ሆሴዕ 5:1-15

ሆሴዕ 5:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ካህ​ናት ሆይ! ይህን ስሙ፤ የእ​ስ​ራ​ኤል ቤት ሆይ! አድ​ምጡ፤ የን​ጉሥ ቤት ሆይ! ልብ አድ​ርጉ፤ ለሚ​መ​ለ​ከት ወጥ​መድ፥ በታ​ቦ​ርም ላይ የተ​ዘ​ረጋ አሽ​ክላ ሆና​ች​ኋ​ልና ፍርድ በእ​ና​ንተ ላይ ነው። የሚ​ያ​ድኑ አዳ​ኞች ያጠ​ም​ዱ​ባት ዘንድ ተከ​ሏት፤ እኔ ግን መካ​ሪ​ያ​ችሁ ነኝ። እኔ ኤፍ​ሬ​ምን አው​ቀ​ዋ​ለሁ፤ እስ​ራ​ኤ​ልም ከእኔ አል​ራ​ቀም፤ ኤፍ​ሬም ዛሬ አመ​ን​ዝ​ሮ​አ​ልና፤ እስ​ራ​ኤ​ልም ረክ​ሶ​አ​ልና። ወደ አም​ላ​ካ​ቸው ይመ​ለሱ ዘንድ ልባ​ቸ​ውን አላ​ቀ​ኑም፤ የዝ​ሙት መን​ፈስ በው​ስ​ጣ​ቸው አለና፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም አላ​ወ​ቁ​ት​ምና። የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ትዕ​ቢት በፊቱ ይመ​ሰ​ክ​ራል፤ ስለ​ዚህ እስ​ራ​ኤ​ልና ኤፍ​ሬም በኀ​ጢ​አ​ታ​ቸው ይደ​ክ​ማሉ፤ ይሁ​ዳም ከእ​ነ​ርሱ ጋር ይደ​ክ​ማል። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም ለመ​ሻት ከበ​ጎ​ቻ​ቸ​ውና ከላ​ሞ​ቻ​ቸው ጋር ይሄ​ዳሉ፤ ነገር ግን እርሱ ከእ​ነ​ርሱ ተለ​ይ​ቶ​አ​ልና አያ​ገ​ኙ​ትም። ዲቃ​ሎ​ችን ልጆች ወል​ደ​ዋ​ልና እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ከድ​ተ​ዋል፤ አሁ​ንም ኵብ​ኵባ እነ​ር​ሱ​ንና ርስ​ታ​ቸ​ውን ይበ​ላ​ቸ​ዋል። በኮ​ረ​ብታ ላይ መለ​ከ​ትን ንፉ፤ በተ​ራ​ሮ​ችም ላይ ጩኹ፤ ብን​ያም በተ​ዋ​ረ​ደ​በት በቤ​ት​አ​ዌን ዐዋጅ ንገሩ። ኤፍ​ሬም በዘ​ለፋ ቀን ለጥ​ፋት ይሆ​ናል፤ በእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ነገ​ዶች የታ​መ​ነ​ውን ነገር አሳ​የሁ። የይ​ሁዳ አለ​ቆች ድም​በ​ርን እን​ደ​ሚ​ያ​ፈ​ርሱ ሆነ​ዋል፤ እኔም መዓ​ቴን እንደ ውኃ አፈ​ስ​ስ​ባ​ቸ​ዋ​ለሁ። ኤፍ​ሬም የተ​ገፋ ሆነ፤ በፍ​ር​ድም ተረ​ገጠ፤ ከን​ቱን ይከ​ተል ዘንድ ጀም​ሮ​አ​ልና። እኔም ለኤ​ፍ​ሬም እንደ ብል፥ ለይ​ሁ​ዳም ቤት እንደ ነቀዝ እሆ​ን​በ​ታ​ለሁ። ኤፍ​ሬ​ምም ደዌ​ውን አያት፤ ይሁ​ዳም ሥቃ​ዩን አያት፤ ኤፍ​ሬም ወደ አሦር ሄደ፤ ወደ ንጉ​ሡም ወደ ኢያ​ሪም መል​እ​ክ​ተ​ኛን ላከ፤ እርሱ ግን ፈጽሞ ይፈ​ው​ሳ​ችሁ ዘንድ አል​ቻ​ለም፤ ከእ​ና​ን​ተም ሕማም አል​ተ​ወ​ገ​ደም። እኔም ለኤ​ፍ​ሬም እንደ ነብር፥ ለይ​ሁ​ዳም ቤት እንደ አን​በሳ ደቦል እሆ​ና​ለ​ሁና፤ እኔም ነጥቄ እሄ​ዳ​ለሁ፤ እወ​ስ​ድ​ማ​ለሁ፤ የሚ​ያ​ድ​ና​ቸ​ውም የለም። እስ​ኪ​ጠፉ ድረስ፥ ፊቴ​ንም እስ​ኪሹ ድረስ እሄ​ዳ​ለሁ፤ ወደ ስፍ​ራ​ዬም እመ​ለ​ሳ​ለሁ።

ሆሴዕ 5:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“እናንተ ካህናት፤ ይህን ስሙ! የእስራኤል ቤት፤ አስተውሉ! የንጉሥ ቤት ሆይ፤ አድምጡ! ይህ ፍርድ በእናንተ ላይ ነው፤ በምጽጳ ወጥመድ፣ በታቦርም ላይ የተዘረጋ መረብ ሆናችኋልና። ዐመፀኞች በግድያ በርትተዋል፤ ሁሉንም እቀጣቸዋለሁ። ስለ ኤፍሬም ሁሉን ዐውቃለሁ፤ እስራኤልም ከእኔ የተሰወረች አይደለችም፤ ኤፍሬም፣ አንተ አሁን አመንዝረሃል፤ እስራኤልም ረክሳለች። “የሠሩት ሥራ፣ ወደ አምላካቸው እንዲመለሱ አይፈቅድላቸውም፤ የአመንዝራነት መንፈስ በልባቸው አለ፤ እግዚአብሔርንም አያውቁትም። የእስራኤል ትዕቢት በራሷ ላይ ይመሰክራል፤ እስራኤላውያንና ኤፍሬምም በኀጢአታቸው ይሰናከላሉ፤ ይሁዳም ደግሞ ዐብሯቸው ይሰናከላል። እግዚአብሔርን ለመሻት፣ የበግና የፍየል መንጋ እንዲሁም የቀንድ ከብቶቻቸውን ነድተው ሲሄዱ፣ እርሱ ስለ ተለያቸው፣ ሊያገኙት አይችሉም። ለእግዚአብሔር ታማኞች አልሆኑም፤ ዲቃሎች ወልደዋልና፤ ስለዚህ የወር መባቻ በዓላቸው፤ እነርሱንና ዕርሻቸውን ያጠፋል። “በጊብዓ መለከትን፣ በራማ እንቢልታን ንፉ፤ በቤትአዌን የማስጠንቀቂያ ድምፅ አሰሙ፤ ‘ብንያም ሆይ፤ መጡብህ!’ በሉ። በቅጣት ቀን፣ ኤፍሬም ባድማ ይሆናል፣ በእስራኤል ነገዶች መካከል፣ በርግጥ የሚሆነውን ዐውጃለሁ። የይሁዳ መሪዎች፣ የወሰን ድንጋዮችን እንደሚነቅሉ ሰዎች ናቸው፤ እንደ ጐርፍ ውሃ፣ ቍጣዬን በላያቸው ላይ አፈስሳለሁ። ጣዖትን መከተል በመውደዱ፣ ኤፍሬም ተጨቍኗል፤ በፍርድም ተረግጧል። እኔ ለኤፍሬም እንደ ብል፣ ለይሁዳም ሕዝብ እንደ ነቀዝ ሆኛለሁ። “ኤፍሬም ሕመሙን፣ ይሁዳም ቍስሉን ባየ ጊዜ፣ ኤፍሬም ወደ አሦር ሄደ፤ ርዳታ ለመጠየቅ ወደ ታላቁ ንጉሥ መልእክተኛ ላከ፤ እርሱ ግን ሊያድናችሁ፣ ቍስላችሁንም ሊፈውስ አይችልም። እኔ ለኤፍሬም እንደ አንበሳ፣ ለይሁዳም እንደ ደቦል አንበሳ እሆናለሁና፤ ሰባብሬና አድቅቄአቸው እሄዳለሁ፤ ነጥቄ እወስዳቸዋለሁ፤ ማንም ሊያድናቸው አይችልም። በደላቸውንም እስኪያውቁ ድረስ፣ ወደ ስፍራዬ እመለሳለሁ፤ ፊቴን ይሻሉ፤ በመከራቸውም አጥብቀው ይፈልጉኛል።”

