ሆሴዕ 4:1-19
ሆሴዕ 4:1-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! እውነትና ምሕረት፥ እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚኖሩትን ይወቅሳልና የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። ነገር ግን ሐሰት፥ ግዳይና ስርቆት፥ ምንዝርናም ምድርን ሞልተዋል፤ ደምንም ከደም ጋር ይቀላቅላሉ። ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፤ በእርስዋም ከሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች፤ ከምድርም ተንቀሳቃሾች ጋር ትጠፋለች፤ የባሕሩም ዓሦች ያልቃሉ። ነገር ግን ሕዝቤ እንደሚከራከር ካህን ነውና እንግዲህ የሚከራከር፥ ማንም አይኑር፥ የሚዘልፍም ማንም አይኑር። በቀንም ትደክማለህ፤ ነቢዩም ከአንተ ጋር ይደክማል፤ እናታችሁም ሌሊትን ትመስላለች። ሕዝቤ አእምሮ እንደሌላቸው ይመስላሉ፤ አንተም አእምሮህ ተለይቶሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እተውሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። እንደ ብዛታቸው መጠን ኀጢአት ሠሩብኝ፤ እኔም ክብራቸውን ወደ ውርደት እለውጣለሁ። ሕዝቤንም ኀጢአታቸው ትበላቸዋለች፤ ሰውነታቸውንም በበደላቸው ይወስዷታል። እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ ይሆናል፤ በመንገዳቸውም እበቀላቸዋለሁ፤ እንደ ሥራቸውም እከፍላቸዋለሁ። እግዚአብሔርንም መጠበቅ ትተዋልና ሲበሉ አይጠግቡም፤ ሲያመነዝሩም አይበዙም። የሕዝቤ ልቡናቸው ዝሙትን፥ መጠጥንና ስካርን ወደደ። ሕዝቤ በዝሙት መንፈስ ስተዋልና ከአምላካቸውም ርቀው አመንዝረዋልና በትርን ይጠይቃሉ፤ በትሩም ይመልስላቸዋል። በተራሮችም ራስና በኮረብታዎች ላይ ይሠዋሉ፤ ጥላውም መልካም ነውና ከኮምበልና ከልብን፥ ከአሆማም ዛፍ በታች ያርዳሉ፤ ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁ ይሰስናሉ፤ ሙሽሮቻችሁም ያመነዝራሉ። ወንዶችም ደግሞ ከአመንዝሮች ጋር ይጫወታሉና፥ ከጋለሞቶችም ጋር ይሠዋሉና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰሰኑ ጊዜ፥ ሙሽሮቻችሁም በአመነዘሩ ጊዜ አልቀጣኋቸውም፤ የማያስተውልም ሕዝብ ከአመንዝራ ጋር ይቀላቀላል። እስራኤል ሆይ! አንተ አላዋቂ አትሁን፤ አንተም ይሁዳ! ወደ ጌልጌላ አትሂድ፤ ወደ ቤትአዊንም አትውጡ፤ በሕያው እግዚአብሔርም አትማሉ። እስራኤል እንደምትደነብር ጊደር ደንብሮአል፤ እግዚአብሔርም በሰፊው ቦታ እንደ ጠቦት ያሰማራዋል። እንዲሁም ኤፍሬም ከጣዖታት ጋር ተጋጠመ፤ ለራሱም ዕንቅፋትን አኖረ። ከነዓናውያንንም መረጣቸው፤ ፈጽመውም አመነዘሩ፤ በክፋታቸውም ውርደትን መረጡ። አንተ በክንፎችዋ ውስጥ የነፋስ መናወጥ ነህ፤ ከመሥዋዕታቸውም የተነሣ ያፍራሉ።
