ሆሴዕ 6:4-10
ሆሴዕ 6:4-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ምሕረታችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ጠል ነውና ኤፍሬም ሆይ! ምን ላድርግልህ? ይሁዳ ሆይ! ምን ላድርግልህ? ስለዚህ ነቢያቶቻችሁን አጨድኋቸው፤ በአፌም ቃል ገደልኋቸው፤ ፍርዴም እንደ ብርሃን ይወጣል። ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለሁና። እነርሱ ግን ቃል ኪዳንን እንደሚያፈርስ ሰው ሆኑ፤ በዚያም ላይ ከዱኝ። ገለዓድ ከንቱን የምትሠራና በደም የተቀባች ከተማ ናት፥ ሰውን እንደሚያደቡ ወንበዴዎች፥ እንዲሁ ካህናት በሴኬም መንገድ ላይ አድብተው ይገድላሉ፤ ዐመፅንም ያደርጋሉ። በእስራኤል ቤት የሚያሰፈራን ነገር አይቻለሁ፤ በዚያ የኤፍሬምንም ዝሙት አየሁ፤ እስራኤልም ረክሶአል።
ሆሴዕ 6:4-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ኤፍሬም ሆይ፤ ምን ላድርግህ? ይሁዳ ሆይ፤ ምን ላድርግህ? ፍቅራችሁ እንደ ማለዳ ጉም፣ እንደሚጠፋም የጧት ጤዛ ነው። ስለዚህ በነቢያቴ ቈራረጥኋችሁ፤ በአፌም ቃል ገደልኋችሁ፣ ፍርዴም እንደ መብረቅ በላያችሁ አበራ። ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ አምላክን ማወቅ እወድዳለሁ። እንደ አዳም ቃል ኪዳንን ተላለፉ፤ በዚያም ለእኔ ታማኝ አልነበሩም። ገለዓድ በደም የተበከለች፣ የክፉዎች ሰዎች ከተማ ናት። ወንበዴዎች ሰውን ለማጥቃት እንደሚያደቡ፣ ካህናትም በቡድን እንዲሁ ያደርጋሉ፤ በሴኬም መንገድ ላይ ሰዎችን ይገድላሉ፤ አሳፋሪም ወንጀል ይፈጽማሉ። በእስራኤል ቤት የሚሰቀጥጥ ነገር አይቻለሁ፤ በዚያ ኤፍሬም ዘማዊ ሆነ፤ እስራኤልም ረከሰ።
ሆሴዕ 6:4-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ምሕረታችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ጠል ነውና ኤፍሬም ሆይ፥ ምን ላድርግልህ? ይሁዳ ሆይ፥ ምን ላድርግልህ? ስለዚህ በነቢያት እጅ ቈረጥኋቸው፥ በአፌም ቃል ገደልኋቸው፥ ፍርዴም እንደ ብርሃን ይወጣል። ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለሁና። እነርሱ ግን እንደ አዳም ቃል ኪዳንን ተላልፈዋል፥ በዚያም ላይ ወንጅለውኛል። ገለዓድ ኃጢአትን የሚሠሩ ሰዎች ከተማ፥ በደምም የተቀባ ነው። ለሰውም እንደሚያደቡ ወንበዴዎች፥ እንዲሁ የካህናት ወገኖች በሴኬም መንገድ ላይ ይገድላሉ፥ ሴሰኝነትንም ያደርጋሉ። በእስራኤል ቤት የሚያስፈራን ነገር አይቻለሁ፥ በዚያ በኤፍሬም ውስጥ ግልሙትና ተገኘ፥ እስራኤልም ረክሶአል።
ሆሴዕ 6:4-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! እናንተን ምን ላድርጋችሁ? እናንተ ለእኔ ያላችሁ ፍቅር እንደ ማለዳ ጉምና እንደ ጠዋት ጤዛ ፈጥኖ ይጠፋል። በነቢያቴ አማካይነት እንደማጠፋቸው በቃሌም አማካይነት እንደምገድላቸው አስጠነቀቅኋቸው፤ ስለዚህ ፍርዴ እንደ ንጋት ብርሃን ያንጸባርቃል። እኔ ከመሥዋዕት ይልቅ የማይለዋወጥ ፍቅርን እወዳለሁ፤ ከሚቃጠል መሥዋዕት ይልቅ እኔን እግዚአብሔርን ማወቃችሁን እመርጣለሁ። “እነርሱ ወደ አገሪቱ በገቡ ጊዜ ‘አዳም’ በምትባል ቦታ ከእኔ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፈረሱ፤ ለእኔ የማይታመኑ መሆናቸውንም ገለጡ። ገለዓድ ክፉ ሰዎችና በደም የተበከሉ ነፍሰ ገዳዮች የሞሉባት ከተማ ሆናለች! ወንበዴዎች ሰውን ለመግደል እንደሚያደቡ የካህናቱም ቡድን እንዲሁ ያደርጋል፤ ወደ ሴኬም በሚወስደው መንገድ እንኳ እያደቡ ሰውን ይገድላሉ፤ አሳፋሪም የሆነ ወንጀል ይፈጽማሉ። እጅግ የሚያሠቅቅ ነገር በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ አይቼአለሁ፤ ይኸውም ሕዝቡ ጣዖትን በማምለክ ዝሙት ረክሶአል።
ሆሴዕ 6:4-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ፍቅራችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ጠል ነውና ኤፍሬም ሆይ! ምን ላድርግልህ? ይሁዳ ሆይ! ምን ላድርግልህ? ስለዚህ በነቢያት እጅ ቆረጥኋቸው፥ በአፌም ቃላት ገደልኋቸው፤ ፍርዴም እንደ ብርሃን ይወጣል። ከመሥዋዕት ይልቅ ጽኑ ፍቅርን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወዳለሁና። እነርሱ ግን በአዳም ቃል ኪዳንን ተላልፈዋል፤ በዚያም ቦታ እኔን አታለውኛል። ገለዓድ በደም የተቀባች የክፉ አድራጊዎች ከተማ ነች። በሰው ላይ እንደሚያደቡ ወንበዴዎች እንዲሁ ካህናት አብረው ተሰበሰቡ፥ ወደ ሴኬም በሚወስደው መንገድ ላይ ይገድላሉ፤ በእርግጥም፥ ሴሰኝነትንም ያደርጋሉ። በእስራኤል ቤት የሚያስፈራን ነገር አይቻለሁ፤ በዚያ የኤፍሬም ዝሙት አለ፥ እስራኤልም ረክሶአል።