ሆሴዕ 5:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ካህናት ሆይ፥ ይህን ስሙ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ አድምጡ፥ የንጉሥ ቤት ሆይ፥ ልብ አድርጉ፥ በምጽጳ ላይ ወጥመድ፥ በታቦርም ላይ የተዘረጋ አሽክላ ሆናችኋልና ፍርድ በእናንተ ላይ ነው። ዓመፀኞችም እርድ አብዝተዋል፥ እኔ ግን እነዚያን ሁሉ እዘልፋለሁ። ኤፍሬምን አውቀዋለሁ፥ እስራኤልም ከእኔ አልተሰወረም፥ ኤፍሬም ሆይ፥ ዛሬ አመንዝረሃል፥ እስራኤልም ረክሶአል። ወደ አምላካቸው ይመለሱ ዘንድ ሥራቸውን አላቀኑም፥ የግልሙትና መንፈስ በውስጣቸው አለና፥ እግዚአብሔርንም አላውቁምና። የእስራኤልም ትዕቢት በፊቱ ይመሰክራል፥ ስለዚህ እስራኤልና ኤፍሬም በኃጢአታቸው ይሰናከላሉ፥ ይሁዳም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይሰናከላል። እግዚአብሔርንም ለመሻት በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ነድተው ይሄዳሉ፥ ነገር ግን እርሱ ከእነርሱ ተመልሶአልና አያገኙትም። ዲቃሎችን ልጆች ወልደዋልና እግዚአብሔርን ወንጅለዋል፥ አሁንም አንድ ወር እነርሱንና ርስታቸውን ይበላቸዋል። በጊብዓ መለከትን፥ በራማ እንቢልታን ንፉና፦ ብንያም ሆይ፥ ከአንተ በኋላ እያላችሁ በቤትአዌን ላይ እሪ በሉ። ኤፍሬም በዘለፋ ቀን የፈረሰ ይሆናል፥ በእስራኤል ነገዶች ዘንድ በእርግጥ የሚሆነውን ነገር ገልጫለሁ። የይሁዳ አለቆች ድምበርን እንደሚነቅሉ ሆነዋል፥ እኔም መዓቴን እንደ ውኃ አፈስስባቸዋለሁ። ኤፍሬም ከትእዛዝ በኋላ መሄድን ወድዶአልና የተገፋና በፍርድ የተጐዳ ሆኖአል። እኔም ለኤፍሬም እንደ ብል፥ ለይሁዳም ቤት እንደ ነቀዝ ሆኜአለሁ። ኤፍሬምም ደዌውን፥ ይሁዳም ቍስሉን ባየ ጊዜ ኤፍሬም ወደ አሦር ሄደ ወደ ንጉሡም ወደ ኢያሪም መልእክተኛን ላከ፥ እርሱ ግን ይፈውሳችሁ ዘንድ፥ ከቍስላችሁም ያድናችሁ ዘንድ አልቻለም። እኔም ለኤፍሬም እንደ አንበሳ፥ ለይሁዳም ቤት እንደ አንበሳ ደቦል እሆናለሁና፥ እኔም ነጥቄ እሄዳለሁ እወስድማለሁ፥ የሚያድንም አይገኝም። በደላቸውንም እስኪያውቁ ድረስ፥ ፊቴንም እስኪሹ ድረስ ሄጄ ወደ ስፍራዬ እመለሳለሁ፥ በመከራቸው ጊዜ እጅግ አድርገው ፊቴን ይፈልጋሉ።