ሆሴዕ 4:1-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እናንተ የእስራኤል ልጆች፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር በምድሪቱ በምትኖሩት ላይ የሚያቀርበው ክስ አለውና፤ ምክንያቱም ታማኝነት የለም፤ ፍቅርም የለም፤ እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድሪቱ የለም። በዚያ ያለው ርግማን፣ መዋሸት፣ መግደል፣ መስረቅና ማመንዘር ብቻ ነው፤ ቃል ኪዳንን ሁሉ ያፈርሳሉ፤ ደም ማፍሰስና ግድያ ይበዛል። ስለዚህ ምድሪቱ አለቀሰች፤ በውስጧም የሚኖሩ ሁሉ ኰሰመኑ፤ የምድር አራዊት፣ የሰማይ ወፎች፣ የባሕርም ዓሦች ዐለቁ። “ነገር ግን ማንም ሰው አይከራከር፤ ማንም ሌላውን አይወንጅል፤ በካህናት ላይ ክስን እንደሚያቀርቡ፣ ሕዝብህ እንደዚያው ናቸውና። ቀንና ሌሊት ትደናበራላችሁ፤ ነቢያትም ከእናንተ ጋራ ይደናበራሉ። ስለዚህ እናታችሁን አጠፋታለሁ፤ ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል። ዕውቀትን ስለ ናቃችሁ፣ እኔም ካህናት እንዳትሆኑ ናቅኋችሁ፤ የአምላካችሁን ሕግ ስለ ረሳችሁ፣ እኔም ልጆቻችሁን እረሳለሁ። ካህናት በበዙ ቍጥር በእኔ ላይ የሚያደርጉት ኀጢአት በዝቷል፤ ክብራቸውንም በውርደት ለውጠዋል። የሕዝቤ ኀጢአት ለመብል ሆኖላቸዋል፤ ርኩሰታቸውንም እጅግ ወደዱ። ካህናትም ከሕዝቡ የተለዩ አይደሉም፤ ሁሉንም እንደ መንገዳቸው እቀጣቸዋለሁ፤ እንደ ሥራቸውም እከፍላቸዋለሁ። “ይበላሉ ግን አይጠግቡም፤ ያመነዝራሉ ግን አይበዙም፤ እግዚአብሔርን በመተው፣ ራሳቸውን ለአመንዝራነት፣ ለአሮጌና ለአዲስ የወይን ጠጅ አሳልፈው ሰጡ፤ በእነዚህም የሕዝቤ ማስተዋል ተወሰደ። ከዕንጨት የተሠራውን ጣዖት ምክር ይጠይቃሉ፤ ዘንጋቸውም ይመልስላቸዋል። የአመንዝራነት መንፈስ ያስታቸዋል፤ ለአምላካቸውም ታማኝ አልሆኑም። በተራሮችም ጫፍ ላይ ይሠዋሉ፤ መልካም ጥላ ባለው፣ በወርካ፣ በኮምቦልና በአሆማ ዛፍ ሥር፣ በኰረብቶችም ላይ የሚቃጠል ቍርባን ያቀርባሉ። ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማውያን፣ ምራቶቻችሁም አመንዝራዎች ይሆናሉ። “ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማውያን ሲሆኑ፣ የልጆቻችሁም ሚስቶች ሲያመነዝሩ አልቀጣቸውም። ወንዶች ከጋለሞቶች ጋራ ይሴስናሉ፤ ከቤተ ጣዖት ዘማውያን ጋራ ይሠዋሉና፤ የማያስተውል ሕዝብ ወደ ጥፋት ይሄዳል! “እስራኤል ሆይ፤ አንቺ ብታመነዝሪም፣ ይሁዳ በበደለኛነት አትጠየቅ። “ወደ ጌልገላ አትሂዱ፤ ወደ ቤትአዌንም አትውጡ፤ ‘ሕያው እግዚአብሔርን!’ ብላችሁም አትማሉ። እስራኤላውያን እንደ እልኸኛ ጊደር፣ እልኸኞች ናቸው፤ ታዲያ እግዚአብሔር እነርሱን በመልካም መስክ ውስጥ እንዳሉ የበግ ጠቦቶች እንዴት ያሰማራቸዋል? ኤፍሬም ከጣዖት ጋራ ተጣምሯል፤ እስኪ ተዉት፤ መጠጣቸው ባለቀ ጊዜ እንኳ፣ ዘማዊነታቸውን አያቆሙም፤ ገዦቻቸውም ነውርን አጥብቀው ይወድዳሉ። ዐውሎ ነፋስ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ መሥዋዕቶቻቸውም ኀፍረት ያመጡባቸዋል።”
