የንጉሥ ቅጥሮቹንም ትበላለች።