ሆሴዕ 5:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“ካህናት ሆይ! ይህን ስሙ! እናንተም የእስራኤል ሕዝብ አስተውሉ! እናንተም ንጉሣውያን ቤተሰብ ይህን አድምጡ! እነሆ ፍርድ በእናንተ ላይ መጥቶአል፤ በምጽጳ እንደ ወጥመድ፥ በታቦርም እንደ ተዘረጋ መረብ ሆናችኋል። ዐመፀኞች የግድያ ሥራቸውን አስፋፍተዋል፤ ስለዚህ ሁሉንም እቀጣቸዋለሁ። “እኔ የአንቺን የእስራኤልን ሁኔታ ዐውቃለሁ፤ ከእኔ መሰወር አይቻልሽም፤ በጣዖት አምልኮ ዝሙት ረክሰሻል።” የዝሙት መንፈስ በእስራኤል ሕዝብ ውስጥ ስላለና እግዚአብሔርንም ስለማያውቁ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ሥራቸው አይፈቅድላቸውም። የእስራኤል ሕዝብ ትምክሕት በራሳቸው ላይ ይመሰክርባቸዋል፤ ኃጢአታቸውም መሰናክል ሆኖ ይጥላቸዋል፤ የይሁዳም ሕዝብ ከእነርሱ ጋር ተሰናክለው ይወድቃሉ። መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ በጎቻቸውንና ከብቶቻቸውን ነድተው እግዚአብሔርን ለመፈለግ ይሄዳሉ፤ ነገር ግን እርሱ ስለ ተለያቸው አያገኙትም። እነርሱ ራሳቸው ጣዖት አምላኪዎች ስለ ሆኑ ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው አልተገኙም። ልጆቻቸውም እንደ ጣዖት ልጆች ተቆጥረዋል፤ ስለዚህ በዚህ ወር መባቻ እነርሱም ምድራቸውም አብረው ይጠፋሉ። ለጦርነት እንዲወጡ በገባዖን የመለከት፥ በራማም የጥሩንባ ድምፅ አሰሙ! በቤትአዌን “የብንያም ነገድ ሆይ! ከአንተ ጋር ነን” እያላችሁ ጩኹ! በቅጣት ቀን እስራኤል ባድማ ትሆናለች፤ ይህም በእርግጥ እኔ በእስራኤል ነገዶች ላይ እንዲደርስ የወሰንኩት ጥፋት ነው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የይሁዳ መሪዎች የእስራኤልን ድንበር እንደሚያፈርሱ ሰዎች ሆነዋል፤ ስለዚህ እኔ ቊጣዬን እንደ ጐርፍ ውሃ አወርድባቸዋለሁ። እስራኤል ከንቱ ነገርን በመከተል ላይ ስለ ጸና ጭቈናና ፍትሕ ማጣት ደረሰበት። ስለዚህ ብልና ነቀዝ እህልንና እንጨትን እንደሚያጠፉ እኔም እስራኤልንና ይሁዳን አጠፋለሁ። “እስራኤል መታመሙን፥ ይሁዳም መቊሰሉን ባየ ጊዜ፥ እስራኤል ወደ አሦር ፊቱን መለሰ፤ ርዳታም ለማግኘት ወደ ታላቁ ንጉሥ መልእክተኛ ላከ፤ ነገር ግን እርሱ ሊያድናቸው ወይም ቊስላቸውን ሊፈውስ አልቻለም። ከዚህ የተነሣ እስራኤልን እንደ አንበሳ፥ ይሁዳንም እንደ ደቦል አንበሳ በመሆን ሰባብሬአቸው እሄዳለሁ፤ ነጥቄ እወስዳቸዋለሁ፤ ማንም ሊያድናቸው አይችልም። “መከራ ሲበዛባቸው እኔን ይፈልጋሉ፤ ስለዚህ የሠሩትን በደል ተገንዝበው ወደ እኔ እስከሚመለሱ፥ ድረስ ከእነርሱ እርቃለሁ።”