ሆሴዕ 4:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እውነትና ምሕረት እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድሩ ላይ ከሚኖሩ ጋር ክርክር አለውና የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። እርግማንና ሐሰት ግዳይና ስርቆት ምንዝርናም ወጥተዋል፥ ደምም ወደ ደም ደርሶአል። ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፥ በእርስዋም የሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ጋር ይደክማሉ፥ የባሕሩም ዓሦች ያልቃሉ። ነገር ግን ሕዝብህ ከካህን ጋር እንደሚከራከሩ ናቸውና ማንም አይከራከር፥ ማንም አይዝለፍ። በቀንም ትሰናከላለህ፥ ነቢዩም ከአንተ ጋር በሌሊት ይሰናከላል፥ እናትህንም አጠፋታለሁ። ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፥ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፥ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። እንደ ብዛታቸው መጠን ኃጢአት ሠሩብኝ፥ እኔም ክብራቸውን ወደ ነውር እለውጣለሁ። የሕዝቤም ኃጢአት መብል ሆኖላቸዋል፥ ልባቸውንም ወደ በደላቸው አድርገዋል። እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ ይሆናል፥ በመንገዳቸውም እበቀላቸዋለሁ፥ ሥራቸውንም እመልስባቸዋለሁ። እግዚአብሔርንም መጠበቅ ትተዋልና ሲበሉ አይጠግቡም፥ ሲያመነዝሩም አይበዙም። ግልሙትናና የወይን ጠጅ ስካርም አእምሮን ያጠፋል። የግልሙትና መንፈስ ሕዝቤን አስቶአቸዋልና፥ እነርሱም ከአምላካቸው ርቀው አመንዝረዋልና በትራቸውን ይጠይቃሉ፥ ዘንጋቸውም ይመልስላቸዋል። በተራሮችም ራስ ላይ ይሠዋሉ፥ ጥላውም መልካም ነውና ከኮምበልና ከልብን ከአሆማም ዛፍ በታች በኮረብቶች ላይ ያጥናሉ፥ ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁ ይገለሙታሉ፥ ሙሽሮቻችሁም ያመነዝራሉ። ወንዶችም ደግሞ ከጋለሞቶች ጋር ይጫወታሉና፥ ከጋለሞቶችም ጋር ይሠዋሉና ሴቶች ልጆቻችሁ በገለሞቱ ጊዜ፥ ሙሽሮቻችሁም ባመነዘሩ ጊዜ አልቀጣቸውም፥ የማያስተውልም ሕዝብ ይገለበጣል። እስራኤል ሆይ፥ አንተ ብታመነዝር ይሁዳ አይበድል፥ እናንተም ወደ ጌልገላ አትግቡ፥ ወደ ቤትአዌንም አትውጡ፥ ወይም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ብላችሁ አትማሉ። እስራኤል እንደ እልከኛ ጊደር እንቢ ብሎአል፥ እግዚአብሔርስ በሰፊው ቦታ እንደ ጠቦት ያሰማራዋልን? ኤፍሬም ከጣዖታት ጋር ተጋጠመ፥ ተወው። ስካርን ፈጽመዋል፥ ግልሙትናንም አብዝተዋል፥ አለቆችዋም ነውርን እጅግ ወደዱ። ነፋስ በክንፍዋ አስሮአታል፥ ከመሥዋዕታቸውም የተነሣ ያፍራሉ።
ሆሴዕ 4:1-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚህች ምድር በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ላይ እግዚአብሔር የሚያቀርበው ወቀሳ አለው፤ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እርሱ የሚልህን ሁሉ ስማ፦ “በምድሪቱ ላይ ታማኝነትና ፍቅር እግዚአብሔርንም ማወቅ ጠፍቶአል። በመሐላ የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰው ይዋሻሉ፤ ይገድላሉ፤ ይሰርቃሉ፤ ያመነዝራሉም፤ ግፍና ግድያ እየበዛ ሄዶአል። በዚህም ምክንያት በምድሪቱ ላይ ድርቅ ይመጣል፤ በእርስዋ የሚኖሩ ሁሉ ይደክማሉ፤ እንስሶች፥ ወፎችና የባሕር ዓሣዎች ሁሉ ያልቃሉ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ የምወቅሰው እናንተን ካህናትን ስለ ሆነ ሕዝቡን የሚከስ ወይም የሚወቀስ አይኑር። እናንተ ካህናት ሆይ! በቀን ብርሃን ትደናበራላችሁ፤ ነቢያትም ሌሊት ከእናንተ ጋር በጨለማ ይደናበራሉ፤ ስለዚህ እናት አገራችሁን አጠፋታለሁ። ሕዝቤ እኔን በሚገባ ካለማወቁ የተነሣ ጠፍቶአል፤ እናንተ እኔን ለማወቅ ስላልፈለጋችሁ እኔም ካህናት ሆናችሁ እንድታገለግሉኝ አልፈልጋችሁም፤ ሕጌንም ስላቃለላችሁና ስለ ረሳችሁ ልጆቻችሁ በእኔ ዘንድ የተረሱ ይሆናሉ። “እናንተ ካህናት ቊጥራችሁ በበዛ መጠን በደላችሁም በፊቴ እየበዛ ሄዶአል፤ ስለዚህ ክብራችሁን ገፍፌ አዋርዳችኋለሁ። የሕዝቤ ኃጢአት ለእናንተ መበልጸጊያ በመሆኑ ሕዝቡ ኃጢአትን አብዝተው እንዲሠሩ ትፈልጋላችሁ። እናንተ ካህናት እንደ ሕዝቡ ሆናችኋል፤ ስለዚህ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው ቅጣት በእናንተም በካህናት ላይ ይደርሳል፤ የክፉ ሥራችሁንም ብድራት ትከፍላላችሁ። ሕዝቤ እኔን እግዚአብሔርን ስለ ተዉ፥ ይበላሉ አይጠግቡም፤ በአሕዛብ መስገጃ ቦታዎች ያመነዝራሉ፤ ግን ልጆችን አይወልዱም።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የዝሙት ሥራ፥ የቈየና አዲስ የወይን ጠጅን መከተል የሕዝቤን አእምሮ አጥፍቶአል። ስለዚህ ከእንጨት የተሠራውን ጣዖት ምክር ይጠይቁታል፤ የጥንቈላ ዘንጋቸውም ለጥያቄአቸው መልስ የሚሰጥ ይመስላቸዋል፤ በዝሙት መንፈስም ተመርተው ከእግዚአብሔር ርቀዋል። በየተራራው ላይ መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ በየኮረብታው ላይ ቊርባን ያቀርባሉ፤ ይህንንም የሚያደርጉት ታላላቅ በሆኑና ቅርንጫፋቸው በተንሰራፋ ጥላቸው መልካም በሆነ ዋርካ፥ በለሳና ጥድ ሥር ነው። በዚህ ምክንያት ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማውያን ይሆናሉ። ምራቶቻችሁም ያመነዝራሉ። ይሁን እንጂ ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማውያት ምራቶቻችሁም አመንዝሮች ስለ ሆኑ አልቀጣቸውም፤ ምክንያቱም እናንተ ወንዶች ራሳችሁ በቤተ መቅደስ የሚሴስኑ ሴቶችን ተከትላችሁ ከእነርሱ ጋር ባዕድ አምልኮ ትፈጽማላችሁ፤ ስለዚህ ማስተዋል የጐደለው ሕዝብ ይጠፋል። “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እናንተ ብታመነዝሩም እንኳ የይሁዳ ሕዝብ በደለኛ እንዲሆን አታድርጉ፤ ወደ ጌልጌላ ወይም ወደ ቤትአዌን አትሂዱ፤ ‘ሕያው እግዚአብሔርን’ ብላችሁም አትማሉ። የእስራኤል ሕዝብ እንደ እልኸኛ ጊደር እምቢተኞች ሆነዋል፤ ታዲያ እግዚአብሔር እነርሱን እንደ በግ ጠቦቶች በመልካም መስክ እንዴት ያሰማራቸዋል? የእስራኤል ሕዝብ ከጣዖት አምልኮ ጋር ስለ ተጣመሩ ተዉአቸው የፈለጉትን ያድርጉ። ብዙ የወይን ጠጅ ከጠጡ በኋላ የዝሙት ሥራቸውን ይቀጥላሉ፤ አለቆቻቸውም አሳፋሪ ነገሮችን ማድረግ አጥብቀው ይወዳሉ። እነርሱም በነፋስ ተጠርገው የሚወሰዱትን ያኽል ርቀው ይሄዳሉ፤ ለጣዖት በመሠዋታቸውም ያፍራሉ።