ሆሴዕ 5:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ካህናት ሆይ! ይህን ስሙ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ! ልብ አድርጉ፤ የንጉሥ ቤት ሆይ! አድምጡ፤ በምጽጳ ላይ ወጥመድ፥ በታቦርም ላይ የተዘረጋ አሽክላ ሆናችኋልና ፍርድ በእናንተ ላይ ነው። ዓመፀኞችም እርድ አብዝተዋል፤ እኔ ግን እነርሱን ሁሉ እገሥጻለሁ። እኔ ኤፍሬምን አውቀዋለሁ፥ እስራኤልም ከእኔ አልተሰወረም፤ አሁን ግን ኤፍሬም ሆይ! አመንዝረሃል፥ እስራኤልም ረክሶአል። ሥራቸው ወደ አምላካቸው እንዲመለሱ አልፈቀደላቸውም፤ የአመንዝራ መንፈስ በውስጣቸው አለና፤ ጌታንም አላውቁምና። የእስራኤልም ትዕቢት በራሱ ላይ መስክሮአል፤ ስለዚህ እስራኤልና ኤፍሬም በኃጢአታቸው ተሰናክለዋል፤ ይሁዳም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ተሰናክሎአል። ጌታንም ለመሻት በጎቻቸውንና በሬዎቻቸውን ነድተው ይሄዳሉ፤ ነገር ግን እርሱ ከእነርሱ ተመልሶአልና አያገኙትም። ዲቃሎችን ልጆች ወልደዋልና ጌታን አታልለዋል፤ አሁን ደግሞ እነርሱን ከርስታቸው ጋር የወሩ መባቻ ይበላቸዋል። በጊብዓ ቀንደ መለከትን፥ በራማ እንቢልታን ንፉ፤ “ብንያም ሆይ! ከአንተ ጋር ነን እያላችሁ በቤትአዌን ላይ የማስጠንቀቂያውን ነጋሪት ድምፅ አሰሙ።” ኤፍሬም በተግሣጽ ቀን ባድማ ይሆናል፤ በእስራኤል ነገዶች መካከል እርግጥ የሆነውን ነገር አሳውቂያለሁ። የይሁዳ አለቆች ድምበርን እንደሚያፈርሱ ሰዎች ሆነዋል፤ እኔም መዓቴን እንደ ውኃ በእነርሱ ላይ አወርድባቸዋለሁ። ኤፍሬም ትእዛዝን መከተል ፈጽሞ አልወደደምና የተጨቆነና በፍርድ የተጐዳ ሆኖአል። እኔም ለኤፍሬም እንደ ብል፥ ለይሁዳም ቤት እንደ ነቀዝ ሆኜአለሁ። ኤፍሬምም ደዌውን፥ ይሁዳም ቁስሉን ባየ ጊዜ ኤፍሬም ወደ አሦር ሄደ፥ ወደ ታላቁም ንጉሥ መልእክተኛን ላከ፤ እርሱ ግን ሊፈውሳችሁ፥ ከቁስላችሁም ሊያድናችሁ አልቻለም። እኔም ለኤፍሬም እንደ አንበሳ፥ ለይሁዳም ቤት እንደ አንበሳ ደቦል እሆናለሁና፤ እኔ ራሴ ነጥቄ እሄዳለሁ እወስዳለሁም፥ ሊያድንም የሚችል ማንም የለም። በደላቸውንም ተቀብለው ፊቴን እስኪሹ ድረስ ወደ ስፍራዬ ተመልሼ እሄዳለሁ፤ በመከራቸው ጊዜ እጅግ አድርገው ፊቴን ይፈልጋሉ።