ሆሴዕ 4:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! እውነትና ጽኑ ፍቅር አምላክንም ማወቅ በምድሪቱ ስለ ሌለ ጌታ በምድሪቱ ላይ ከሚኖሩ ጋር ሙግት አለውና የጌታን ቃል ስሙ። መራገምና መዋሸት፥ መግደልና መስረቅ፥ ማመንዘርም ገደባቸውን አልፈዋል፤ ደም ማፍሰስ ደም ማፍሰስን አስከትሏል። ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፥ በእርሷም የሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ጋር በድካም ይዝላሉ፤ የባሕሩም ዓሦች እንኳ ያልቃሉ። ነገር ግን ሙግቴ ከካህን ጋር ነውና ማንም አይከራከር፥ ማንም አይዝለፍ። በቀንም ትሰናከላለህ፥ እንዲሁም ነቢይ ከአንተ ጋር በሌሊት ይሰናከላል፤ እናትህንም አጠፋታለሁ። ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ትተሃልና ለእኔ ካህን እንዳትሆን ትቼሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። እነርሱም እጅግ በበዙ ቍጥር አብዝተው ኃጢአትን በእኔ ላይ ሠሩ፤ እኔም ክብራቸውን ወደ ውርደት እለውጣለሁ። የሕዝቤም ኃጢአት መብል ሆኖላቸዋል፥ ልባቸውንም ወደ በደላቸው አዘንብለዋል። እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ ይሆናል፤ ስለ መንገዳቸውም እበቀላቸዋለሁ፥ እንደ ሥራቸውም ብድራትን እከፍላቸዋለሁ። እነርሱም ይበላሉ አይጠግቡም፥ ያመነዝራሉ አይበዙም ምክንያቱም ጌታን ትተው ዝሙት ተከትለዋልና፤ ወይንና አዲስ ወይን ጠጅ ልብን አጥፍቶአልና። የዝሙት መንፈስ አስቶአቸዋልና፥ እነርሱም ከአምላካቸው ርቀው አመንዝረዋልና ሕዝቤ ግዑዝ እንጨታቸውን ይጠይቃሉ፥ በትራቸውም ይመልስላቸዋል። በተራሮችም ራስ ላይ ይሠዋሉ፤ ጥላውም መልካም ነውና ከባሉጥና ከልብን ከአሆማም ዛፍ በታች በኮረብቶች ላይ ያጥናሉ፤ ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማውያን ይሆናሉ፥ ምራቶቻችሁም ያመነዝራሉ። ወንዶችም ደግሞ ከአመንዝሮች ጋር አብረው ይሄዳሉና፥ በአማልክቶቻቸውም መቅደስ ከሚያመነዝሩ ሴቶች ጋር ይሠዋሉና ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማዊ በሆኑ ጊዜ፥ ምራቶቻችሁም ባመነዘሩ ጊዜ አልቀጣቸውም፤ የማያስተውልም ሕዝብ ይጠፋል። አንተ ብታመነዝር እንኳ እስራኤል ሆይ! ይሁዳ በደለኛ አይሁን፤ እናንተም ወደ ጌልገላ አትግቡ፥ ወደ ቤትአዌንም አትውጡ፥ ወይም፦ “በሕያው ጌታ እምላለሁ!” ብላችሁም አትማሉ። እስራኤል እንደ እልኸኛ ጊደር እልኸኛ ሆኖአል፤ ጌታስ በሰፊው ማሰማርያ እንደ ጠቦት ያሰማራዋልን? ኤፍሬም ከጣዖታት ጋር ተጣምሯል፤ እርሱንስ ተወው። ስካራቸውን ፈጽመዋል፥ ለምንዝርናም ራሳቸውን ፍጹም አስገዝተዋል፤ ከክብራቸው ይልቅ ውርደታቸውን እጅግ ወድደዋል። ነፋስ በክንፉ አስሮአቸዋል፤ ከመሥዋዕቶቻቸውም የተነሣ ያፍራሉ።